ሁሉም ሰው በውስጡ የሞላውን ነገር ነው የሚያንፀባርቀው። ውስጡ በጥላቻ ከተሞላ ዕድሜ ልኩን ጥላቻን ይሰብካል። ውስጡ ፍቅርን የተሞላ በፈታኝ ጊዜ እንኳን ቢሆን ፍቅርን ይመርጣል፤ ይላበሳልም። ፍቅር ደግሞ እንደ ሰው የሚያስቆጥር አገርና ሕዝብን የሚያሻግር፤ በፈጣሪ ዘንድም የሚመረጥ ተግባር ነው። ምን ጊዜም ቢሆን ችግሮችን ለመፍታት ከፍቅር ከሚመነጩት አንድነትና ይቅርታ የተሻለ አማራጭ ኖሮ አያውቅም።
ሰዎች አንድ በሆኑ ቁጥር ኃይል ያሰባስባሉ፤ ጥቃት አድራሽ ጠላቶችንም ለመቋቋም ተጋፍጠው ለማለፍ አይቸገሩም። ኢትዮጵያችን ዛሬ ላይ አንድ ሆኖ የሚቆምላት፣ የሚያበረታታት እንጂ ችግሮቿን እየመዘዘ፤ ቁስሏን እየነካካ በእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚሆናት አትፈልግም። ይልቁንስ ቁስሏን እየጠረገ እንዲደርቅላት ጨርሶም እንድትፈወስ የሚያደርግ እውነተኛ መድኃኒት የሚያስገኙላትን ጽኑ ዜጎቿን ትፈልጋለች። የችግሮቹ የመፍትሄ አካል የሚሆኑ ዜጎቿን ካጣች ግን ለማንም የማትሆን በምኞትና በተስፋ ተስላ የምትቀር አገር የመሆኗ ነገር አይቀሬ ነው።
ዛሬ ላይ ይህች ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር ለመበታተን፤ ሕዝቧንም ለችግርና እንግልት ብሎም ለሞት ለመማገድ ታጥቀው በተነሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተከባለች። የውጭዎቹ ለምን እንደዚህ እንደሚያደርጉ ሀቁን ሁላችንም እናውቃለን፤ ከእነሱ እኩል እንዳንሆን፣ ሰርተን እንዳንለወጥ፣ በሀብታችንን ተጠቅመን የእነሱን እጅ ከማየት እንዳንወጣ፤ ሁል ጊዜ በድህነት መዝገብ ላይ ተጽፈን ደጅ ስንጠናቸው እንድንኖር በመሻት ነው። የተወሰኑት የውጭ ኃይሎች ደግሞ የተፈጥሮ ሀብታችንን አልምተን እንዳንጠቀምና የእኛ ልማት የሚያስፈራቸው በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያን ሰላም የሚነሷት፣ ሕዝቦቿን የሚያፈናቅሉትና የሚገድሉት ግን የእኛው ጉዶች ናቸው። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የእነዚህን ኃይሎች ሴራ ተሸክመው የአገራቸውን ሰላም የሚነሱ ባንዳዎች አሉ። አባቶቻችን በስንት መስዋዕትነት አንድነቷን አስጠብቀው ያቆዩአትን አገር ለሥልጣን ሽሚያና ለግል ጥቅም ሲሉ አገራቸውን እንደ ሶሪያ፣ ሊቢያና የመን እንድትሆን የሚሰሩ ባንዳዎች መኖራቸው በተግባር እየታየ ነው።
ዛሬ ላይ የሚያማምሩ ከተሞቻቸው ፈራርሰው ሕዝባቸው ለስደትና እንግልት ብሎም ለሞት የተዳረጉት እነ ሊቢያና የመን ሲጀምራቸው እንደዚህ ነበር ያደረጋቸው፤ እርስ በእርሳቸው መደማመጥ አቅቷቸው እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሰይጣናዊ መንፈስ ታውረው፤ የእኔ ወገን ሥልጣን ላይ ካልወጣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በማለት የማያቋርጥ ግጭት ውስጥ ገብተዋል። የውጭ ኃይሎችም ይህንን ቀዳዳ ተጠቅመው ግጭቱ ላይ ቤንዚን በማርከፍከፋ በእነዚህ አገራት ላይ ዛሬ የምናየውን አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ታዲያ እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ምን እንማራለን? ወይስ እኛም እንደነሱ «እኔ ካልበላሁት ጭሬ ላፍሰው» በማለት ለወንበር ጥማት ብለን በብዙ ሺዎች ደምና አጥንት የተገነባችን አገር ለማፍረስ ሌት ተቀን እንሰራለን። እንግዲህ ምርጫው የእኛው ቢሆንም ቆም ብሎ በሰከነ አእምሮ ማሰብ መቻል ግን ችግሩን ባያስቀረውም የሚያስከትለውን ጉዳት ሊቀንሰው ይችላልና ሰከን እንበል።
የሙስሊሙም፤ የክርስቲያኑም ሃይማኖት የሌለውም ጭምር መኖሪያ የጥቁሩም፣ የቀዩም የሁሉም ማደሪያ የሆነችን አገር በብሔር በቡድን አልያም በሃይማኖት ተከፋፍለን እንቃረጣት ካልን ጉዳቱ የከፋ ይሆናል። ችግሩም በየቤታችን መምጣቱ አይቀርም። ቀድም ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ እንዳለው የአገሬ ሰው የምናየውና የምንሰማው ሁሉ በእኛ ላይ አይደርስብንም ብለን የጦርነት የአልቂት ነጋሪት ከመጎሰም መቆጠቡ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም አለው።
እስከ ዛሬ እኮ ሃይማኖታችን አልያም ብሔራችን አይደለም አብሮ ያኖረን ኢትዮጵያዊነታችን አልፎም ሰው መሆናችን እንጂ። ዛሬ ላይ ሰው መሆን እንኳን ቢያቅተን እንዲያው ለአንዲቷ አገራቸን ስንል ለምን ሰከን ብለን ችግር ፈጣሪ ሳይሆን የመፍትሄው አካል ለመሆን አቃተን። ምክንያቱም ዛሬ በስሜት አልያም በግብታዊነት የጀመርነው የሃይማኖትም ይሁን የዘር ፍትጊያ ነገ ላይ የሚያስከፍለን ዋጋ ቀላል የሚባል አይሆንም ።
አቀንቃኙም ……ተዋዶ ያለበት
እስላም ክርስቲያኑ
ተዘነጋኝ እንዴ ኢትዮጵያ መሆኑ…
አንቺም በሃይማኖትሽ እኔም በሃይማኖቴ
መኖር እንችላለን አይጠበንም ቤቴ…..! ያለው እኮ በምክንያት ነው። እስከ ዛሬ የኖርነው ኑሮ ሃይማኖትንና ዘርን ማዕከል ያላደረገ ሰው በመሆናችን ብቻ አብረን ተዋደን የኖርን መሆናችንን የሚያመላክት ነው። አሁን ምን ተፈጠረ የተለወጠው ነገርስ ምንድን ነው። እንደ እኔ እንደ እኔ ታሪክን ያለመረዳት፣ በስሜት መነዳት ብሎም ጥቅመኝነት ያመጣው ጣጣ ይመስለኛል። ነገር ግን ጥቅምን ማሰብ የት ላይ ቆሞ? የፈረሰች የተበተነች አገር እኮ ለማንም አትጠቅምም፤ እንኳን ጥቅሙ ይቅርና ሰርተው ያገኙትን ሀብት መና መቅረቱ አይቀርም።
እንዲያው ነገሮችን ከራሳችን ጥቅም አኳያ ብቻ የማየት ትልቅ ችግር አለብን እንጂ አሁን ላይ የሚታየው እሰጣ ገባ መዘዙ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ነው። በተለይም በሃይማኖት የሚጀመር ፉክክር ደግሞ መጨረሻው እጅግ አስፈሪ ነው። በመሆኑም ሰከን በሉ። ሁሉም ችግር በእርጋታ፣ በጊዜው ይፈታል።
አንድነታችን ፈርሶ ከተባላን የላስቲክ ቤት ወጥረን ጎናችንን የምናሳርፍበት የአጥር ጥግ የምናጣበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል። ጊዜው አስቸጋሪ ከመሆኑ አንጻር ትእግስት እጅጉን ያስፈልገናል። ሶሪያና ሊቢያን ዕጣ ፈንታቸው በዚህ መልኩ ለመደምደሙ መንስኤው ይኼው አልጠግብ ባይነትና ሕዝብን ከሕዝብ ለማናከስ የሚሸረቡ ሴራዎች ናቸው።
በመሆኑም እኛም ዛሬ ላይ በአገር ውስጥ ቁጭ ብለው ከውጭ ጥላቶቻችን ምንዳ እያገኙ እኛን ለማባላት የሚጥሩ ኃይሎችን ከምን ጊዜውም በላይ ተጠንቅቀን መጠበቅ አለብን ። ኢትዮጵያዊነት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለውን ባንዲራ ለብሶ ፎቶ በመነሳት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ይልቁንም በሥራ በምግባር በመቻቻል አንዱ የአንዱን ሃይማኖት በማክበር፤ ብሔር ከብሔር እንዲስማማ እንዲጋባ እንዲዋለድ በጠቅላላው አገር በአንድነትና በህብረት እንድታብብ ማድረግንም ይጨምራል።
ኢትዮጵያዊነት ለእድገቷ እውቀት፣ ገንዘብንና ላብን ማፋሰስ፣ ለሰላሟ ደግሞ ዘብ ቆሞ ደም ማፍሰስን ይጠይቃል። አገር በተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በሕዝቦቿ ጥንካሬና መስዋዕትነት ነው ታፍራና ተከብራ የምትኖረው። ስለዚህ ነገ ለእኛም ሆነ ለልጆቻችን የተመቸች አገር ለማድረግ ሁላችንም ኃላፊነታችንና አገራዊ ግዴታችን በንቃት መወጣት ይኖርብናል። ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥማትም እነዚህን ፈተናዎች አልፋ ድል ለመቀናጀት ዛሬም የልጆቿን ሁለተናዊ ተሳትፎ ትፈልጋለች።
በእምነት
አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም