
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሚዲያዎች የተወጣጣ የልኡካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ በመላክ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመትን እንዲጎበኙ ማድረጉን አስታወቀ።
በቦርዱ ከፍተኛ አመራር ፍቅሬ ገብረ ሕይወት ለተመሩት ከፓርቲዎች እና ከሚዲያዎች ለተውጣጡ ተወካዮች የድምፅ መስጫ ወረቀት የኅትመት ሂደቱን፣ የቴክኒክና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱ ዝርዝር ገለጻ እንደተደረገላቸው አመልክቷል።
ቦርዱ የፍትሐዊ አሠራሩ አንዱ ማሳያ አድርጎ ከሚወስደው የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል መወሰኛ ሎተሪን በይፋ ካስጀመረበት ከመጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመት መጀመሩን ጠቁሟል።
ሥራውን ከሚያካሂዱት ሁለት የኅትመት ድርጅቶች አንዱ በሆነውና በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የሬን-ፎርም ኅትመት ማኅበር ከፓርቲዎች እና ከሚዲያዎች የተወጣጡ የታዛቢ ቡድኑ አባላት መጎብኘታቸውን አስታውቋል።
በጉብኝቱም የሥራ ሂደትና የኅትመቱ የደኅንነት አጠባበቁን ምን እንደሚመስል በኅትመት ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ መደረጉን ያመለከተው ቦርዱ፣ ጎብኝዎች ግልፅ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉትን ነገር በሥራ ኃላፊዎቹና በቦርዱ አመራር ፍቅሬ ገብረ ሕይወት አማካኝነት ማብራሪያ መሰጠቱን አመልክቷል።
ጉብኝቱ የኅትመት ሂደቱ ምን እንደሚመስል፤ ከጥሬ ማቴሪያል ምርት አንስቶ እስከ ኅትመት ሂደቱና የማሸግ ሥርዓቱ ድረስ ያለውን አጠቃላይ ሂደት ያካተተ እንደሆነም ገልጿል።
ፓርቲዎቹም ከጉብኝቱ በኋላ ለብዙኃን መገናኛ አካላት በሰጡት አስተያየት፤ ባዩት ነገር መደሰታቸውን፤ ጉብኝቱም የቦርዱን ግልጽ አሠራር ማሳያ እንደሆነ፤ አጋጣሚውም ፓርቲዎቹ ተቀራርበው ለመወያየት እድል የፈጠረ እንደነበር መግለጻቸውን አመልክቷል።
በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው ኅትመት የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመቱን 45% የሚሸፍን ሲሆን፤ ይኸውም የደ/ብ/ብ/ክ፣ የአማራ ክልል፣ የሲዳማ ክልልና የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሣኔን ያካትታል። ቀሪውና 55% የሚሸፍነው የኅትመት ሥራ ዱባይ በሚገኘው አል-ጉህራር ማኅበር እየተከናወነ ይገኛል።
ለአራት ቀናት በቆየው ጉብኝትም የብልጽግና ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የህብር ኢትዮጵያ ተወካይ (ህብር)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው እና የሚዲያ አካላትም መሳተፋቸውን አስታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም