አዲስ አበባ:- ጾታዊ ጥቃትን ቀድሞ ለመከላከልና ለመመርመር እንዲቻል በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለሚዋቀሩ የፖሊስ ግብረ ኃይሎች ልዩ ስልጠና ሊሰጥ መሆኑ ተገለጸ።የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና ዩ.ኤን.ኤፍ.ፒ.ኤ በጋራ ልዩ ፖሊሳዊ ስልጠናውን ለመስጠት የሚያስችላቸውን ስምምነት ትናንት ተፈራርመዋል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ እንደገለጹት፤ የፖሊስ ግብረ ኃይሉ በመደበኛ የፖሊሳዊ ስልጠና ከወሰዱት ትምህርት በተጨማሪ የልዩ ፖሊሳዊ ስልጠና መውሰዳቸው ጾታዊ ጥቃቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያግዝ ነው።ጥቃቱ ተፈጽሞ ሲገኝም ተጎጅዎችን በሥነ ልቦና በቶሎ ለመደገፍ እንዲሁም ጥቃት አድራሾችን አነፍንፎ ይዞ ለፍትህ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን አቅም የሚያጎለብት ነው።
በአገሪቱ ግጭት በተከሰተባቸውና በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶችና ህጻናት ለጥቃቱ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ይሄን ከመከላከል አኳያ መንግሥት ምንም አይነት ጾታዊ ጥቃትን አልታገስም የሚል ፖሊሲ ነድፎ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።ይሁን እንጂ ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ የሚያስችል ሥርዓትና መዋቅር ባለፉት ዓመታት ባለመዘርጋቱ በተለይ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ጾታዊ ጥቃትን ቀድሞ ለመከላከል አለመቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም አንዳንድ ሰዎች ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን በመንግሥት ተዋናይነት እንደሚፈፀም አድርገው እንደሚያወሩ የሚናገሩት ሚኒስትሯ፤ ነገር ግን ጥቃቱን የሚፈጽሙት ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ ለማድረግ ጠዋትና ማታ የሚታትሩ የጥፋት ኃይሎች እንዲሁም የሞራል ልዕልና የሌላቸው ግለሰቦች እንደሆኑ ገልጸዋል።
ይሄን በመገንዘብም መንግሥት ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማምጣት የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በተለይ ግጭት በተከሰተበት አካባቢ ጾታዊ ጥቃትን ቀድሞ መከላከልና መመርመር የሚችል የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ግብረ ኃይል ልዩ ፖሊሳዊ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቱ ከወዲሁ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ለዚህ የሥልጠና ሂደትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጀት የማፈላለግ፣ ሥልጠናውን የማስተባበር፣ ሰልጣኞች ሰልጥነው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ውጤቱን የመገምገምና የመከታተል ሥራዎችን እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ዩ.ኤን.ኤፍ.ፒ.ኤ ለሥልጠናው ቴክኒካልና የበጀት ድጋፍ ሲያደርግ፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል የትምህርት ካሪኩለም ቀርጾ ለሰልጣኞች ሥልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ሥልጠናው ቅድሚያ የሚሰጠው ግጭት በተከሰተበት ክልሎች ላሉ የፖሊስ ግብረ ኃይል ነው።በዚህ መሰረት በትግራይ ክልል ካለው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ቅድሚያ ሥልጠናው በክልሉ ለሚገኙ የፖሊስ ግብረ ኃይል ይሰጣል። አንድ ሺህ 400 የክልሉ ፖሊሶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሥልጠናውን ወስደው ወደ ስራ የሚገቡ ሲሆን፤ ከክልሉ የሕዝብ ብዛት አንጻር ለሥልጠናው ዩኤንኤፍፒኤ አምስት ሚሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል።
ለሥልጠናው የሚውል በጀት ከክልሎች የሕዝብ ብዛት አንጻር ለሁሉም ክልሎች የተመደበ ሲሆን፤ ችግሩ በስፋት ለሚስተዋልባቸው ክልሎች ቅድሚያ እየተሰጠ በቅደም ተከተል ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በቀጣይ ሶስትና አራት ወራት ውስጥ ስልጠናውን የሚያገኙ ይሆናል።
የፌዴራል ፖሊስ ም/ኮ/ጄ እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መስፍን አበበ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ኃላፊነት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በአጭር ጊዜ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ዜሮ ፐርሰንት በማድረስ ከአገር አልፎ ለአህጉር የሚያኮራ ተግባር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የዩኤንኤፍፒኤ የኢትዮጵያ ተወካይ ዴኒየ ጋይሌ በበኩላቸው፣ መንግሥት ፆታዊ ጥቃትን እንደማይታገስ በገባው ቃል መሰረት ዩኤንኤፍፒኤ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ጾታዊ ጥቃትን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችሉ አሰራርና መዋቅር ለመዘርጋት በበጀትም በቴክኒክም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም