
አዲስ አበባ:- የሀገርና የህዝብ ሀብትን በሚያባክኑ አካላት ላይ የህግ አስፈፃሚ አካላት ክንድ መጠንከር አለበት ሲሉ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለጹ። ከዘርፉ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ለውጭ ገበያ መቅረቡንም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአስር ወራት የእቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫውን አስመልክቶ ትናንት በሰጠው መግለጫ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እንደገለጹት፤ የሀገር ሀብት በሚያባክኑ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።
የሀገርን ሀብት ባባከኑ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃዎች ተወስደዋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የማእድን ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ፣ ስራውን ያጓተቱና ቃላቸውን ማክበር ያልቻሉ 27 ተቋማት ፈቃድ ተሰርዟል ሲሉ ጠቁመዋል።
ለሶስት ተቋማት ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠም ጠቅሰው፣ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ምክንያቶች 67 የኢንቨስትመንት ፈቃዶች መሰረዛቸውንም አስታውሰዋል።
‹‹ህግና ስርአትን የማስከበር ጉዞ ከህግ ተጠያቂነት ጋር የሚቀጥል ይሆናል›› ሲሉም ኢንጅነር ታከለ አስገንዝበዋል። ባለፉት ወራት ከተሰሩት የፈቃድ ማጣራት ስራዎች በተጨማሪም ለማዕድን ኤክስፖርት ዘርፍ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠውም ተናግረዋል። ህግና ስርአትን እያስከበሩ የማእድን ዘርፉን በዘመናዊ መልኩ የመገንባት ስራ የሚጠናከርና እያደገ የሚሄድ ይሆናልም ብለዋል።
ሚኒስትሩ፣ ባለፉት 10 ወራት ለውጪ ገበያ በቀረቡ የተለያዩ ማዕድናት ዘርፍ 513 ሚሊዮን ዶላር ማስገባት መቻሉንም ገልፀዋል። የተገኘው ገቢ 6785 ነጥብ 72 ኪሎ ግራም ከሚመዝኑ ማዕድናት መሆኑን አስታውቀዋል። አፈጻጸሙ በእቅድ ከተያዘው 5921 ነጥብ 52 ኪሎ ግራም የመሸጥና 501ነጥብ 73 ሚሊዮን ዶላር የማስገባት እቅድም ብልጫ አለው ብለዋል።
ከዘርፉ በከፍተኛ መጠን ወደ ውጪ ገበያ የቀረበው የወርቅ ምርት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህም 504 ነጥብ 73 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት ችሏል። የዘርፉ ዋነኛ ትኩረት የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን ማበረታታትና ከፍተኛ ማዕድን ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ የውጪ ምንዛሬን ማሳደግ መሆኑንም ኢንጂነር ታከለ አመልክተዋል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም