ጋሞ ሲነሳ የሽመና ባህሉ አብሮ ይነሳል።በደማቅ ቢጫ፣በቀይና በጥቁር ቀለማት ተዥጎርጉሮ የሚሰራው የሽመና ውጤቱም የቀለም አገባቡ የእጅ ጥበቡ ትኩረትን ይስባል።ሰዓሊው ብሩሹን ከቀለም አዋህዶ ተጨንቆ በሸራው ላይ ያሳረፈው ይመስላል።የባህል አልባሱ በተለይም ለወንዶች የሚዘጋጀውን ሱሪ እንደኔ አስተውላችሁ ከሆነ መኻል ለመኻል ወደታች የወረደ በመሆኑ ከሌሎች ስፌቶች የተለየ ነው።ይህም ትኩረትን ይስባል።በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ቀድሞ የሚታወሰውን ሽመናውን አስቀደምኩ እንጂ የምግቡ፣የጋብቻ፣የለቅሶና ሌሎችም የባህል እሴቶቹ አይዘነጉም።እሴቶቹን ጠብቆ የቆየ ማህበረሰብ እንደሆነም የጋሞ አባት አቶ ካው በቀለ ብዙነህ አጫውተውናል።
አቶ ካው በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጋሞ ዞን ገረሴ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ ተወልደው ያደጉትም በዚሁ አካባቢ ነው።በአሁኑ ጊዜ በመምህርነት አገልግለው በጡረታ ላይ ይገኛሉ።ጋሞን ወክለው ብዙ የኢትዮጵያን ክፍል የመጎብኘት ዕድል አግኝተውም የብዙዎችን ባህልና እሴት አይተዋል። የራሳቸውንም አጋርተዋል። አሁን ደግሞ የጋሞ አባት ሆነው በአካባቢያቸው የተጣላ እንዲታረቅ፣የተበደለ እንዲካስ፣በአካባቢያቸው ሰላም እንዲሰፍን ማህበረሰቡ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆና አብሮነቱን አጠናክሮ እንዲኖር በሀገር ሽማግሌነታቸው ብቻ ሳይሆን በመምህርነታቸውም ብዙ ትውልድ ያፈሩ በመሆናቸው ሰፊውን ተሞክሯቸውን ለህዝብ ጥቅም በማዋል ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ።
ከጋሞ አባት ካው ጋር ስለአካባቢው የለቅሶ፣ የምግብና ሌሎችም እሴቶች አንስተን በተጨዋወትን ጊዜ በሽመና ሥራቸው ተደጋግሞ ወቀሳ ስለሚቀርብባቸው የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ጉዳይ አነሳሁላቸው። እርሳቸውም አልሸሸጉም።‹ግን አሉ› ‹‹ለህፃናቱ የሚሰጠው ቀላል የሆነው የማዳወር ሥራ ነው።ህፃናቱ ግን በአነስተኛ ሥራ ተለማምደው ወደዋናው የሽመና ሥራ ፈጥነው ይገባሉ።ይህ ተለምዶ ህፃናቱን ለጉልበት ብዝበዛ ዳርጓቸዋል።አሁን ግን ዘመኑም እየተሻሻለና ወቀሳውም ስለበረታ እየቀነሰ መጥቷል። ሙያውን መማራቸው ጋሞ የሚታወቅበት የሽማና ሥራ በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል ስለሚያስችል በአቅማቸው እንዲያውቁት መደረጉ ክፋት የለውም››በማለት እርሳቸውም ግንዛቤ እንዲፈጠር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ነግረውኛል።
በአካባቢው ስላለው የጋብቻ ሁኔታም እንዲህ ሲሉ ነው ያጫወቱኝ። ቀደም ባሉት ዓመታት በአካባቢው ያለ ዕድሜ ጋብቻ የተለመደ ነበር።በአካባቢው ትምህርት ቤት መስፋፋቱና የማህበረሰቡም ንቃተ ህሊና እያደገ በመምጣቱ ያለዕድሜ ጋብቻ ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም እንኳን ቀንሷል።የሰርግ ሥርዓቱም ቀድሞ የነበረውን ያህል ሰው ተቸግሮ ሳይሆን፣በአቅሙ የሰርግ ሥነሥርዓት በማዘጋጀት ወጭን መቆጠብ ችሏል።በምግብ ረገድም በአካባቢው ሁሉም አይነት የእህል ዘር ስለሚበቅል ማህበረሰቡ ሁሉንም ይጠቀማል።ለየት የሚለው ግን በአንድ አካባቢ የዶሮ ወጥ አዘጋጅቶ እንግዳ መጋበዝ ትልቅ ክብር እንደሆነው ሁሉ በጋሞ ለተከበረ እንግዳ ገንፎ ማቅረብ የተለመደ ነው።ገንፎው ከእህል ዘርና ከእንሰት ውጤት የሚዘጋጅ በመሆኑም ጣፋጭ ነው ።የለቅሶ ሥርዓታቸውም እንዲሁ ትልቅ ክብር ይሰጠዋል።ከሩቅም ከቅርብ ዘመድ ወዳጅ ተሰብስቦ ነው የቀብር ሥነሥርዓት የሚከናወነው።ከቀብር መልስ ቀባሪ እህል ሳይቀምስ ወደቤቱ አይመለስም።ዛሬም እነዚህ መልካም እሴቶቹ እንደቀጠሉ አጫውተውኛል።
በተለይም ስለባህላዊ የዕርቅ ሥርዓታቸው እንደገለጹልኝ፤ተበዳይ ለጋሞ አባቶች ስለበደሉ ሲያቀርብ ሽማግሌዎች ጊዜ ሳይሰጡ ነገሩን ለማጣራት ወደ በዳይ ቤት ይሄዳሉ።ጉዳዩ በአንድ ጊዜ የሚፈታ ካልሆነም ይመላለሳሉ።በተለይም ሽምግልናው በሁለት ወገኖች መካከል የተፈጠረው ፀብ ወደቤተሰብ እንዳይዘልቅና የነበረው ማህበራዊ ትስስር እንዲቀጥል በመከላከል ረገድ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የጋሞ አባቶች ይሰራሉ።ይህ የሚሆነው የሁለቱ ጉዳይ ከሽማግሌዎችም በላይ ሆኖ በዘመናዊው የህግ ሥርዓት በፍርድ ቤት ሊዳኝ የሚችልበት አጋጣሚ ስለሚኖር ችግሩ እንዳይሰፋ ነው።በጋሞ አባቶችም በቀላሉ የሚፈታ ከሆነም እንደአስፈላጊነቱ በዳዩ ካሳ በመክፈል ወይንም በይቅርታ ፀበኞች እንዲታረቁ ይደረጋል።ነፍስ ያጠፋ ከሆነ ግን ካሳው ከበድ ይላል።ሟች ልጆች ካሉት በዳይ ልጆቹን የማሳደግ ኃላፊነት አለበት።ተጎጂው በቂም ተነሳስቶ በበዳይ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ይመከራል።አጥፍቶ ከተገኘ ግን ከቅጣት አያመልጥም።የጋሞ አባቶች ከሚወጡት ኃላፊነት በተጨማሪ ጉዳዩን የያዘው ፍርድቤት ውሳኔም ይከበራል።
የጋሞ አባቶች ዕርቁ ተሳክቶላቸው በዳይና ተበዳይ ይቅር ሲባባሉ ዕርድ ተከናውኖ እህል ውሃ ይዘጋጃል።በባህሉ መሠረት ዕርዱን የሚያከናውን ሰው የተዘጋጀ በመሆኑ ያ ሰው የታረደውን ከብት አንጀት በማውጣት በዳይና ተበዳይ አንጀቱን እንዲረግጡ ያደርጋል።አንጀቱን ረገጡ ማለት ዕርቁ ከልብ ተፈጸመ ማለት ነው።የጋሞ አባቶች ለአካባቢያቸው ማህበረሰብ እንዲህ ያለውን አገልግሎት ሲሰጡ እርቅ ሲፈፀም የሚዘጋጀውን ምግብ ከመቋደስና ለእርቅ የሚሄዱበት አካባቢ እሩቅ ከሆነ ለመጓጓዣ ተብሎ ከሚሸፈንላቸው ወጪ ውጭ የወር ደመወዝ ክፍያም ሆነ የተለየ ጥቅም አያገኙም።የማህበረሰባቸውን ባህልና ወግ በትውልድ ቅብብሎሽ የወረሱትን ነው የጋሞ አባቶች እየተገበሩ ያለው።
ጥቅም የሌለበት እንዲህ ያሉ የጋሞን የባህል እሴቶች ብቻ ሳይሆን፣ጋሞ ዞን የብዙ የተፈጥሮ ሀብት ፀጋ ባለቤት እንደሆነም በሥፍራው በነበረኝ ቆይታ ለማወቅ ዕድሉን አግኝቻለሁ።ከተፈጥሮ ሀብቱም አባያና ጫሞ ወንዞች፣አርባ ምንጮቹ ይጠቀሳሉ።የዞኑ ከተማ የሆነችው አርባምንጭም ስያሜውን ያገኘችው በውስጧ ከያዘችው ምንጮችዋ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም።አርባምንጭ ሲነሳ የአዞ እርባታውም አብሮ ይወሳል።
አባያና ጫሞን ማዕከል አድርገው በአጠቃላይ የአካባቢውን መልክአምድር በሚያሳይ ስፍራ በባህላዊና በዘመናዊ የቤት አሰራር የተዋቡ የሎጅ መዝናኛዎችም ትኩረትን ይስባሉ።በከተሞች በህንጻዎች ውስጥ መኖርና ማየት የሰለቸው፣ከከተማው ግርግርና ሁካታ ራቅ ብሎ ተፈጥሮን እያደነቀ ለራሱ ዕረፍት መስጠት ለሚፈለግ ሰው ምቹ ናቸው።ከሎጆቹ መካከል ፓራዳይዝ ሎጅ አርባምንጭ ይጠቀሳል።በዚህ የመዝናኛ ሎጅ ላይ ሆኜ ድንቅ ተፈጥሮውን እያየሁ ነበር የደቡብ ቅርጫፍ ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ዳዊት መስፍን ጋር ቆይታ ያደረግነው።እርሳቸውም እንደነገሩኝ ሎጁ ጥብቅ የአርባምንጭ ደንና የእግዜር ድልድይን እይታ መሠረት አድርጎ ነው በሥፍራው የተሰራው።
ቤቶቹም በአካባቢው የባህልቤት በሚሰሩ በጋሞና ኮንሶ ባለሙያዎች የተሰራ ሲሆን፣ ከሥር ቤቱን ከተሸከመው ወይም ከመሠረቱ የሲሚንቶ ግብዓት ከመሆኑ በስተቀር ውጫዊና ውስጣዊ ገጽታውን ጨምሮ የውስጥ ቁሳቁስ መጠቀሚያው ባህላዊ መሠረቱን የያዘ ሎጅ ነው።ለከተማው የመጀመሪያው የቱሪስት መዳረሻ ሎጅ መሆኑም ለከተማው ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።ሎጁ የሀገርውስጥንም ከውጭ የሚመጡትንም የሚያስተናግድ ቢሆንም አብዛኞቹ እንግዶች የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው።
ነጭ ሳር ፓርክ፣ደቡብ ኦሞ ሀመር አካባቢዎች ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻዎች በመሆናቸው አካባቢው በቱሪስቶች ይመረጣል።እንዲህ ያለው ውብ ቦታ ለአንድ ዓመት ያህል በውጭ እንግዶች ሳይጎበኝ ቆይቷል።ምክንያቱም ዓለምአቀፍ ሥጋት የሆነው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ነው።ፓራዳይስ ሎጅ ብዙ ቱሪስቶችን ማጣቱ ገቢውን አዳክሞታል።ምንም እንኳን ሰራተኞቹ ሳይበተኑ ለማቆየት ጥረት ቢያደርግም ፈተናው በቀላል የሚታይ አልነበረም።ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ በመታየቱ ሎጁ መልሶ ለማገገም ችሏል።
ወደሌላው የአካባቢው ቱሪስት መዳረሻ ልውሰዳችሁ።አዞ ራንች ወደሚባለው የአዞ እርባታ ወደሚገኝበት ሥፍራ።የአዞ እርባታው ከአርባምንጭ ከተማ ወጣ ባለ ቦታ ከዋናው መንገድ ገባ ብሎ ይገኛል።ወደ እርባታ ጣቢያው የሚወስደው መንገድ አጭር ቢሆንም በመንገዱ ላይ የፈሰሰው ጠጠር ምቹ አይደለም።ቱሪስቱን አያበረታታም።ወደ ግቢው ሲዘልቁም ከግቢው ስፋት በስተቀር ተጨማሪ የሚታይ ነገር የለም።በአንድ የዛፍ ጥላ ሥር ከሚሸጥ የጀበና ቡና በስተቀር የጎብኝውን ፍላጎት የሚያሟላ መዝናኛ የለም።አዞዎቹን ለማየት ከፍለን በአንዱ የጥበቃ ሰራተኛ እየተመራን ወደ አዞዎቹ ሄድን።ከሦስት ወር እስከ 30 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን አዞዎች አስጎበኘን።በርቀት ሆነን አዞዎቹን አየናቸው።ትላልቆቹ ባልና ሚስት ናቸው።ከጉብኝቱ በኋላ በአዞ እርባታው ማዕከል ውስጥ የቱሪዝም ባለሙያ የሆኑትን አቶ መሠረት ደምለው አጠቃላይ ሁኔታውን እንዲያስረዱኝ ጠየኳቸው።
አቶ መሠረትም እንዲህ ገለጹልኝ፤አዞ ቆዳውና ሥጋው ስለሚፈለግ አዳኙ ብዙ ነው።በመሆኑም በአደን እየተመናመነ የመጣውን አዞ ለመታደግ የማዕከሉ ዋና ተልዕኮ የጥበቃ ሥራ ማከናወን ቢሆንም አዞዎቹን በቱሪዝም መስህብነት እንዲሁም ሥጋና ቆዳቸውን በመሸጥ ገቢ በማግኘት ይጠቀምባቸዋል።ሥጋውና ቆዳው ገዥ ሲያገኝ በማዕከሉ ውስጥ በተዘጋጀ ቄራ እርድ ተከናውኖ ለገበያ ይቀርባል።አዞው አራት ዓመት ሲሞላው ነው ለዕርድ የሚዘጋጀው።ደንበኞች ፈረንሳይና ጀርመን ሌሎችም የውጭ ሀገራት ናቸው።ማዕከሉን ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ከመከሰቱ በፊት በቀን እስከ ሁለትሺ የሀገር ውስጥ ጎብኝ፣የውጭ ሀገር ደግሞ እስከ 150 ይጎበኝ ነበር።ከወረርሽኙ በኋላ ግን የጎብኝው ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል፡፤የተሻለ የሚባለውም የሀገር ውስጥ ጎብኝ ነው ያለው።የሥጋና የቆዳ ንግዱ ግን ለጊዜው ቆሟል።
አዞዎቹ በሚገኙበት ሥፍራ የተጀመረ ግንባታ አይቼ ስለነበር አቶ መሠረት እንዲያስረዱኝ ጠየኳቸው።ግንባታው እድሳት መሆኑንና በዚህ ዓመት መጀመሩን ነበር ምላሽ የሰጡኝ።ነገር ግን በኮቪድና በተለያየ ምክንያት በሚፈለገው ፍጥነት እንዳልተጠናቀቀ ነው ምላሽ የሰጡት።አቶ መሠረት እንዳሉት ወደፊት ከአዞ በተጨማሪ ሌሎች እንስሳትን በመጨመር የቱሪስት መዳረሻነቱን ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል።መንግሥት ለቱሪዝም እንደስትሪው እየሰጠ ያለው ትኩረት አበረታች በመሆኑም ዕቅዱ ይሳካል የሚል መነቃቃት ተፈጥሯል።
በአጠቃላይ በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የቱሪስት መዳረሻ ምን ይመስላል? በሚለው ዙሪያም የአርባምንጭ ባህልና ቱሪዝም ስፖርት ጽህፈትቤት ቱሪዝም ምስል ጥናት ልማት የሥራ ሂደት ባለሙያ አቶ ዘካሪያስ ሳዳ እንዲህ አስረድተዋል።በተለይም አርባምንጭ ከተማ ከዞኑ ከተሞች እምቅ የሆኑ ታሪካዊ፣ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች የሚገኙባት የቱሪዝም መስህብ አሏት።ከቱሪዝም መዳረሻዎቹም ብሄራዊ ነጭሳር ፓርክ፣አባያና ጫሞ ሐይቅ፣የእግዜር ድልድይ፣ተፈጥሮ ጥቅጥቅ ደን ይጠቀሳሉ።እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች ለጎብኚው ምቹ በማድረግና በማልማት ረገድ ስለተሰሩት ሥራዎች አቶ ዘካሪያስ እንዳስረዱት ደረጃውን የጠበቀ የመሠረተልማት ተሟልቷል ለማለት አልደፈሩም።በተለይም ወደ ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ የሚወስደው መንገድ ፒስታ የሚባለው አይነት እንደሆነ ገልጸዋል።በማልማት በኩል በመስህብ አካባቢዎች በየክረምቱ በሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃግብር የደን እንክብካቤ ይደረጋል።
እንደ አቶ ዘካሪያስ ገለጻ፤በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት 24ሺ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ለማስተናገድ ጽህፈትቤቱ በዕቅድ የያዘ ሲሆን፣በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ተጽዕኖ ምክንያት ዕቅዱን ማሳካት ባይቻልም በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ 810 የውጭ ዜጎች መጎብኘታቸውን ጽህፈትቤቱ በከተማዋ ካሉ ሎጆች፣ሪዞርቶች፣ሆቴልቤቶችና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለመሰብሰብ ችሏል።የሀገር ውስጥ የቱሪስት ፍሰት ግን አልቀነሰም።ጽህፈትቤቱ የሀገር ውስጥ ጎብኝን በዕቅድ የያዘው ባስ 50ሺ ሲሆን፣ነገር ግን ከዕቅድ በላይ 63ሺ302 ሰው ከተማዋን ጎብኝተዋታል።በገቢ ደረጃም በሩብ ዓመት ከውጭ ሀገርና ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ወደ 27ሚሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ጽህፈትቤቱ በዕቅድ የያዘ ሲሆን፣24ሚሊየን 766ሺ377ብር ገቢ ሰብስቧል።
በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ የማደሪያና የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴልቤቶች ባይኖሩም በማህበር ተደራጅተው የለስላሳና የታሸጉ ውሃዎችና ትኩስ ነገሮችን የሚያቀርቡ መኖራቸውን ጫሞ ሐይቅ ላይም የጀልባ አገልግሎት የሚሰጡ መኖራቸውን የሚገልጹት አቶ ዘካሪያስ፤ቱሪስቶቹ ከጉብኝት መልስ ወደ አርባምንጭ ከተማ ተመልሰው ነው የመኝታ አገልግሎት የሚያገኙት ብለዋል።ወደፊት ባለሀብቶች በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴልና መዝናኛዎች በመሥራት እራሳቸውንና አካባቢውን እንዲጠቅሙ ጽህፈትቤቱ የማበረታታትና የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ዘካሪያስ ስለአዞ ራንች ይዞታም እንዲያስረዱን ጠይቄያቸው በሰጡት ምላሽ አዞ ራንች አንዱ የቱሪስት መዳረሻ በመሆኑ እንክብካቤና ትኩረት ይሰጠዋል።ቀደም ሲል የአዞ እርባታ ይከናወንበት የነበረው ሥፍራ አባያና ጫሞ ሐይቅ ከመጠን በላይ በመሙላቱ ምክንያት በመስመጡ የክልሉ መንግሥት በሚሊየን የሚቆጠር ብር በጀት በመመደብ መልሶ በማቋቋም የእርባታ ሥራው እንዲከናወን አድርጓል።ይህ የሆነው ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ሲሆን፣አሁን እርባታው የሚከናወንበት ቦታ አዲስ ነው። የአዞዎች ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው ጨምሯል።አዞ ራንች አካባቢውን በቱሪስት ተመራጭ እንዲሆን ካስቻሉት የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል እንደሆነና በስጋና በቆዳ ሽያጩም ገቢ በማስገኘት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ቢሆንም እነዚህን ጥቅሞች ማዕከል ያደረገ የሚመጥን ሥራ ተሰርቷል ለማለት የሚያስችል ነገር በሥፍራው በነበርኩበት ወቅት አላየሁም።
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጋሞ ዞን በነበረኝ ቆይታ አርባምንጭ ለእይታ ምቹና ቀለል ያለች ከተማ ሆና አግኝቻታለሁ።ምንም እንኳን ኮቪድ እንደ አንድ ተግዳሮት እየተጠቀሰ ቢሆንም በቱሪስት መዳረሻዎች ዙሪያ ያሰባሰብኳቸው መረጃዎች በዘርፉ ብዙ ሥራዎች እንደሚጠበቁ ተገንዝቤያለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2013