በቁጥር ብዛት ያላቸው የአለም ሀገራት የተማሪዎች የመማር ውጤትና የሀገር ዕድገትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ይተገብሩታል። ሀገራቱ መርሃ ግብሩ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለመጪው ትውልድ ስኬት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ሰርቶ ማስረከብ እንደሆነ በማመን ትኩረት ሰጥተው ተግባራዊ ሲያደርጉት ይታያሉ። ይህም የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩ ተግባራዊ የሚደረገው ድህነት ስላለ ብቻ እንዳልሆነ ያመላክታል።
የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርን ከድህነት ጋር አቆራኝቶ የመመልከት እሳቤ የተሳሳተ ቢሆንም ቅሉ፤ በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ቢደረግ የበለጠ ውጤት እንደሚያሳይ ሳይታለም የተፈታ ነው። ተማሪዎችን በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት የተጎዱ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙና በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል።
በሌላ በኩል የመማር ማስተማሩ ሂደት የተማሪዎች ተሳትፎ ከማሳደግ ባሻገር እንደ ሀገር ውጤታማና ንቁ ዜጎችን በፍትሃዊነት ለማፍራት የሚያግዝ እንደሆነም ይታመናልና። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ቢደረግ ውጤቱ ብዙ እንደሚሆን እሙን ነው። ምክንያቱም በሀገራችን የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት አሁንም ድረስ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡
የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የማይታሰብ ሆኖ 40 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የቀነጨረ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ማኅበራዊ ችግር ሕፃናት ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡ ጾማቸውን ክፍል የሚገቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል እስኪያቅታቸው ይራባሉ፡፡ ራሳቸውን ስተው የሚዘረሩ፣ በዚህ ምክንያት ከክፍል የሚቀሩ ከነአካቴው ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ይህንን ሥር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርን በስፋት ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት የሚያስችል እንደሚሆን የብዙዎች እምነት ነው።
በእርግጥም የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ለሀገራችን እንግዳ ነውን? መልሱ አይደለም ነው። መረጃዎች እንደሚያስረዱት መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ቢደረግም በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ያለመቻሉን ነው። ኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው በ1987 ዓ.ም በዓለም የምግብ ፕሮግራም ነበር። በተለይም በአገሪቱ ድርቅ በተከሰተበት በ2009 ዓ.ም መንግሥት 570 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ በስምንት ክልሎች ከሦስት ሚሊዮን በላይ ለሚጠጉ ዜጎች ምገባ ማከናወን መቻሉ ይታወሳል።
በመንግስት ደረጃ በመርሃ ግብሩ ታምኖበት ተግባራዊ ሲደረግ ቢቆይም፤ ትኩረት ያገኘው ከባለፉት ሦስት ዓመት ወዲህ ነው። በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ። የመርሃ ግብሩ ውጤታማነት በተግባር፣ በጥናት ለማረጋገጥ የተቻለው በእነዚህ ጊዜያት ነበር። ለአብነትም ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ኢት-አለም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ የንግድ ድርጅት ይፋ ያደረገውን የጥናት ውጤት እንመልከት።
የኢት-አለም እንዳመላከተው፤ በአዲስ አበባ በ42 ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የምገባ ፕሮግራም በተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ውጤት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣቱን በጥናት ግኝቱ ማረጋገጡን አስታውቋል። የምገባ ፕሮግራሙ በተማሪዎቹ የትምህርት አቀባበልና ተክለ ሰውነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል። የተማሪዎች ዓመታዊ ውጤት ከ62 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 70 በመቶ፣ ምዝገባ በዘጠኝ በመቶ፣ የአካል እድገታቸው 21 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ እንዲልና ተመጣጣኝ ክብደት እንዲኖራቸው አስችሏል። የተማሪዎችን መጠን የትምህርት ማቋረጥን በ64 በመቶና በምግብ ምክንያት ከትምህርት ቤት የሚቀሩትንም በ59 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረጉን ድርጅቱ ያደረገው የጥናት ግኝት ያመለክታል።
ከጥናቱ ውጤት መረዳት የሚቻለው ቀደም ሲል የነበሩትን ክፍተቶች በማረቅ በቁርጠኝነት መስራት እንደተቻለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በመነሳት የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ቢቻል ምን ያህል ውጤታማ መሆን ስለመቻሉ ነው። መንግስት የአዲስ አበባን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ ወደ ተግባር የተሸጋገረ መሆኑን ለመመልክት ተችሏል። የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በአንድ መድረክ ላይ፤ ̋የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም አማራጭ ሳይሆን ትውልድን የማስቀጠል የህልውና ጉዳይ ነው˝ ማለታቸው መንግስት የመርሃ ግብሩ ተግባራዊነት ብቻም ሳይሆን ለውጤቱ ትኩረት መስጠቱን ያመላክታል ተብሏል። ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በሲዳማ ክልል ተግባራዊ የተደረገው መርሃ ግብር የዚሁ አካል እንደሆነ ይታመናል።
የትምህርት ሚኒስቴር ከህፃናት አድን ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ሰፋ ያለው ይህ አካታች ሀገር በቀል የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብሩ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ተግባራዊ ለማድረግ ውል ገብተው እንደነበር ይታወሳል። ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፤ ̋የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም አማራጭ ሳይሆን ትውልድን የማስቀጠል የህልውና ጉዳይ ነው˝ ባሉት መሰረት ቃላቸው ወደ ተግባር በመለወጥ እያሳዩ ይገኛሉ። አቶ ሚሊዮን እንደተናገሩት፤ አካታች ሀገር በቀል የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮጀክት የነገ ተስፋ የሆኑ ህፃናት ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ እና በትምህርት ቤት ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የህፃናት አድን ድርጅት በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ኢኪንኦጉቶ ጉላሪ ደግሞ፤ የተቀናጀ አካታች ሀገር በቀል የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በ499 ትምህርት ቤቶች የሚተገበር መሆኑን እና የምገባ ፕሮግራሙ ህፃናት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ይረዳል፡፡ በሀገር በቀል የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብሩ በአምስት ክልሎች የሚተገበር መሆኑን ያስታወቁት ዳይሬክተሯ፤ ˝በአጠቃላይ 499 በላይ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 163 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ይህን የምገባ ፕሮግራሙን እውን ለማድረግም ‘ግሎባል ፓርትነር ሺፕ ፎር ኢጁኬሽን’ የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት 21 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል˝ ሲሉ ነበር። የተቀናጀ አካታች ሀገር በቀል የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራሙን ለማሳካት ብዙ ርቀት ጉዞ መደረጉን ያመላከቱት ዳይሬክተሯ፤ ፕሮጀክቱ ድርጅቱ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው መስኮች መካከል አንዱ እንደመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
በአጠቃላይ የትምህርት ሚኒስቴር ከህፃናት አድን ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ሰፉ ያለው ይህ አካታች ሀገር በቀል የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ይኖሩታል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ደግሞ በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱና ሌሎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ በማድረግ ረገድ ያለው ሚና ትልቅ ነው።
በፕርግራሙ ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚካተቱ እንደመሆኑ በትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነትን ከማረጋገጥ ረገድ ወሣኝ ሚና እንደሚኖረው እሙን ነው። ምክንያቱም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ጥራት ያለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላል።
በተጨማሪም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ሳይለዩ ትኩስና ንጽህናው የተጠበቀ ምግብ በመመገብ ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም ለአንድ ዓመት ተግባራዊ በሚደረግባቸው አካባቢዎች የተሳካ ስራን መስራት እንዲቻል፤ ከክልል መንግስታት ጋር በተቀናጀ መልኩ በማከናወን የተግባሩን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይገባል። ምክንያቱም ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ፍላጐትና ተሳትፎ እንዲጨምርና የትምህርት አቀባበላቸው እንዲሻሻል የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። በመሆኑም ብዙ ተሥፋ የተጣለበት ሀገር የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩ ከትግበራው ትይዩ ቀጣይነቱ ትኩረትን ይሻል!!!