የአካባቢ ደህንነት መብት የዜጎችን ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት የሚያመላክት ነው።ይህ ንፁህና ለጤና ተስማሚ የሆነ አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች ሊበከል ስለሚችል በአካባቢያችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ብክለት በመከላከል ንጹሕ፣ ጽዱ እና ለኑሮ አመቺ የሆነ አካባቢን ለመፍጠርና ለመጪው ትውልድም ለማስረከብ አካባቢን ከሚያበላሹ ነገሮች መጠበቅ ያስፈልጋል።ከዚህ አንፃር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወሰዱ የቆዩ ሲሆን ኢትዮጵያም የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ የተለየዩ የሕግ ማዕቀፎችና ሌሎች እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች፡፡
አካባቢ ማለት በመሬት፣ በአየር፣ በአየር ሁኔታ እና በአየር ንብረት፣ በውሃ፣ በህያውያን፣ በድምጽ፣ በሽታ፣ በጣም፣ በማህበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በስነውበት ሳይወሰን በተፈጥሯዊ ሁኔታ ወይም በሰው አማካኝነት ተሻሽለው ወይም ተለውጠው የሚገኙ ነገሮች በሙሉና ያሉበት ቦታ፤ እንዲሁም መጠናቸውን ወይም ሁኔታቸውን አልያም ደግሞ የሰው ወይም የሌሎችን ሕያዋን ሁኔታን የሚነኩ መስተጋብሮቻቸው ድምር መሆኑን የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/995 ይደነግጋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃን ከማረጋገጥ አንፃር በአገሪቱ ከተዘጋጁት የሕግ ማዕቀፎች መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት፣ በ1987 ዓ.ም የወጣው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መቋቋሚያ አዋጅ (በ1995 ዓ.ም የተሻሻለው)፣ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/1995፣ የአከባቢ ብክለት አዋጅ ቁጥር 300/1995፣ የ1997ቱ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ይጠቀሳሉ፡፡
በ1987 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ለአካባቢ ደህንነት እውቅናና ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን፤ በአንቀጽ 44 (1) ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው።እንዲሁም በአንቀፅ 92 መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው ጥረት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጓል።በተጨማሪም ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት እርምጃ የአካባቢውን ደህንነት ያገናዘበ እንዲሆን እና የሕዝብን የአካባቢ ደህንነት የሚመለከት ፖሊሲ እና ፕሮግራም በሚነደፍበት እና ስራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ ሰፍሯል።
ሌላው ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ ከወጡ ሕጎች አንዱ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/995 ነው።በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጁ መሰረት የልማት ንድፈ ሀሳብ ሲዘጋጅ፤ ቦታው ሲመረጥ፤ ሲገነባ ወይም ሲተገበር የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በመተንበይ እና አስቀድሞ በማረም በውል የታሰበበትን ልማት ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑን ይደነግጋል።
በአዋጁ ላይ እንደተቀመጠው ተፅዕኖ ማለት በአካባቢ ወይም በንዑሳን ክፍሎች ላይ በሚፈጠረው ለውጥ ምክንያት ማንኛውንም በሰው ጤና ወይም ደህንነት፣ በእጽዋት፣ በእንስሳት፣ በአፈር፣ በአየር፣ በአየር ንብረት፣ በውሃ፣ በተፈጥራዊ ወይም በባህላዊ ቅርስ፣ በሌላ ቁሳዊ አካል በአጠቃላይ ሲታይ በአካባቢያዊ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ወይም በባህላዊ ገጽታዎች ላይ ሚከሰት ተከታይ ለውጥ ነው።
እንዲሁም በካይ ማለት ፈሳሽ፣ ጠጣር ወይም ጋዝ ሆኖ በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ያረፈበትን የአካባቢ ክፍል ጥራት በመለወጥ ጠቀሜታ የመስጠት አቅሙን የሚያጎድል፣ በሰው ጤና ወይም በሌሎች ሕያውያን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ወይም ሊያደርስ የሚችል መርዝን፣ በሽታን፣ ሽታን፣ ጨረርን፣ ድምጽን፣ ንዝረትን፣ ሙቀትን ወይም ሌላ ክስተትን የሚያመነጭ ማንኛውም ነገር ነው፡፡
በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጁ መሰረት ማንኛውም ሰው የአካባቢ ግምገማ ተጽእኖ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ወይም ከሚመለከተው የክልል አካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት ይሁንታ ሳያገኝ መከናወን እንደሌለበት ያስቀምጣል።የአካባቢ ግምገማ ተጽእኖ ጥናት ከፕሮጀክቱ ከባለቤቱ ወጭ መከናወን እንዳለበት እና ባለስልጣኑም ይህን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል።
ይህ አዋጅ በአንቀጽ 8 (2) ስር የአካባቢ ግምገማ ተጽእኖ ጥናት ሊያካትት የሚገባውን ነገሮች በዝርዝር ያስቀምጣል።የፕሮጀክቱ ባህሪ በጥቅም ላይ የሚያውለውን ቴክኖሎጂ እና አጠቃቀም፣ ፕሮጀክቱ ሲተገበር እንዲሁም ቋሚ ስራው ሲከናወን ወደ አካባቢው የሚለቀቀውን የበካይ ይዘት እና መጠን፣ የሥራው እንቅስቃሴ የሚጠይቀውን የኃይል ፍጆታ እና ምንጭ፣ ሊከተል ስለሚችል ክልል ተሻጋሪ የአካባቢ ተጽዕኖ መረጃ መታወቅ አለበት፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይከተላሉ ተብለው የተተመኑ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖዎች ባህሪያትና የሚቆዩበትን ጊዜ እንዲሁም አሉታዊ ተጽዕኖን ለማስወገድ፣ ለመቀነስ ወይም ለማቃለል የታቀዱ እርምጃዎች፤ የአካባቢ አያያዝ ችግርን ለማቃለል የተነደፉ እቅዶች፤ የአደጋ መከላከያ ዝግጁነት እና ፕሮጀክቱ በሚተገበርበት ወቅት የውስጥ የቁጥጥር እና የክትትል ስራዎች የሚካሄዱበትን መንገዶች ማስቀመጥ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
ስለዚህ ከተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች አንጻር የአካባቢ ጥበቃ ሕጎችን ጥሰትና የሕግ ተጠያቂነት ስንመለከት በ1996ዓ.ም የወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 521 እንደሚደነግገው፤ ማንኛውም ሰው የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲደረግበት በሕግ የታዘዘውን ማንኛውንም ፕሮጀክት ከተገቢው አካል ፍቃድ ሳያገኝ ተግባራዊ ያደረገ እንደሆነ ወይም ይህንኑ በተመለከተ ሀሰተኛ መግለጫ ያቀረበ እንደሆነ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል።
እንዲሁም በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ መሰረት ማንኛውም የፕሮጀክት ባለቤት የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሳያደርግ እና የባለስልጣኑን ይሁንታ ሳያገኝ ተግባራዊ ያደረገ እንደሆነ ወይም በጥናቱ ሀሰተኛ መግለጫ ያቀረበ እንደሆነ ከ50 ሺህ ብር በማያንስ እና ከ100 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።
በተጨማሪም በዚህ አዋጅ መሰረት ማንኛውም ሰው ፍቃድ ሲሰጠው የተጣለበትን ግዴታ ካልተወጣ ወይም ተፈላጊ ዝርዝሮችን በመዝገቡ ሳያሰፍር ከቀረ ከ10 ሺህ ብር በማያንስ እና ከ20 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ ተቀምጧል።ከዚህ ባሻገር ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ጥፋት ሲፈጽም ድርጅቱ እንዲከፍለው ከተፈረደበት መቀጮ በተጨማሪ የድርጅቱ የሥራ መሪ ከአምስት ሺህ ብር በማያንስ እና ከ10 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ መሆኑ ተደንግጓል።
ይህን አዋጅ ወይም በሥሩ የሚወጣውን ደንብ ወይም መመሪያ በመጣስ ጥፋተኝነቱ የተረጋገጠበት ሰው ከሚወሰንበት ማንኛውም ቅጣት በተጨማሪ ያደረሰውን ጉዳት በሙሉ እንዲያስተካክል ወይም እንዲተካ ፍርድ ቤቱ ማዘዝ እንደሚችል አዋጁ አስቀምጧል፡፡
በአጠቃላይ አካባቢን ከሚጎዱና ከሚበክሉ ድርጊቶች የመጠበቅና ተፈፅሞ ሲገኝ የመከላከል ወይም ለሚመለከተው አካል ጥቆማ የመስጠት ኃላፊነት ከሁሉም ዜጎች፣ ድርጅቶችና ከመንግሥት አካላት ይጠበቃል።እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃንና ልማትን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ሕጎች ሲወጡ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንዲሆን ማድረጉ ህብረተሰቡን ከአካባቢ ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ንፁህ እና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር ያግዛል፡
ምንጭ:- ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም