አንድነት፣ ሕብረትና አብሮነት ትልቅ ዋጋ ያላቸው የኢትዮጵያውያን እሴቶች ናቸው። በአንድነት ውስጥ ትልቅ ጉልበት አለ። ሰው በሕብረት ሆኖ ሲሰራ እንጂ በተናጠል የሚሰራው የተሻለ ውጤት ሊያመጣ አይችልም። በተናጠል የምናደርጋቸው ነገሮች በሕብረት ከምናደርጋቸው ነገሮች በላይ ፍሬያማ ሊሆኑ አይችሉም። ኢትዮጵያም የተገነባችው በዚሁ መሰረት ላይ ነው። አገሪቱ እንደ አገር እስካሁን መቀጠል የቻለችው አባቶች እነዚህን እሴቶች ከዘመን ዘመን ጠብቀው በማቆየታቸውና ለትውልድ በማስተላለፋቸው መሆኑን ታሪክ ያወሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን በአንዳንድ ሁኔታዎች የሚታየው ትኩሳት ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን የሚሰብክ ብሎም እስካሁን የመጣንበትን የአንድነትና የአብሮነት መንገድ የሚንድ ሆኗል። በመሆኑ ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩት እሴቶቻችን አሁን ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እየተስተዋለ ነው። ለዚህም ምክንያቱ አንዳንድ ሰዎች በአንድነት ውስጥ ያለውን እምቅ ኃይል በመካድና ለዚህ የተከፈለውን ዋጋ በማቅለል ልዩነትን ለማስፋት ስለሚፈልጉ ነው።
አበው ያስተማሩን ነገር ቢኖር ሰው ለአንድነት ዋጋ መክፈል ሳይፈልግ ሲቀር በውስጡ ያለውን እምቅ ጉልበት ያባክነዋል። በዚህም ጠላት በመጣ ጊዜ በቀላሉ ይሰበራል። አሁን አገራችን በውስጥና በውጭ ያሉ ጠላቶች በሚመዙት ሴራ የሕዝቦቿን አንድነት እና አብሮነት ለማለያየት ሌሊትም ቀንም እየሰሩ ይገኛሉ። ይህን ያህል እየለፉ ሊሳካላቸው ያልቻለውም ሕዝቡ በአንድነቱ ላይ የማያወላዳ አቋም ስላለው ክፍተት ሊያገኙ ስላልቻሉ ነው። አዎ፣ አንድነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ጉልበት አይጠረጠርም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ሶስት ዓመታት አልፈዋል። በእነዚህ ሶስት ዓመታት ውስጥ አገራችን ኢትዮጵያም በለውጥ ጉዞ ላይ በመሆኗ በአገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ተደርጓል። በዚህም ሒደት በቀደመው ጊዜ በፀረ ሽብር ሕግ የተከሰሱ የሚዲያ ተቋማትና ፓርቲዎች ምሕረትና ይቅርታ ተደርጎላቸው በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ መፈቀዱ የሚታወስ ነው። በዚህም በአገሪቱ የነበረውን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት ሰላም ለማምጣት ተሞክሯል።
ነገር ግን አሁንም በኢትዮጵያ በርካታ የጸጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛሉ። ይህም የሆነው ለ27 ዓመታት የሕዝቡን አንድነት በመሸርሸር ሲሰራ የነበረው በአሁኑ ወቅት በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት ከሞት ለመነሳት የሚያደርገው መፍጨርጨር መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። በተጨማሪም በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በማድረግ በአገሪቱ ሽብር እየፈጠረ የሚገኘው ሸኔ በሚጠነስሰው ሴራ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
በርግጥ ባለፉት ሶስት ዓመታት የመጡ በጎ ነገሮች ያልተመቻቸው የለውጡ ተሰናባቾች በዛኑ ልክ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት መፈናቀል እንዲደርስባቸው፣ ሕዝብን በየጊዜው እንዲሸበር ከማድረጋቸውም ባለፈ የተለያዩ ግጭቶችን በማስነሳት አገር አደጋ ላይ እንድትወድቅ ከመዳከር አልቦዘኑም። ጥረታቸው ባይሳካላቸውም፣ አሁንም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንቅልፍ ተኝተው እያደሩ አይደሉም።
ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚቆሰቁሱት እሳትም እዚህም እዚያ ሰዎች ይሞታሉ፣ ቤት ንብረት ይወድማል፣ ሕዝቡ ተረጋግቶ ማህበራዊ ኑሮውን መቀጠል ይቸገራል። እነዚህ የሽብር ወላፈኖች ለውጭ ጠላት በር የሚከፍቱ በመሆኑ አቅማችን በፈቀደው መጠን ጠብቀነው የቆየነውን የአንድነታችንን እሴት አጠናክረን በመያዝ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በመረባረብ ልንመክታቸው ይገባል።
በአጠቃላይ የበለፀገችና የተረጋጋች እንዲሁም ዜጎች መብቶቻቸው ተጠብቆ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መፍጠር የምንችለው አንድነታችንን እና ሕብረታችንን ስናጠናክር ብቻ ነው። ይህንንም ማድረግ የምንችለው ራሳችንን ከነጣቂ ተኩላዎች ጠብቀን ሀገራችን የቀደመ አንድነቷን እና ክብሯን ይዛ እንድትቀጥል ስንሰራ ብቻ ነው። ስለዚህ ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከእህት ወንድሞች ጋር አንድነት እየፈጠርን፣ በሰላም በአብሮነት የመኖርን እሴት እያጎለበትን፣ የነገይቱን የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት በልዩነት ውስጥ የደመቀውን የአንድነትና የአብሮነት እሴቶቻችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013