አዲስ አበባ፦ በትግራይ ሕዝብን ማእከል ያደረገ የተረጋጋ ሕዝባዊ ሰላምና አስተዳደርን ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ጥሪ አቀረቡ።
በሕዝቦች ዘላቂ ትብብርና በሰላምና መረጋጋት የመኖር ፍላጎት ላይ የተጋረጠውን ጉልህ አደጋ በተመለከተ በግልፅ በመተማመን ተገቢውን ፍትህ መስጠት እንደሚያስፈልግ አመለከቱ።
ዶክተር አብርሃም ለኢዜአ በላኩት መግለጫ እንዳስታወቁት ፤ በአገራችን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ጀምሮ በተከሰተው ግጭት መነሻነት በተፈጠሩት መጠነ ሰፊ ጉዳቶች በወገኖች ላይ የደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳተኝነት ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፣ መፈናቀሎች ፣ ጥልቅ የስነ ልቡና ጉዳቶች ፣ የንብረት ዘረፋ መጥፋትና ውድመት፣ አላስፈላጊ መገፋፋትና የተካረሩ አመለካከቶች በአጠቃላይም ውጥረት በሕዝቦች ዘላቂ ትብብርና በሰላምና መረጋጋት የመኖር ፍላጎት ላይ የተጋረጠውን ጉልህ አደጋ በተመለከተ በግልፅ በመተማመን ተገቢውን ፍትሕ መስጠት ይፈልጋል።
የሚደርሰው ጉዳትና ቁስልን በመቀነስና በመሻር እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በተግባር በመቀየር በይቅርታ መንፈስና የቁርጠኛ የሰላም ወዳድነት ማረጋገጫ እርምጃዎችን በመውሰድ አገሬንና ሕዝቦችዋን እንዳገለግል በተሰጠኝ በዚህ ትልቅ ኃላፊነት ተመድቤ ስራዬን ስጀምር በክልሉ ሕዝብ ፣ በፌደራል መንግስት፣ በመላው የአገራችን ሕዝቦች ፣ በዲያስፖራ ኮሚዩኒቲው እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጭምር ለዚህ ወሳኝ ተልእኮዬ ስኬት ሙሉ ድጋፍና እገዛ እንደማገኝ ከወዲሁ በሙሉ ልብ በመተማመን ነው ብለዋል ።
በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ በተለይም ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና መፍትሔን በመፈለግ ሒደት የችግሮችን ስሪተ ነገር የመረዳት፣ የተያያዥ መሰረታዊ ጉዳዮችን ተፅዕኖ መለየትና ከሙሉ ስዕል እይታ ያልጎደሉ ደረጃ በደረጃ የሚተገበሩ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማፍለቅና በሕዝባዊ ይሁንታ በርብርብና በድፍረት በተግባር የመፈፀም ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ባለፋት ወራቶች በትግራይ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ለመቀየር በተሰሩ በርካታ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ጉልህ ተግዳሮቶች የመኖራቸው እውነታ ለፖለቲካ ትክክለኝነት የማይመቹ ከመሆናቸውም በላይ ቅድሚያ ለሚሰጠው የሰው ልጆች ህይወት ማዳን ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይባባስ የመስራት አንገብጋቢ ጉዳይና በአካባቢው የተሻለ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋትን የማረጋገጥ ስራውን ፈታኝ በማድረግ ለተጨማሪ የከፋ ጉዳት የሚዳርጉ ጉልህ ችግሮች መሆናቸውን መገንዘብም አስፈላጊ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በትግራይ የተከሰተውን ግጭት በማስቆም ሰብዓዊ ቀውሱን የመግታት ጉዳይ ቀደም ሲል እንዳስቀመጥኩት የችግሮችን ስሪተ ነገርን መረዳትንና ሚዛናዊ አቋም መያዝን የሚጠይቅ፣ የችግሮችን ተያያዥነትና ተፅዕኖዎችን በጥንቃቄ መለየትን የሚሻ፣ እንዲሁም የመፍትሔ አሰጣጥንም በተመለከተ የሙሉ ስዕል እይታን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ፣ ለህይወት ማዳን ሰላምና መረጋጋት ቀዳሚ አጀንዳነት የተለየ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን በሚገባ መረዳት ለዘላቂ መፍትሔ አሰጣጥ ውጤታማ አቀራረብ ሲሆን በዚህ ውስጥም የሕዝብ ፍላጎትና ምልአተ ተሳትፎም አስኳል ጉዳይ መሆኑን መገንዘብን የሚጠይቅ እንደሆነ አመልክተዋል ።
በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል ቀደም ሲል በተከሰቱ ችግሮችና በየቦታው በሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ ጥቃቶች ለዜጎች አስፈላጊውን መሰረታዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እና አስተማማኝ ፀጥታና ሰላምን ለማረጋገጥ በሕዝብ ተሳትፎ ላይ የተለየ ሥራ መስራትን የሚጠይቅ ሁኔታ መኖሩን መረዳት የሚያስፈልግ ነው። በዚህ ረገድ በመንግሥት በኩል የሕዝቡን ፍላጎት የዕለት ተዕለት ችግሩንና ሁነኛ ስጋቱንም ጭምር በሚገባ በማድመጥ ሳይውል ሳያድር ለመፍታትና በሒደትም ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መሰረት የሚጥሉ አፋጣኝ ስራዎችን መስራት ላይ ትኩረት ማድረጉን በመልካም እድገትነት ሊወሰድ የሚገባ መሆኑን ሰላም ወዳድ ኃይሎችና በተለይም የሰላሙ ባለቤትና ዋና የሆነው የትግራይ ሕዝብ በአስተውሎት እንዲገነዘቡት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ሰላም የጀግኖች አጀንዳ ነው! ብዙ መታገስን ፣ አስፍቶ ማሰብን፣ ብዙ አይቻልሞችን መድፈርን ፣ ነገን ማየትንና በትናንት እውነታዎች ላይ ግልፅ መሆንንና መጨከንን የሚጠይቅ! ከቅርብ ግዜ ወዲህ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል ውጥረትን ለመፍጠር ለዓመታት የተሰሩ ስራዎችና በቸልተኝነትና በእልህ በተተዉ ጉዳዮች የሰውን ህይወት ማጥፋትና ከኖረበት ቀዬው ማፈናቀል የመሳሰሉ መራራ የጥላቻ ፍሬዎችን እየተመለከትን ቢሆንም ለዓመታት ከተገነባው የአብሮነት እና የመተሳሰብ መልካም ዘመናት የጉዞ ታሪካችን ጋር የማይወዳደር በመሆኑ እንደ ሕዝቦች ወደ ማስተዋል እና ስክነት ለመመለስ ሳንውል ሳናድር መስራት በመጀመር ለትውልዶች የምንሰንቀውን ስንቅ ከቂም ከጥላቻና ከበቀል ይልቅ መተማመን ፣ ይቅር መባባል ፣ መደጋገፍንና አብሮነትን ለማጎልበት የሚበጁ መሆናቸውን የማረጋገጥ የትውልድ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
በዚህ አጋጣሚ በትግራይ ፀጥታና ሰላምን በማስፈን፣ ፍትህን በማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን በማምጣት፣ ሰብዓዊ እገዛ በማድረግና መልሶ ግንባታ ሒደት መላው የአገራችን ሕዝቦች በተለይም የአጎራባች ክልሎችና የኤርትራ ሕዝቦች፣ የፌደራል መንግስት ፣ የዲያስፖራ ኮሚዩኒቲ አባላት ፣ ምሁራን ፣ ባለሀብቶች ፣ የኮሚዩኒቲ ማዕከሎች ፣ የሙያ ማህበራት ፣ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ተቋማትና ግለሰቦች ፣ የሚዲያ አካላት ማህበረሰብ አንቂዎች ፣ የሐይማኖት አባቶች ፣ የአገር ሽማግሌዎች ፣ የወጣት እና ሴቶች አደረጃጀቶች ፣ በግል እና በመንግስት ስራ የምትተዳደሩ ዜጎች ለዚህ አንገብጋቢ ተልእኮ ልባችሁን ግዜያችሁን ድጋፋችሁን እና አቅማችሁ የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግ እንድትሳተፋ የአደራ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይን ወቅታዊ ችግር በሁሉም መስክ በዘለቄታ ለመፍታት በሚያግዙ ገንቢና ሰላማዊ እንዲሁም ሕጋዊ የአሰራርና የመፍትሔ አማራጮች ካላቸው አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት ሙሉ በሙሉ ዝግጅት ያለው መሆኑን ስገልፅ በዚህ የታሪክ ኃላፊነት ወቅት ዜጎች የበኩላቸውን ለማድረግ እንዲረባረቡ የአደራ መልእክቴን በማስተላለፍ ጭምር ነው ብለዋል ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም