ወይዘሮ ሣራ ዘመኑ ሠናይ በጋዜጣችን ለወላጆች መልዕክትን ማስተላለፍ ከጀመሩ ሠነባብተዋል። ወይዘሮ ሣራ የህክምና ባለሙያ ሲሆኑ፤ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ለወላጆች የተለያዩ ሀሳቦችን እያነሱ ያካፍላሉ።
ልጆቻችን ከ6 እስከ 12 ዓመት ያሉበት ዕድሜ ኃላፊነትን ለማስተማር የምንችልበት ጥሩ ዕድሜ ነው። በዚህ ዕድሜ ውስጥ ያሉትን ታዳጊ ልጆቻችንን እንዴት አድርገን ነው እኛ ወላጆች ኃላፊነትን ማስተማር የምንችለው? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ከዚህ በታች ይህንን ማድረግ የሚያስችሉን ሦስት ዋና መንገዶች ለማሳየት እሞክራለሁ። የመጀመሪያው ዋና መንገድ ለልጆቻችን ገደብ መስጠት ነው። ይህም ማለት ሁሉ የጠየቁትን ነገር አለመፍቀድ ማለት ነው። አቅሙ ስላለን ብቻ የጠየቁንን ማድረግ እንፈልግ ይሆናል፤ በተለይ እኛ በልጅነታችን ያላገኘነውን ነገሮች። ይኼ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ማመዛዘን ያለብን የጠየቁንን ነገሮች ያስፈልጋቸዋል ወይ? ለዕድገታቸው ይጠቅማቸዋል ወይ? የሚለውን ነው። በዚህ መሠረት ለልጆቻችን ገደብ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።
ሁለተኛው ዋና መንገድ ደግሞ ኃላፊነት ሊያስተምሩ የሚችሉ አንዳንድ ቀላል የሆኑ ስራዎችን መስጠት ነው። ለምሣሌ ሁልጊዜ አልጋቸውን እንዲያነጥፉ ወይም የሚበሉበትን ዕቃ በልተው ሲጨርሱ አጥበው እንዲያስቀምጡ መመሪያ መስጠት ነው። እንዲህ ዓይነት መመሪያ በምንሰጥበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን መመሪያው በጣም ግልጽና በዝርዝር መሆኑን ነው። ይኸውም ከእነርሱ ምን እንደሚጠበቅባቸው በግልጽ እንዲረዱት ማድረግ ያስፈልጋል።
በደፈናው አልጋህን ሁሌ እንድታነጥፍ ከማለት ፋንታ ሁልጊዜ ጠዋት ተነስተህ ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድህ በፊት ወይም ትምህርት ቤት በሌለ ቀን ደግሞ ከቁርስ በፊት አልጋህን እንድታነጥፍ እጠብቃለሁ ብሎ በዝርዝር ማስረዳት ያስፈልጋል።
ሦስተኛውና በጣም ወሣኙ መንገድ ደግሞ ኃላፊነት የተሰጣቸውን ሥራዎች መሥራታቸውን መከታተል ነው። ይህ መንገድ ደግሞ በጣም ጥንቃቄና ዕውቀት የሚፈልግ ነው። ምክንያቱም በምንከታተላቸው ጊዜ ሥሜታቸውን የሚጎዳ ነገር እንዳንላቸው በጣም መጠንቀቅ ይኖርብናል።
ለዚህም ዋናው ሁልጊዜ ሥሜታችንን ተቆጣጥረን ልጆቹ ላያ ያተኮረ ሣይሆን የተሠራው ወይም ያልተሠራው ሥራው ላይ ብቻ ያተኮረ ንግግር በማድረግ ነው።
ለምሣሌ አልጋውን እንደታዘዘው ያላነጠፈን ልጅ አንተ ሠነፍ ማለት አይገባም። ምክንያቱም ሥሜቱን ከመጉዳት በላይ ይህ ዓይነት ንግግር ትርፍ ስለሌለው ነው። በዚህ ፋንታ ግን አልጋህን እንዳልተነጠፈ አይቻለሁ፤ ሄደህ እንድታነጥፈው እፈልጋለሁ በማለት በትዕግስት እስኪያነጥፍ ድረስ ደግሞ ደጋግሞ በመጠየቅ እንዲያነጥፍ ማድረግ ነው። በዚህ መንገድ ከጊዜ በኋላ አልጋውን ማንጠፍ ልማድ ያደርገዋል።
እነዚህን ከላይ የተገለፁትን ሦስት ዋና መንገዶች በመከተል እኛ ወላጆች ታዳጊ ልጆቻችንን ኃላፊነትን በቀላሉ ማስተማር እንችላለን። ከእኛ የሚያስፈልገው ሐሳቡና ትዕግሥት ማድረጉ ነው። ወላጅነት ትውልድ መሥራት ማነፅ መሆኑን ተረድተን በተረጋጋ መንፈስ ልጆቻችንን ለማስተማር እንትጋ። ለበለጠ ማብራሪያ ወ/ሮ ሣራን ማግኘት ለሚፈልግ በዚህ (Enatleenat@ gmail.com) ኢሜይል አድራሻቸው ሊያገኟቸው ይችላሉ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2013