አውዳ’መታት ኃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ እርካታን ብቻ ይዘው የሚመጡ ባህላዊ እሴቻችን አይደሉም፤ መዝናኛም ናቸው። ታሪክ ይናገራሉ፤ ፖለቲካም ሊንፀባረቅባቸው ይችላል። (በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሁሉ ነገር በግልና ቡድን ማንነት ዙሪያ በሚሽከረከርባት ዓለማችን ይህ ብርቅ ሳይሆን እየሰለቸ ያለ ተግባር ነው።) ለዛሬው ግን ከእነዚህ ሁሉ ወጣ እንበልና ወደ አንድ፣ የዘንድሮው ፋሲካ ወደ አስመዘገበው “ሪኮርድ” እንምጣ – የኢኮኖሚ ሪኮርድ – “ሪኮርድ” ከተባለና መስፈርቱን ካሟላ ማለታችን ነው።
ከዓመት በአል መገለጫዎች አንዱ ገበያና ውሎው፤ ግብይቱ ነው። በተለይ እነፋሲካ፣ ገናና እንቁጣጣሽን የመሰሉት ያለ ገበያና ግብይት ነፍስ የላቸውም። ገበያና ግብይት ደግሞ ያለ ገበያተኛ አይሆንምና እሱንም እዚሁ ላይ ማካተት ተገቢ ሲሆን፤ ሁሉም ግን ያለ ኢኮኖሚ ወይም የመግዛት አቅም የሚታሰቡ አይሆኑምና የገበያ፣ ገበያተኛና ግብይት ምህዋሩ ኢኮኖሚ መሆኑን ገዥና ሻጭ ያውቁታል። በመሆኑም የዘንድሮው ፋሲካና እሱን የተሟላ ለማድረግ ሲባል ይከናወን ስለነበረው ግብይቱና ሥርአቱ ላይ ጥቂት ለታሪክ ማስታወሻ፤ የወደፊት ጥናት ጉዝጓዝ ይሆን ዘንድ አቅልመን እንለፍ።
አንድ ሰው ሁለት ነገሮችን እኩል ሊወድ ይችላል – ገንዘቡንና የሚገዛውን “ነገር”። ይሁን እንጂ በኢኮኖሚክስ ሕግ መሰረት ባ’ንዴ ሁለቱንም የራሱ ማድረግ አይችልም፤ ማለትም የሚፈልገውን (ለምሳሌ መኪና) ለማግኘት የግድ ገንዘቡን መክፈል (ማ(ው) ጣት) ይኖርበታል። ሻጭንም በዚሁ መንገድ ማሰብ ይገባል፤ ማለትም በሬውንም ገንዘቡንም የራሱ ማድረግ አይችልም። ገንዘቡን ለማግኘት የግድ መኪናውን መሸጥ ይኖርበታል። እንግዲህ እዚህ ጋር የጉዳዩ አስኳል (ፍሬ ነገር) ገንዘብ ወይም ኢኮኖሚ ሆኖ ይመጣል ማለት ነው። ይህንን ሰፊ ጉዳይ በዚሁ እናቆየውና “ገንዘብ” የሚለውን ጥለን “ኢኮኖሚ” የሚለውን አንጠልጥለን እንቀጥል።
የዘመኑ የዓመትባ’ል ገበያም ሆነ ግብይቱ እንደድሮው ማንም ሣንቲም የቋጠረ ሁሉ ዘው እያለ የሚፈልገውን መዥርጦ የሚወጣበት የጋራ ሌማት አይደለም፤ ያ ላይመለስ ተረት ሆኗል። የዘመኑ ግብይት ሰው፤ ከሰውም ሰው ይመርጣል – የአስቱን “አይ ያለው ማማሩ”ን ያስቆዝማል።
ዛሬ ገበያው ያቀረበው ምርት ተጠቃሚ ለመሆን ገዥው እንደድሮው (ወርቃማው!!!) ዘመን የአላድና ባወንድ ባለቤት መሆን ምንም አያዋጣውም። ድሮ “ይዞ መገኘት” ነው የሚለው ቀልድም ዛሬ ፌዝ ሆኗል። ፌዝ የሆነበትም ምክንያት አንድ ገበያተኛ (ገዢው) ይዞ መገኘት ሳይሆን “ሆኖ መገኘት” ነው የሚጠበቅበት። “መሆን ማለት?” ለሚል “ባንክ ሆኖ መገኘት” – ገዥው ራሱ ተንቀሳቃሸ ባንክ ሆኖ ካልተገኘ አባ ከና የሚለው የለም። ይህን እንደ አጉል ማጋነን አድርጎ የሚወስድ ካለ ቀደም ሲል እንዳልነው እሱ እዚህ አገር አልነበረምና፤ አንድ በሬ 115 ሺህ፣ አንድ በግ 13 ሺህ … መሸጡን አልተረዳም ። ከበሬው ሳንወጣም ሌላው አስደናቂውና የደሀ-ሀብታም ልዩነት ጣሪያው ማሳያ የበሬው ውጤት (አንድ ኪሎ ስጋ) ከ500 እስከ 1000 (ለምሳሌ ካሳንችስ አካባቢ) ብር ድረስ መናሩና የልዩነቱ ልዩ ገደል ሆኖ መከሰቱ ነው።
(እዚህ ላይ ከጊዜያቸው ቀድመው የወደፊቱን የሚያመላክቱ ሰዎችን ማንሳት ተገቢ ሲሆን፤ አንዱም ኮመዲያን ተስፋዬ ካሣ ነው። የዛሬ 20 ዓመት ገደማ በግ ተራ ሄዶ ጠይቆ 347.00 ብር ቢሉት “ምነው ዲፕሎማ አለው እንዴ?” (በወቅቱ በዲፕሎም የትምህርት ማዕረግ የተመረቀ የሚቀጠረው በዚህ የብር መጠን ነበርና ነው። ዲግሪ ያለው 500.00) ሲል የቀለደው “ቀልድ” የዛሬውን ቢያይ ምን ይል ይሆን? ያሰኛል።)
ከዚሁ ከበግ ጋር በተያያዘ አንድ “ጆክ” ጣል በማድረግ የዓመት ባ’ል ገበያው ከገንዘብ በላይ የአገሪቱን አጠቃላይ ኢኮኖሚ እየፈለገ መሆኑ ላይ እናመላክትበት። በዚሁ ፋሲካ ሰውየው በግ ገዛ፤ ላዳ ታክሲ ጠራ፤ ተስማሙ። ባለታክሲው በጉን ፖርቶመጋሊያው ላይ ሊጭን እላይ ወጥቶ በማስተካከል ላይ እያለ “ምን እያደረክ ነው?” በማለት ባለበግ ተቆጣ። “ልጭነው” ይላል ባለ ላዳ። “በል ኋላ ወንበር ላይ አስቀምጠው።” ሲለው “እንዴ በግ …” ከማለቱ “እምልህን ትሰማለህ 11 ሺህ ብር የተገዛ በግ እኮ …”፤ ሾፌር ሆዬ በመደንገጥ “እንደሱማ ከሆነ ገቢና ነው …”። አበሻ እንዲህ…እንዲህ እያለ ነው እንግዲህ ታሪክን በትዝብት እያሸ፤ በ”ጆክ” እየለወሰ የሚያስተላልፈውና ዘመኑ ይህንን ይመስላል፤ እድገት / ልዩነቱም እንደዚያው።
እንደሚታየውም ሆነ እንደሚታወቀው ገበያችንና ስርአቱ አብደዋል፤ ጨርቃቸውን ከጣሉ ሰንብተዋል፤ “የእድሩ ስንፈት ነው እንጂ …” እንደተባለው ሁሉ፤ … ነው እንጂ ገበያችንና የግብይት ስርአቱ ይፈወሱ ዘንድ ህክምና ካስፈለጋቸው ጊዜው ዛሬ አይደለም። ያለወቅቱና እውቀቱ ከተበተባቸው ነፃነት ነፃ ሊወጡ እንደሚገባ ሲነገርም እንደዚያው። ሀላፊነት ከማይሰማው ነፃነታቸው፤ ከስርአት ግብይታቸው ሁሉ ነፃ ይወጡ ዘንድስ ቢሹም እስካሁን አልተቻላቸውም።
የአሁኑ ዘመን ገበያና ግብይቱ በምንም አይነት ስርአት፣ ደንብና መመሪያ፣ ስነምግባርና ሞራል እንደሚመራ ማንም አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም። ፆም ተይዞ በተፈታ ቁጥር በድፍን አገሪቱ የኪሎ ስጋ ዋጋ እላይ ወጥቶ ቁጭ፤ ክረምት አልፎ መስከረም በጠባ፣ ትምህርት ቤት ተዘግቶ በተከፈተ…፤ ሰላምና ፀጥታ ትንሽ ደፍረስ ባለ… ቁጥር በቃ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ቢሆን ወደኋላ የማይመለስ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አለ።
በበዓላትም ያው ሲሆን፤ ገና አልፎ ፋሲካ፣ እንቁጣጣሽ ተራውን ለመስቀል፤ ሞውሊድ አልፎ ረመዳን ሲመጣ…አብሮ እንኳን ሳይሆን ቀድሞ የሚመጣው ከጣራ በላይ የሆነና ገንዘብ ሳይሆን በስድስት ዲጂት የሚሰላ ምጣኔ ሀብትን (አንድ በሬ 115, 000.000) ብር ነው።
የእኛ አገር ገበያ አይኑን በጨው ያጠበ፤ ይሉኝታ ብሎ ነገር በህሊናው ሽው እንኳን የማይል፤ ራሱን በ”ነፃ…” ስም በወንጀል ያነፀ፤ የዶሮ ዋጋ የበሬን፣ የበሬ ዋጋ የጋሻ መሬትን የወረሱበትና ሁሉም ነገር ለሰሚ ግራ የሆነበት ያደባባይ ሚስጥር፤ የገበያ አሻጥር ነው።
ባጭሩ እያልን ያለነው ገበያና ግብይቶች (በተለይ የአውዳመት ግብይት) ነፃነትን በማያውቁ ነፃ ገበያዎች ተወሯል፤ በእንቅርት ላይ.. እንደሚባለው በዚሁ ላይ ደግሞ ንፋስ አመጣሽ (ለአንድ ሲሲ አልኮል መጠጥ እስከ 43 ሺህ ብር፣ ለአንድ ሲጋራ እስከ 1000 ብር የሚከፍሉ) ሀብታሞች እርስ በርሳቸው በመፎካከር (በዚህ ላይ የስልጣን መባለግ (economics of corruption)ን ጨምሩበት) ገበያውን የእብዶች አድርገውት ደሀው የት እንደሚገባ ጠፍቶበት የእነሱን የፉክክር፤ በየገበያው ባንክ ሆኖ የመገኘት ዜና ሲሰማ ውሎ ያድራል። (ከሰሞኑ የቢቢሲ “… አንድ በሬ 115 ሺህ…” ዜና እኔ የገባኝ በዚህች አገር በደሀና በሀብታሙ መካከል ምን ያህል ልዩነትና ኢፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል መኖሩን ለማሳየነት የተጠቀመው ቅኔ እንጂ የአንድ በሬ ጉዳይ አስደምሞት አለመሆኑ ነው።) መላ ያስፈልገዋል ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም