“ኢትዮጵያን ነው?” የእኛ ጥያቄ!
“አዎን ኢትዮጵያን ነው!” – የእነርሱ መልስ። “እርሷን አግኝተን ምን አጥተን፤ ሁሉ በእጃችን ሁሉ በደጃችን”…የጠላቶቻችን የምኞት ጨዋታ ይቀጥላል። “እንዳማራችሁ፣ እንዳስጎመጃችሁና እንዳቃዣችሁ ይቅር እንጂ ኢትዮጵያማ አትገኝም። ” የእኛ የቁርጥ ቀን ልጆቿ መልስ።
“ልጅነት ተመልሶ አይመጣም” ያለው ማን ነበር? በስህተት የተነገረ አባባል መሆን አለበት። የልጅነት የህልም ሩጫና የማይጨበጥ ምኞት በስተ ጉልምስናም ይሁን በስተ እርጅና ነፍስ ዘርቶ የሚከሰትባቸው መንገዶች ብዙዎች ናቸው። አንድም በምኞት፣ አንድም በድፍረት፣ አንድም ቃዥቶ በመጃጀት የልጅነት ጠረን እንደገና አገርሽቶ ሊያውድ ይችላል። ሲበረታም “የሌላውን ጭብጦ ካልቀማሁ” አሰኝቶም ያስለቅሳል።
በልጅነት ዕድሜያችን በእሳት ዳር ተሰባስበን ወይንም በለምለም መስክ ላይ ክብ ሰርተንና ተንጋለን ከዘመን እኩዮቻችን ጋር ከምንፍነከነክባቸው፣ ከምንወራረድባቸው፣ የአእምሮ ብስለታችንን ከምንፈታተንባቸውና የዕውቀት ልካችንን ከምንመዛዘንባቸው የሥነ ቃል ቅርሶቻችን መካከል የእንቆቅልሽ ጨዋታ የየባህሉ ታላቅ እሴት ነው።
ዕድሜያችንን የሚመጥን አንድ የእንቆቅልሽ ጥያቄ ወርውረን ተገቢውን መልስ ከእኩዮቻችን ካላገኘን አሸናፊነታችንን የምናረጋግጠው “አገር” በመጠየቅ ይሆናል። ከሠፈርና ከቀዬአችን ተንጠራርተን፣ ድንበርና ወሰን ሳያግደን “እከሌ የሚባለውን አገር ውሰድ/ውሰጂ” ማለት የተለመደ የተሸናፊነት ማረጋገጫ ነው። ይህ የቅን ዘመን የቅን ጨቅላዎች ጨዋታ ዛሬም በጉልምስናና በእርጅና ዕድሜያችን አምባገነን መንግሥታትና እብሪት ያሰከራቸው ደቂቀ ዲያቢሎስ ወፍ ዘራሽ ቡድኖች ለሰከሩበት የእንቆቅልሽ ቅዠታቸው “አገር ካልሰጣችሁን፤ ለዚያውም ኢትዮጵያን” እያሉ በስውር ሲያሴሩና በግላጭ ሲጮኹ ማድመጥ የጀመርነው ታሪክንም ዕድሜያችንንም ዋቢ አቁመን ነው።
አገር እንደ ሕጻናት የእንቆቅልሽ ጨዋታ የተረት ተረት ውጤትና ለተረብ እንደሚቀለው ቸርነት “ውሰዷት” ተብሎ የምትበረከት የምናብ ትርት (የምትተረት) አይደለችም። “ኢትዮጵያን እነሆ!” እየተባለም በከንቱነት ላበዱ ዘመንኛ ወፈፌዎችና ምንደኞች “በእንቁልልጮሽ” ማማለያ ለምሳሌነት የምትጠቀስ እንደሆነች መቆጠርም የለባትም። ይህ እንዲሆን የሚፈልጉ ህልመኞች በሩቅ ያሉ ጠላቶች ብቻም ሳይሆኑ በራሳችን እቅፍና ብብት ውስጥ የተወሸቁትን ጭምር ያጠቃልላል።
ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም፤ “የመጻተኛ አገር” የሚል ርዕስ ያለውና በምናብ አተያይ የመጠቀና መልእክቱም የደደረ አንድ ድንቅ ግጥም አበርከቶልናል። እንዲህ ይነበባል፤
አገር ድንኳን ትሁን፣
ጠቅልዬ የማዝላት፣
ስገፋ እንድነቅላት፣
ስረጋ እንድተክላት።
በገጣሚው ምልከታ የግጥሙ መልእክት ብዙ ሊባልለት የሚችል ነው። ይሁን እንጂ ብዕረኛውን ይቅርታ ጠይቀን ግጥሙን ከዘመናችን ዐውድ ጋር አጋጥመን ለተለየ አተያይ መዋሱ መልካም ሆኖ ታይቶኛል። በተለይም ለቤት አደጎቹ “ሳይሞቅ ፈላ” የእኩይ ዓላማ አስፈጻሚዎች ጥሩ መገለጫ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ።
የሕዝብን ሰላም እያናወጡ፣ የንጹሐንን ክቡር ሕይወት እየቀጠፉና በዓመታት የድካምና የላብ ውጤት የካበተውን የሕዝብና የመንግሥት ንብረቶች የሚያወድሙ መሰሪ የአገር ጠላቶች፤ ለመሆኑ እንደ ሕጻናት ጨዋታ “በነጋ በጠባ እንቆቅልሽ እያመሳጠሩ አገር ካልሰጣችሁን” እያሉ የሚያብዱት በርግጡ የፖለቲካው ሥልጣን “ሙልሙል ሽታ” ውል ስለሚላቸው ብቻ ይሆንን ወይንስ ከሌሎች ታሪካዊ ጠላቶቻችንና አዲስ መጤ ባላጋራዎቻችን ጋር በጋሻ ጃግሬነት ስለተማማሉ? ምንም ምክንያት ቢደረድሩ “ምን አውቅልህ!” ብለን በግላጭና በድፍረት ልንሞግታቸው ይገባል። ገጣሚው በስንኞቹ አማካይነት በምናብ እንደተራቀቀው እነርሱ እንደሚያስቡት አገር እንደ ተራ ድንኳን ተጠቅልላ ሲያሻ የምትተከል፣ ሲፈልጉ እንደ ቅዠታቸው የሚያዋቅሯት ተራዳ አይደለችም።
አገር የቀዳሚ ጀግኖችን ደም ደሟ፣ አጥንታቸውን ማገር፣ ላባቸውንም ወዟ አድርጋ በትውልዶች ቅብብሎሽ ውስጥ የተሰራች፤ በመወለድ የእትብት መቀበሪያ፤ ለዘለዓለምም የአጽም ማረፊያ ዘላለማዊት ቅርስና ውርስ እንጂ ከንቱዎች በከንቱ ትምክህታቸው እንደ ሳሏት በአራት ካስማ ተጠናክሮ እንደሚዘረጋና አገልግሎቱ ሲያበቃ እንደሚጠቀለል ድንኳን የምትመሰል አይደለችም። ቢሆን ኖሮማ ይሄኔ ስንቴ አፍርሰው ስንቴ በደኮኗት፤ ምን ያህል ጊዜ ሸንሽነው በተቀራመቷት ነበር።
በእብሪት፣ በትምክህት፣ በጉራ የሚንተከተከውን የትንፋሻቸውን ወላፈን እንደ ወኔ ማጋጋያ፣ በንጹሐን ደም የተበከለውን ጠብመንጃቸውንም እንደ ነፃ አውጪ በመተማመን ምን ያህል ያልተሳካ ሙከራ እንዳደረጉና እያደረጉ እንዳሉ የምናስተውለው ሐቅ ነው። ከተወሸቁበት የፍልፈል ጉድጓድ ውስጥ ብቅ እያሉና ጨለማን ተገን አድርገው አገር ማተራመሳቸውንም እንደ ጀብድ ቆጥረው ኢትዮጵያን ከቅዠት ድንኳን ጋር አመሳስለው ይፋንኑ ካልሆነ በስተቀር እነርሱ ፈርሰው ቼ እያሉ የሚጋልቧቸው ጌቶቻቸው በሀዘን ድንኳን ውስጥ ልቅሶ ይቀመጡላቸው ካልሆነ በስተቀር “የአገር ስጡን” እንቆቅልሻቸው ሩቅ አያስጉዛቸውም። አገሬ እንደ ድንኳን ተጠቅልላ ከአንድ ወይንም ከሁለት ብሔሮች ጎጥ ውስጥ ገብታ የምትወሸቅ ምስኪንም አይደለችም። ጥበቧና እስትንፋሷ ብሔረሰቦቿ ናቸው። ቋንቋቸውና ባህላቸውም ጌጧና አይተኬ መኩሪያዎቿ ናቸው።
እርግጥ ነው አንዳንዶች የተቀመጡበት የሥልጣን ወንበር ይበልጥ ሰፋ ብሎ እንዲደላደልላቸው በመቃዠት ቀን ቀን ስለ ፍትሕና ሕጋዊነት እያወሩ ሌሊት ሌሊት ደግሞ “ኢትዮጵያ ተገፍታ ስለምትወድቅበት ዘዴ” ሲያመነዥኩና በህልም ዓለም ሩጫ ሲወራጩ ማደራቸው እውነት ነው። ይህን መሰሉ ምኞታቸው ከእንቅልፋቸው ሲባንኑ በንኖ እንደሚጠፋ ጉም የማይጨበጥና የማይዳሰስ ከንቱ ነፋስ መሆኑን ያለመረዳታቸው የግብዝነታቸው መገለጫ ነው።
አንዳንድ ደፋሮችም አሉ። ባህር ማዶ፤ ከአድማስ ባሻገር ካለው የስደት መጠለያቸው ውስጥ ተወሽቀው እንዳሉ የሟርት ጠጠር እየበተኑ አገርን ከድንኳንም አሳንሰው በምላስና በፌስ ቡክ ገፍተው ሊጥሏት ሲሞክሩ ማየቱ በእጅጉ “የጅልነታቸውን ልክ” የሚያሳይ ምስክር ነው። በሰልፈኞች ጩኸት እንደፈረሰው የኢያሪኮ ቅጥር የኢትዮጵያ ጠላቶች በዙሪያዋ እየዞሩ ሲያገሱ ቢውሉ ራሳቸው ሟሙተው ያልቁ ካልሆነ በስተቀር በአንድ ጀንበር መጯጯህ የምትፈርስ የካብ ድርድር አይደለችም።
ደፋሮቹ የደርቡሾች ዝርያዎችም “ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልን ጠቅልለን ካልወሰድን” በማለት አገርን ከሠልስት በኋላ እንደሚፈርስ ድንኳን ሲያመሳስሉ አለማፈራቸው ያስደንቃል። የአደባባይ ጬኸታቸው ውስጣችንን ቢያውክም ተረጋግተን “የተረታቸውን ኬላ በማፍረስ” በመረባረብና በመተባበር እርቃናቸውን አቁመን የእብደታቸውን ጥግ ማሳየቱ አግባብ ይሆናል።
ከፈርኦን ልጆች የምናስተውለው መቅበዝበዝም እንዲሁ ምንም እንኳን ለዘመናት የተጠናወታቸው የክፉ ደዌ ቅንዓት ውጤት መሆኑ ባይጠፋንም ደግመን ደጋግመን ኢትዮጵያ እነርሱ እንደሚያስቡት በጫና የምትጠቀለል ድንኳን ያለመሆኗን አስረግጠን ልንነግራቸው ይገባል። “ከገነት” የሚፈልቀውን ውሃችንንም ቢሆን እንዳሻን ለመጎንጨትም ይሁን ላቀድነው የብርሃን ምንጭነት ያለከልካይ እንዳሻን ልንገለገልበት ሙሉ መብት አለን።
ቀደምቶቹን እንኳን ለጊዜው ትተን ከአንድ ምዕተ ዓመታት በፊት የአድዋው፣ ከስምንት ዐሠርት ዓመታት በፊት የፋሽስቶች፣ ከአራት ዐሠርት ዓመታት በፊት ደግሞ የዚያድ ባሬ ወራሪዎች በእንቆቅልሽ ተረት ታውረውና ኢትዮጵያን ልክ እንደ ድንኳን አጣጥፈው ለመቀራመት ሙከራ አድርገዋል። “ኢትዮጵያን አግኝተን ምን አጥተን፤ ሁሉ በእጃችን ሁሉ በደጃችን” እያሉም ለማቅራራት ሞክረዋል። ነገር ግን ትንኮሳቸውና ድፍረታቸው በጀግኖች አባትና እናቶቻችን ብርቱ ክንድ መክኖ ኢትዮጵያ ድንኳን ያለመሆኗ በግልጽ ምላሽ ተረጋግጦላቸው ተምረዋል።
የዛሬዎቹ የሉዓላዊ ክብራችን ጠላቶች ያለፈው ቅጣትና ታሪክ ትምህርት አልሆናቸው ብሎ ዛሬም ድረስ የዘመነ ስብስቴ መዝሙራቸውን እያንጎራጎሩ ሲወራጩ እያስተዋልን ነው። “ተረት ተረት?” – “የላም በረት!” እያሉ እንደሚፎካከሩት ሕጻናት “ከእንስሳት ጭንቅላት” ያነሰ አስተሳሰብ ያላቸው የጥፋት ኃይሎቹ ስብስብ “በላም በረት” ቢመሰል ያንሳቸው ካልሆነ በስተቀር ይበዛባቸዋል የሚባል አይደለም።
ለጊዜው አገሬ ከተለያዩ ወደረኞቿ እጅግ በርካታ የሆኑ “የእንቆቅልሽ ጥያቄዎች” እየተዥጎደጎዱላት እንደሆነ አይጠፋንም። ምናልባትም በታሪኳ ውስጥ እንደዚህ ወቅት “እንደ ድንኳን ሊጠቀልሏት” ያሰፈሰፉ ክፉ ጠላቶች ገጥመዋት ስለመሆኑ በእርግጠኝነት ለመናገር ያዳግታል። ቢሆንም ግን ዙሪያዋን እየዞሩ የሚያገሱት ጠላቶቿ በድምጻቸውና በድርጊታቸው የሚያፍሩት እነርሱ ራሳቸው እንጂ የአገሬ ክብርማ ከነሞገሱ ነበር፣ አለ፣ ለወደፊቱም በግርማው ደምቆ ለእንቆቅልሽ አመሳጣሪዎቹ የጥፋት መልእክተኞች ድንጋጤ እየፈጠረ መገስገሳችን አይቀሬ እውነት ነው።
መከራ ያጠነክራል እንጂ አሟሙቶ አያደቅም። በተለይም በአገር ላይ ጠላቶች ከግራ ከቀኝ እያፏጩ መፏለላቸው ዜጎችን እንደ ብረት ያጠነክር ካልሆነ በስተቀር እንደ ሰም አያቀልጣቸውም። ከበደ ሚካኤል ይህ እውነት ገብቷቸው ስለነበረ ነው “የዕውቀት ብልጫ” ለሚለው መጽሐፋቸው እንደ ማሳረጊያነት በሚከተለው ግጥም የደመደሙት።
ሰው ሲበድላችሁ እስቲ አትናደዱ፣
ጠላትን አትጥሉ ክፉን ሰው ውደዱ።
የክፉ ሰው ክፋት ጠቃሚ ነው ትርፉ፣
ያነቃቃችኋል እንዳታንቀላፉ።
የልቦናው ስሜት እየተራቀቀ፣
ሁልጊዜ ወደ ላይ በጣም እየላቀ፣
በሥራ በጥበብ ግሎ ለመነሣት፣
ቆስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደ እሳት።
ይህ ጸሐፊም ሃሳቡን የሚጠቀልለው በዚሁ የጠቢብ አባት ምክር ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2013