“አዋጁ የወጣው አንዱን ማኅበረሰብ ለመግፋትም ሆነ በሌላ ለመተካት አይደለም” – ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ

አዲስ አበባ፡- ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀው የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ያለውን አንድን ማኅበረሰብ ለመግፋትም ሆነ በሌላ ለመተካት የወጣ አይደለም ሲሉ የምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ (ዶ/ር) በተለይ ለኢፕድ እንዳስታወቁት፤ የአዋጁ ዓላማ ግልጽ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከእኩልነት ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር እንደነበር ይታወቃል። እስካሁን የተመጣበት ሥርዓት ራሱ አንዱን አቅፎ ሌላውን የሚገፋ በመሆኑ አካታች አልነበረም። ሥርዓቱ ቢቀየር እንኳ በአንዳንድ ሰው አዕምሮ ውስጥ ሥርዓቱ እስካሁን አልተቀየረም። በዚያ ምክንያት ደግሞ አንዳንድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ከማዕከላዊ መንግሥቱ ራሳቸውን አግልለውና ሥርዓቱ ራሱ ዳር አስቀምጧቸው ቆይተዋል።

በመሆኑም አዋጁ፣ ብቃትንና ወድድርን በዋናነት መሠረት ያደረገ አካታችነትና አቃፊነትም ከግምት ያስገባ እንዲሆን የተቀረጸና የፀደቀ እንጂ በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ያለውን አንድን ማኅበረሰብ ለመግፋትም ሆነ በሌላ ለመተካት የወጣ አይደለም ብለዋል።

አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ሰፊ ጥናት የተካሔደበት መሆኑን የተናገሩት ነገሪ (ዶ/ር)፣ የቀድሞውን የተካው አዲሱ አዋጅ ነባሩን መሠረት አድርጎ የተሻሻለ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ጥናቱ እንዳመላከተው፤ የፐብሊክ ሰርቪሱን የአገልግሎት አሰጣጥ ትልቅ ችግር እንዳለና በአገልግሎት አሰጣጡ የሕዝብ እርካታ እንደሌለ የሚያመላክት ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጡ ጥራትም ፍጥነትም የሌለው ከመሆኑም በላይ የሥነምግባር ችግር የተስተዋለበትም ነው። ይህ ደግሞ የሚያስከትለው ጉዳት በተገልጋዩ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገር ላይ ጭምር ነው። ምክንያቱም ፐብሊክ ሰርቪሱ ላይ ጥራት ያለው አገልግሎት ካለመኖሩም በተጨማሪ ያለእጅ መንሻ እና ማጉላላት አገልግሎት የማይሰጥ ከሆነ ሕዝቡ ቅሬታ ውስጥ ስለሚገባ ይህን ችግር በሚፈታ መልኩ የተሻሻለ አዋጅ ነው።

እንደ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ገለጻ፤ ይህን ለማስተካከልና መሰል የሠራተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ ዓላማው አድርጎ የወጣውን አዋጅ፣ አንዳንድ አካላት አንድን የማኅበረሰብ ክፍል የወከሉ በመምሰል አዋጁ ያንን የማኅበረሰብ ክፍል ሊገፋ የወጣ ነው ብለው ደምድመዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መድረክ ለሕዝብ ክፍት ስለሆነ ያቺን ዕድል ለመጠቀም ሞክረዋል። ይህን የሚያደርጉትም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ነው።

ኢትዮጵያን የሚመስል የሲቪል ሰርቪስ መገንባት አስፈላጊ ነው ያሉት ነገሪ (ዶ/ር)፣ በአዋጁ ክፍል ዘጠኝ አንቀጽ 71 ላይ ያለው ሁሉ አቀፍ ብዝኃነት፣ አካታችነት እና ተጨማሪ የድጋፍ እርምጃ አፈፃፀም ሲባል እዚህ ውስጥ ያለው ብሔር ብቻ አይደለም። እንዲያውም አንቀጽ 71 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ኢትዮጵያን የሚመስል የመንግሥት ሠራተኞች ስብጥር መኖሩን በማረጋገጥ የብሔር ብሔረሰቦች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የፆታ ተዋፅዖ የመሳሰሉትን ብዝኃነት እና አካታችነትን ያገናዘበ የመንግሥት አገልግሎት እና አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ መደረግ አለበት ይላል። ይህ አባባል ደግሞ የሚጎዳው ማንንም አይደለም ብለዋል።

የፌዴራል ሠራተኞች አዋጅ ከቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መፅደቁ ይታወቃል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You