
አዲስ አበባ፦ የሁሉንም ሜጋ ፕሮጀክቶቻችንን ሪቫን እየቆረጥን ለዓለም ኢትዮጵያዊነት ማለት ነፃነት እና ክብር መሆኑን እናረጋግጣለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ ። የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ የማይደራደር ሕዝብ መሆኑንም አመለከቱ።
ጠቅላ ሚኒስትሩ ትናንት የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው በከፈቱበት ወቅት፣ ከሰመራ ኢንደስትሪያል ፓርክ ባለፈ በሁሉም ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ሪቫን እየቆረጥን ለዓለም ኢትዮጵያዊነት ማለት ነፃነት እና ክብር መሆኑን እናረጋግጣለን ብለዋል።
የየትኛውንም አገር የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሀሳብ ሳንቀበል ብልጽግናችንን እውን እያደረግን እንቀጥላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ኢትዮጵያዊነት ማለት ነፃነት እና ክብር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን በቅኝ ያልተገዛን እና የማንገዛ ያልተንበረከክንና የማንንበረከክ ሕዝቦች መሆናችንንም አመልክተዋል።
የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ የማይደራደር ሕዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለወደብ ቅርብ በሆነችው ሰመራ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ በአንድ ዓመት ተገንብቶ መጠናቀቁ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ለማርካት ቁርጠኞች መሆናችንን ያሳያል ብለዋል፡፡

የአፋር ክልል በተለያዩ ማዕድናት የበለጸገና ለወደቦች የቀረበ መሆኑን አመልክተው፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ገብተው የሚሰሩ ኢንቨስተሮችን በአግባቡ መቀበልና ማስተናገድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ፓርኩ በአጭር ጊዜና በጥራት መሰራቱ የሚያስደንቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፓርኩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በሃይማኖትና በብሔር ሳንከፋፈል በጋራና በአንድነት ኢትዮጵያን እናበለጽጋለን ብለዋል፡፡
የፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ50 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ፤ በውስጡ 5 ሺ 500 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ስምንት የማምረቻ ሕንፃዎችን የያዘ፤ ለማምረቻ ኢንዱስትሪ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ነው።
ፓርኩ አገሪቱ እየተገለገለችበት ከምትገኘው የጅቡቲ ወደብ እና ሌሎች በአቅራቢያ ለሚገኙ ወደቦች በቅርብ ርቀት መገኘቱ በወጪ ንግድ ዘርፍ ለሚሰማሩ አምራቾች ተፈላጊ እንደሚያደርገው፤ በአገራቱ ከተገነቡ ፓርኮች 13ኛ መሆኑም በሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም