ህዝበ ሙስሊሙ ባለፉት 30 ቀናት በጾምና በስግደት ፈጣሪውን ሲያመሰግን እና ሲማጸን ቆይቷል። ሀይማኖታዊ አስተምህሮቱ በሚያዘው መሰረትም ረመዳን ያለው የሌለውን የሚጎበኝበት ወር ነው። ላጡ ለነጡ የሚሰጥበት ፣ በጋራ ጾሞ በጋራ የሚፈጠርበት ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ መተሳሰብ ከሌላው ጊዜ በተሻለ የሚገለጽበት ወር ነው። ህዝበ ሙስሊሙም ይሄን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። ከትንሹ ጀምሮ አለው እስከሚባለው የእምነቱ ተከታይ ድረስ ካለው ላይ በማካፈል የረመዳንን ወቅት አሳልፏል። ዛሬ ደግሞ የጾሙ ወቅት ተጠናቅቆ 1442ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል የሚከበርበት ዕለት ነው።
በዓሉ ሲከበርም ህዝበ ሙስሊሙ ከዘመዱ፣ ከጎረቤቱ እና ከሌላው እምነት ተከታይ ወገኑ ጋር በጋራና በደስታ ማሳለፍ አለበት። ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰብ እንዲሁም የተለያየ እምነት ተከታዮችን አቅፋ የያዘች፤ ልዩነቶች መለያያ ሳይሆን ውበት ሆነው የሚታዩባት ለሁሉም እኩል የሆነች ሀገር ናት። የተለያየ የእምነት ተከታዮች በአንድነት የሚኖሩባት፣ ተጋብተው ተዋልደውና ተዛምደው የሚኖሩባት የዓለም ተምሳሌትም ናት ። ይሄ በልዩ ልዩ ነገር የተዋበው ማንነት እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ ሆኖ ቆይቷል።
በሌላው ዓለም የማይታይ በሀገራችን አስደናቂ ባህል ሆኖ የኖረው የአንዱ እምነት ተከታይ የሌላውን እምነት አክብሮ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ መኖሩ ነው። ‹‹ አንቺም በሀይማኖትሽ እኔም በሀይማኖቴ አብረን እንኖራል አይጠበንም ቤቴ›› ተብሎ የተዜመላት ድንቅ ሀገርም ናት- ኢትዮጵያ።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፖለቲካን ሽፋን ያደረጉ፤ ለጥቅም የተገዙ ፤ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ አካላት ከውስጥና ከውጪ ሆነው ይሄንን ዓለምን ያስደመመ ፣ ብዙዎችን ያስቀናን አንድነትና መተሳሰብ ለማደፍረስ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል።
አሁንም የተለያየ አጀንዳ በመቅረፅና በማሰራጨት ጭምር በሙስሊሙ ላይ ክርስቲያኑን፤ በክርስቲያኑ ላይ ደግሞ ሙስሊሙን በማነሳሳት ለማጋጨት ቀን ከሌሊት እየሰሩ ናቸው። በማህበራዊ ሚዲያ ሳይቀር ጸብ ጫሪ፣ ስሜት ቀስቃሽ አጀንዳዎች በመልቀቅ የሀይማኖት ግጭት እንዲነሳና ሀገር እንዲበጠበጥ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በፖለቲካው ያላገኙትን የበላይነት በአቋራጭ ለማግኘት ታጥቀው ተነስተዋል። ነገም ተመሳሳይ አጀንዳ በመቅረጽ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት መስራታቸውን ይቀጥላሉ። ይሄ የተለመደና የተበላ የሴራ እቁባቸው ነው።
ህዝቡም ይሄን ሴራ በመረዳት የሚወረወሩ ጸብ ጫሪ አጀንዳዎችን ባለመቀበል ሴራቸውን ሊያከሽፍ ይገባል። ይልቁንም የተለያየ እምነት ያለን የአንድ እናት ሀገር ዜጎች መሆናችንን አንድነታችንን በሚያጠናክር በመከባበርና በመረዳዳት ማሳየት ይጠበቅብናል። እንደ ከዚህ ቀደም የሙስሊሙ በዓል ሲከበር ክርስቲያኑ የማፍጠሪያና የመስገጃ ቦታዎችን በማጽዳት፣ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑትን በበዓል መዋያ በመደገፍ በደስታ እንዲያከብሩ ማድረግ ይገባል። ሀገር ወዳድና ወገኑን አክባሪ ሁሉ ይሄንን ማድረግ አለበት። ይሄ ሲሆን የሴረኞች ሴራ ከንቱ ሆኖ ይቀራል።
ትናንትም ዛሬም ኢትዮጵያ የሙስሊሙም የክርስቲያኑም ሀገር ናት፤ ነገም በዚሁ መልኩ ትቀጥላለች። የተለያየ እምነት ነገር ግን የአንድ ሀገር ህዝቦች መሆናችን ጠቅሞናል እንጂ አልጎዳንም። በአንድነት ክንድ እንድንበረታና ከውጪም ከውስጥም የሚነሱ ጠላቶችን መክቶ የሀገራችንን ሉአላዊነት አስከብረን በጀግንነት እንድንቆም ጉልበት ሆኖኗል። መነጣጠል ለጠላት በር ከፍቶ ማስገቢያ መንገድ መሆኑንንም ለስደት ከተዳረጉ ከሌሎች ሀገሮች ስህተቶች መማር አለብን።
ዛሬም ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በመረዳዳት፣ በመተሳሰብና በአንድነት መንፈስ መሆን ይኖርበታል። በሀገራችን ከሀገር ውስጥም ውጪም የሚታዩ የተለያዩ ችግሮች እንዲጠፉ ዱኣ ወይም ፀሎት በማድረግና ከክርስትያን ወንድም እህቶቹ ጋር ያለውን ፍቅር በማጥበቅ መሆን አለበት። የጸብ አጀንዳዎችን ከራስ በማራቅ በአንድነት ሀገርን ለማሳደግ መስራት ከእያንዳንዱ የእምነቱ ተከታይ የሚጠበቅ ተግባር መሆን አለበት! መልካም የኢድ አልፈጥር በዓል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም