የልእለ ሃያሏ ሀገር አሜሪካ የምንጊዜም የንግድ ተቀናቃኝ የሆነችው ቻይና የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ በእጇ መዳፍ ካስገባች ሰነባብታለች። ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከአውሮፓ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ ከደቡብ አሜሪካ እስከ አውትራሊያ ድረስ በንግድ እግሯ ያልረገጠችው አገር የለም። የቻይና እቃ የማይሽይጥበት አገር አይገኝም ቢባልም ማጋነን አይሆንም። ይህ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣው የቻይና ዓለም አቀፍ የንግድ የበላይነት ታዲያ ለአንዳንድ አገራት በተለይ ደግሞ ለአሜሪካ አልተዋጠላቸውም። ለዚህም ይመስላል አሜሪካና ቻይና ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ ወደተካረረ የንግድ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ የሚስተዋለው። በዚሁ የንግድ እስጥ አገባም አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ የንግድ ማእቀብ ሲጣጣሉ ቆይተዋል።
በዘመነ ትራምፕ በእጅጉ ተካሮ የቆየው የአሜሪካና የቻይና የንግድ ጦርነት ጆ ባይደን አዲሱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ከቻይና ጋር አዲስ የንግድ ግንኙነት እንደሚጀምሩ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ በመጠኑም ቢሆን ለዝቧል። ከዚህ በኋላ አሜሪካ ከቻይና ጋር ወደተካረረ የንግድ ጦርነት እንደማትገባ ነገር ግን ቻይና ከአሜሪካ ጠበቅ ያለ የንግድ ፉክክር እንደሚገጥማት ይጠበቃል።
የአብዛኛው አውሮፓ አገራት የንግድ ሚዛን ወደቻይና ባመዘነበት በዚህ ጊዜ፤ ሁኔታው ያልጣመው የአውሮፓ ሕብረት ከቻይና በኩል ሊገጥመው የሚችለውን ስጋት ለመጋፈጥ ከህንድ ጋር የንግድ ግንኙነት ዳግም ለመጀመር ተስማምቷል ሲል ብሉምበርግ ከሰሞኑ አስነብቧል።የአውሮፓ ሕብረትና ህንድ እየጨመረ የመጣውን የቻይና የንግድ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለመጋፈጥና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማጠንከር በነፃ ንግድ ስምምነት ዙሪያ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ንግግር ለመጀመር መስማማታቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ስምምነቱ በቨርችዋል ስብሰባ በአውሮፓ ህብረት መሪዎችና በህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ መካከል ባለፈው ሐሙስ የተካሄደ ሲሆን የአውሮፓ ህብረትና የህንድን ግንኙነት ዳግም ለመጀመርና በዲጂታላይዜሽን፣ በጤናና በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፎች ላይ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ ላይ ያለመ መሆኑ ተነግሯል። ከስብሰባው በኋላ የአውሮፓ *** ህብረት ካውንስል ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል ‹‹ይህን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማስፋት በሚያስችሉ ተጨባጭ ደረጃዎች ላይ ተስማምተናል›› ሲሉ ተናግረዋል። በንግድ፣ በኢንቨስትመንት ጥበቃ እና በጂኦግራፊያዊ ጉዳዮች ላይ እርስ በእርስ ሊያጠናክሩ በሚችሉ ስምምነቶች ላይ ድርድር ለመጀመር ተስማምተናል ሲሉም ገልፀዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ከህንድና ከሌሎች የእስያ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጥበቅ የተነሳው ከቻይና ጋር ያለው ውዝግብ እያደገ በመምጣቱና በአውሮፓ ባለስልጣናት ላይ በቻይና የተጣለው ማዕቀብ መሆኑ በዘገባው ተጠቁሟል። እንደ አውሮፓ ኮሚሽን ከሆነ ደግሞ በ2020 የአውሮፓ ህብረት ከአጠቃላዩ የህንድ ንግድ 11 ከመቶ ያህል ወይም 96 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 117 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ የእቃና አገልግሎት ንግድ ከቻይናና አሜሪካን በስተጀርባ ማከናወኑ ተጠቁሟል።
ቀደም ሲል በአውሮፓ ህብረት እና ህንድ መካከል የንግድ ውይይቶች የነበሩ ቢሆንም በታሪፍ መቁረጫ፣ አዕምሯዊ ንብረት እና በአውሮፓ ውስጥ የሚሰሩ የህንድ ባለሙያዎች መብቶች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የማያቋርጥ ልዩነት የፈጠረ በመሆኑ ውይይቱ በ2013 ቆሞ እንደነበር በዘገባው ለተውስታ ተቀምጧል። ይሁንና የአሁኑ ስምምነት ለአውሮፓ ህብርትም ሆነ ለህንድ ምጣኔ ሀብት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑ ተጠቅሷል። በተለይ ህንድ አሁን ከተጋረጠባት የኮቪድ -19 ወረርሽኝ አደጋ ለመውጣትና ራሷን ዳግም ለመገንባት አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑም ተነግሮለታል።
ከንግድ ውይይቱ ጎን ለጎን የአውሮፓ ህበረትና ህንድ በኢንቨስትመንት ጥበቃና ጂኦግራፊያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሁለት የተለያዩ የስምምነት ድርድሮችን ለማስጀመር ስምምነት ማድረጋቸውም በመረጃው ተገልጿል። ስምምነቶቹም ‹‹ሻምፓይን›› ወይም ‹‹ፓርማ ሃም›› የተባሉ ሀገር በቀል ምርቶችን ለመጠበቅ እንደሚያስችሉ ተነግሯል። የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናት አሁንም በንግድ ድርድሩ ላይ እንደገና ለመሳተፍ ፈቃደኝነት ቢኖራቸውም፣ የህንድ የሸቀጦች ታሪፍን ጨምሮ በተለይ በተሽከርካሪዎችና የአዕምሮ ንብረት መብቶች ዙሪያ ማሻሻያዎች ገና እንደሚቀሩ አስጠንቅቀዋል።
ከአውሮፓ ጋር የተደረገው ስምምነት የተደረሰው ከቀናት በፊት ህንድ እና እንግሊዝ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ ቃል ኪዳን ካሰሩ በኋላ መሆኑንና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በ2030 በእጥፍ ለማሳደግ ከተስማሙ በኋላ መሆኑም በዘገባው ተጠቀሷል። ቃልኪዳኑ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ከወጣች በኋላ ከህንድ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህብረቶችን ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት አካል መሆኑም ተጠቁሟል።
ከአውሮፓ ህብረት ጋር የተደረገው ውይይት ህንድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በገባችበትና ከፍተኛውን የሞት ቁጥር እያስተናገደች ባለችበት በዚህ ወቅት መሆኑ ወሳኘ መሆኑ በመረጃው የተመላከተ ሲሆን የአውሮፓ ህብረትና ህንድ በተለይ ወረርሽኙን ለመዋጋትና የኮቪድ 19 ክትባት ተደራሽነተርን ለማረጋገጥ፣ ለመርከመርና ለማከም የሚያስችላቸውን የትብብር ማእቀፍ ለመዘርጋት ፍላጎት እንዳላቸው ተጠቁሟል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013