
ከአስተዳደሩ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ የተገነባውን ሁለተኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በይፋ ስራ በማስጀመር ነዋሪዎችን መግበዋል።
አንዳችን ለሌሎች የተስፋ ብርሃን በመሆን መደጋገፍ እና መረዳዳት ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከኮቪድ ወረርሽን ጊዜ ጀምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመደገፍና የመርዳት ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ያለንን ሀብት በአግባቡ ካዋልን ብዙ ችግሮቻችን መቅረፍ እንችላለን ያሉት አዳነች አበቤ፣ ማእከል በቀን አንድ ጊዜ ከ1000 በላይ ዜጎችን መመገብ የሚችል ነው ብለዋል።
መንግሥት ከለውጡ ወዲህ ዜጎቻችን ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች እየሰራ ነው ያሉት አዳነች ፣የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ምገባ ማዕከሉ ዜጎችን መመገብ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ስልጠናም አግኝተው ራሳቸውን እንዲችሉም ማዕከሉ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የከተማ አስተዳደሩም አቅም የሌላቸው ዜጎችን ለመርዳት ፍላጎት ያላቸውን በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶችን እና ተቋማትን በማስተባበር በአምስት ክፍለ ከተሞች በቋሚነት የምገባ ማዕከል የማደራጀት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራርና ሰራተኞች፣ ቴምፕል ኦፍ ጋድ ቤተክርስቲያን እንዲሁም ስካይ ላይት ሆቴል በቦሌ ክ/ከተማ ስራ የጀመረውን ተስፋ የምገባ ማእከል ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የቦሌ ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ከ1ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፋሲካ እለት በአራዳ ክፍለ ከተማ ከ1ሺህ በላይ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የምገባ ማዕከል በይፋ ስራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም