በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች ያለችው አዲስ አበባ ባስመዘገበችው ለውጥ ልክ ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ጨምሮ ሥራ አጥነት፣ ድህነትና ኢ-ፍትሐዊነት እየተንፀባረቀባት እንደሆነ ነዋሪዎቿ ይናገራሉ። በቀንና በሌሊት በጎዳና ላይ ከሚኖሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ለምኖ አዳሪውን ጨምሮ በቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን የሚያንቀሳቅስ ቱጃር ይኖርባታል። መኖሪያዎቿም እንዲሁ የከተማዋን ገጽታ ከሚያጠለሹ የላስቲክ ቤቶች፤ የደሃ ጉሮኖዎችና ወንዝ ዳር ከሚገኙ ደሳሳ ጎጆዎች ጀምሮ በወር በመቶ ሺህ ብር እና ከዚያም በላይ የሚከራዩ ትላልቅ ቪላ፣ አፓርታማዎች እና ህንፃዎች አሏት።
ከዘመናዊ የሪል ስቴት የመኖሪያ ቪላዎች እስከፈራረሱ የቀበሌና የወንዝ ዳር መጠለያና ላስቲክ ቤቶች ተቀላቅለው ያሉባት አዲስ አበባ ከተማ ከነችግሯም ቢሆን ዛሬም እንደ ሁልጊዜው ሁሉ በለውጥ ሒደት ላይ ትገኛለች። በተለይም አላፈናፍን ብሎ የያዛትን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ መካከል “የወንዞች እና የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ መናፈሻ” ፕሮጀክት አንዱ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው የወንዝ ዳርቻ የልማት ፕሮጀክት በአዲስ አበባ አቋርጠው በሚያልፉ ሁለት ታላላቅ ወንዞች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተሰራው ህዝብ በብዛት የሚኖርባቸው ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ የሚዘረጉ ወንዞች ናቸው።
እነዚህ ወንዞች የከተማዋን አካባቢዎች አቋርጠው የሚያልፉ ሲሆን፤ የእንጦጦ ተራራ 23 ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር እንዲሁም የአቃቂ ወንዝ ደግሞ 27 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ናቸው። ፕሮጀክቱ ታሪካዊ ወንዞችን እና የወንዝ ዳርቻዎችን መልሶ በማልማት አዲስ አበባን የከተማ ቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ፤ የጎርፍ መጥለቅለቅን በመቀነስና የህዝብ መናፈሻ ቦታዎችን፣ የብስክሌት መንገዶችን እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ የእግረኛ መንገዶችን በመፍጠር የከተማዋን ነዋሪዎች ደህንነት ማረጋገጥ፤ የአረንጓዴ ቦታዎች እና ተያያዥ አገልግሎት ዘርፎችን በማጠናከር የአገሪቷን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ህልም እውን የማድረግ ዓላማ ያለው ነው።
ለአዲስ አበባ አረንጓዴ ልማት፣ የተፈጥሮ ሃብቷን ለማሳደግ እና ለማስፋፋት የሚያስችል አስተዋፅዖ ይኖረዋል ተብሎ የሚታመነው የአዲስ አበባ የተፋሰስ ወንዞች ዳርቻ ፕሮጀክት የከተማዋን ነዋሪዎች ደህንነት በማሻሻልና የከተማዋን እይታ ይበልጥ በመለወጥ ረገድም ብዙ ሚና መጫወት የሚችል ነው። በተለይም በወንዞች ዳርቻዎች አካባቢ ያሉት የማህበረሰብ ክፍሎች ካለባቸው ስጋት መላቀቅ የሚችሉና ፕሮጀክቱ በሚፈጥራቸው የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች እንዲሁም ለጎብኚዎች የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት የውጪ አገርና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ወደ አዲስ አበባ መሳብ ያስችላሉ።
እነዚህን እና መሰለ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚሰጡት የተፋሰስ ወንዞች በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ። በርካታ ነዋሪዎችም የወንዞቹን ዳርቻዎች ተከትለው በተሰሩ ደሳሳ ጎጆዎች ውስጥ መኖሪያቸውን አድርገው ይኖራሉ። እኛም መኖሪያቸውን በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ በሚገኙ ወንዞች አካባቢ ያደረጉ የከተማዋን ነዋሪዎች ኑሮን በወንዞች ዳርቻ ላይ ማድረግ ምን ስጋት አለው?፤ እንዴት ባለ መንገድስ እየኖራችሁ ነው? በማለት ላነሳነው ጥያቄ ምላሽ ከሰጡን ነዋሪዎች መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ራስ መኮንን ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው ወንዝ አጠገብ የሚኖሩት ወይዘሮ አበበች ጌታሁን አንዷ ናቸው።
ወይዘሮዋ በአካባቢው ላለፉት 27 ዓመታት የኖሩና በስፍራው አራት ልጆችም አፍርተዋል። በግቢ ውስጥ በአማካይ ከአስር የሚበልጡ መኖሪያዎች አሉ። ነዋሪዎች ማዕድ ቤትና መጸዳጃ ቤትን በጋራ ይጠቀማሉ። መጸዳጃ ቤቱ ከመኖሪያቸው ይበልጥ ለወንዙ የቀረበ ነው። ምንም እንኳን ወንዙ በክረምት ወቅት የሚሞላ ቢሆንም በአሁን ወቅት ብዙም ስጋት የሌለባቸው እንደሆነና ከዚህ ቀደም ግን ጅቦች በቀን እየመጡ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
በአንድ ወቅት ህጻናት ልጆቻቸውን በግቢው ውስጥ ትተው ሰርግ ቤት በሄዱበት አጋጣሚ ገና ሳይመሽ በቀን ብቅ ያለው ጅብ ልጃቸውን ያስደነገጠውና በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ያዳኑላቸው መሆኑን አስታውሰዋል። ልጁ ውሻ መስሎት የተጠጋው ጅብ አንጠልጥሎ ሳይወስደው በመትረፉ ዛሬም ድረስ ሲያስታውሱት ፈጣሪን ያመሰግናሉ። ከዚህ ውጭ ወንዙን ተጠቅመው የተወሰኑ አትክልቶችን አልምተው ይጠቀሙ እንደነበርና እንደዛሬ በኤሌክትሪክ ማብሰል ሳይጀመር በፊት ከወንዙ አካባቢ ጎርፍ ጠራርጎ የሚያመጣውን ማገዶ ለቅመው ይጠቀሙ ነበር።
በተለይም ይላሉ ወይዘሮ አበበች ‹‹በተለይም ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ በሶቢላ፣ ጤና አዳምና የመሳሰሉትን ከወንዙ ዳር ዳር ያለውን ቦታ ቆፍረን እንተክላለን። ብዙዎቻችን ተክለን የተጠቀምን ሲሆን፤ በተለይ ከባለቤቴ ጋር በጋራ አልምተን እንጠቀም ነበር። የማገዶ እንጨትም ከዚሁ ወንዝ ለቅሜ እንጀራ እጋግራለሁ። ነገር ግን አሁን ላይ እንጨቱም የለም፤ እኛም የኤሌክትሪክ ምድጃ ከመጣ ወዲህ በኤሌክትሪክ ማብሰል ጀመርን። የወንዙን ዳርቻም እንደቀደመው ጊዜ አልምቶ የሚጠቀም ሰው የለም። አሁን ላይ ማንም ሰው ወደ ወንዙ ዞር አይልም። እንዲያውም አጥር አጥረን የከለልነው በመሆኑ እንደ ከዚህ ቀደሙ አይታየንም። አልፎ አልፎ ሲሞላና መጸዳጃ ቤት ስንገባ ድምጹ ይሰማ ይሆናል እንጂ ብዙም አይሰማም። ለዚህም አጥሩ መታጠሩ ጠቅሞናል።›› ሲሉ የነበረባቸውን ችግር በማስታወስ ይናገራሉ።
አጥሩን ለማጠር ምክንያት የሆነንም ጅቡ እየተንፏቀቀ ወደ እኛ በመምጣቱና ዱርዬዎችም ሰርቀው እየመጡ መደበቂያ በማድረጋቸው እንደሆነ የገለጹልን ደግሞ ወይዘሮ ሙሉ አንተነህ ናቸው። እርሳቸውም ከወይዘሮ አበበች በበለጠ ከአጼ ሀይለስለሴ ዘመነ መንግስት ጀምረው መኖሪያቸውን በዚሁ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ በሚገኘው የወንዝ ዳርቻ አድርገዋል። በዚያን ዘመን ነው መኖር የጀመርኩት ያሉት ወይዘሮዋ በዚሁ ቦታ ሆኜ ሶስት መንግስታትን አይቻለሁ ብለዋል። ታድያ የወንዙ ነገር ብዙም ሀሳብ ሆኖባቸው እንደማያውቅና እንዲያውም ድሮ ድሮ ወንዙ ራሱ የማይታይ መሆኑን እና አሁን ግን እየቀረባቸው መምጣቱን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የጓሮ አትክልት ዳር ዳር በማልማትና የወንዙን ውሀ በማጠጣት ይጠቀሙበታል። እንዲሁም ንጽህናቸውን የሚጠብቁት (ልብስ ማጠብ) ብዙዎቹ በወንዙ ውሀ ነበር። ቀደም ባለው ዘመናት ወንዞች ንጹህ ነበሩ። ስለዚህ ቀድቶ ለመጠቀም እንዲህ እንዳሁኑ ፀያፍ አልነበረም። አሁን ግን ብዙዎች የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ፣ ኬሚካል እና ቆሻሻዎችን ወደ ወንዝ ውስጥ የሚጨምሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በወንዝ ውሀ መጠቀም ቀርቷል።
ወይዘሮ ሙሉ ምንም እንኳን ለወንዙ ቅርብ ቢሆኑም እንደሌሎች ጎረቤቶቻቸው በወንዙ ዳርቻ እንጨት አልለቀሙም፤ ሽንኩርት፣ በሶቢላና ጤናዳምን ጨምሮ ሌሎች አትክልቶችን ተክለው አልተጠቀሙም። የግቢው እና የአካባቢው ሰው ሁሉ ተጠራርቶ እንጨት ሲለቅም አትክልት ተክሎ ሲያለማ እኔ ዞርም ብዬ አላውቅም። ምክንያቱም ከልጅነቴ ጀምሮ የልፋትና የድካም ስራ አልወድምና ነው ብለዋል። ነገር ግን ወንዶች ልጆቼ የተወሰነ ጊዜ እንጨት ለቅመው አምጥተውልኛል። አልፎ አልፎ ጅብ ይመጣባቸው እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሙሉ፤ ከጅቡ በበለጠ ግን ብዙ ጊዜና በተደጋጋሚ ወደ ግቢያቸው ሞባይል፣ ቦርሳና የተለያዩ ነገሮችን ሰርቀው የሚገቡ የፒያሳ አካባቢ ሌቦች አማረዋቸው ነበር።
ሌቦች ከፒያሳ አስፓልት ላይ ሰርቀው እየሮጡ ግቢ ውስጥ ገብተው ወንዙ ጋር ይደበቃሉ። በመሆኑም ወንዙ ከሚያሳድርባቸው ስጋት በበለጠ ሰርቀው የሚገቡት ሌቦች ስጋት ስለሆኑባቸው ቀበሌውን በማስፈቀድ በጋራ ገንዘብ አዋጥተው አጥሩን አጥረዋል። አጥሩም ከታች ወንዙን እንዲሁም ወደ ላይ መለስ ብሎ ደግሞ ግቢያቸውን ከልሎላቸዋል። አጥሩ ከታጠረ ወዲህም የተወሰነ አጠር ያለ በመሆኑ ሌቦቹ ከታች በወንዙ አድርገው ዘለው ይወጡ ነበር። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ አጥሩን ከፍ አድርገው በማጠር አሁን ላይ ከነበረባቸው ስጋት መላቀቅ ችለዋል።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የዱርዬውም ሆነ የወንዙ ስጋት የማያሳስባቸው ቢሆንም የሀገር ሰላም ግን እጅጉን የሚያሳስባቸው ትልቁ ጉዳያቸው መሆኑን ያጫወቱን ወይዘሮ ሙሉ፤ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንኖራለን፤ ኖረናልም። እኛ እዚህ ስንኖር ብዙ ነገር አሳልፈናል። ምንም ዓይነት ኮሽታ አይሰማም። ሜዳ ላይ እንኳን ሰው እያደረ ምንም ሲሆን አላየንም። አሁን…አሁን የሚሰማው ነገር ግን እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ ነገር ነው። ስለዚህ ሀገር ሰላም እንድትሆን መፀለይ ያስፈልጋል። አገር ሰላም ካልሆነች ሁሉም ነገር ዋጋ ያጣልና አሁን ላይ ስለ ሀገር ሰላም አብዝተን መጨነቅና መፀለይ አለብን በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እኛም ወይዘሮዋ ስለ ሀገር ሠላም ያስተላለፉትን መልዕክት ተቀብለን ሀገሪቷ ሠላም ውላ ሠላም እንድታድር ያለንን መልካም ምኞት እንገልጻለን። በመጨረሻም በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የወንዝ ዳርቻዎች ላይ መኖሪያቸውን ያደረጉ በርካታ ነዋሪዎች በራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ በሚገኘው ወንዝ አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎች ያላቸውን ሥጋት ዓይነት እንዲሁም የተለየ ሥጋት ስለመኖሩ በማመን መንግስት የጀመረውን የወንዞች ዳርቻን የማልማት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥል እያልን ለዛሬ በዚሁ አበቃን።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2013