ስለ አገር ብዙ ተነግሯል፣ ብዙ ተጽፏል፤ ብዙ ተዘምሯል፣ ብዙም ተዜሟልም። ስለ አገር ዜጎች ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን ከዚህም በላይ ሕይወታቸውን ያለ ስስት ገብረዋል፤ በተጋድሎ የመስዋዕትነት ደም አገር እስከ ሙሉ ክብሯ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሸጋገር ውድ ዋጋ ተከፍሏል። ይህ ሁሉ ትርክት የአገር ዋጋ የቱን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ሊያሳይ ይችል ይሆናል እንጂ ለአገር ሙሉ ትርጉም ሊሰጥ የሚችል አይደለም።
በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የአገር ጉዳይ የቱን ያህል ትርጉሙ ከፍያለ እንደሆነ የቀደሙ የተጋድሎ ታሪኮቻችን ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው። በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ስለአገራቸው የከፈሉት መስዋዕትነት በየዘመኑ አንገቱን ቀና አድርጎ፣ በማንነቱ ኮርቶ የሚኖር ዜጋ እንዲኖረን አስችሏል። ዛሬ ላይ እንደ አገርና ሕዝብ በእጃችን ያለው ነፃነት፣ ከነፃነቱ የሚመነጨው በራስ የመተማመንና የመቆም ጠንካራ የማንነት መሠረት የተገኘው በየዘመኑ ሕይወታቸውን ሳይሰስቱ በጀግንነት ለአገር መስዋዕት አድርገው ባቀረቡ አባቶቻችንና አያቶቻችን ነው። እነዚህ አባቶቻችንና አያቶቻችን ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የሰጡት ተለዋጭ ሕይወት ስላላቸው ሳይሆን አገር ከምንም በላይ መሆኗን በመረዳትና ከዚህ መረዳት በሚመነጭ ቁርጠኝነት ነው።
አገራችን በብዙ መስዋዕትነት ከትውልድ ወደትውልድ እየተሸጋገረች አሁን ላይ የደረሰችው የታሪክ ዘመናት ውስጥ አገርን አሳንሰው የሚያዩ ወይም በአገር መነገድ የሚፈልጉ ባንዳዎች ስላልነበሩ አይደለም። ለአገር ክብር የሌላቸው፣ በሚመዘንና በሚለካ የግል ጥቅም አገርን አሳልፈው የሰጡ፣ በዚህ ባንዳነት ተግባራቸው አገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ ቀደም ሲል ነበሩ፣ አሁንም አሉ። እንዲያውም በየዘመኑ በተፈጠሩ የማንነት ተቃርኖዎች ውስጥ ያደጉ ጥቂት የማይባሉ መንድሞቻችን አገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ አስከፍለው የታሪካችን ጥቁር ገጾች ሆነው አልፈዋል። ብዙዎች መተኪያ የሌለው ሕይወታቸውን የገበሩላትን አገር በሚለካና በሚመዘን ጥቅም አሳልፈው በመስጠት በታሪክ ውስጥ ቀለው ያለፉ ጥቂት አይደሉም።
በተለይም በየዘመኑ ያጋጠሙንን ታሪካዊ የለውጥ ምዕራፎችን እንደ አንድ አዋጭ የገበያ ሸቀጥ አድርገው ያሰቡና በዚህም አስተሳሰባቸው ለውጦች ያመጡልንን መልካም አጋጣሚዎች እንድናጣ ያደረጉን አሉ። እነዚህ ኃይሎች መሠረታዊ የሆነ ሕዝባዊና አገራዊ የአስተሳሰብ መሠረት የሌላቸው የግል ጥቅም በሚፈጥረው መሻት ታውረው አገርን ሕዝብን ዋጋ እንደሚያስከፍሉ እንኳን በአግባቡ ማስተዋል ሳይችሉ ነገር ግን አገርና ሕዝብን ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍለው ያለፉ ናቸው።
እነዚህ ኃይሎች በታሪክ አጋጣሚ የአገሪቱን የመንግሥት ሥልጣን ይዘው በቆዩባቸው ያለፉት 27 ዓመታት አገርን ፍጹም አደጋ ውስጥ የሚከቱ በተቃርኖ የተሞሉ አስተሳሰቦችን በሕዝብ ውስጥ በመዝራት በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የአገር ጉዳይ ቀሎ እንዲታይ አድርገዋል። መንደርንና ማንነትን መሠረት ያደረጉ ለአገር አደጋና ስጋት የሆኑ አስተሳሰቦችን በተደራጀና በታቀደ መንገድ በዜጎች ላይ በመዝራታቸው አሁንም አገርንና ሕዝብን ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
የዘሩት የክፋት ዘር ለአገር አገርነት የላቀ ትርጉም ያለውን አገራዊ ሰላም በማወክ ዜጎች ተረጋገተው የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን መምራት እንዳይችሉ፤ የጀመርነውም ለውጥ በተጀመረበት እርምጃ እንዳይቀጥል ተግዳሮት፤ ተስፋ ላደረግነው የብልጽግና ጉዞም ከፍያለ መንገጫገጭ ሆኗል። ቀደም ሲል መንግሥት ከቀደሙ የለውጥ ታሪኮቻችን በመማር በብዙ ሆደ ሰፊነት ነገሮችን የማየቱ ጉዳይ አቅመ ቢስነት እስኪመስል ድረስ ለነዚህ ኃይሎች የልብ ልብ የሰጠና ስለራሳቸው የተዛቡ ግምገማዎች እንዲኖራቸው ያስቻለም ሆኗል። አገራዊ ቀይ መስመሮችን በማለፍ ዜጎች እንደ ሕዝብ ካለሙት የጋራ ህልም ወጥተው የቁዘማ ድባብ ውስጥ እንዲገቡም አድርጓል።
ዜጎች ብዙ ዋጋ ከፍለው በጀመሩት ለውጥና ለውጡ በወለደው ተስፋ እንዲጠራጠሩ፤ ከዚያም አልፈው ስለነገዎቻቸው የጠሩ ምስሎች እንዳይኖራቸው ሊያደርጉ የሚችሉ ጭጋጎች የሆኑ ያህል አቅመኞች ሆነው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። በአሁኑ ወቅት ይህንን እውነታ ለመቀልበስ መንግሥት በተቀናጀ መልኩ የአገሪቱም ሰላም ከአደጋ ለመከላከል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው። እነዚህን ውጤቶች መላው ሕዝብ መጠበቅ ካልቻለ ግን ታጥቦ ጭቃ ያህል መሆኑ የማይቀር ነው።
አገር የሕዝቦች ነች። ሕዝቦችም የአገር ተስፋዎች ናቸው። አገራችን ከአደጋ ነፃ የሆነችበት የታሪክ ምዕራፍ ባይኖራትም አሁን ያለችበት ተጨባጭ እውነታ ግን ከቀደሙት ዘመናት የተለየና የሞትና ሽረት የሚባል ታሪካዊ ምዕራፍ ውስጥ ነች ማለት ይቻላል። አገራችን አሁን ላይ ከውስጥና ከውጭ የተደቀነባትን አደጋዎች ተሻግራ በለውጡ ማግስት እንዳሰብነው፣ አገራዊ ዕጣ ፈንታችን ብሩህ እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ ሰላም ዘብ ሊቆም፤ ነገዎቹም ይህን ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ ከመወጣት ጋር የተሳሰረ መሆኑን ሊረዳ ይገባል።
አገር አገር ሆና ለዜጎቿ ተስፋ የምትሆነው ሰላም ሲኖር ነው። ያለ ሰላም ስለነገ ማሰብ አይቻልም። ስለነገ ማሰብ በማይቻልበት ሁኔታ ደግሞ እንኳን አገር ሰው መሆን በራሱ ትርጉም የሌለው እውነታ ነው። ካለንበት የአሮጌ ታሪክ መዝጊያ ምዕራፍ ወጥተን አዲስን ታሪክ በአዲሱ መንፈስ ለመጻፍ ሁላችንም የሰላም ሐዋርያ ልንሆን ይገባል። ሐዋርያነታችን የሰላምን አስፈላጊነትን ከመስበክ ባለፈ የሰላም ምስጢር እንደገባው ትውልድ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በጽናት በመታገልና ስለሰላም የሚጠየቀውን ዋጋ እስከመክፈል ቁርጠኛ መሆን ድረስ መሄድ አለበት። የቀደሙት አባቶቻችንና አያቶቻችን ስለ አገር የከፈሉት ዋጋ ዛሬ እኛ ለሰላማችን ከምንከፍለው ዋጋ የሚያንስ አይደለም። ሁለቱም ስለ አገር የሚከፈሉ ውድ ዋጋዎች ናቸውና!
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013