ልጆች እንዴት ናችሁ ሠላም ነው? ልጆች ለዛሬ በሀገራችን ከሚነገሩ ተረቶች መካከል ስለበግና ፍየል የተተረተውን መርጠንላችኋል።
በዱሮ ጊዜ አንዲት በግና አንዲት ፍየል መስኩ ላይ ሣር ይግጡ ነበር። በጓም ፍየሏን “ወደ ቤታችን እንሂድ!” አለቻት። ፍየሏ ግን “ለምን? እኔ መጋጥ እፈልጋለሁ።” አለቻት። በጓ ግን ስለበረዳት “ዋሻው ውስጥ ለምን አልገባም?” ብላ ወደ አንዲት ቀበሮ ዋሻ ገብታ መሞቅ ጀመረች።
በዚህ ጊዜ አንዲት ጥንቸል መጥታ “በቀበሮዋ ቤት ውስጥ ያለው ማነው?” ብላ ስትጠይቅ በጓም “እኔ የተጠጋኝን ሁሉ በጭንቅላቴ የምማታው በግ ነኝ።” አለች።ጥንቸሏም ፈርታ ሄደች።
ጅቡም መጥቶ “በቀበሮዋ ቤት ውስጥ ያለው ማነው?” ሲል አሁንም በጓ “እኔ የተጠጋኝን ሁሉ በጭንቅላቴ የምማታው በግ ነኝ።” አለችው። ጅቡም ፈርቶ ሸሸ።
ቀበሮዋም መጥታ ተመሳሳይ ጥያቄ ስትጠይቅ በጓም ተመሳሳይ መልስ ስለሰጠቻት ሮጣ ተመለሰች። ከዚያም ቀበሮዋ ጅቡን ምን ማድረግ እንዳለባት ስትጠይቀው ጅቡም “ወደ ዋሻው ሄደሽ ‘በግ ሆይ፣ ገረድሽ መሆን እችላለሁ’ በያት አላት።
ቀበሮዋም እንደተባለችው ሄዳ በጓን “አንቺ ጋር ገብቼ እንዳገለግልሽ ገረድሽ ልሁን?” ብላ ስትጠይቃት በጓም ረዳት በማግኘቷ ደስ ብሏት “እሺ” ብላ ስትከፍት ቀበሮዋ ገብታ ከቤቷ አስወጣቻት።
ልጆች የራሳችሁ ባለሆነ ነገር ድርቅ ማለት ተገቢ አይደለም። የራሳችሁን ነገር ለማስመለሰ ደግሞ ሀይል
ሳይሆን ጥበብን መጠቀም ይቻላል። ሁልጊዜ ከሀይል ይልቅ ፍቅርና ብልሀትን የህይወት መመሪያችሁ አድርጉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2013