እግር ጥሎኝ ወርቃማ የቅፈላ ሰፈር ከሚባለው አካባቢ ተሰይሜያለሁ፡፡ (ለደህንነት ሲባል የቦታውን ስም አልጠቅስም) ቦታው ላይ ደርሼ የቀጠርኩትን ሰው ጥበቃ አውራ መንገድ ላይ የመብራት ቋሚ ምሰሶ ‹‹ፖል›› ተደግፌ ቆሜያለሁ፡፡ በቅፈላና ሽቀላ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል አንዱ ‹‹አባቴ ታጥበሽ የተቀሸርሽ ደረጃ አንድ የይርጋ ጫፌ ቁጥር አንድ…›› ብሎ ሊያናግረኝ ሲቃጣው በአካባቢው ላይ ያሉት የተዋጣላቸው ቀፋይ መሆናቸውን ተረዳሁ፡፡ በግርግሩ አልበላም ‹‹ነቄ›› ነኝ ብለህ እዚህ ሰፈር ብትመጣ ስርቆት ወደ ዘመናዊ ልመና ይዞርና እያባባሉ ይበሉሃል፡፡
በቅፈላ ሰበብ ቦታ ግብር እየከፈልክ መመለስህ አይቀሬ ነው፡፡ ዘንድሮ ዘመናዊ ልመና የአለማመን ወጉ ተቀይሯል፡፡ በተለይ ሱሰኞች ቀዝቃዛ የስርቆት ትርክት እያቀረቡ፤ አፍዝ አደንዝዝ ወሬያቸውን በማላተም ዘና እያደረጉ፤ በሀዘኔታ ሆዳችንን እየበሉ፤ የአረቄ ቤት ጨዋታዎችን በብዛት በማውጋት ‹‹ቅፈላን›› ከኛ ሌላ ላሳር በማለት ያለምንም ይሉኝታ ድፍን ድፍኑን ይቀበሉናል፡፡ በሌላ ቀን እንዲሁ ብቻዬን በተመስጦ የየመንገዱን ሁኔታ እየቃኘሁ በትዝብት መዝገቤ ውስጥ ማስፈር ያለብኝን እያመረጥኩ ስጓዝ አንድ ነገር ተመለከትኩ፡፡ በተክለ ሰውነቱ ስፖርተኛ የሚመስል በመንገድ ዳር ቆሞ ወጭ ወራጁን ብር የሚቀፍል ጎረምሳ ከመንገዱ ከወዲያ ማዶ በጸሐይ ብርሃን እንዲለበለብ የተሰጣ ቆዳ መስሎ ተቀምጧል፡፡
ረጅም ሰዓት ጸሐይ ላይ ለመቆየቱ ፊቱ ላይ ያለው የድካም ስሜትና ጥውልግልግ ያሉ ዓይኖቹ፣ የደረቁ ከንፈሮቹ ያስታውቃሉ፡፡ ‹‹እናቱ አረ ለዳቦ፣ አባቱ ለምሳ ሙላልኝ፣ ፋዘር አትለፉኝ…›› እያለ ቅፈላውን ያሯሩጠዋል፡፡ አንድ ከፊት ለፊቱ ሸክም ያዘለ ማለቴ ቦርጭ የለጠፈ ሰው መኪናውን አቁሞ በጣቶቹ የመኪናውን ቁልፍ እያሽከረከረ በአስፈሪ አረማመድ መንገዱ ላይ ወዳለው ካፌ ያቀናል፡ ፡ ዓላማዬ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ማንኛውንም የመንገድ ላይ እንቅስቃሴ መታዘብ ስለሆነ ቀፋዩንም ተቀፋዩንም በትኩረት መመልከቴን ተያያዝኩት፡፡
የተሸከመው ቦርጭ ባለሥልጣን አስመስሎታል፡፡ በነገራችን ላይ ሁሉንም ወፍራምና ቦርጫም የሆኑ ሰዎች ሁልጊዜ እንደ ባለሥልጣን ማየት ልምድ ሆኗል፡፡ አሁን ላይ እኮ ቦርጭ ማውጣት መታወቂያ ከማውጣት በላይ ቀላል ሆኗል፡፡ ዳሩ የደሃ ቦርጭ መጠጥ እስካለ ብቻ ስለሆነች ዘላቂ አይደለችም፡፡ በአንድ ወቅት አውቶቡስ እየጠበቅኩ አጠገቤ የቆመው ቦርጫም ሰውዬ በሰውነቱ ጦር በመሰለው ሌላ ሰው እግር ላይ ቆመ (ሳያስበው) ቀጭኑ ሰውዬም ብዙ ከታገሰው በኋላ በፍራቻ አንደበት ‹‹ጌታዬ ባለሥልጣን ነዎት እንዴ?›› ብሎ ጠየቀው ቦርጫሙ ሰውዬም ‹‹አይደለሁም!›› ሲለው ቀጭኑ እንደ መባነን ብሎ‹‹ ታዲያ ለምን አባክ እግሬ ላይ ትቆማለህ›› ብሎ በቁጣ ገሰጸው፡፡ ወደ ቦርጫሙ ባለመኪና ሰውና ቀፈዩ ልመለስ ሰውዬው ካፌ ውስጥ ሊገባ ጥቂት ሲቀረው ቀፋዩ ሮጥ ብሎ ‹‹ እባክዎ ጋሼ ቢጫ ይቦጭቁልኝ ›› አለው አራዳ ነኝ በሚል የቃላት ጨዋታ፡ ፡
ሰውዬው ቋንቋውን ተረድቶ ኖሮ ‹‹ሳንቲም አልሰጥህም ከፈለግክ ቁርስ ልግዛልህ›› አለው፡፡ ቀፋዩም ምርር ብሎት ‹‹ ኧረ ምንሼ ነው ከነጋ አራተኛውን ቁርስ በልቼ ልፈነዳ ነው እኮ ጨላዋን ቢገጩኝ ይሻላል›› አለ፡፡ ቦርጫሙ ጥሎት ወደ ካፌው ገባ፡፡ በልቤ ተመጽዋች መሆን ካልቀረ የምን ማማረጥ ነው አልኩና ደግሞ ሌላ ክስተት ፍለጋ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ ተመጽዋች ሰው ብዙ ልምድ አለው፡፡ ማንን ምን ብዬ ልጠይቅ የሚለው ሀሳብ ብዙ አያለፋውም፡፡ ብቻ ደግ ሰው ይግጠመው፡ ፡ አለበለዚያ በቃላት ጨዋታ ህሊናን የሚሰብር ንግግር ከውስጣቸው መውጣቱ አይቀርም፡፡
በአንድ ወቅት አንድ ጎልማሳ ተመጽዋች ‹‹ጌታዬ ለዕለት ጉርስ የሚሆን ሳንቲም ይስጡኝ›› ብሎ ታዋቂ ሰው ይጠይቃል፡፡ ታዋቂው ሰውም ኪስ ከመግባት ይልቅ ትንሽ አወቅኩ ዓይነት ትዕቢት አብራው ስላለች ምክር ቢጤ ሊሰጥ ቃጣው፡፡ እናም ‹‹ ለኑሮህ የሚበጅ ስራ ለምን አትሰራም ከገንዘብ ይበልጥ የሚያስፈልግህ ጭንቅላት ነው›› አለው ተመጽዋቹን፡፡ ተመጽዋቹም መለሰና ‹‹እርሱስ ልክ ነው ጌታዬ እኔም የጠይቅኮት እርስዎ በደንብ ያልዎትን ነው›› አለው ይባላል፡፡
ከሊቅ እስከ ደቂቁ የሚቀፍሉት ሰዎች የራሳቸው አይነተኛ መገለጫ አላቸው፡፡ ከፊሉ ተሸቀርቅሮ ‹‹የትራንስፖርት ብር ጎድሎኝ››፣ ሌላው ‹‹ዋሌቴን ቢሮ ረስቼ ወጥቼ››፣ የተቀረው፣ መንገድ ላይ አውቆ ቆሎ በመድፋት አጭር ቴሌቶን በማዘጋጀት ‹‹ቆረጠኝ፣ ፈለጠኝ፣ ያዙኝ ልቀቁኝ›› በማለት ከዚህ ምስኪን ህዝብ ይቀፍላል፡፡ ምን አይነት ዘመን ላይ ደረስን በሚያስብል ሁኔታ አንድ ‹‹ጩጬ›› ምሳ በሚበላበት ምግብ ቤት ገብቶ ‹‹ እማዬ እንዳለቻችሁ…እ እ እ… አጉርሱት›› ማለቱም ልብ ይሏል፡፡ ወገን ዘመድ ከዚህ ሰውረኝ ከማለት ይልቅ ለቅፈላ ለሚመጡ ቀፋዮች የሚሆን አንደበት እንደሚያሻን እንረዳ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
አዲሱ ገረመው