አንጋፋ ሠዓሊ ናቸው። ከበርካታ ዓመታት በፊት በውጭ አገር በሙያቸው ዘመናዊ ትምህርት ቀስመዋል። በሶቭየት ኅብረት በ1979 በማቅናት ከተሰጦ በተለየ ትምህርቱን በሚገባ ተከታትለዋል። በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ቢያንስ ለአስር ወራት ያህል በቅድመ ዝግጅት ኡዝቤኪስታ በሚባል ከተማ ቆይታ አድርገዋል። ከዚያም ወደ አካዳሚ ለመግባት የሚሰጠውን ፈተና ወስደው ያልፋሉ፤ ፈተናውንም አልፈው ቀጥታ ወደ ሌኒንግራድ የሥነ ጥበብ ትምህርት አካዳሚ ገቡ።
በ1986 ትምህርታቸውን በግራፊክስ ዘርፍ አጠናቀው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ኢትዮጵያ ሲመጡ መጀመሪያ ወደ ሥራው ዓለም የተቀላቀሉት የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት በሚባለው ተቋም ውስጥ ነበር። በዚያም ኮሜርሻል አርቲስ ፣የሥነ ጥበባት ክፍል ኃላፊ እንዲሁም ባለሙያ ሆነው ለ9 ዓመታት አገልግለዋል።
የውጪ ትምህርት ዕድል ከማግታቸው ቀደም ብሎ ደግሞ ለሁለት ዓመታት አገር ፍቅር ቴአትር ቤት አገልግለዋል። ከ1996 ጀምሮ እስከአሁን የስቱዲዮ አርቲስት ናቸው። በዚህ ሁሉ ጊዜ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፉም ይናገራሉ። አሁን ያሉበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ እንቅፋቶችን ማለፋቸውን ነው የሚገልጹት። ‹‹ሥራ ላይ ማተኮር ግን አስፈላጊ ነው። ያኔ እግዚአብሔርም ይረዳል›› የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። የዛሬው የዝነኞች የዕረፍት ውሎ እንግዳችን አንጋፋው ሠዓሊ ሉልሰገድ ረታ!
የህይወት ዘመን ተሸላሚ
በቅርቡ “የህይወት ዘመን ሽልማት” ቦርድና ኮሚቴ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር የጥበብ ባለሙያዎችን “ኢትዮጵያን በሙያችሁ ስላገለገላችሁ እናመሰግናለን” በሚል የወርቅ ኒሻን ሽልማት አበርክቷል። በዚህ ሽልማት ደግሞ በስነ ጥበብ ዘርፍ አንጋፋውና ተወዳጁ ዓሊ ሉልሰገድ ረታ ቀዳሚው ተሸላሚ ነበሩ።
“ለአገርህ በጎ ተግባር ሠርተሃል በሚል የመጨረሻውን የወርቅ ኒሻን መሸለሜ በአንድ በኩል የሚያበረታኝ በሌላ ወገን ደግሞ እስከአሁን ከሠራሁት በላይ የበለጠ እንድሠራ ኃላፊነት እንዲሰማኝ የሚያደርግ ነው” በማለት ለተደረገላቸው የክብር ሽልማት ምስጋናቸውን ያቀርባሉ።
ይህን ክብር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እጅ መቀበላቸውም እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ። በተለይ ከታላላቅ የኪነ ጥበብና አንጋፋ የስነ ጥበብ ባለሙያዎች እኩል ይህን ክብር እንድናገኝ መደረጉ ልፋታችን ትርጉም እንዳለው እንዲሰማን ያደርጋል ይላሉ። አሁን እየመጡ ላሉ ወጣቶችም በእጅጉ እንዲሠሩ የሚያነቃና በሚሠሩት ሥራ እንደሚከበሩ የሚያስገነዝብ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በተለይ ይህን ታላቅ ሥራ የሠሩት ኮሚቴዎችና አጠቃላይ የሽልማቱን አባላት አመስግነዋል።
የአንጋፋው ሠዓሊ አበርክቶ
ሣዓሊ ሉልሰገድ በግላቸው ልህቀት እና በርካታ ስኬቶችን ቢያገኙም በዚያ ብቻ ረክተው አልተቀመጡም። ስነ ጥበብ የሚገባው ክብር እና ደረጃ ላይ እስኪደርስ ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ሰፊ ትግል እያደረጉ ናቸው። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት በግል ከሚያቀርቡት ዓውደ ርዕይ በተጓዳኝ ለሌሎች ዕድል ለመክፈት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ወጣቶችን በስፋት በማሳተፍ ከአስር ዓመታት በላይ የዘለቀውና በሸራተን አዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የሚካሄደው ‹‹አርት ኦፍ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ ተጠቃሽ ነው። ይህ ጥረት የመጣው ሠዓሊው “በአገሬ ያሉ ባህላዊ እንቅስቃሴዎችን ወደ ዘመናዊነት መለወጥ” የሚል የስነ ጥበብ ፍልስፍና ስላላቸው ነው፤ ይሄን ለማጉላትና ሃሳባቸውን ለሌሎች ለማስተላለፍ ካላቸው ጽኑ እምነት የመነጨም ነው።
“አርት ኦፍ ኢትዮጵያ” በ8 ሠዓሊያን በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2008 ነው የተጀመረው። የመጀመሪያው መጠሪያም ‹‹መርጅ›› የሚል ነበር። በወቅቱ የሸራተን ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዣንፔር ማኒንጎፍ ለኢትዮጵያ ትልቅ ህልምና ብዙ ዓላማ እንደነበራቸው እና በእርሳቸው እገዛ ሃሳቡ መሳካቱን ሠዓሊሉል ሰገድ ይናገራሉ። በ2007 አንድ ቦታ ተቀምጠው በመጨዋወት ላይ እያሉ ሃሳቡን እንደጠነሰሱትም ነው የሚገልጹት። አሁን ይሄ ዓውደ ርእይ ስኬታማና በጉጉት ከሚጠበቁ የስነ ጥበብ ዝግጅቶች ውስጥ ቀዳሚው ለመሆን መብቃቱን ይጠቅሳሉ።
አንጋፋው ሠዓሊ “ስነ ጥበብ እንዲያድግ የራሱ ተቆርቋሪ ያስፈልገዋል” በማለት አንዳንድ የጋለሪ ባለቤቶችና ለሙያው ክብር ያላቸው ባለሙያዎች ከሚያደርጉት ጥረት በዘለለ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው አስተያየት ይሰጣሉ። በተለይ ለሥዕል ግብአትነት የሚውሉ ካንቫስ፣ቀለም እና መሰል ቁሳቁስ ብዙ ሠዓሊ በሌለባቸው እንደ ጅቡቲ ባሉ አገራት ርካሽ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የማይቀመስ መሆኑን ይናገራሉ።
ስነ ጥበብ የሚገባው ክብር ላይ እንዲገኝ ይህን መሰል እጥረቶች መፈታት እንዳለባቸው ያምናሉ። በህብረት መሥራት ሙያውን ያሳድገዋል የሚል እምነትም አላቸው። ሌላው በአደባባይ የሚተቹ ሃያሲዎች መኖር እንዳለባቸው ተናግረው፣ ሙያው እንዲያድግ ይሄም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይገልፃሉ።
የሠዓሊው የዕረፍት ውሎ
ሰፊውን ጊዜውን ሥዕል በሚሠራበት ስቱዲዮ ያሳልፋሉ። “የዕረፍት ጊዜ አስበን የምናመጣው አይደለም” ይላሉ ሠዓሊ ሉልሰገድ። ብዙውን ጊዜያቸውን በስነ ጥበብ ሙያው ላይ ተፅእኖ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በማከናወን ያሳልፋሉ። መፅሐፍትን ማንበብና እውቀታቸውን ማዳበር ምርጫቸው ነው። ጊዜ ሲገኝ ከቤተሰብና ከጓደኞች ጋር ለምክክርና ለጨዋታ ምቹ የሆነና ራስን ዘና የሚያደርግ ስፍራ በጋራ በመምረጥ በዚያ ማሳለፍ ይወዳሉ።
ሠዓሊው በሥራ ላይም ሆነ የጥሞና ጊዜ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ሙዚቃ ማድመጥ ይመርጣሉ። ታዲያ ክራርና ማሲንቆን ይወዳሉ። የአገራቸውን ሙዚቃ ማድመጥ ስሜት ይሰጣቸዋል። ከዚያ ባለፈ ብሉዝ፣ የአፍሪካ ሙዚቃና መሰል ክላሲካል ሙዚቃዎችን ማድመጥ የረጋ መንፈስ እንዲኖራቸው እንደሚያግዛቸው ይናገራሉ። አንጋፋው ሠዓሊ ለሙዚቃ ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ “ህይወት ያለሙዚቃ የለም” የሚል ጠንካራ አመለካከት አላቸው። በተለይ የጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ መሀሙድ አህመድ ከድሮዎቹ ከአሁኑ ደግሞ ቴዲ አፍሮ እንዲሁም ሮፍናን የመሳሰሉ ታላላቅ ሙዚቀኞች አድናቂ ናቸው።
ከዚህ በተረፈ በዕረፍት ጊዜ ቀለል ያሉ እንደ “ፖሎ” የመሳሰሉ አልባሳትን መጠቀም ይመርጣሉ። በተለያዩ በዝግጅቶች ሲጋበዙ ቦታውን የሚመጥኑ አልባሳትን ተጠቅመው ጥሪ አክብረው ዘንጠው በስፍራው ይታደማሉ።
መልዕክት-ለትውልዱ
አዲሱ ትውልድ አገሩን ለመጠበቅ ማሰብ፣ ሰከን ብሎ መጠየቅና መረጋጋት ያስፈልገዋል በማለት አሁን ላይ ኢትዮጵያ በተለያየ አቅጣጫ የመጡባትን ፈተናዎች ለመመከት ትውልዱ ከፊት መቆም እንዳለበት ይናገራሉ። አገርን በግንባር ቀደምነት፤ ባንዲራን ከፊት አድርጎ መሥራት ከብዙ ነገር ይጠብቃል፤ ይሄን ኃላፊነት ለመሸከምም ወጣቱ ትውልድ ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል በማለት የመቋጫ ምልዕክታቸውን አድርሰውናል። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2013