
አዲስ አበባ፡- የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር መመስረት ተበታትነው ሲሰሩ የነበሩ የዘርፉን ሥራዎች በማቀናጀት መረጃ ለማዳረስ፣ የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና የቱሪዝም ፀጋዎችና ሀብቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚያስችል የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሩ የማህበሩን መመስረት አስመልክተው በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር መመስረት ለኢትዮጵያውያንና ለመላው ዓለም የቱሪዝም መረጃዎችን ለማዳረስ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የባህል፣ የታሪክና የቱሪዝም ፀጋዎችና ሀብቶችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ለማስተዋወቅ ያግዛል።
የአገር ገጽታ ግንባታ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ በማከናወን በኩልም የጎላ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪዝም አዋቂና ፈላጊ ማህበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል። ‹‹ይህንን በቀላሉ ለማሳካት ደግሞ ሚዲያ ወሳኝ ሚና ስላለው በዘርፉ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ጋዜጠኞች መኖራቸው ትልቅ እድል ነው›› ብለዋል ።
ቱሪዝም ላይ ትኩረት አድርገው ሲሰሩ የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞች በገንዘብ ችግር ምክንያት ዘርፉን ጥለው ይወጡ እንደነበር አስታውሰው፤ የማህበሩ መመስረት ከመንግስትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያገኙና አቅማቸው እንዲጠናከር ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፤ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል። በቀጣይም ከባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ጋርም በቅንጅት ይሰራል፤ ለማህበሩም ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል። በተለይም በዲጂታል ሚዲያው ላይ ከእስካሁኑ የተሻለ ሥራ ለመስራት ጥረት ያደርጋል።
የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በበኩሉ፤ ቱሪዝም ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ከራሱ ተዋንያን ውጭ አገራዊ የሆነ ግንዛቤ የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሶ፤ ‹‹በኢትዮጵያ የቱሪዝም እውቀት በሚፈለገው ደረጃ ላይ ስላልደረሰ የቱሪስት ቦታዎችን ለማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ምንነትና በፋይዳው ላይ ጭምር አገራዊ እሳቤ ለመያዝ ሚዲያ ወሳኝ ሚና አለው›› ሲል ገልጿል።
የማህበሩ መመስረትም እስካሁን ድረስ በተበታተነ መልኩ ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን በማቀናጀት በዘርፉ የተሻለ ሥራ ለመስራት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግሯል። ለዚህ ዓላማ መሳካት ሲደክሙና እገዛ ሲያደርጉ ለቆዩ አካላትም ምስጋና አቅርቧል።
በኢትዮጵያ የቱሪዝም ጋዜጠኝነት ጽንሰ ሀሳብን ለማስረጽ፣ ባለሙያዎችን የማብዛትና በአቅም በማሳደግ ድርሻ ለማበርከት የማህበሩ መመስረት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ጠቁሞ፣ እንደሌላው ዓለም ለኢንዱስትሪው እድገት የራሳቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ የጉዞ ጋዜጠኞችን፣ የባህል፣ የታሪክና የተፈጥሮ መስህብ ተቆርቋሪዎችን ለመፍጠር ማህበሩ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አመልክቷል።
ፋንታነሽ ክንዴ