ስደተኛና ከስደት ተመላሾች እንዲሁም ዜጎች በአገራቸው ውስጥ እየደረሰባቸው ስላለው መፈናቀል ላይ ትኩረቱን አድርጎ የመከረው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ሰፊ አጀንዳዎች ላይ ሲወያይ ከርሞ በውሳኔ አጠናቅቋል፡፡ ጉባኤው የተለያዩ አስተያየቶችም ቀርበውበታል፡፡ ህብረቱ ከሚያካሂደው ዓመታዊ ጉባኤ ውጭም በአሰራሮቹ ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት ይነገራል፡፡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በጉባኤው ላይ ከተሳተፉት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራተጂ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ሙሉዓለም ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጉባኤው ላይ ተሳታፊ ስለነበሩ ጉባኤውን እንዴት ገመገሙት ምንስ ታዘቡ?
አቶ መላኩ፡- ጉባኤው አዲስም የተለመዱም ነገሮች ነበሩት፡፡ የጉባኤው አጀንዳ ስደትና በአገር ውስጥ የዜጎች መፈናቀል ላይ ትኩረት ማድረጉ በተለይ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ነው ብዬ ወስዳለሁ፡፡ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ከጎረቤት ሀገሮች የተሻለች እንደሆነች ይነገራል፡፡ነገር ግን በአገሯ ውስጥ ዜጎቿ ከመኖሪያቸው ይፈናቀላሉ፡፡ ስለዚህ መፈናቀልም ስደትም ኢትዮጵያን ይመለከታታል፡፡ የተለመደው ነገር በአንድ ጊዜ ብዙ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ማካሄዳቸው ነው፡፡ ለውይይት የቀረቡት አጀንዳዎች ሰፊ ናቸው፡፡ አጋርነት፣ የንግድ ልውውጥ፣ ሰላምና ፀጥታ፣ አሸባሪነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፋይናንስ አቅም እጥረት፣ አየር ንብረት ለውጥ፣ እዳ ስረዛ፣ ሴቶችን ከማስተማር እና መውጣት ስላለባቸው አዳዲስ ህጎችና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው የተነሱት። ለእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች መቋጫ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ ከአጋርነት ጋር ተያይዞ የተነሳው አፍሪካ አገሮች ከአውሮፓ ሀገሮች ጋር አጋርነት ሲመሰርቱ በድብቅ መሆን እንደሌለበትና አህጉራቱ እንደ አቋም የያዙትን ነገር የሚሸረሽር መሆን እንደሌለበት እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ከንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ጋር ያስቀመጠውን መስፈርት መጣስ የለበትም የሚል ነው፡፡ ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘም ታዳጊ አገሮች በዓመት አንድ መቶ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአደጉ አገሮች ማግኘት እንዳለባቸው የሚያሳስብ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ሌላው እንደአቋም የተያዘው በፀጥታው ምክርቤት ኮሚሽን ውስጥ ህብረቱ የወከላቸው ሁለት ቋሚ እና አምስት ተለዋጭ አባላት እንዲኖሩ፣ የተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክርቤት (ሴኪዩሪቲ ካውንስል) አደረጃጀት ጉዳይም በተደጋጋሚ አጀንዳ ሆኖ ተነስቷል፡፡ ካውንስሉ ከተቋቋመ 74 ዓመቱ ሲሆን፤ እስካሁን ፀጥታው ምክርቤት አደረጃጀቱ አልተከናወነም፡፡የአባል አገራቱ ዕዳ ስረዛ ጉዳይም እንዲሁ ሌላው አጀንዳ ነበር፡፡ በተለይ ሶማሊያ አዲስ የተቋቋመች መንግሥት በመሆኗ ብዙ ዕዳ አለባት፡፡ በመሆኑም ዕዳዋ ተሰርዞላት እንድትጠነክር የሚል ውይይት ተካሂዷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከተነሱት አጀንዳዎች በተለየ የሚጠቅሱት ይኖራል?
አቶ መላኩ፡- የፀጥታው ምክርቤት ጉዳይ በተደጋጋሚ የሚነሳ ቢሆንም በአሁኑ በቋሚም በተለዋጭም ውክልና ሊኖራቸው እንደሚገባ ጎልቶ የወጣና አቋም የያዙበት ጉዳይ ነበር፡፡ አፍሪካን የሚወክል ይኑር የሚለው ለእኔ ከፍ ብሎ ታይቶኛል፡፡ ለአጼ ኃይለስላሴ ሃውልት መቆሙና ክብር ማግኘታቸውም ከሃውልቱ በስተጀርባ ብዙ መልዕክቶችን የያዘ በመሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- መሪቃሉ ላይ የህብረቱ መሪዎቹ አፅንኦት ሰጥተው ያነሱት ጉዳይ ነበርን?
አቶ መላኩ፡- ደሀ ሀገር ሆነው ስደተኞችን ይሸከማሉ፡፡እነዚህ አገሮች እንዳደጉት አገሮች ስደተኞች እንዳይገቡባቸው አለመከላከላቸው በጉባኤው ላይ እንደ ጥሩ ጎን ተነስቷል፡፡ አዲስ ዘመን፡- የአፍሪካ መሪዎች በየዓመቱ ችግሮቻቸው ላይ ይወያያሉ ግን ዛሬም ዜጎቻቸውን ከስደት እንዳላስቀ፣ ሁከትና ግርግር እንዳልተለያቸው፣ ሙስና መስፈኑ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው አለመቀረፋቸው ይተቻል በዚህ ላይ ምን ምላሽ አለዎት? አቶ መላኩ፡- ትክክል ነው፡፡ እንደ አጀንዳ ያልተነሳ ጉዳይ የለም፡፡ ከተነሱት አጀንዳዎች ውስጥም ያልጸደቁ አሉ፡፡ 44 ዓመት ሙሉ ረቂቅ አዋጅ ሆኖ የቀረ አለ፡፡ መሪዎች የተስማሙባቸውን ጉዳዮች ከተፈራረሙ በኃላ በየሀገሮቻቸው በፓርላማ ማጸደቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአብነትም መሪዎች በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዘርፍ ለመረዳዳት እ.ኤ.አ. በ1975 ዓ.ም መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ ዛሬ በየሀገራቸው በፓርላማ ባለማጽደቃቸው 44ዓመት ሳይፀድቅ ተንጠልጥሎ ተቀምጧል፡፡ በርካታ ውሳኔዎች ደግሞ ትግበራቸው አነስተኛ ሆኖ ይታያል፡፡ በሙሁራንም የሚተቸው መሪዎች በጉባኤያቸው ውሳኔ የማሳለፍ ችግር የለባቸውም፡፡ የተወሰነውን ሥራ ላይ ማዋል ግን ሰፊ ክፍተት አለባቸው፡፡ አንድ አዋጅ ከወጣ በኃላም መተግበሩን የመከታተል ክፍተት አለባቸው፡፡ በጉባኤውም የክትትልና ግምገማ ስርዓት ጠንካራ መሆን እንዳለበት ተነስቷል፡፡ ለማሻሻልም ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ሙስናን ለመዋጋት ጉዳዩን የሚከታተል ከማዳጋስካር፣ ከቡርኪናፋሶ፣ ከቻድ፣ ከቤኒን፣ ከዛምቢያ፣ ከሌሴቶ የተውጣጣ አማካሪ ቦርድ በማቋቋም ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ የሚፈለገው ውጤት ባለመምጣቱ ክፍተቱ ይስተዋላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አፍሪካዊያን ህብረታቸውን ተጠቅመውበታል ይላሉ?
አቶ መላኩ፡- አንድን ነገር ለመተግበር የህግ ማዕቀፍ ወይም መሰረት ማስቀመጥ ነው፡፡ እዚህ ላይ ችግር የለባቸውም፡፡ ያሳለፉት ውሳኔ እና ያወጡት ህግ በትክክል መተግበሩን ተከታትሎ መፈጸም ላይ ክፍተት አለባቸው፡ ፡ ችግሩ የሚመስለኝ የአፍሪካ መሪዎች ስልጣንን አለማሸጋገራቸውና የስልጣን ገደብ አለመኖር እንዲሁም በመሪነት ላይ ለመቆየት ህገ-መንግሥቱን ለእነርሱ በሚመች መልኩ የማሻሻል ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ሩዋንዳን፣ አልጀሪያንና ሱዳንን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር አለመኖር የፈጠረው ጫናም አለ፡፡ ሁሉንም በአንድነት መደምሰስ ባይቻልም ችግሩ አብዛኞቹ ዘንድ ይስተዋላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- መሪዎቹ በጉባኤያቸው ላይ እርስ በርስ የመተቻቸት ባህል አላቸውን?
አቶ መላኩ፡- እገሌ ይህንን አድርገሀል ብሎ ለመተቸት ዕድሉ የለም፡፡ በአንድ እርዕሰ ጉዳይ የሚቀርብ ሪፖርት እንኳን በቡድን በጋራ የተመከረበትና ውይይት የተደረገበት ነው፡፡ ለምሳሌ የኬንያው ፕሬዚዳንት መልካም አስተዳደር ላይ ያቀረቡት ሪፖርት ለብቻቸው ያዘጋጁት አይደለም፡፡ የሌሎች አገሮች መሪዎች በጉዳዩ ላይ ተወያይተውበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጉባኤው ሌሎችን አሳታፊ ነውን?
አቶ መላኩ፡- ህብረቱ የሚጋብዛቸው ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ህብረቱን በተለያየ መንገድ የሚደግፉ ተሳታፊዎች በጉባኤው ላይ ይገኛሉ፡፡ አዲስ ዘመን፡- ተሳታፊዎቹ ሀሳብ መስጠት ይችላሉ?
አቶ መላኩ፡- ከዋና ስብሰባ ጎን ለጎን የሚካሄዱ ስብሰባዎች አሉ፡፡ በዛ ላይ ነው የሚሳተፉት፡፡ተሳታፊዎቹ አቋም ይዘው ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በህብረቱ ውስጥ የህዝብ፣ የወጣቶች፣ የሴቶች ተሳትፎ የተከበረ አይደለም ብለው ጫና በሚፈጥር መልኩ ሀሳብ ሊያነሱ ይች ላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህብረቱ በጉባኤው በሌላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ውሳኔ ያሳልፋል?
አቶ መላኩ፡- 55ቱም አገሮች አንድ ሲሆኑ ነው ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉት፡፡ አህጉራቱ ከአው ሮፓና ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር አጋርነት ከመፍጠራቸው በፊት አሳው ቁን የሚል እና በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥም ውክልና እንዲኖራ ቸው አቋም የያዙትም ተጽዕኖ ለመፍጠር ነው፡፡ አፍሪካዊያን የሚከራ ከሩበት ጉዳይ አለ፡፡ እንደ አህጉር ያላቸው የህዝብ ብዛት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ሆኖ፣ በዓለም ላይም አንድ ሰባተኛውን ህዝብ ይዘውና በአገር ብዛትም 55 ሆነው እንዴት በፀጥታው ምክርቤት ውክልና እናጣለን የሚል መከራከሪያ ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ የሆኑ ብቻ ተሰባስበው ነው በእኛ ጉዳይ ላይ የሚወስኑት በማለትም ተቃውሞ ያነሳሉ፡፡ በቅርቡ የአሜሪካን መንግሥት በፀጥታ አማካሪው በኩል የተናገረው ነገር አለ፡፡ የፀጥታ መደፍረሶችን ለማስቆም የሚያስችለውን ለሰላም ማስከበር የገንዝብ ድጋፍ አላደርግም በሚል ውሳኔ እያስተላለፈ ነው፡፡ አፍሪካዊያን ይህን ለማቋቋም ነው አንድ እንሁን እያሉ ያሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሀሳብ ባለፈ የወሰዱት እርምጃ አለን?
አቶ መላኩ፡- እዚህ ላይ የኢኮኖሚ ድህነቱ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሀብታም አገሮች እጅ የመጠምዘዝ አቅሙ አላቸው፡፡ ዶላርና ዲፕሎማሲ የሚባል አለ፡፡ ገንዘብ በማፍሰስ ሀሳብ የማስቀየር ነገር አለ፡፡የህብረቱ አባል አገራት ክፍያ ወይም መዋጮ አለባቸው፡፡ ግን በአቅም ውሱንነት ጥገኛ ይሆናሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የህብረቱ አባል አገራት በህዝብ እና በአገር ብዛት የተሻሉ ሆነው በሃያላን አገራት ተጽዕኖ ስር ለመውደቃቸው መንስኤው ምንድ ነው ይላሉ? አቶ መላኩ፡- ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው ። አንዱ በኢኮኖሚ አለማደግ ነው፡፡ የአብዛኞቹ አፍሪካዊያን የንግድ ልውውጥ ከቅኝ ገዥዎቻቸው ጋር ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ያነሱትን መጥቀስ ይቻላል። ወደ አምስት ቢሊዮን ቶን የሚጠጋ በቆሎ እናመርታለን፡፡ የምንጠቀመው ግን አንድ ቢሊዮን ቶን ነው፡፡ቀሪውን ባለመጠቀማችን ዋጋው ወደቀ፡፡ አፍሪካ ውስጥ የገበያ ትስስር ቢኖረን እርስ በርስ መረዳዳታችን ይጎለብታል፡፡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችንም ያድጋል፡፡ ይህ አፍሪካ ውስጥ የንግድ ትስስሩ አነስተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የህብረቱ አባል አገራት ለተለያየ ወጭ የሚውል የሚጠበቅባቸውን ክፍያ አይፈጽሙም ይባላል እዚህ ላይ ምን ሀሳብ አለዎት?
አቶ መላኩ፡- ክፍያው ከውጭ አገር ገንዘብ ወይንም ዶላር ጋር ይያያዛል፡፡ የመክፈል አቅም ስለሌላቸው የሀብታም አገሮችን ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ እስከመቼ ይቀጥላል የሚል ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ ዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶ ሁሉም ከገቢው ላይ እያዋጣ አፍሪካ እራስዋን ትቻል በሚል እየሰሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ግን በዚህ አትወቀስም ቀዳሚ ከፋይ አገር ናት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በህብረቱ ኮሚሽን ውስጥ ከሌሎች አገሮች አንጻር የመሪነት ሚናዋ አናሳ እንደሆነ ይነሳል ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ መላኩ፡- አመራሩ በተራ የሚከናወን እንጂ በቋሚነት ተይዞ የሚኬድ አይደለም፡፡ በየጊዜው ይቀያየራል፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መርተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ውስጥም ቢሆን እንዲሁ ነው ያሉት55 አገሮች ስለሆሉ ዕድሉ ጠባብ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱን ግን በእርግጠኝነት ለመግለጽ ይቸግረኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከህብረቱ የስራ ቋንቋ ጋር በተያያዘም የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ መላኩ፡- ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች በአንግሊዝና በፈረሳይ አገሮች በቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ያን ቋንቋ የመጠቀም ዝንባሌ አለ፡፡ አንዳንዴ አቋም ሲይዙም እንደ አፍሪካ ሳይሆን፣ እንደ ቋንቋ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ እኛ ፍራኮፎኖች ወይም አንግሎፎኖች የሚል ነገር ያንጸባርቃሉ፡፡ አንዳንዴም ፍራኮፎኖች አቋም ይዘው የሚመጡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የቋንቋ ጉዳይ አፍሪካን ይከፍላታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህብረቱ ባሳለፈው ረጅም ዓመት ይህ ነው የሚባል የሚጠቀስ ነገር አለው?
አቶ መላኩ፡- ያልተቋረጠ ስብሰባ ማካሄዳቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ አጀንዳ ይቀርጻሉ፡፡ በአጀንዳው ላይም ይወያያሉ፡፡ መፍትሄም ያስቀምጣሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደፊት ከህብረቱ ምን እንጠብቅ?
አቶ መላኩ፡- ስልጣንን ለረጅም ጊዜ ለማስቀጠል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሊያዩት ይገባል፡፡ ህዝብ የመረጣቸው መሪዎች ሲበዙ የአፍሪካ አንድነት እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ ሙስና ላይ ይሰራ ሲባል መሪው ሙሰኛ መሆን የለበትም፡፡ በመካከላቸው የንግድ ልውውጥ በማጠናከር ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ጠንካራ ተቋም በመገንባት ችግሮችን እየፈቱ መሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡አምባገነን መሪ ሆኖ በህብረቱ የተላለፉ ውሳኔዎች ይተገበራሉ ማለት አይታሰብም ፡፡ስለዚህ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
ለምለም መንግሥቱ