አዲስ አበባ፦ በመከባበር እና በመረዳዳት መንፈስ ለአገር አንድነት ፣ ሰላምና ልማት መላው ሕዝብ እንዲዘጋጅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር እድሪስ ጥሪ አቀረቡ ።
በአዲስ አበባ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የኢድ አልፈጥር ጾም ማጠናቀቂያ የጎዳና ላይ የአፍጥር መርሐ ግብር በተካሄደበት ወቅት ፣ ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር እድሪስ ፤ በመከባበር እና በመረዳዳት መንፈስ ለሀገር አንድነት ለሀገር ሰላምና ልማት መላው ሕዝብ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል ።
“አገራችን ሰላም ትሁን ፣ አማን ትሁን፤ ለአገራችንን አንድነት ይስጥልን “ ያሉት ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር፣ በልማቱም ዘርፍ ሀገራችን ከፍ ብላ እንድትታይ ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።
የበላያችንን እንድናከብር ለበታቾቻችን እንድናዝን የአደራ መልእክት ያስተላለፉት ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር እድሪስ ፣ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ማከናወን እንደሚስፈልግም አሳስበዋል ።
በአዲስ አበባ የተካሄደው የጎዳና ላይ አፍጥር መርሐ ግብሩ ከዚህ ቀደም ያልተካሄደ መልካም ዝግጅት መሆኑን የገለጹት ሐጂ ሙፍቲ፤ ሕዝባዊ እና አገራዊ ዝግጅት በመሆኑ መርሐ ግብሩን ላሰናዱት አካላት እና ፍቃድ ለሰጡት ለከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች። ዝግጅቱ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ሲሰሩ ለነበሩ የጸጥታ አካላት በሕዝበ ሙስሊሙ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ፤ አገራችን ኢትዮጵያ እና መዲናችን አዲስ አበባ የብዙ እምነቶችና ብሔሮች መገናኛ በመሆናቸው በቀላሉ እሳት መጫር ይቻላል ብለው የሚታትሩ ግብዞች ቢኖሩም አላማቸው እንደማይሳካ ግን የእምነት አባቶቻችን አሳይተዋልና ለዚህ ተግባራቸው ክብርና ምስጋና እንደሚገባቸው አመልክተዋል ።
ከተማችን በጋራ በወንድማማችነት ማሳደግ የሚቻለው ስንከባበር እና ስንተሳሰብ ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር፤ መከባበራችን እና ፍቅራችን የሚያስቀናቸው አካላት ሁልጊዜ ይነሱብናል። በተለይ አሁን ብርሃናችን የሆነው የህዳሴ ግድብ እንዳይሳካ አንዴ በብሔር አንዴ በሃይማኖት ሊያጋጩን ቢፈልጉም እኛ ኢትዮጵያውያን ሀቀኛ ወንድማማች ሕዝቦች መሆናችንን በማሳየት ልናሳፍራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
መዲናችን አዲስ አበባ የፍቅር ከተማ በመሆኗ ሁሉም ሃይማኖቶች በነጻነት የሚያስተምሩበት እና እምነቶች አንዱ ለአንዱ ከለላ የሚሆኑባት ከተማ ነች። የአፍጥር ዝግጅቱ ባማረ እና ለሌላው ዓለም አስተማሪ በሆነ መንገድ የተከናወነ ነው። በዚህ ረገድ እምነትን በግል ይዞ መተባበር አስፈላጊ ነው፣ የአፍጥር ሥርዓቱ እንዲሰምር ለታተሩ የክርስቲያን ወንድሞችም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ።
የአፍጥር ስርዓት ታዳሚው አቶ ሙስተጃብ አብዱራህማን ፣ኢትዮጵያውያን ሊከፋፍሏቸው ለሚመጡ አጥፊዎች ሁሉ ቦታ እንደሌላቸው በተግባር እያሳዩ የመጡ በመሆናቸው ይህንን ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስታውቀዋል። የሐይማኖታዊ ትውፊቱን ተከትለው የእራሳቸው መጠቀሚያ ሊያደርጉ ከሚመጡ አካላት ሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሊጠነቀቅ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አገራችን ሊያጠፉ ለሚመጡ አካላት ሕዝበ ሙስሊሙ ቦታ የለውም ያሉት አቶ ሙስተጃብ፤ ሕዝቡ ከፖለቲከኛውም በላይ ቀድሞ አገሩን እየተከላከለ የማንም መጠቀሚያ ከመሆን ስለተጠበቀ ምስጋና ይገባዋል። በቀጣይም አንድነቱን እና አብሮነቱን የሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የአገሩን ሰላምና አንድነት ሊያስጠብቅ ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው ከ15 ሺህ ሕዝብ በላይ በተካፈለበት የጎዳና ላይ የአፍጥር ሥነ ሥርአት ሕዝበ ሙስሊሙ ለሀገሬ ዘብ ነኝ፤ የህዳሴው ግድብ የአንድነታችን አርማ ነው ፤ ያለችን ሀገር አንድ ኢትዮጵያ ነችና እንጠብቃታለን የሚሉ መፈክሮችን አሰምቷል።
ጌትነት ተስፋ ማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም