የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን በያዝነው ወር የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በዝግጅቱ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን የጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ሀይሌ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን:- ውድድሩና ፌስቲቫሉ በየዓመቱ መካሄዱ አላማውና ፋይዳው ምንድን ነው?
አቶ በላይነህ:- ይህን ውድድርና ፌስቲቫል ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ እንዲካሄድ የሚያደርገው ከፍተኛ አላማና ፋይዳ ስላለው ነው። የኢትዮጵያ ብሔርና ብሔረሰቦች ህዝቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆነውን ባህላዊ ስፖርት አንዱ ክልል ከአንዱ ክልል፣ አንዱ ከተማ አሰተዳደር ከአንዱ ክልል እና ከተማ አሰተዳር በከፍተኛ ሁኔታ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችና መላው የሀገራችን ህዝቦች ከመሆናቸው አንጻር፤ አንዱ አርሶአድር ከአንዱ አርሶአደር የተለያየ ልምድ የሚያገኙበት ነው። በቀጣይ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በሌሎች የአለም ሀገራት የባህል ስፖርቶቻችን እንዲታወቁ ውድድሩ ትልቅ ሚና ይጫዎታል። ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የመጀመሪያው የአለም የባህል ስፖርት ፌስቲቫል ብራዚል ላይ በተካሄደበት ወቅት በፌስቲቫሉ ኩርቦ የምትባለውን የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርት ጨዋታ ለአለም ማስተዋወቅ ችለናል። ከዚህ አንፃር ውድድሩና ፌስቲቫሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ መካሄዱ በቀጣይ ባህላዊ ስፖርቶቻችን ወደ ኦሊምፒክ ስፖርት የሚመጡበትን ሁኔታ በር የሚከፈት ነው። ስለዚህ ይህ እቅዳችን እንዲሳካ ፌዴሬሽኑ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በርካታ ስራዎችን መስራት ይጠበቅበታል፡፡
በኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውስጥ በኦሊምፒክ ከሚካሄዱ ስፖርቶች የማያንሱ ስፖርቶች አሉ፡፡ እነዚህ ስፖርቶች በኦሊምፒክ ውድድሮች እንዲካተቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል። የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻና አጋር ተቋማትና ድርጅቶች የባህል ስፖርቱ እንዲጠናከርና በአለም መድረክ ገኖ እንዲወጣ የበኩላቸውን ደጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። በአጠቃላይ ባለደርሻና አጋር አካላት ድጋፍ የሚያደረጉ ከሆነና በአንድነት ለአንድ አላማ ከሰራን የባህል ስፖርቱ በአለም መድረክ የማይታወቅበት ምንም ምክንያት የለም።
አዲስ ዘመን፡- የባህል ስፖርት ፌስቲቫሉ ባለፈው ዓመት ለምን አልተካሄደም? አቶ በላይነህ፡- ባህል ስፖርቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የማንነታቸው መገለጫ በመሆኑ በየዓመቱ ሊካሄድ ይገባ ነበር። ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን 19ኛው ጠቀላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የባህል ስፖርት ወድድርንና ፌስቲቫሉን እንዲያዘጋጅ ዕድል የተሰጠው ቢሆንም፤ ፌዴሬሽኑ ሙሉ ዝግጅቱን ካጠናቀቀ በኋላ በሀገራችን በነበረው ወቅታዊ የጸጥታና አለመረጋጋት ምክንያት ውድድሩና ፌስቲቫሉ እንዲራዘም የተደረገበት መንገድ ነው ያለው። አዲስ ዘመን:- ኦሮሚያ ክልል ይህን ውድድርና ፌስቲቫል ለማዘጋጀት እድሉን እንዴት አገኝ? አቶ በላይነህ:- 16ኛው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ውድድርና 12ኛው የኢትዮጵያ ባህል ሰፖርት ፌስቲቫል ከየካቲት 16 እስከ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ‹‹የባህል ስፖርት ተሳትፏችን ለሰላምና ለአንድነታችን›› በሚል መሪቃል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምእራብ ሸዋ ዞን በአንቦ ከተማ አዘጋጅነት የሚካሄድ ይሆናል።
ውድድሩና ፌስቲቫሉን የአምቦ ከተማ ለማዘጋጀት በጠየቀው ጥያቄ መሰረት የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን 20ኛው ጠቅላላ ጉባኤውን መሰከረም 12 ቀን 2011ዓ.ም አካሂዶ፤ ጠቅላላ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ የአምቦ ከተማን በመምረጡ ውድድሩንና ፌስቲቫሉን ከተማዋ እንድታዘጋጅ እድሉን አግኝታለች፡፡ አዲስ ዘመን:- ውድድሩና ፌስቲቫሉ እንዴት ወደ የካቲት ወር ሊመጣ ቻለ? አቶ በላይነህ:- ውድድሩና ፌስቲቫሉ በጀት በሚዘጋበትና የበጀት እጥረት በሚገጥምበት ግንቦትና ሰኔ ወራት ላይ የሚካሄድ ስለነበር፤ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በበጀት እጥረት ምክንያት ውድደራቸውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ይቸገሩ ነበር። ባህል ስፖርታችን የማንነታችን መገለጫ ስፖርት ስለሆነ ከማንኛውም ስፖርት በፊት ቀድሞ ውድድሩ መካሄድ እንዳለበት በመታመኑ ነው፡፡ 20ኛው የፌዴሬሽኑ ጠቀላላ ጉባኤ ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት ውድድሩ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተሳካ እንዲሆን ጠቅላላ ጉባኤው የካቲት ወር ላይ እንዲካሄድ ወስኗል።
በመሆኑም አሁን ላይ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ምንም አይነት የበጀት ችግር ሳይገጥማቸው የውስጥ ውድድራቸውን እያካሄዱ ይገኛሉ። ቡዙ ክልሎችም የውስጥ ውድድሮቻቸውን ጨርሰው ስፖርተኞቻቸውን ቅድመ ሁኔታ ሪፖርት አድርገውልናል። ክልሎችና ከተማ አሰተዳደሮችም ውድድሩን የሚመጠን ስፖርተኞችን ይዘው የሚቀርቡ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን:- ስንት ስፖርተኞች፤ በስንት የስፖርት አየነቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል?
አቶ በላይነህ:- ዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ውድድራቸውን ያካሂዳሉ ተበሎ ይጠበቃል። መረጃው በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተጠናቀረ ቢሆንም ከ900 በላይ ስፖርተኞች ይሳተፉሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ህግና ደንብ አውጥቶላቸው ወደ ውድድር በገቡ 11 የባህል ሰፖርት አይነቶች ተሳትፎ ይደረግባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን:- በዘንድሮው የባህል ሰፖርት ውድድር ለየት ያሉ የስፖርት ውድድሮች ይካሄዳሉን?
አቶ በላይነህ:- በዘንድሮው የባህል ሰፖርት ውድድር በ‹‹ቀስትና በኮረቦ ድብልቅ›› ወንድና ሴት ተደባልቀው የሚጫወቱበት የስፖርት ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑ ባህል ስፖርት ውድድሩንና ፌስቲቫሉን ልዩ ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን:- የባህል ስፖርት ውድድሩንና ፌስቲቫሉን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅቱ ምን ይመስላል? ከባለፈው ዓመት ለየት ያለ ተሞክሮስ አለ?
አቶ በላይነህ:- ውድድሩና ፌስቲቫሉ የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ባህል ሰፖርት ፌዴሬሽን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሰራዎችን ሰርቷል። በዚህም ውድድሮቹን በብቃት የሚመሩ ዳኞችን አሰልጥኗል። ፌዴሬሽኑ ለባህል ስፖርት ኢንስትራክተሮችና በከፍተኛ ደረጃ ለሚገኙ ዳኞች የዳኝነት ስልጠናዎችን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር እንዲሰጥ አድርጓል:: በየክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ ችሎታቸውና ብቃታቸው ተመዝኖ 16 የባህል ሰፖርት ኢንስትራክተሮች ውድድሩን እንዲመሩ ተመርጠዋል:: እነዚህ የተመረጡ ዳኞች ለበርካታ ዓመታት ባህላዊ ስፖርቱን በዳኝነት የመሩ በመሆናቸው ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፌዴሬሽኑም ለውድድሩ የሚመጥኑ ዳኞችን መልምሏል፡፡ አምቦ ከተማን በተመለከተ፤ በተጨባጭ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በጋራ አምቦ ከተማ እያደረገች ያለው ዝግጅት ተገምግሟል፡፡ ወደ ከተማዋ ከመሄዳችን በፊት ቀድመን ‹‹ቼክሊስት›› በመላክና እኛም በከተማይቱ ተገኝተን በቼክሊስቱ መሰረት ግምገማ አድርገን ምንም ክፍተት ሳይኖር ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ተገኝተዋል። ለስፖርተኞች፣ ለአሰልጣኞች፣ ለቡድን መሪዎች፣ ለአስተባባሪዎች እና ለዳኞች ማደሪያ የሚሆኑ ከ900 በላይ አልጋዎች ቀድመው ተዘጋጅተዋል። ከጸጥታ አኳያ ማህበረሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ በርካታ የቅስቀሳ ስራዎች ተሰርተዋል። ከተማዋ የተለያዮ ኮሚቴዎችን በማደራጀት የስፖርት ውድድሩ በተሳካ ሁኔታና በሰላም እንዲጠናቀቅ ወደ ስራ የተገባበት ሁኔታ አለ። በመሆኑም በአሁኑ ስዓት አምቦ ከተማ ፍጹም የተረጋጋና ሰላም የሰፈነባት ከተማ ከመሆኗ አንፃር ውድድራችን ፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነትና ሰላም በተሟላበት ሁኔታ እንደሚካሄድ ተሰፋ አለን።
በአጠቃላይ በከተማይቱ ያለው ዝግጅት በጣም ጠሩና የደመቀ ነው። ቁሳቁስን በተመለከተ፤ የባህል ስፖርት ውድድሩን በተሳካ መንገድ ለማካሄድ የሚያገለግሉ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ቀደም ተብሎ ተገዝተዋል:: የባህል ሰፖርት ውድድር ለማካሄድ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችም በአግባቡ አደራጅተን አዘጋጀተናል። አስተናጋጇ ከተማም ሙሉ ለሙሉ የመወዳደሪያ ቁሳቁሶችን፣ ሜዳዎችንና ፈረሶችን አሟልታለች።
ለአብነትም ለፈረስ ጉግስና ሸርጥ መወዳደሪያ የሚሆኑ ከ400 እስከ 600 ሜትር እርዝመት ያላቸው ደረጃውን የጠበቁ ሜዳዎች ተዘጋጅተዋል:: በቂ የሆነ የገና ጨዋታ ውድድር የሚካሄዱባቸው ሜዳዎችም ዝግጁ ናቸው፡፡ ገበጣና መሰል ስፖርቶች የሚካሄዱባቸው ሁለት ደረጃውን የጠበቁ የመወዳደሪያ አዳራሾችም ተዘጋጅተዋል፡፡ በጀትን በተመለከተ፤ እንደፌዴሬሽን ውድድሩ የተሳካ እንዲሆን በርካታ ስራዎችን ሰርተናል። በዋነኛነት ለዚህ ውድድር መሳካት ፌዴሬሽናችን ቁርጠኛ አቋም ይዞ ከተበጀተለት በጀት ላይ የባህል ስፖርት ውድድሩንና ፌስቲቫሉን በተሳካ ሁኔታ ለመምራት የሚያስችል በቂ የሆነ ዝግጅት አድርጓል::
ይህንን ውድድር ከኢፌዲሪ ሰፖርት ኮሚሽን ጋር በጋራ በመተባበር የምንመራው በመሆኑና፤ ኮሚሽኑም የበጀት ድጋፍ ያደረገልን በመሆኑ ምንም አይነት የበጀት ችግር አይገጥመንም።
አዲስ ዘመን:- በቅድመ ዝግጅቱ ወቅት የገጠማችሁ ችግር አለ?
አቶ በላይነህ:- እንደ ችግር ብዬ የታየው ሁለት ክልሎች በተጨባጭ በውድድሩ ላይ መሳተፍ እደማይችሉ አሳውቀዋል። በተለይም ቤኒሻንጉል ጉምዝ የውስጥ የባህል ስፖርት ውድድራቸውን በክልላቸው ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ማካሄድ ባለመቻላቸው ‹‹አንሳተፍም›› የሚል ሀሳብ እያነሱ ነው። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ከአሁን በፊት ክልሉን ወክለው ሲወዳደሩ የነበሩ የባህል ስፖርት ስፖርተኞች የሚታወቁ በመሆኑ፤ እነዚህን ስፖርተኞች ባለው አጭር ጊዜ ዝግጅት አደርገው በውድድሩ እንዲሳተፉ በጽሁፍ ማሰጠንቀቂያ የላክንበት ሁኔታ አለ፡፡ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚወክላቸውን የተወዳዳሪ ስፖርተኞች ስም ዝርዝርና መረጃዎች የፊታችን ሰኞ ይልካሉ፡፡ በዚህ መሠረትም በውድድሩ ላይ የሚሳተፉና የማይሳተፉ የሚለዩ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን:- ውድድሩ በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነትና በሰላም እንዲጠናቀቅ ጸጥታ በማስከበር በኩል ምን አይነት የቅድመ ዝግጅት ስራ ተሰርቷል?
አቶ በላይነህ:- የጸጥታና የሰላሙን ጉዳይ በተመለከተ አንቦ ከተማ የጸጥታ፣ የመስተንግዶ፣ የጤና፣ የቅስቀሳና የሽብርቅ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ውድድሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ ትገኛለች። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ለዘጠኙ ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የውድድር ደንብ ስንልክላቸው የስፖርታዊ ጨዋነት ሰነዶችን አካተን ሰጥተናቸዋል፡ ፡ በስፖርታዊ ጨዋነት ሰነዱ ላይ ክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ ተወያይተው እንዲመጡ በደብዳቤ ያሳወቅን በመሆኑ፤ በከፍተኛ ሁኔታ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተወዳዳሪዎቻቸውን በስፖርታዊ ጨዋነት ገንብተው ይመጣሉ የሚል ተስፋ አለን። ቀጣይም በቅድመ ውድድር ስብሰባ ማለትም ውድድሩ የካቲት 16 ቀን 2011ዓ.ም ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፤ የካቲት 15 ቀን 2011ዓ.ም የቅድመ ውድድር ስብሰባ ይካሄዳል:: በባህል ስፖርት ውድድሩ ለመሳተፍ ለሚመጡ ሁሉም የስፖርት ሉካን የስፖርታዊ ጨዋነት ግንዛቤን ለመፍጠር ከወዲሁ ፕሮግራም ይዘናል። የባህል ስፖርት የማንነታችን መገለጫ ነው::
የማንኛውም ዜጋ ባህልና ወግ የሚንጸባረቅበት ስፖርት ከመሆኑ አንጻር ስፖርታዊ ውድድሩን በመቻቻልና በመከባበር እንደሚካሄድ እምነቱ ስላለኝ ስፖርታዊ ጨዋነት ይደፈርሳል የሚል እሳቤ የለኝም። ከዚህ በፊትም ባደረግናቸው መሰል ውድድሮች በሰላም የተጠናቀቁና ምንም የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር አጋጥሞን የማያውቅ በመሆኑ፤ ዘንድሮም እንደ ወትሮው በሰላም ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል። በአጠቃላይ ከቡድን መሪዎች፣ አሰልጣኞችና አሰተባባሪዎች ጋር በጋራ በመስራት ውድድሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ እንሰራለን። በዋናነትም የውድድሩ መሪቃል ‹‹የባህል ስፖርት ተሳተፏችን ለሰላምና ለአንድነታችን›› የሚል ስለሆነ ህዝባችን ወደ አንድነት መጥቶ ሀገራችን የተሻለች የሰላም ሀገር እንድትሆን ከምንም በላይ እንደፌዴሬሽን መሰራት ይጠበቅብናል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም መሪቃሉን አክብረው በፍጹም ሰፖርታዊ ጨዋነት ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን አጉለተው ውድድራቸውን እንደሚያካሂዱ ሙሉ እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን:- አካል ጉዳተኞች በባህል ስፖርት ውድድሩ ተወዳዳሪ ይሆናሉ?
አቶ በላይነህ:- አካል ጉዳተኞች በባህል ስፖርት ውድድሩ መሳተፍ ይችላሉ። ማለትም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ይወክሉናል ብለው ካመጡና አሸናፊ ሆነው ከመጡ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞች የሚሳተፉ ይሆናል። ነገር ግን እነርሱ ብቻ ተለይተው እራሳቸውን ችለው እርስበርስ የሚወዳደሩበት የስፖረት አይነቶችና ውድድሮች አላዘጋጀንም። አካል ጉዳተኖችና ሴቶች ላይ ትኩረት ሰጥተን አለመሰራታችን ክፍተት ነው። ከኢትዮጵያ ፓራ ኦሊምፒክ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በቀጣይ በዕቅድ ይዘን የምንሰራው የቤት ስራ ይሆናል። ዕቅዱንም ወደ ተግባር ለመለወጥ እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን:- የባህል ስፖርቱ እንዲያድግ ፌዴሬሽኑ ለማህበረሰቡ ምን ያህል ግንዛቤ እየፈጠረ ነው? አቶ በላይነህ:- የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን በርካታ ባለድረሻና አጋር አካላቶች አሉት። ከነዚህ ባለድርሻ አካላት ውስጥ በዋናነት የምንጠቅሰው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ነው። ፌዴሬሽናችን በያዝነው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ከ2008ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ቢያንስ ከ10 ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ የሁለተኛ ደረጃ የስፖርት ሳይንስ መምህራን የባህል ስፖርት የአንደኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና እየሰጠን ነው፡፡ በተጨማሪም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በርካታ ስራዎችን በመስራት ለ99 የስፖርት ሳይንስ መምህራን የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነትና የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጠተናል። መምህራኖቹም በስልጠናው ስለባህል ስፖርቱ ተገቢውን ግንዛቤ ጨብጠው ተማሪዎቻቸውን እያበቁ ይገኛሉ።
በዓመት እስከ176 ዳኞችን በማሰልጠን ስለባህል ስፖርቱ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እያደረግን እንገኛለን። ነገርግን ብዙ የተማሪ ቁጥር ባለባት ሀገር እነዚህን መምህራኖች ብቻ በማሰልጠን ግንዛቤ መፍጠር ይቻላል ተብሎ ባይ ታሰብም፤ ለወደፊት አጠናክረን በመስራት ግንዛቤው እንዲሰፋ ለማደረግ ፌዴሬሽኑ ጠንክሮ እየሰራ ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ላሉ የስፖርት ሳይንስ ተመራቂ ተማሪዎች የባህል ስፖርት ስልጠና እየተሰጠ ነው:: ስለባህል ስፖርቱ ግንዛቤ አግኝተው ወደ ስራው አለም ሲገቡ በተግበር ተማሪዎቻቸውን በማስተማር የባህል ስፖርተኞችን እንዲያፈሩ ለማስቻል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው። አዲስ ዘመን፡- ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ አቶ በላይነህ፡- በቀጣይ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስና በአለም መደረክ እንዲተዋወቅ ባለድርሻና አጋር አካላት ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርጉልን በፌዴሬሽኑ ስም ጥሪየን ላቀርብ እወዳለሁ። እንዲሁም 16ኛው የባህል ስፖርት ውድድርና 12ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጾ እንዲያደርግ በፌዴሬሽኑ ስም ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሠጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ በላይነህ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
ሶሎሞን በየነ