የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ፣ ቅዳሜና እሁድ የሚካሄዱ ሲሆን፤ የሊጉ የሳምንቱ ትልቁ ጨዋታ ‹‹ቀያይ ሰይጣኖቹን›› ማንቸስተር ዩናይትድንና ‹‹ቀያዮቹ››ን ሊቨርፑልን የሚያገናኘው ታሪካዊ ደርቢ እሁድ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ከአስራ አንድ ስዓት ከአምስት ጀምሮ ይካሄዳል። ጨዋታውም ተጠባቂ የሚያደርገው ‹‹ቀያይ ሰይጣኖቹ›› በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ ውጤቱ ወሳኝ በመሆኑ ነው።
ዩናይትዶች በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 5ኛና 6ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት አርሰናልና ቼልሲ ያላቸው የነጥብ ልዩነት አንድ ብቻ በመሆኑ አራተኛ ደረጃን አስጠብቀው ለመጓዝ ውጤቱ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ባለፈው ሳምንት ማንቸስተር ሲቲ ቼልሲን በሰፊ የጎል ልዩነት (ስድስት ለዜሮ) ማሸነፉ በተሻለ የግብ ክፍያ ሊቨርፑልን በልጦ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጡ በመሆኑ ቀያዮቹ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት እንዳይሰፋና ከዋንጫ ፉክክሩ ውጭ እንዳይሆኑ የሚችሉትን ያክል እልህ አስጨራሽ ትግልና ትንቅንቅ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምንም እንኳ ሊቨርፑል በማንቸስተር ሲቲ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አንድ ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ እያለው ቢሆንም የደርቢውን ጨዋታ አሸንፎ አስተማማኝ ልዩነት የሚፈጥር ነጥብ መያዝ ይፈልጋል፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ ኖሮዌያዊውን የቀድሞ ተጨዋቹን ኦሌገነር ሶልሻየርን ጊዜያዊ አሰልጣኝ አድርጎ ከቀጠረ ወዲህ ካደረጋቸው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል በአንዱ ብቻ አቻ ተለያይቶ ሎቹን በድል ማጠናቀቁና በጀርመናዊው የርገን ክሎፕ የሚመራው ሊቨርፑል ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ በመሆኑ ‹‹ጨዋታውን ማን ያሸንፋል›› የሚለውን ግምት ለመገመት በጣም አዳጋች አድርጎታል፡፡
18 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ያሸነፈው ሊቨርፑል የሊጉን ዋንጫ ካሸነፈ 29 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ቡድኑ ዘንድሮ እያሳየ ያለው አቋም ዋንጫውን ለማንሳት ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ ይህም ጨዋታው ሊቨርፑሎች የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ባለቤትነት ለማሳካት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ባላንጣቸውን ማንቸስተር ዩናይትድን ማሸነፍ ስለሚፈልጉ ለጨዋታው ልዩ ትኩረት ሰጥተው ወደ ሜዳ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ጨዋታው ወቅታዊ የውጤት አስፈላጊነትና ታሪካዊ ተፎካካሪነት የሚስተናገዱበት በመሆኑ በጉጉት እንዲጠበቅ ሆኗል፡፡
በሊጉ መርሃ ግብር ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ምሽት አራት ስዓት ከአርባ አምስት ላይ ይካሄዳሉ። ነገ ደግሞ ስድስት ጨዋታዎች የሚከናወኑ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በርንሌይ ከቶተንሀም ሆትስፐርስ እንዲሁም አርሰናል ወራጅ ቀጠና ውስጥ ከሚገኝው ሳውዝሃምፕተን የሚገኙባቸው ጨዋታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ቼልሲ በስታንፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ብራይተን ኤንድ ሆቭአልቢየንን የሚስተናግድበት ጨዋታ ለሌላ ቀን ተራዝሟል። ማንቸስተር ሲቲ 27 ጨዋታዎችን ተጫውቶ ፕሪሚየር ሊጉን በ65 ነጥብ ሲመራ፤ የመርሲሳይዱ ሊቬርፑል በ26 ጨዋታ በግብ ክፍያ ተበልጦ በእኩል 65 ነጥብ ይከተላል። ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ60፣ ማንቸስተር ዩናይትድ በ51 ነጥብ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ ሳውዝሃምፕተን፣ ፉልሃም እና ሀደርስፊልድ ታውን ደግሞ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ያሉትን የመጨረሻዎቹን ሦስት ደረጃዎች ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
ሰለሞን በየነ