የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ቅዳሜ እንዳስታወቀው፤ ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እስከ አሁን በ43 ሺህ 017 ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ሲሆን፣ መግለጫው እስከተሰጠበት ቀን ድረስም 31 ሚሊዮን 724 ሺህ 947 መራጮች ተመዝግበው ድምጽ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ እጃቸው አስገብተዋል:: ለምርጫው የተመዘገቡት መራጮች ቁጥር ባለፈው የምርጫውን ሂደት በመገምገም የተወሰዱ እርምጃዎችን ተከትሎ ለውጥ የታየበት መሆኑን መረጃው ይጠቁማል:: እርምጃው ትክክልና ተገቢ መሆኑንም ያመለክታል::
ቦርዱ የምርጫውን ሂደት መገምገሙን አሁንም ቀጥሏል ፣ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በሂደቱ ላይ ውይይት ተደርጓል:: ይህን ተከትሎም አሁንም በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ እርምጃዎችም ተወስደዋል:: በዚህም መሰረት ምርጫው አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል:: በቅርቡ በአዲስ አበባ በኮንዶሚኒየም ሳይቶች አዳዲስ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተዋል፣ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ምዝገባ ባልተጀመረባቸው አካባቢዎችም ምዝገባው ሰሞኑን እንዲጀመር ተደርጓል:: እነዚህ እርምጃዎች በቀጣይ በርካታ ዜጎች የለምንም እንግልት ለምርጫው በመመዝገብ ካርድ መውሰድ እንዲችሉ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል::
በየምርጫ ጣቢያው ህዝቡ ካርድ ለመውሰድ እየቀረበ ያለበት ሁኔታና በተለያዩ መንገዶች እየተካሄደ ያለው ቅስቀሳም ተጠናክሮ መቀጠሉና የመመዝገቢያ ቀኑ አሁንም መራዘሙ በቀጣይ በርካታ ዜጎች በምርጫው እንዲመዘገቡ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ:: በዚህ በኩል ምርጫ ቦርድ የደረሰበት ውሳኔ መንግሥት ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ያሳየው ቁርጠኝነት አንድ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል::
መንግሥት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባሻገር ይህን ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ ለማስፈጸም በትኩረት እየሰራ ይገኛል:: አሁንም ከዚህ በኋላ ከምርጫ ውጪ ስልጣን እንደማይያዝ አጥብቆ ማስገንዘቡን ቀጥሏል:: የምርጫውንም ሂደት እየተከታተለና እየገመገመ የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እያደረገ ያለበትም ሁኔታ ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የገባው ቃል አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል::
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ ቆሞ እየጠበቀ ጭምር ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ እንዲሆን ሰርቷል:: አሁንም እድሜው ለመምረጥ የደረሰ ዜጋ በሙሉ በምርጫው ድምጹን እንዲሰጥ ቆሞ እየጠበቀ ነው:: በምርጫ ሂደቱ የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ አብቅቷል፤ ችግሩ የራሳችሁ ነው ብሎ ግን አልደመደመም::
የግንቦት ወር ትናንት ግብቷል::ድምጽ የሚሰጥበት ቀን ከወር ያነሰ ጊዜ ብቻ ይቀረዋል ማለት ነው:: ምርጫው ሊካሄድ ቀኑ እየቀረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዜጎች ድምጽ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ እንዲያወጡ በሚል ምዝገባው ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም አድርጓል:: ከዚህ በላይ ቁርጠኝነት አለ ተብሎ አይገመትም::
ህዝቡም በተለይ ካርድ ያልወሰደው ህብረተሰብ ይህን የመንግሥት ቁርጠኝነት በሚገባ በመረዳት በምርጫው በንቁ ለመሳተፍ ድምጽ መስጠት የሚያስችለውን ካርድ አሁንም የምዝገባ ጊዜው ሳይጠናቀቅ መውሰድ ይኖርበታል::
ይህ ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆን መንግሥት አረጋግጧል:: ዴሞክራሲያዊነቱ በመንግሥት ቁርጠኝነት ብቻ አይረጋገጥም፤ መንግሥት ምቹ ሁኔታ ነው የሚፈጥረው:: ህዝቡ ነው ዴሞክራሲያዊነቱን በነጻነት ድምጹን በመስጠት ማረጋገጥ ያለበት:: ይህም ህዝቡ በዚህ ምርጫ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ያመለክታል::
እንደሚታወቀው ይህ ምርጫ እየተካሄደ ያለው ሀገራችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ነው:: አንዱ አስቸጋሪ ሁኔታም ምርጫው እንዳይካሄድ የሚፈልጉ አካላት ባለ በሌለ ኃይላቸው እየተረባረቡ መሆናቸው ነው:: እነዚህ ኃይሎች የውስጥ እና የውጭ ናቸው:: የውስጦቹ ተላላኪዎች :: የውጪዎቹ ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት እንዳይኖራት የሚፈልጉ ናቸው:: ይህ ምርጫ ሀገሪቱን የጠንካራ መንግሥት ባለቤት ያደርጋታል የሚል ስጋት አላቸው:: በመሆኑም ያለ የሌለ ሀብታቸውን ለእዚህ እኩይ ተግባር እያዋሉ ናቸው:: እጃቸው ረጅም ነው:: ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በሀገር ውስጥ ባንዳዎች ድጋፍ በማድረግ ነው::
እነዚህ ኃይሎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የጸጥታ ችግር በመፍጠር የምርጫ ሥራው እንዲስተጓጎል መራጮች ለምርጫው እንዳይመዘገቡ እያደረጉ ናቸው:: ህዝቡ በእነዚህ ኃይሎች በተለያየ መንገድ ሊደርስበት የሚችለውን ጫና ከቁም ነገር ሳይቆጥር በምርጫው በንቃት መሳተፍ የሚያስችለውን ካርድ መውሰድ ይኖርበታል::
ቀጣይ እጣ ፈንታውን በሚወስነው በዚህ ምርጫ ላይ በንቃት ለመሳተፍ የሚደቀኑበትን ፈተናዎች ለማለፍ እንደ መንግሥት ሁሉ ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል:: ችግሮች ሲያጋጥሙም በቅርቡ ለሚገኙ የመንግሥት አካላት በማሳወቅ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል::
የኢትዮጵያ ህዝብ ለምርጫው መመዝገቡን በማጠናከር የሀገሪቱን የምርጫ ታሪክ መቀየርና በዴሞክራሲ ስርዓቱ መሰረት ማስቀመጥ ላይ በማስቀመጥ ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎችን ማሳፈር ይኖርብሃል:: ካርድ የወሰዳችሁ ካርድ ያልወሰደውን ህብረተሰብ በማሳመን የምርጫ ካርድ እንዲወሰድ አጥብቃችሁ ስሩ::
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የምርጫው ባለቤት ፣ በምርጫው ተጎጂም ተጠቃሚም ከመሆኑ አንጻር በዚህ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረትን ለመጣል በእያንዳንዱ የምርጫው ሂደት በንቃት መሳተፍ ይጠበቅበታል:: የተራዘመውን የመራጮች የምዝገባ ቀንን በኃላፊነት ተጠቅሞ የአንድ ድምጽ ዋጋ የቱን ያህል ዋጋ እንዳለው በተጨባጭ ሊማርበት ይገባል ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013