ኢትዮጵያ ሰማንያ በላይ ብሄረሰቦች የሳሏት የጋራ ምስላቸው ናት። ብዙ ሀሳቦች፣ ብዙ ታሪኮች የተዋሀዱባት የሚጸባረቁባት ድብልቅ እውነት ናት። ብዙ አይነት ባህሎች፣ ብዙ አይነት ስርዐቶች በአንድነት ያቆሟት የሰውነት ስጋና ደም እንዲህም ናት። በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ አለች። የእውነት ጥጋችንም ናት። ኢትዮጵያ ሲባል አቤት የምንለው ሁላችንም ነን። በደስታዋ የምንደሰተው በሀዘኗ የምናዝነው በጋራ ነው። ምክንያቱም የጋራ ስዕላችን ናትና።
በኢትዮጵያዊነት ውስጥ እኔነት የለም። እኛ ብለን በጋራ እንድንጠራ የሚያደርግ የጋራ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን። በትልቅ አለም ላይ የደመቅን ገናና ህዝቦች ነን። አሁን ላይ አንዳንዶች ይሄን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ አንድነት ለማላላት የተንኮል ሴራ ሲሸርቡ ይታያል። ውብ መልካችን እንዳይጠይም፤ ለዘመናት የገነባነው ታሪካችን እንዳይበላሽ ለጠላት ጆሮ መስጠት የለብንም። በትላንትናዋም ሆነ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የእያንዳንዳችን አሻራ ጎልቶ ይታያል።
ከትላት እስከዛሬ የሌለንበት ጊዜ የለም። የእኔና የእናንተ በጋራ መቆም ከሀይልና ከሞገስ ባለፈ ኢትዮጵያ ሙሉ ሆና እንድትታይ የሚያደርጋት ደማቅ ውበቷ ነው። ከመካከላችን አንዳችን ከጎደልን ኢትዮጵያ ጎዶሎ ናት ማለት ነው። ኢትዮጵያ እንዳትጎድል እኛ መጉደል የለብንም። ስለዚህም ሙሉ ሆነን እንድንታይ አንዳችን ለአንዳችን እናስፈልጋለን ማለት ነው። ኢትዮጵያን ከባህላችን፣ ከወግና ስርዐታችን ውስጥ ያበቀልናት የወርቅ ሙዳያችን ናት። ከመልካችን፣ ከታሪካችን ውስጥ የመዘዝናት የአብሮነታችን ውጤት ናት። በተናጠል እንገነባታለን ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል። በህብረት እንጂ በተናጠል የምትገነባ ኢትዮጵያ የለችም።
በውይይትና በመነጋገር እንጂ በቅራኔ የምትበለጽግ ሀገር የለችንም። በስራና በሀሳብ የበላይነት እንጂ በኔነትና በአጉል ራስ ወዳድነት የምትቆም ሉዐላዊ ሀገር የለችም። ቀለማችን እንዳይደበዝዝ.. የአባቶቻችን የአደራ ቃል እንዳይታጠፍ ለጋራ ጥቅም በጋራ መቆም አለብን። እኛ የኢትዮጵያ መልኮች ነን። እኛ የሀገራችን ውበትና ደም ግባት ነን። ኢትዮጵያ እያንዳንዱ ሀበሻ ከደሙ እያጠቀሰ የቀለማት ውብ ስዕሉ.. ውብ ፊደሉ ናት። በውብ ስዕላችን ውስጥ ነው ያለነው። በውብ ፊደላችን ውስጥ ነው የተጠለልነው።
እንደ ዜጋ በእውቀታችንም ሆነ በምንችለው በማንኛውም ነገር ለሀገራችን ምርጡን ልናደርግ ይገባል። የምንፈልጋት ሀገራችን በሀሳባችን ውስጥ ናት። አሁን ላይ ከዚም ከዛም የተለያዩ አፍራሽና ገንቢ ሀሳቦች የሚሰሙበት ጊዜ ላይ ነን። የበግ ለምድ ለብሰው ጥሩ መስለው በመታየት ሀገር ለማፍረስ ከላይ ታች የሚሉ በርካታ ግለሰቦች የመኖራቸውን ያክል በመልካምነት ለሀገራቸው የቻሉትን በጎ ነገር ለመስራት ደፋ ቀና የሚሉም አይጠፉም። እናንተ ከየትኛው ወገን ናችሁ? በጊዜአዊ ጥቅም ተታላችሁ ሀገራችሁ ላይ ክፉ የምታደርጉ ከሆነ እመኑኝ የእጃችሁን የምታገኙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ክፉዎች ሁልጊዜም እንደተቀጡ ነው። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የአምላክ አይኖች ክፉን በሚያደርጉ ላይ እንደሆኑ ልታውቁ ይገባል። የአባቶቻችን አደራ ይፋረደናል። የድሀ ህዝብ እንባ ይቀጣናል። እውነቱ ይሄ ነው። ያሉብንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች በንግግር እየፈታን ነገ ላይ ለምትፈጠረው ለአዲሲቷ ሀገራችን የበኩላችንን ማዋጣት ነው የሚበጀን።
በሀገራችን ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ከሀገር ፍቅር መገለጫዎች ውስጥ አንዱ ነው። ከስሜታዊነት ወጥተን በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ ለሀገራችንም ሆነ ለህዝባችን ምርጡን የምናደርግበት ጊዜ እንዲመጣ ሁላችንም መትጋት ይኖርብናል። ስሜት አደገኛ ነው.. መጥፎ ነገሮች ሁሉ ካለምክንያትና ካለማሰብ የተፈጠሩ ናቸው። የእስካሁኑ የሀገራችንም ችግር ከዚህ የዘለለ አይደለም። በስሜት ሀገር የምንመራ፣ በስሜት ታሪክ የምናበላሽ፣ በስሜት በወንድማማቾች መካከል ጠብን የምንዘራ፣ በስሜት ሀገር የምናፈርስ ንብረት የምናወድም የሰው ህይወት የምናጠፋ ብዙዎች ነን።
ስሜት ውስጥ እውቀት የለም..ስሜት ውስጥ ማሰላሰል የለም። ስሜት የሰይጣን መንፈስ ነው። ምንም ነገር ለማድረግ ከመወሰናችን በፊት በትክክለኛ ሁኔታ ላይ መሆናችንን ማጤን ያስፈልገናል። ሀገር በምክንያት እንጂ በስሜት አትመራም። አሁን ላይ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የምንሰማቸው ችግሮች ስሜት የወለዳቸው ስለመሆናቸው ተጠራጣሪ የለም። ከላይ እስከታች ድረስ ባለው ፖለቲካዊ መዋቅር ውስጥ በምክንያት የተቃኘ አሰራር ያስፈልጋል።
ስልጣን ህዝብ ማገልገያ እንጂ መታበያ ወይም ደግሞ መኮፈሻ አይደለም። አብዛኞቹ በሀላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ አመራሮች ቅንነት የጎደላቸውና ለህዝብ ከመታዘዝ ይልቅ ህዝብ መበደልን የመረጡ ናቸው። ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ወንጀል ከመሆኑም በላይ የህዝብን አደራ መብላትም ጭምር ነው። ብዙ ቦታ ለመታዘብ እንደሞከርኩት ከህዝብ ላይ የሚሰርቅ እንጂ ለህዝብ የሚሰጥ ባለስልጣን እንደሌለን ነው የተረዳሁት። አሁን ላይ ብዙ ነገራችን ልክ ያልመጣው ስልጣናችንን በአግባቡ ባለመጠቀማችን በፈጠርነው የተሳሳተ አካሄድ ነው። ህዝብ በሰጣቸው ስልጣን ሀገርና ህዝብን ከመጥቀም ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት በሚሯሯጡባት ሀገር ላይ ስልጣኔ መናፈቅ ዘበት ነው የሚሆነው።
ሀገራችን የተማሩ ብቻ ሳይሆኑ ህዝብን በቅንነት የሚያገለግሉ ባለስልጣናት ያስፈልጓታል። ስልጣናቸውን ህዝብ ከመጥቀም ይልቅ ህዝብ ለማስፈራሪያነት የሚጠቀሙ ባለስልጣናትን አውቃለው። ቤታቸውን በግንብ አጥረው፣ በዘበኛና በወታደር እየተጠበቁ፣ የተሰራ እየበሉ የተሰፋ እየለበሱ ከማርቼዲስ ሳይወርዱ በድሀ ሀብትና ንብረት እንዳሻቸው እየሆኑ በጎ ያደረገላቸውን ህዝብ መልሰው የሚጎዱ ብዙ የመንግስት ባለስልጣናት አያለሁ።
ስልጣን ከህዝብ ለህዝብ የህዝብ ነው። ስልጣን ለህዝብ መቆም፣ ለባለጉዳይ መነሳት፣ መልፋት ነው። ስልጣን ሀገርና ህዝብን በታማኝነት ማገልገል፣ ከራስ ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያ መስጠት እንደሆነ አውቃለሁ። በተቃራኒው ግን በስልጣናቸው ህዝብ እንዲፈራቸው የሚታበዩ፣ ህዝብ እንዲሸሻቸው ራሳቸውን አውሬ አድርገው የቀረጹ ብዙ ናቸው። ህዝብ በሰጣቸው ወንበር ላይ ሆነው ህዝብ እንዲፈራቸው፣ እንዲነሳላቸውና እንዲያጎበድድላቸው የሚፈልጉ በርካታ አመራሮች እዛም እዚም አሉ።
በዚች ሀገር ላይ የተባረኩ ነፍሶች ያስፈልጋሉ። ከትላንት እስከ ዛሬ ነውጥ ፈጣሪዎች ሆነው በክፉ የምናነሳቸው ሁሉ ያልተባረኩ ስለሆኑ ነው። ሊቀ ነብያት ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ያወጣው ስለተማረ ሳይሆን ስለተባረከ ነበር። የተማረው፣ ሁሉን የሚያውቀው አፈ ቀላጤው አሮን እያለ እግዚአብሄር ግን ሙሴን መርጦት ነበር። በየትኛውም የህይወት ጉዟችን ውስጥ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ጠቃሚ ሆነን እንድንቆም እግዚአብሄርን ማወቅ ይጠበቅብናል።
አለም በእውቀታቸው ጥግ የደረሱ በርካታ የተማሩ ልጆች አሏት። አሁንም ግን ሰቆቃ ውስጥ ናት። ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ፊደል የቆጠሩ ልጆች አሏት። ግን መከራዋ ሁሉ በእነሱ በኩል የመጣ ነው። ምክንያቱም ባልተባረከ ልብ ውስጥ የበቀለ እውቀት ስቃይና ሞት ከመሆን ባለፈ ደስታ መሆን አይችልምና ነው። ታላቅነታችሁን በእውቀታችሁ ውስጥ ሳይሆን በመባረካችሁ ውስጥ ፈልጉት። የተባረከ ልብ በሌሎች ላይ ስቃይን ለመፍጠር አይቻለውም። የተባረከ ሰውነት ለሌሎች የሚሆን ብዙ ደስታ ብዙ በረከት ያለው ነው። ስልጣኑን ለህዝብ ያላደረገ፣ በወንበሩ የሚመካ፣ በውሸትና በተንኮል በሀጢያትም ድሀ ሀገሩንና ድሀ ወገኑን የሚያታልልና የሚበድል የመንግስት ሹመኛ ታሪክ እንደሚወቅሰው የታመነ ነው።
በተባበረ ክንድ፣ በጸኑ መዳፎች ህያው አድርገን ያቆምናት ኢትዮጵያችን ዛሬም ጸንታ እንድትቆም የጥንቱ አብሮነታችን ዋጋ አለው። ከሀሳባችን መካከል ምርጡን እያዋጣን ባለንበት በቆምንበት ቦታ ሁሉ ለአንድነታችን የምንተጋ ከሆነ ክብራችንን ማንም አይወስድብንም። በአብሮነት የምትደነቀው የጥንቷ ኢትዮጵያ አልናፈቀቻችሁም? እኔ ግን ናፍቃኛለች። የአባቶቻችን የኩራት ጥግ የሆነችው፣ እውነት ባወቁ..ፍቅር በሰነቁ ነፍሶች የቆመችው ያቺኛዋ ኢትዮጵያ ናፍቃኛለች። አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ናፍቆኛል። ሳባዊቷን.. ምኒሊካዊቷን ጥቁር ወይዘሮ..ያቺን አክሱማዊቷን.. ቴዎድሮሳዊቷን..አብዲሳ አጋይቷን እመቤት ልቤ እሷን ይለኛል።
ያቺ የአፍሪካ ኩራት፣ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ሰንደቅ የነበረችው እንቆጳ ጊዮን ምድር ነፍሴ እሷን ትሻለች። ድሮነትን በዛሬአችሁ ውስጥ ፍጠሩ። የአባቶቻችን ፍቅር የአያት ቅድመ አያቶቻችን መዋደድ ዛሬ በእኔና በእናንተ ነፍስ ላይ ያቆንጉል። አለም ያከበራትን፣ የዮቶርን ርስት ቅድስቲቱን..የግሪክ ጸሀፍት፣ የአቴንስ ልኡላን በድርሰቶቻቸው ያወደሷትን ከነአናዊት ኢትዮጵያ በሁላችን ነፍስ ውስጥ እንድትበቅል እፈልጋለው። ቀለማችን እሷ ናት። እውነተኛ መልካችን፣ እውነተኛ ማንነታችን እሷ ናት።
ዛሬ ላይ ሌላ ነን..የአባቶቻችን ጸዐዳ መልክ መልካችን ላይ የለም። የአያት ቅድመ አያቶቻችን መልካም ነፍስ ነፍሳችን ላይ የለም..በፍቅር ያጌጡ የፊተኞቻችን ቅን ልቦች በልቦቻችን ላይ የሉም። ዛሬ ሌላ ነን። በወንድሞቻችን ሞትና መፈናቀል የምንደሰት፣ በሀጢያት የምንስቅ፣ ፈጣሪን በመርሳት የምንኖር እንደዚህ ነን። ብዙ ነገራችን አባቶቻችንን አይመስልም።
እነሱ የሌሎች መደነቂያ ነበሩ። ዛሬ እኛ በሌሎች መደነቅ ግብራችን ሆኗል። በሌሎች ሀገራት ባህልና ወግ እምነትና ስርዐት ኖረን የእኛ የሆነውን አጥተናል። እኛነታችንን ተነጥቀናል። የአባቶቻችንን የአደራ መልክ አጠይመናል። የሌሎችን ለብሰን፣ በሌሎች አጊጠን የእኛ የሆነውን ድንቅ ባህል፣ ውብ ተፈጥሮ በርዘናል። የውጭውን የባዕድ አስተሳሰብ አንድ ሳይቀር ወስደን ብዙዎች የሚፈልጉትን ምርጡን ሀበሻነት ከሌላ መጤ ባህል ጋር ቀይጠንዋል። አሁን እኛ የቱን እንደሆንን አናውቅም። ብዙ ነገራችን ድብልቅ ነው። የራሳችን መልክ ጠፍቶብናል። መሀል ላይ ነን..ገና ራሳችንን ፈልገን አላገኘነውም።
የእውቀት ማነስ በፈጠረብን አደገኛ ተጽዕኖ ከሁሉም ትልቁን ራሳችንን አጥተን የሰዎች ሆነናል። አባቶቻችን እንዲህ አልነበሩም። ሌሎች እየፈለጓቸው፣ ሌሎች እየናፈቋቸው በብዙ መፈለግ ውስጥ ኖረው ያለፉ ነበር። እኛ የነሱ ልጅ ዛሬ ላይ ስልጣኔ መስሎን ሀገር ሸጠን ባህል በርዘን በሀበሻና በፈረንጅኛ መካከል ላይ ቆመናል። አውሮፓና ኢሲያ ለአንድ ወር ሄደን አማርኛ የሚጠፋብን። ተወልደን ያደግንበትን ኢትዮጵያዊነት የምንረሳ እንዲህ ነን። ራሳችንንም ሆነን ታሪካችንን ለመታደግ ጊዜው አሁን ነው።
የእኛ የሆነውን ወግና ባህላችንን፣ እምነትና ስርዐታችንን፣ ቋንቋና ልማዳችንን ትሩፋታችንንም በሚገባ በመጠቀም አንቆ ከያዘን ፈረንጅኛ አስተሳሰብ እንወጣለን ብዬ አስባለሁ። ለአዲሷ ኢትዮጵያ አዲስ ሆነን መብቀል አለብን። የእኛ የሆነውን የአባቶቻችንን እውነት በመኖር ቀጣይ እድላችንን እንወስን እላለሁ። ያኔ ምናልባት ካሰብነው የስልጣኔ ጥግ እንደርስ ይሆናል። አለምም ራሳችንን ሆነን ሲያየን በባህላችንና በስርዐታችን ተደንቆ እኛ እነሱን ለመምሰላችን ቀርቶ እነሱ እኛን የሚመስሉበት ጊዜ ይፈጠራል። ስልጣኔ ያለው ራስን በመሆንና የራስ የሆነን ነገር በማድነቅ ውስጥ ነው። ወደ ኋላ ሄደን የተውነውን፣ የረሳነውን ማንነታችንን ማየትና መረዳት ይኖርብናል። ከስማችን ጀምሮ ሁሉ ነገራችን የሌሎች በሆነበት ሁኔታ ላይ ከዚህ የተሻለ አማራጭ የሚኖረን አይመስለንም። ወዛችሁን መልሱት። የመጣንበት፣ የበቀልንበት የአባቶቻችን ማህጸን ድንቅ ነው።
ሀገራችሁን በሀሳባችሁ አኑሯት እንጂ አትግደሏት። ኢትዮጵያን እንደፈለጋችሁ አድርጋችሁ ልትስሏት ብሩሹም ሸራውም እጃችሁ ላይ ነው። ልብ ልትሉት የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ባበላሻችኋት ሀገር ላይ የምትኖሩት እናንተና ልጆቻችሁ ናችሁና የዛሬ ድርጊታችሁ ነገም ይከተላችኋልና ምርጧን ሀገር ለመሳል ምርጥ ሰአሊ መሆን ይጠበቅባችኋል። በአባቶቻችን ስም እንጠራ። መልካም አባት፣ መልካም ትውልድ አናጺና መሀንዲስም በመሆን ይቺን ሀገር ላቆዩልን ጥበበኛ እጆች፣ ቅን ልቦች፣ አዛኝ ነፍሶች ራሳችንን እናስገዛ እያልኩ ላብቃ። ቸር ሰንብቱ።
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም