
- ሕዝቡን ከቡድኖቹ የሽብር ተግባር እንደሚታደግ ተገለጸ
አዲስ አበባ፡- ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ “ህወሓት“ እና “ሸኔ“ በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ለጸጥታ አስከባሪው ተጨማሪ የሕግ ድጋፍ እንደሚያስገኝለት ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ፍቃዱ ፀጋዬ አስታወቁ።
አቶ ፍቃዱ ፀጋዬ ቡድኖቹ በአሸባሪነት መሰየማቸውን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት ፤ የጥፋት ቡድኖቹ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አሰቃቂ ጥፋቶችን ሲያደርሱ ቆይተዋል። በአሸባሪነት መፈረጃቸው የጸጥታ አስከባሪው ተጨማሪ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኝ ያግዘዋል፤ ሕዝቡንም ከሽብር ይታደገዋል።
ሁለቱም የጥፋት ቡድኖች የሽብርተኝነት ትርጓሜን ያሟሉ ናቸው። የተለያዩ ሕገ ወጥ ተግባራትን እና አሰቃቂ ወንጀሎች ሲፈጽሙ ቆይተዋል ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ህወሓት በ2011 ዓ.ም ‹‹የትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ›› በማለት ሕገወጥ የታጠቀ ኃይል እንዲደራጅ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መወሰኑን አመልክተዋል ።
ከአገር መከላከያ ሰራዊት በጡረታ በተገለሉ ጄኔራሎች እና ኮሎኔሎች እንዲመራ አድርጓል። ወታደራዊ መኮንኖቹ የትግራይ መከላከያ ኃይል የተባለ ወታደራዊ ኃይል ለመገንባት የሚያስችል ወታደራዊ ዶክትሪን አርቅቀው ለህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅርቦ ኮሚቴውም ዶክትሪኑ ላይ ተወያይቶ በማፅደቅ እንዲተገበር መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
በተደራጀው ወታደራዊ ኃይል በማንኛውም ሁኔታ የክልል መንግሥታት ሊታጠቁ የማይገባውን መካናይዝድ እና የቡድን መሳሪያ ስልጠና በመስጠት ለጦርነት ዝግጅት ማድረጋቸውን ። ድርጊቱም በሥራ አስፈፃሚው ታምኖበት የተወሰነ ነው ብለዋል።
የፌዴራል መንግሥቱ በክልሉ ላይ ምንም አይነት ሥልጣን እንዳይኖረው እንዲያደርግ ቅስቀሳ ከማድረጉም በላይ በክልሉ ይገኝ የነበረው የአገር መከላከያ ሰራዊት በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ እንዳይችል በየቦታው ኬላዎችን በማቋቋም የአገር መከላከያ ሰራዊት ፍተሻ እንዲካሄድበት ማድረጉን ጠቁሟል።
የህወሓት የጥፋት ቡድን የአፋር ክልል ላይ ችግር በመፍጠር ደጋፊ እንዲሆነው የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ለተባለ ፓርቲ በጀት በማቅረብ እና የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም አመልክተዋል።
የአማራ ክልልን ሰላም ለማደፍረስም ከተለያዩ አካላት ጋር ስምምነት አድርጎ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ባደረገው ስምምነት መሰረትም የቅማንት ሕዝብን ደህንነት ለመጠበቅ በሚል ከፍተኛ ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ በመመደብ በአካባቢው ላይ የሚነሳ ግጭትን በመሳሪያ እና ገንዘብ ሲደግፍ ነበር ብለዋል።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ከአፋር ሕዝብ ጋር እንዲጋጭ የመሳሪያ ድጋፍ አድርጎ በሕዝቦች መሐል ግጭት ለማባባስ አስቦ ከ100 በላይ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ለማስታጠቅ ሙከራ አድርጎ በፀጥታ ኃይሎች ክትትል መሳሪያውን የሚቀበል ሰው በመያዙ ውጥኑ ሳይሳካለት መቅረቱን ጠቁመዋል።
በጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሕዝባዊ ግጭት እንዲነሳ እና ሕዝቦች ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትህ ለሰላም ልማትና ዲሞክራሲ እና የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ለሰላም እና ዲሞክራሲ ለሚባሉ ድርጅቶች የመሳሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ግጭት ለመቀስቀስ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የሸኔ የጥፋት ቡድን፤ የትጥቅ እንቅስቃሴውን እንዲያቆም ከሕዝብ የተውጣጡ አባገዳዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የኃይማኖት አባቶችን ያቀፈ ስብስብ ተዋቅሮ ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለስ ጥሪ ተደርጎለት ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አሳውቋል። በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ውስጥ እንዲሁም ከክልሉ ውጪ በመንቀሳቀስ ሰላማዊ ህብረተሰብን በመግደል እና ከቤት ንብረት በማፈናቀል የሽብር ወንጀል ፈጽሟል ብለዋል።
እንደ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ማብራሪያ ፣በቡድኑ የሽብር ተግባር በ2013 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 463 ሰዎች ላይ አደጋ ደርሷል። 112 የፖሊስ አባላት፣ 57 ሚሊሺያ አባላት እና 18 በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ አመራሮች ህይወት አልፏል። 76 ፖሊሶች 36 ሚሊሽይ እና 2 አመራሮች ላይ አካል ጉዳት ደርሷል።160 መኖሪያ ቤቶች 44 ተሽከርካሪዎች እና 84 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል።
ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም እስከአሁን በምርመራ በተረጋገጠው መሰረት በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንካ ቀበሌ ንፁሃን ዜጎች ላይ በፈጸመው ጥቃት 36 ንፁሃን ዜጎችን በመግደል እና በርካታ ቤቶች በማቃጠል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ከአካባቢው እንዲፈናቀል ማድረጉን አመልክተዋል።
በጫካ ውስጥ ሆኖ ለሕዝብ እታገላለሁ የሚለው ሸኔ ተብሎ የሚጠራው ቡድን ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደል እና ጥቃት ለማድረስ አባ ቶርቤ የተባለ የገዳይ ቡድን በማዋቀር ይንቀሳቀሳል። ይህ የገዳይ ቡድን በተለይ የመንግሥት አመራሮች ላይ በማተኮር በአሳቻ ሰዓት በመጠበቅ የመንግሥት አመራሮች እና ንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽም ስለመሆኑ የተለያዩ የምርመራ ውጤቶች ማሳየታቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አረጋግጧል ብለዋል።
ሸኔ ማለት ከኦነግ ተገንጥሎ ጫካ የገባው የጦር ክንፍ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አስታውቀዋል ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም