
አዲስ አበባ፦ ከሱዳን በአምዳይት በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ 320 የጁንታው አባላት መደምሰሳቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር ኃይል ስምሪት ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ አያሌው አስታወቁ። በሀገር ውስጥ የቀሩ የጁንታው ርዝራዦችን ለማደን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ ።
ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በማይካድራ ጭፍጨፋ አድርሰው ወደ ሱዳን በመሸሽ ተደራጅተው ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ የሞከሩ 320 የጁንታው አባላት በመከላከያ ሰራዊት ተደምስሰዋል።
የጁንታው አባላት ከውጭ በሶስት ቡድን ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ እና ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበርም የገለፁት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ፣ ኃይሉ በሦስት ቡድን ተደራጅቶ ለወራት ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር መከላከያ መረጃው እንደነበረው አመልክተዋል።
አንዱ ቡድን አሜሪካ ቀደም ብሎ የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩና ሃገርን ወክለው በሄዱ ከሃዲዎች የሚመራ፣ አሜሪካ ያለውን የጁንታውን ደጋፊዎች የሚያስተባብር እንደነበር የጠቆሙት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ፣ ሌላው ካርቱም ተቀምጦ እዚያ ያለውን ደጋፊ እያስተባበረ ኃይል የሚያደራጅ የሚያሰለጥን መሆኑን ገልጸዋል።
ሶስተኛው ሀገር ውስጥ ያለው የጁንታው ርዝራዥ መሆኑን የጠቆሙት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ፣ ቡድኖች በተቀናጀ መንገድ ይሄን ኃይል ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ እንደነበር አስታውቀዋል።
ከሁለት ወር በፊት በሃገር ውስጥ ተበታትኖና ተደብቆ ያለውን የጁንታውን አመራሮች በሱዳን በኩል በማስወጣት ይሄን ኃይል ለማስገባት አቅደው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አመልክተዋል።
ጀግናው ሰራዊታችን ቀንና ማታ ያለ እረፍት በሚያደርገው አሰሳና ደፈጣ ይህን እቅዳቸውን ማሳካት አለመቻላቸውን ያመለከቱት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ፣ በሀገር ውስጥ ያለው የጁንታው ርዝራዥ እቅዱ አለመሳካቱን ሲያውቅ ወደ መደበቂያ ዋሻው መመለሱን ገልጸዋል።
የመጨረሻ ሙከራ እናድርግ በሚል ከሱዳን ተነስተው በአምዳይት አቅጣጫ፣ ሁመራን መነሻ አድርጎ ወደ ሃገር ውስጥ ለመግባት ሙከራ ማድረጋቸውን ያስታወቁት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ፣ ሙከራውን ያደረገው ኃይል ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታውቀዋል።
ኃይሉ 320 አካባቢ ይገመታል። ከፊሉ በውሃ ጥም እዚያው መንገድ ላይ ተንጠባጥቦ ቀርቷል ያሉት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ፣ ከፊሉም እጅ ሰጥቷል። እጅ ያልሰጠው ሠራዊታችን ባደረገው ስምሪትና አሰሳ ተደምስሷል ብለዋል።
በዚህ ወቅት በርካታ ንብረቶች ፣ ከኢትዮጵያ ጠላቶች የሰበሰቧቸው በርካታ ትጥቆች፣ የሳተላይት ስልኮች፣ የግንኙነት ሬዲዮኖችና ሃገር ውስጥ ላለው አመራር መድሃኒት ይዘው እንደነበር፤ ሁሉም ሙሉ በሙሉ በሠራዊታችን ቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል። ወደ ጁንታው የተላከ ወታደራዊ ምስጢር በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጠቁመዋል።
ይህ ለሰራዊታችንም ለሃገራችንም ከፍተኛ ድል ነው። በመሆኑም አሁንም ይህንን ኃይል የሚደግፍ ከኋላ የቀረ ተደራጅቶ ሊመጣ ያሰበ ኃይል አለ። አሁንም ከመጣ እኛ እንደወትሮው እንጠብቀዋለን። ያለውም መውጣት አይችልም ብለዋል።
በሀገር ውስጥ የቀሩ የጁንታው ርዝራዦችን ለማደን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና “መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እያደረስን ነው” በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን አስታውቀዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም