
አዲስ አበባ፡- የኢትዮ- ቻይና ግንኙነት በኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ትብብርም የጠነከረ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታ ገለጹ። የቻይና ጦር ሀይል ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ፤ የኮቪድ – 19 መከላከያ ክትባትና የገንዘብ ድጋፍ ርክክብ በተካሄድበት ስነ ስርዓት ላይ እንዳሉት፤ የቻይናና ኢትዮጵያ ግንኙነት በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ትብብርም የጠነከረ ነው። ቻይና በኢትዮጵያ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ሰርታለች፤ ኢትዮጵያና ቻይና መከላከያ ለመከላከያ ትብብሮችን አድርገዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት ባደረገበት ወቅት፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚያስከብር ደረጃ አቋም የወሰዱ ቻይና እና ሩሲያ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በቢሾፍቱ እና ጦር ሃይሎች እየተሰሩ ያሉ ሆስፒታሎች ባለሙያዎችን በመመደብ በቻይና መንግስት ትብብር የሚሰሩ ናቸው።
ቻይና ለኢትዮጵያውያን እስከ ፒ ኤች ዲ ድረስ የትምህርት ዕድል እየሰጠች እንደምትገኝ በመጠቆም፤ የመከላከያ ሠራዊትም በእዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆኗን ተናግረዋል። የሁለቱ አገራት በትብብር መሥራት ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታና ግንኙነቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢያን እንደገለጹት፤ ድጋፉ እና ወታደራዊ ትብብሩ የኢትዮጵያና ቻይናን ጥንታዊ ግንኙነት ያሳያል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የቻይና ጦር ሃይል ፈተናዎችን ሲቋቋም ቆይቷል፤ ለኢትዮጵያም ድጋፍ አድርጓል። የኢትዮጵያና የቻይና መከላከያ በሌሎች ጉዳዮችም ሲተባበሩ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው የቁርጥ ቀን ወዳጆች ናቸው። አስከፊ በሚባለው የወረርሽኙ ወቅትም የመከላከል ሥራውን በጋራ ሰርተዋል ብለዋል።
በሁለቱ አገራት አመራሮች የተፈረመው የስትራቴጂክ ግንኙነት የአገራቱን ጠንካራ ግንኙነት እንደሚያሳይ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያና የቻይና ወታደራዊ ግንኙነት በተለያዩ መልኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም