
ታሪክም ተረትም
በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ከሚታዩት እንቅስቃሴዎች መካከል የመጽሐፍት አዟሪዎች ይጠቀሳሉ። መጽሐፍ አዟሪ መጽሐፉን ተሸክሞ ገዢውን ፍለጋ በእግሩ ይንቀሳቀሳል። በመንገድና በካፌ ውስጥ በመገኘት መጽሐፍቱን እያሳየ ይሸጣል። ገዢውን ለመሳብ በገዢው ቀልብ ውስጥ ስለገባው መጽሐፍ የሚያውቀውንም የማያውቀውንም በመናገር ትንታኔ ይሰጣል። እርስዎ መጽሐፉን ሲያነቡ አዟሪው ስለ መጽሐፉ የመሰከረው አንዱንም ቢያጡበት መገረም የለብዎትም፤ የአዟሪ ግብ መጽሐፉን መሸጥ ነውና። ጥቅሙን ማስጠበቅ።
አንድ ማለዳ በአንድ ካፍቴሪያ ውስጥ የተገኘው መጽሐፍ አዟሪ ከአንድ በእድሜ ጠና ያሉ ሰው ጋር ተገናኘ። እኒህ ሰው አዟሪው የተሸከመውን መጽሐፍት በአይናቸው ገረፍ አድርገው ተመለከቱ። መመልከታቸው የሚፈልጉትን መጽሐፍ ከአዟሪው እጅ እንደሚያገኙት አስበው ነበር።
አዟሪው ግን በተለመደው አሰራሩ “… በቅርቡ የወጣ፤ የእከሌ የታሪክ መጽሐፍ …” በማለት ትንታኔውን መስጠት ጀመረ።
ሽማግሌው አሁንም በጨረፍታ የአዟሪውን መጽሐፍት ገረፍ አድርገው “ልጄ እኔ እንኳን የፈለኩት ጃፓን እንዴት ሰለጠነች የሚለውን መጽሐፍ ነበር። የመጨረሻ ልጄ በቅርቡ ከዩኒቨርሲቲ ሰለተመረቀ ለእርሱ ስጦታ ለመስጠት መጽሐፉን እየፈለኩት ነበር።” በማለት ምላሽ ሰጡት።
መጽሐፍ አዞሪውም “አይ አባባ እንዲህ አይነት መጽሐፍትን አንይዝም፤ ምክንያቱም ብዙም ገዢ የላቸውም።” ሲል መለሰ።
አዟሪው የያዛቸውን መጽሐፍትን ይዘት ገምግመው ውስጣቸው የሚብላላውን ሃሳብ ከአዟሪው አንደበት መስማት የፈለጉት አባት “ምን አይነት መጽሐፍት ናቸው ፈላጊ ያላቸው?”በማለት ጠየቁት።
የአዟሪው ምላሽ “የታሪክ መጽሐፍት ናቸዋ። የእኛ ህዝብ በትላንት ታሪኩ ውስጥ ባለው ደም መፋሰስ ዛሬ ላይ በትዝታ እያሰብ መዝናናት ይወዳል መሰለኝ ሁሉም የሚፈልገው የታሪክ መጽሐፍ ነው።” ሲል መለሰላቸው።
እርሳቸውም አዟሪው ከያዛቸው መጽሐፍት የተረዱት እውነት ይኸው ነበር። በምናባቸውም ታሪክን ማወቅ በእርግጥ ያስፈልጋል፤ ነገርግን ታሪክን ማወቅ ለምን እንደሚጠቅም መረዳትም እንዲሁ ይገባል በማለት ለራሳቸው ተናገሩ። አዟሪው ጥቅሙን ለማስጠበቅ ስለ ሽያጩ ሲል እንደሚያስበው አንባቢው በህይወት ጉዞ በሚጠቅመው እውቀት ተቃኝቶ ለመራመድ እንዲረዳው። ጥቅምን በማስጠበቅ!
የመጽሐፍ አዟሪው ንግግሩን በመቀጠል “ትልልቆቹ ታሪክን ሲመርጡ፤ ህጻናት ደግሞ ተረት ተረት ይወዳሉ። ለዚያ ነው በአብዛኛው የታሪክና የተረት መጽሐፍ ይዘን የምንዞረው። እርስዎ እንዳሉት ሥልጣኔ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሥራ፣ ምናምን የሚባሉ መጽሐፍት የተወሰኑ ኮስተር ያሉ ሰዎች የሚፈልጉት ናቸው።”
ሽማግሌውም ቀበል አድርገው “ኮስትር ማለት ስትል?” አሉት። አዟሪውም “ኮስተር ያሉ ማለት ያው ነገሮችን እያሰቡ፣ በሚዛናዊነትና በእውቀት የሚያደርጉ ማለቴ ነው።” በማለት ምላሽ ሰጠ።
ሽማግሌው በሀሳባቸው ጭልጥ ብለው ራሳቸውን ‘ታሪክም ተረትም ስለ ምን?’ ብለው ጠየቁ።
ታሪክ
ስለ ታሪክ ብዙ ተብሏል፤ እየተባለም ነው። የታሪክ ባለሙያዎች ስለ ታሪክ በማስረዳቱና ለማስገንዘብ በመድከሙ ግንባር ቀደሙን ይዘዋል። ታሪክን በባለሙያዎቹ ትርጉም ውስጥ ከማየት በማፈንገጥ ለራስ ጠባብ ዓላማ ለማዋል የሚደረገው ጥረት ግን ልምድ ሆኖ የሚታይበት ደረጃ ላይ መድረሱ፤ ስለ ታሪክ እንድናስብ የሚያደርግ ሆኗል።
መስፍን ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” (2005 ዓ.ም) በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ታሪክ የሕዝብ የተከታታይ ትውልዶች ሥራ ነው…የኋለኛው ትውልድ በአለፉት ትውልዶች መስዋዕትነት በተጣለው መሠረት ላይ የተሻለ፣ የጠነከረና የበለጸገ ማኅበረሰብ ለማነጽ የሚያደርጉትን ጥረት ከአለፈው ጋር የሚያስተያይ መዝገብ ነው፤ ስለዚህም የኋለኛው ትውልድ ለቀድሞው ትውልድ ያለበት ዕዳ ወይም ውለታ ነው፤ ታሪክ ያለፉትን ተከታታይ ትውልዶች ከዛሬውና ከወደፊት ትውልዶች ጋር የሚያገናኝ፣ የሚያስተዋውቅና የሚያስተሳስር ሰንሰለት ነው፤ የዛሬው ትውልድ የትናንቱ ትውልድ ሥራ ውጤት ነው፤ የነገው ትውልድ ደግሞ የዛሬው ትውልድ ሥራ ወጤት ነው፤ ያለፉት ትውልዶችና የወደፊቶቹ ትውልዶች የሚገናኙት በዛሬው ትውልድ ላይ ነው።›› በማለት ታሪክ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ያለውን ድርሻ ገልጸዋል።
ፒተር ስቲርነስ የተሰኙ የታሪክ ባለሙያ ስለ ታሪክ ሲጽፉ “ሰዎች በአሁን ውስጥ ይኖራሉ። ነገን በማሰብ ያቅዳሉ ደግሞም ይፈራሉ። ታሪክ ግን ስለትላንት የሚያጠና ነው። ትላንትን በማጥናት ውስጥ ዛሬን በተሻለ መኖር በምንችልበት አቅጣጫ ላይ የሚያስኬድ እንዲሁም ሊመጣ ስላለው የሚያዘጋጅ። ”ብለዋል።
ታሪክ መረጃዎችን በማሰባሰብ እውቀት የሚቀመርበት ነው። ይህ ማለት ግን ታሪክ ማለት መረጃዎች ጥርቅም ብቻ አድርጎ መታሰብ አለበት ማለት አይደለም። ልክ እንደ ልብ-ወልድ የፈጠራ ጽሁፍ ወይን አንድን ጉዳይ ከየት ተነሥቶ በምን መንገድ አድርጎ የት እንደሚደርስ በመተረክ አንባቢን/አድማጭን ለማዝናናት ታልሞ የሚሰራም አይደለም።
‹‹አባ ጤና ኢያሱ›› በተባለው መጽሐፋቸው ጎበዜ ጣፈጠ (ዶ/ር) ስለ ታሪክ ሲጽፉ“ታሪክ በዓለም ላይ በአንድ ሰው ሕይወተ ሥጋ ዘንድ የሆነውን ጠቅላላ ነገር እንደሰንሰለት አያይዞ የሚያቀርብ ነው። ታሪክን ማወቅ ክፉውንና በጎውን ለመለየት አካሄድንና ጠባይን ለማረምና ለማሻሻል በብዙ ነገር ይጠቅማል። …ሰብዓዊ ፍጡር በዚህ ዓለም ሲኖርና ሲመላለስ፣ በዘመኑ የፈጸመው በጎም ሆነ ክፉ ሥራው እርሱ ካለፈ በኋላ ለተከታዩ ትውልድ ማስታወሻ ሆኖ ይኖራል እንጂ እንደ ሥጋው ወደ አፈርነት አይለወጥም። የአንድ ሰው አነሳስና አወዳደቅም በመካከሉም ከተደረገው ትግል ጋር በታሪክ ውስጥ ተሳስሮ ይገኛል። ስለዚህ ያለፈን ታሪክ ጠንቀቆ ለማወቅ መሞከር ይጠቅማል፣ ትምህርትም ይገኝበታል። ብለዋል።
ታሪክን ሌሎች ምሁራንም ሆኑ ጸሃፍት ያሉትን ስናስቀምጥ የምንረዳው ነገር ታሪክን በአላማ ውስጥ የመመልከትን አስፈላጊነት ነው። ታሪክን በአላማ ውስጥ መመልከት የግድ የሚልበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ዋናው ጉዳይ ግን ታሪክ በመስራትም ሆነ ታሪክን በማንበብ ውስጥ ከታሪክ ለመማር የሚጥር ሰው ነውና፤ ታሪክ ሰውን በሰውነቱ በመመልከት መሆን አለበት።
አለቃ ታዬ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ›› በሚል ርዕስ በ 1914 ዓ.ም. ስለ ታሪክ በጻፉት መጽሐፍ ‹‹ታሪክን መማርና ማወቅ ለብዙ ነገር ይጠቅማል፡- መጀመሪያ የድንቁርና ዕውር ዓይን ይከፈታል፤ ሁለተኛ ሰው የእግዚአብሔርን ቻይነት፣ የፍጥረቱንም ብዛትና የልዩ ልዩ ወገንንም ዓይነት የዓለምንም ታላቅነትና ስፋት ያይበታል። …በዓለም ያሉትን ልዩ ልዩ ሕዝቦች አገራቸውና ጠባያቸውን፣ የአምላካቸውንና የመንግሥታቸውን ሥርዓትና አኗኗራቸውንም በታሪክ ሲመለከት ሲመረምር፣ ሲያስተውልም፣ በቤቱ ተቀምጦ ዓለምን ሁሉ ዞሮ… እንዳየ ሰው ይሆናል። የሰውን ደካማነትና ብርታትን፣ በጎነትንና ክፋትን፣ ስንፍናንና ብልሃትን፣ ሐሰትንና ዕውነትን፣ ቁም ነገርንና ተረትን፣ ተንኮልንና ቅንነትንም ያለበትን ነገር ሁሉ አይቶ ያውቃል። በዓለም የሚነገረውን ከንቱነት ሁሉ ይንቃል ለበጎ ነገርም ይተጋል። የሰውን ጠባይ ደካማነትን አውቆ ልቡን በማስፋት ይታገሣል፣ ክፉ ነገርንም አይቶ ለበጎ ነገር ይነሳሳል። በዘመኑም ወደፊት በዕውቀትና በብልሃት፣ በበጎነትም ልቡ ይታደሳል። ሰነፎችንም በምክሩና በትምህርቱ ከድንቁርና ወደ ጥበብ ይመልሳል።›› በማለት ታሪክን በጥልቅ ገልጸውታል።
ከዚህ በላይ ስለ ታሪክ በተሰጠው ገለጻ ውስጥ ጎልተው የሚታዩት ሦስት የጊዜ ቀለበቶች አሉ። ሦስቱ የጊዜ ቀለበቶች ማለትም ትላንት፣ ዛሬና ነገ በታሪክ ውስጥ እንዴት መመልከት እንደሚቻል እንመልከት።
ታሪክ በሦስቱ የጊዜ ቀለበቶች፣
ትላንት፣ ዛሬና ነገ ሦስቱ የጊዜ ቀለበቶች ውስጥ የታሪክ አሻራ ሰፊ ነው። ከዚህ በላይ በቀረበው የፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ ውስጥ ያለፉት ትውልዶችና የወደፊቶቹ ትውልዶች ስለሚገናኙበት መገናኛ ስፍራ እርሱም የዛሬው ትውልድ ማንሳት ይኖርብናል። ታሪክ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑ የማይካድ ቢሆንም በተጨባጭ የዛሬው ትውልድ እንዴት እየተጠቀመበት መሆኑን መመልከት መቻል ታሪክ በሦስቱ የጊዜ ቀለበቶች ውስጥ ያለውን ቦታ ሙሉ ያደርገዋል።
የዛሬው ትውልድ ያለበት ጦርነት የዛሬው ጦርነት ነው። ዛሬ በንግዱ፣ በቴክኖሎጂው፣ በባህል፣ በእምነት ወዘተ ጦርነቶች አሉ። እኒህ ጦርነቶች ትላንትም የነበሩ ቢሆንም የዛሬው ትውልድ ጦርነቶች ሆነው በወቅታዊ ቅርጻቸው ላይ ይገኛሉ። እያንዳንዱ ሰው በጦርነቶቹ ላይ የሚሳተፈው በራሱ ትውልድ ወቅት በመሆኑ እንዴት መዋጋት እንዳለበት ለማወቅ ትምህርትን ፍለጋ ወደ ትላንት መዞሩ የግድ ነው። በታሪክ አማካኝነት ከትላንት የሚወሰደው ትምህርት ብዙ መሆኑን ወደ ትላንት መመልከት ለዛሬ አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን፤ የግድምነው። ታሪክን በትምህርትነት እንጂ ወደ ኋላ መልሶ የትላንትን ጦርነት ዛሬ ላይ መዋጋት በፍጹም መሆን የሌለበት ለዚህ ነው።
የታሪክን አስፈላጊነት አንስተው የሚሞግቱ ጸሃፍት ታሪክን ለምን መጠቀም እንደሚገባ ሲጽፉ ከሚያነሷቸው ቁልፍ ነጥቦች መካከል ለዛሬው ትውልድ ትምህርት ይሆኑ ዘንድ ሦስቱን እናንሳ።
1. ታሪክ ሰዎችን በግልም ሆነ እንደ ማህበረሰብን በሚገባ እንድንረዳ የሚረዳ ነው፣
በመጀመሪያ ደረጃ ታሪክ ማለት በሰው ልጅ ጉዞ ውስጥ የተፈጠሩ የማህበረሰብ መረጃዎች ታጭቀው የሚገኙበት ግምጃቤት ማለት ነው። ዛሬ ላይ የሚታየው የማህበረሰባዊ መልክ በትላንት ውስጥ የተሰራ መሆኑን ታሪክ በሚገባ ያስረዳል። ዛሬ እንዴት መኖር እንዳለብን ለማወቅ ትላንት የተመጣበትን መንገድ መመልከቱ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው።
በሳይንሱ እድገት ውስጥ የተመጣባቸው የጽንሰ-ሃሳብ ነደፋና የተግባር ሙከራዎች ውስጥ የታየው የትላንት ጉዞ ወዘተ የሄዱበት እርቀት ለዛሬ መነሻ ሊሆን የግድ ስለሚል ታሪክ መዝግቦ ይይዛቸዋል። ዛሬ ላይ የተደረሰበት ቴክኖሎጂ ዛሬ ድንገት የተገኘ ሳይሆን በትላንት ቅብብሎሽ ውስጥ እያደገ የመጣ ነው።
ታሪክን ስናስብ እንዲህ መመልከት ሳንችል ከቀረን በትላንት ውስጥ ተደብቀን መገኘታችን ዛሬን አሳልፎ ለስንፍና ከመስጠት ባሻገር የዛሬው ትውልድ ለነገ የሚያወርሰው የማይኖረው የሚያደርግ ነው። የማህበረሰብ ጉዞ ውስጥ የተፈጠሩትን እውቀቶች ለዛሬ ለትምህርት ለመውሰድ ታሪክ የሚገባውን እንዲሰራ እንፍቀድለት እንጂ እኛ ያሰብነውን ለመጫን ታሪክን እየጠመዘዙ ያለአቅጣጫው እንዲፈስ ማድረግ በብዙ ዋጋ ያስከፈለን መሆኑን መረዳት ይገባል።
2. ታሪክ ለውጥን እንድንረዳ የሚያደርግ መሆኑ፣
ስለ ለውጥ ለማስተማር ከታሪክ የሚቀርብ የለም። የታሪክ ገጾች የለውጥ ገጾች ናቸው። ሰዎች ተስፋ ወደ መቁረጥ የሚሄዱት የለውጥ ተስፋ ሲሟጠጥባቸው ነው። በታሪክ ውስጥ ግን ለውጥ ትልቁን ቦታ ይይዛል። ስለ ለውጥ በሚታገሉና ለውጥ እንዳይሆን በሚታገሉት መካከል የሚገኘው ትምህርት በታሪክ ገጾች ውስጥ የሚገኝ ትምህርት ነው። አንድ ሰው የሚሰራውን ታላቅ ለውጥ ለማየት፣ ሁለት ሰዎች በአንድ ሀሳብ ተስማምተው ተአምር የሚባል ለውጥን ሲያመጡ ተመልክቶ ለመማር፣ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ የሚፈጥራቸውን የጋራ ለውጦች ውስጥ በመገረም ለመገኘት የታሪክ ገጾች የግድ ይላሉ።
በታሪክ ውስጥ በጉልህ ቀለማት ከሚነበቡት ለውጦች መማር ያልቻሉ ሰዎች የትላንቱን ስህተት ደግመው በአደባባይ ይታያል። የሚያሳዝነው ግን ሰው በዚህ ረገድ ከታሪክ መማር አለመቻሉነው። በርናርድ ሻውና ሄግል የሚባሉ ሁለት የታሪክ ምሁራን ይህን ሐቅ በተመለከተ ትዝብታቸውን ሲያስቀምጡ፡- ‹‹ከታሪክ የምንማረው ትልቅ ቁምነገር ቢኖር የሰው ልጅ ከታሪክ መማር አለመቻሉን ነው›› ብለዋል። (Hobsbawn, Eric J (1990). Nations & Nationalism Since 1780).
3. ታሪክን በህይወታችን ውስጥ ሞራልን ለመፍጠር
የታሪክ ጸሃፍት ለአብዛኛው አንባቢያን በሚጽፉበት ጊዜ የሚጠቀሙት ቋንቋና የአጻጻፍ ስልት ተደማምሮ አንባቢያን ውስጥ ሞራልን ለመፍጠር ትልቅ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል። ታሪኩ ሲሰራ የነበረው ህመምን በጥበባዊ ለዛ አዋዝቶ ተደራሲውን ወደ ሌላ የሞራል አቅም፤ የትጋት ደረጃ፤ የመሰጠት ትርጉም ወዘተ ለማምጣት ታሪክ ትልቅ ስራ ይሰራል። ሀገራት በታሪክ ውስጥ ሊተላለፍ ስለሚገባው መልእክት አብዝተው ጥንቃቄ የሚያደርጉት ዜጎቻቸው በድምሩ ሊይዙት የሚገባውን ጤናማ ስነ-ልቦና እንዲይዙ ስለሚፈለግ ነው። በፈተና ውስጥ ጽናትን፣ በዘገየ ተስፋ ውስጥ ልብን መጠበቅን፣ በመከዳት ውስጥ የውስጥን ሰላም ለመጠበቅ መሞከርን ወዘተ ለማስፈን ታሪክ የማይተካ ሚና አለው።
በኢትዮጵያችን ግን በተቃራኒው ሆኖ እናስተውላለን። ታዬ ቦጋለ የተሰኙ ጸኃፊ መራር እውነት በተሰኘ መጽሃፋቸው በኢትዮጵያ የታሪክ ገጽታ ላይ ትችታቸውን ሲያቀርቡ። ምንጊዜም ቢሆን ያለፈውን ታሪክ የሚዘነጉ ሰዎች መልሰው መሳሳታቸው አይቀሬ ነው። ታሪክን የሚያስታውሱ አንዳንዶች ደግሞ ሊማሩበት ሳይሆን የጥንቱን ቁስል በመነካካት የበለጠ ለማድማት፣ ለመበቀል፣ የጥላቻን እሳት ለማቀጣጠል ሊጠቀሙበት ይጥራሉ፤ ይህ አካሄድ ግን ኋላቀርነት እንጂ የሰለጠነ አካሄድ ሊሆን አይችልም። የታሪክ መሠረታዊው ጠቀሜታ ግን መጥፎውን ታሪካዊ ክስተት ለማውገዝና ከዚያ ልምድ በመቅሰም ዳግመኛ እንዳይከሰት ለመከላከል፣ በአንጻሩ መልካሙን ክስተት ደግሞ ለማበረታታት (ደጋግሞ እንዲከሰት ለማድረግ) ነበር። በምንም መንገድ የትላንቱን የምናጠናው ጥላቻን ለመቀስቀስ፣ ግጭቶችን ለማራገብ፣ ቁስሎችን ለመነካካትና እንዳይድኑ ለማመርቀዝ አይደለም (ታየ ቦጋለ፤ መራራ እውነት፤ 2011፡ 37)።
ዛሬ ታሪክንም ተረትንም ለጥቅማችን እንዲሆን ማድረግ የግድ የሚለን ይመስላል። ዛሬዎቻችን እየባከኑ፤ አብሮነታችን እየተናደ፤ ክቡሩ የሰው ልጅ ከእንስሳት በወረደ ደረጃ ታይቶ አሰቃቂ ሞትን እንዲሞት እየተደረገ በምድራችን ላይ መረጋጋትን ማምጣት ከባድ ነው።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታሪክንም ተረትንም ለጥቅማችን እንዲሆን እንደ ታላቅ ትምህርት ቤት በመመልከት ከትላንቱ በመማር ለነገው መብቃትን ትልም በማድረግ ልንገኝ ይገባል።
በመነሻችን ላይ ያገኘናቸው ከመጽሃፍ አዟሪው ጋር ቃላትን የተቀያየሩት አባ ‘ታሪክም ተረትም ስለ ምን?’ ብለው ይጠይቃሉ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም