አዲስ አበባ፡- 22 ሀገራትና ከ400 በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት አሕጉራዊ የሠላም ኮንፍረንስ (ጉባኤ) ኅዳር 16 እና 17 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ትላንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ የበለፀገችና ሠላማዊ አፍሪካን እንገንባ በሚል መሪ ሀሳብ አሕጉራዊ የሠላም ኮንፍረንስን ኅዳር 16 እና 17 በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች፡፡
በኮንፍረንሱ ላይ 22 የአፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን ዘጠኝ አገራት በሚኒስትሮቻቸው እንደሚወከሉ የገለጹት ከይረዲን (ዶ/ር)፣ በኮንፈረንሱ በመዲናዋ የሚገኙ የአፍሪካ፣ የአሜሪካና አውሮፓ አገራት አምባሳደሮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የወጣት ተወካዮች፣ የተመድና ኢጋድ ተወካዮችን ጨምሮ ከ400 በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ ያላቸውን ልምድ እንደሚያቀርቡ በመግለጽ፣ ኢትዮጵያም ባለፉት ዓመታት የዓለምንና የአፍሪካን ሠላም ከማጽናት አኳያ ያደረገቻቸውን ተጋድሎዎች እንደምታቀርብም ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ችግሮችን በሠላማዊ መንገድና በዘላቂነት ለመፍታት እያደረገ የሚገኘውን ጥረት እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል፡፡
የጉባኤው ዓላማ ኢትዮጵያ አንጻራዊ ሠላም ያላትና ከራሷ አልፋ ለቀጣናው፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሠላም አስተዋፅዖ እያደረገች ያለች ሀገር መሆኗ የሚገለጽበት እንደሚሆን የገለጹት ከይረዲን (ዶ/ር)፣ ታላላቅ ኮንፍረንሶችን የማዘጋጀት አቅም እንዳላት የምታሳይበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
ኮንፍረንሱ የአፍሪካ ኅብረት በ2063 ካስቀመጠው ዋና የሠላም ግብ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያም የአፍሪካ ሀገራትን እህት፣ ወንድሞች የምታስተናግድበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መድረኩ በሠላም ጉዳይ ላይ ያተኮረ መሆኑ ከሌሎች ጉባኤዎች ለየት እንደሚያደርገው ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች የአፍሪካ እህት፣ወንድሞች በልኩ እንዲረዱ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ የሕጻናትና ሴቶች ተወካይ በውይይቱ ላይ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ ያሉት ከይረዲን (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ኅብረት የሠላምና ደኅንነት ምክር ቤትና የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብት አስተባባሪም መልዕክት ያስተላልፋሉ ብለዋል፡፡
ከውይይቱ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ሠላምን ለማጽናት ያደረገቻቸውን እንቅስቃሴዎች የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ለዕይታ እንደሚቀርብ በመግለጽ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተ.መ.ድ ምሑራን ስለ ኢትዮጵያ ሠላም መልዕክት የሚያስተላልፉበት ዘጋቢ ፊልም እንደሚቀርብም ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ከመድረኩ በኋላ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ ዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየምንና የሠላምና ደኅንነት ተቋማትን እንደሚጎበኙና የልምድ ልውውጥ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም