የ ቱሪስት መዳረሻ ከሆኑ ሀገሮች መካከል ስሟ የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ ሰፊ ከሆነው የቱሪዝም መስህብ ሀብቷ መካከል የዱር እንስሳትና ጥብቅ ደን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጥብቅ ደኑን ከሚጎበኙ ቱሪስቶች፣ ለምርምር ከሚመጡና ከስፖርታዊ አደን ገቢ የሚገኝበት ሲሆን፤ በየዓመቱ አምስት በመቶ ገቢ በማስገኘት እያደገ የመጣ ኢንዱስትሪ እንደሆነና በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ በማህበራዊ አገልግሎቶችም ጉልህ ሚና እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
እንዲህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የሚነገርለት የዱር እንስሳት ጥብቅ ሀብት የሚደረግለት ጥበቃና እንክብካቤ አናሳ በመሆኑ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ እንዳላደረጋት በዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ዙሪያ የሚሰራ ቦርን ፍሪ ፋውንዴሽን በተባለ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶክተር ዘላለም ተፈራ ያስረዳሉ፡፡ ዶክተር ዘላለም የዱር እንስሳት ልማት ያለውን ዘርፈብዙ ጥቅም፣ የዘርፉን ተግዳሮቶችና መሰራት ስላለበት ሥራ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡፡
የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የዱር እንስሳት መኖሪያ ወይም ፓርኮች አስፈላጊው እንክብካቤና ጥበቃ ከተደረገላቸው የውሃ ቋቶች ናቸው፡፡ኢትዮጵያ 12 የውሃ ተፋሰሶች አሏት፡፡ ከእነዚህ መካከልም ትልቁ አባይ ነው፡፡ ወንዞቹ ውሃ የሚያገኙት፡፡ ከተራራማና ከዱር እንስሳት መኖሪያ ጥብቅ ደኖች ነው፡፡ የባሌ ተራሮች ፓርክ ለአብነት ይጠቀሳል። ከፓርኩ ውስጥ 49 ወንዞች ይፈስሳሉ፡፡ ወደ ታችኛው ባሌ፣ አርሲና መልካዋከና አካባቢ የሚገኙ ትላልቅ ግድቦች እና ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚገመተው የአካባቢው ነዋሪ ከባሌ ተራራ በሚፈስሱ ወንዞች በመጠቀም የግብርና ሥራውን ያከናውናል፡፡ የመጠጥ ውሃም የሚያገኘው ከእነዚሁ ወንዞች ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ሙቀት መጨመርን መቋቋም የሚቻለው ጥብቅ የዱር እንስሳት ደንን መንከባከብና መጠበቅ ሲቻል ነው፡፡ የደን ቦታዎች እንደ ስፖንጅ ሆነው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛው‹‹ካርበን ሲንክ›› ይባላል፡፡ የተቃጠለውን አየር ‹‹ካርበንዳይኦክሳይድ›› በቅጠሎች፣ በዛፎችና በግንዶች እንዲሁም በመሬት ውስጥ ሰብስበው በማስቀመጥ ንጹህ አየር ያወጣሉ፡፡አካባቢው የማይረበሽና ምቹ በመሆኑም ለንብ ማነብ የጎላ ጠቀሜታ አለው። አካባቢው ካልተጠበቀና አስፈላጊው እንክብካቤ ካልተደረገለት የጫካ ማር ሊኖር አይችልም፡፡ በሀገር ደረጃም በሚመረተው የማር ምርት መጠን ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ለምርምር፣ ለጉብኝትና ለአደን ከተለያዩ ዓለማት ወደ ስፍራው የሚሄዱ ቱሪስቶች ለትራንስፖርት፣ ለሆቴል፣ ለምግብና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚያወጡት ወጪ ገቢ በመሆኑ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ የዱር እንስሳት ልማቱ ከተጠናከረ ከእርሻ ስራ ወደ ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለመሸጋገር ዕድል ይፈጥራል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በሰሜን ሸዋ ጓሳ አካባቢ ምንም ቱሪስት ያልነበረ ሲሆን፤ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ በመቻሉ የቱሪስት ፍሰቱ ጨምሯል፡፡ይህም የአካባቢውን ነዋሪ ለሥራ በማነሳሳትና የገቢ አማራጭ በመሆንም አግዟል፡፡ የዱር እንስሳት ጥብቅ ደን ለምርምር እያበረከተ
በመሆኑ በእጽዋት ላይ የሚከናወኑት የምርምር ሥራዎች በሰው ልጅ ህልውና ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው ህብረተሰብ መድኃኒት የሚያገኘው ከተፈጥሮ ሲሆን፤ ጤናአዳም፣ ዳማከሴ፣ እንዶድ የመሳሰሉት ዕጽዋት ይጠቀሳሉ፡፡ጥብቅ የዱር እንስሳት ደን እነዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ቱሪስቶች የዱር እንስሳትን በመጎብኘት ብቻ ሳይሆን በስፖርታዊ አደንም ይዝናናሉ፡፡ የእንስሳት አደኑ በዘፈቀደ ሳይሆን ዕድሜያቸው ለአደን የደረሱ የዱር እንስሳት ተመርጠው ነው የሚታደኑት፡፡ ለዚህም ህግ ተቀምጧል፡፡
ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበት በመሆኑ በዚህ ረገድም ህግን ተከትሎ ከተሰራበት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡ ፡ ከዱር እንስሳት ጥብቅ ደን የሚገኝ ገቢ ኢትዮጵያ ከዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎች በዓመት 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ታገኛለች። ዘርፉን በመጠበቅና በመንከባከብ ውጤታማ ስራ ተሰርቶ ቢሆን ግን ዓመታዊ ገቢዋን በእጥፍ ታሳድግ ነበር፡፡ለዜጎቿ የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍም ያግዛት ነበር። ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ የሚያገኘው ከጥብቅ ደኑ በመሆኑ አስፈላጊው እንክብካቤና ጥበቃ መደረግ ይኖርበታል። ዘርፉ በዓለም ላይ ትልቅ ኢንዱስትሪ ተደርጎ የሚወሰድና በየዓመቱም በአምስት በመቶ እያደገ የመጣ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የዘርፉ ማነቆዎች አብዛኞቹ የዱር እንስሳት ጥብቅ ደኖች መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ እና ሌሎችም መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ባለመሆናቸው ለቱሪስቶች ምቹ እና ሳቢ አይደሉም፡፡ ድንበሩ የተጠበቀ ባለመሆኑ ለእርሻ፣ ለግጦሽና ለሰዎች መኖሪያ እየዋለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዱር እንስሳቱ እንዲሰደዱ ከማድረጉ በተጨማሪ ለጤና ችግርም እያጋለጣቸው ነው። በአሁኑ ጊዜ ቀይ ቀበሮ በውሻ
በሽታ እየተጠቃ ነው፡፡ ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ይገኛል፡፡ ህገወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርና አደንም ለዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት እየሆኑ ናቸው። ቀይ ቀበሮ፣ ዋልያ፣ ማውንቴን ኒያላ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የዱር እንስሳት ናቸው፡፡ እነዚህን በማስተዋወቅ ገቢ ለማግኘት የሚደረገው ጥረትም ደካማ ነው፡፡
የባለሙያዎች፣የባለድርሻና የመንግሥት ጥረት የዱር እንስሳት ጥብቅ ደን ለእርሻ እንዳይውል እርሻውን ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ በአነስተኛ ቦታ ላይ ከፍተኛ ምርት የሚገኝበትን አሰራር በመከተል ችግሩን ማቃለል አንዱ ዘዴ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣት በመሆኑ ዘርፉን የሥራ ዕድል ማግኛ ማድረግ ይቻላል። የቤተሰብ ምጣኔም አብሮ መሰራት አለበት። የመሬት ፖሊሲ ለማውጣት የሚደረገው ጥረትም መጠናከር አለበት፡፡ በባለሙያው በኩል እንቅስቃሴዎች ተጀም ረዋል። በዘርፉ ላይ የምንገኝ ጥቂት ሰዎች ተሰባስበን ‹‹ቲንክታንክ›› በሚል ስያሜ ተሰባስበናል።
ለፖሊሲ አውጭዎች የሚያግዝ ጥናት በማካሄድና የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን። አንዴ የሚወጣ ህግ በቂ ባለመሆኑ የዘርፉን ችግሮች በየጊዜው እየፈተሹ ህጉን ማሻሻል ይጠበቃል፡፡ ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ካልተሰጠ ተጽዕኖው በኢኮኖሚው ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የውሃ ቋትነታቸው ተጠብቆ ካልቆየ በሰው ልጅ ህልውና ላይም ትልቅ አደጋ ይጋረጣል፡፡ እነዚህን ሁሉ ግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አካባቢ፣ ደንና የአየርንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከልማታዊ አጋር ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን፣ ሀገራዊ አቅም በመፍጠር እንዲሁም ህዝቡን ከልማቱ ጋር አቀናጅቶ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እና የተቀመጡ ግቦችንም ለማሳካት እንዲቻል ምክክር እየተደረገ መሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
ለምለም መንግሥቱ
機票 價格比較了一下發現HOPEGOO很便宜,這網站也很方便容易用,有中英文介面。之後會推薦我的朋友來這邊訂!
機票 價格比較了一下發現HOPEGOO很便宜,這網站也很方便容易用,有中英文介面。之後會推薦我的朋友來這邊訂!