
አዲሰ አበባ፦ አስትራዜኒካ የተባለውን የኮቪድ 19 ክትባት አንድ ሚሊዮን 413 ሺህ ሰዎች መከተባቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጤና ሚኒስቴር የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ላቀው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ ያለውን ክትባት በየደረጃው በሁሉም ክልሎች ተዳራሽ ማድረግ በመቻሉ የተከታቢው ቁጥር ጨምሯል። በአሁኑ ወቅትም ለአንድ ሚሊዮን አራት መቶ
አሥራ ሦስት ሺ ሰዎች ክትባቱን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
ክትባቱን ለመስጠት መጀመሪያ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ስለነበረባቸው የመዘግየት ሁኔታ ነበር ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ ክትባት ለሚሰጠው የጤና ባለሙያ ሥልጠና መስጠት፤ ለክትባቱ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችም ጊዜ የሚፈልጉ በመሆናቸው ክትባቱን በሁሉም ክልሎች እኩል ማስጀመር እንዳልተቻለ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ጠረፋማ አካባቢዎችን ጨምሮ ከአንድ ሺ በላይ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 20 ሺ የሚጠጉ ቀበሌዎች ስድስት ሺ የጤና ተቋማት እንዳሉ ያመለከቱት አቶ ዮሐንስ፤ በክትባቱ ሁሉንም ቦታዎች ለማድረስ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ አምስት ቀን መውሰዱን አስታውቋል።
እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ክትባቱ ወደ አገር ውስጥ እንደገባ በሳምንቱ ክትባቱን መስጠት መጀመሩን ያስተወቁት አቶ ዮሐንስ፣ አሁን ላይ ክትባቱ ለሁሉም በሚባል መልኩ ተደራሽ መሆኑን ገልፀዋል። በሌላ በኩል የበዓል ቀኖች መደራረብ፤ በረመዳን ፆም ምክንያት ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች በብዛት ባለመንቀሳቀሳቸው ክትባት መስጠቱ መጓተት እንደታየበት አመልክተዋል።
በእርዳታ የተገኘው ሲኖፋርም የተባለው ክትባት በአዲስ አበባ ብቻ በሥራ ምክንያት ከሕዝብ ጋር የሚገናኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተከተቡ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ፣ ይህ ቁጥር ከላይ የተጠቀሰው ቁጥር ውስጥ የማይካተት መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ እየተሰጠ ያለው ይኸው ሲኖፋርም የተባለ ክትባት ለጋዜጠኞች፣ ለፖሊሶች፣ ለጉምሩክ ሠራተኞች፣ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤተ ሠራተኞች፣ ለውልና ማስረጃ ሠራተኞች፣ ለባንክ ሠራተኞች በአጠቃላይ በሥራቸው ምክንያት ከብዙ ሰው ጋር የሚገናኙ ሰዎች የሚከተቡበት መሆኑንም አስታውቀዋል።
አስትራዜኒካ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ዕድሜያቸው ከፍ ያለና ሌሎች በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች ሲወስዱት ቆይተዋል ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ አሁን ደግሞ ሲኖፋርም ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተከተቡት እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ክትባት ወረርሽኝን ለማጥፋት ዘላቂ መፍትሄ እና ዋና መሣሪያ ነው የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ክትባቱ ባልተጠናቀቀባቸው አካባቢ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየአካባቢያቸው በጤና ተቋማት በመገኘት መከተብ የሚገባቸው መሆኑን አሳስበዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም