የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና አመራሩ ከወዲያ ወዲህ ሲሉ ለተመለከተ በአንዳች ጥድፊያ ውስጥ እንዳሉ መረዳት አያዳግትም፡፡ አንድም በትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ መምከሩ አንድም ደግሞ የተማሪዎች ቅበላ ወቅት እንደመሆኑ ዝግጅቱ ለጥድፊያቸው መነሻ ቢሆንም በተለይ በተለይ ግን ከሞቀ ቀያቸው ለተፈናቀሉ፣ ቤት ንብረታቸውን ትተው ሰላም ፍለጋ ተሰደው ከግቢያቸው ውስጥ ለተጠለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተቻላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ተፍ ተፍ ማለታቸው፣ ከወዲያ ወዲህ እንዲሯሯጡ አስገድ ዷቸዋል፡፡
‹‹ለዚህ ችግር የተዳረጉ ተፈናቃዮች ዘላቂ ሰላም ሊያገኙ የሚችሉት በምን ዓይነት መንገድ ነው›› በማለት ለዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጥያቄ ባነሳንላቸው ወቅት እንዳስረዱት፤ ዋናው ጉዳይ የግጭቱን መንስዔ ለማወቅ መስራት አንዱ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ሆነ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ማህበረሰብ መካከል መቀራረብ እንዲኖር መስራት ደግሞ ሌላው ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተርና በጆርናሊዝም ክፍለ ትምህርት መምህር የሆኑት አቶ ያሬድ ደሳለኝ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰብ አገር ናት፡፡ ህንድም ወደ 324 የሚጠጉ ብሄር ብሄረሰብ ያለባት አገር መሆኗም የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁንና አንድም ቀን በኢትዮጵያ የሚታየው ዓይነት ግጭት ተነስቶ አያውቅም፡፡ የብሄርም ጉዳይ ሲነሳ አይስተዋልም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ማህበረሰቡ ግንዛቤው የሰፋ በመሆኑ በብሄር ጉዳይ ጥያቄ አያነሳም፡፡ በተጨማሪም ድንበር አይገድበውም፡፡
‹‹አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰብ መኖሪያ ስለሆነች አንዱ ብሄር ሌላው ዘንድ ሄዶ መኖር፣ ሌላውም መጥቶ መስራት ይችላል፡፡ ይህ ጉዳይ ህገ መንግሥቱም ላይ የተቀመጠ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ይህ ሲጣስ ይታያልና ጉዳዩን ማህበረሰቡ በአግባቡ ማወቅ እንዲችል ማድረግ የመጀመሪያ እርምጃ መሆን ይገባል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ መንግሥት በዚህ ላይ ትልቅ ሥራ መስራት ይኖርበታል ይላሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ አነጋገር፤ ከውስጥም ከውጭም እንደዚህ ዓይነት ግጭት እንዲከሰቱ የሚያደርጉ ኃይሎች በመንግሥት በኩል ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ማስጠንቀቂያ ብቻ ሳይሆን እርምጃም ሊወስድ ይገባል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሁለቱም ክልል ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ እርስ በርሱ የሚተዋወቅና ለዘመናትም ተዋዶና ተዋልዶ አንድ ላይ የኖረ እንደመሆኑ አሁን ላይ እየታየ ያለውን አለመግባባት ፈር ማስያዝ የግድ ይላል፡፡
አቶ ያሬድ እንደሚሉት አገርን መገንባት የሚቻለው በጥላቻ፣ በተንኮልና በማባላት ሳይሆን በፍቅር፣ በሰላምና በመደጋገፍ ብቻ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ አገራችንን እየታየ ካለው ችግር መታደግም በልማቱ በኩል ማሳደግም ይቻላል፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች በአገራቸው ድሃም ይሁኑ ሀብታም ተረጋግተው መኖር ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ያመለክታሉ፡፡
‹‹የግጭቱ መንስዔ ምንድን ነው፤ ችግሩስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መቀጠል አለበት ወይ፤ መንግሥትስ ይህን ነገር እንዴት ነው መፍታት ያለበት በሚሉ ሐሳቦች ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው ሥራ ከመስራት አልቦዘነም›› የሚሉት ደግሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲፕሬዚዳንት ዶክተር ኤባ ሚጀና ናቸው፡፡
ዶክተሩ፣ አንድ የምርምር ኮሚቴ መዋቀሩን ያመለክታሉ፡፡
‹‹የግጭቱ መንስዔ ምንድን ነው፤ ችግሩስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መቀጠል አለበት ወይ፤ መንግሥትስ ይህን ነገር እንዴት ነው መፍታት ያለበት በሚሉ ሐሳቦች ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው ሥራ ከመስራት አልቦዘነም›› የሚሉት ደግሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤባ ሚጀና ናቸው፡፡ ዶክተሩ፣ አንድ የምርምር ኮሚቴ መዋቀሩን ያመለክታሉ፡፡ ለዚህም ሥራ ያመቸው ዘንድ የኮሚቴው አባላት የተለያዩ መጠይቆችን በማዘጋጀት መረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡ በቅርብ ጊዜም ውጤቱ እንደሚታወቅ ያመለክታሉ፡፡
እንደ ዶክተር ኤባ ገለጻ፤ በጉዳዩ ላይ በምሁራኑ ጥናት ተካሂዶ መፍትሄ የሚሆን ነገር በተቻለ ፍጥነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመንግሥት ለማቅረብ በመሰራት ላይ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው አማካይነት የህዝብ ለህዝብ ትስስር ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋርም ለማድረግ ታስቧል፡፡ እስካሁን ተፈናቅለው የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥራቸው ከፍና ዝቅ ይበል እንጂ የተለያዩ ብሄረሰቦች መሆናቸው ታውቋል፡፡
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ዳይሬክተርና የታሪክ ምሁር የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ቶሌራ በበኩላቸው፤ ከታሪክ አኳያ ሲታይ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድ ወይም በሌላ የተቆራኙ፣ የተሳሰሩ እንዲሁም የተጋቡ ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ መካከል ከስር መሰረታቸው አብረው በመተሳሰብና በመከባበር የኖሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይላሉ ዶክተር ደሳለኝ፣ በአሁኑ ወቅት እየተከሰተ ያለው ጉዳይ ለህዝቡም ሆነ ለመንግሥት ግራ የገባ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ለዘመናት ሲኖር ችግሩን፣ ኀዘኑንም ሆነ ደስታውን አብሮ የተካፈለ እንደመሆኑ አሁን ላይ ግጭቱ ከወደየት የመጣ ነው የሚያስብል መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
እንደ አንድ ምሁር ችግሩ በዘላቂነት እንዴት ይፈታል ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ህብረተሰቡን ማቀራረብ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት በአንድ በኩል ፀጥታ የማስከበር እና የህዝቡን ሰላም የማስጠበቅም ግዴታ አለበት፡፡ ይሁንና በመንግሥት በኩል ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ አለመሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
እንደ ዶክተር ደሳለኝ አባባል፤ ዋናው ነገር የግጭቱን ምንጭ መሰረቱን ለማድረቅ ህብረተሰቡን እንደገና ማቀራረብ ያስፈልገዋል፡፡ ህብረተሰቡ የራሱ የሆነ ባህልና ወግ አለው፡፡ በኦሮሞ በኩልም ሆነ በቤኒሻንጉል ጉምዝ በኩል የየራሳቸው እሴት ስላላቸው ይህን እሴት በመጠቀም ሁለቱንም ማህበረሰቦች የማቀራረብና እርስ በርሱ የሚደጋገፍ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ዜና ሐተታ
አስቴር ኤልያስ
Your blog has quickly become one of my favorites I am constantly impressed by the quality and depth of your content
I always look forward to reading your posts, they never fail to brighten my day and educate me in some way Thank you!