በአንድ ወቅት አንድ ባልና ሚስት ከወንድ ልጃቸው ጋር ይኖሩ ነበር:: ታዲያ አንድ ቀን ሰውየው ነፍሰ ጡር ሚስቱን ትቶ ወደ ጦርነት ሊሄድ ተነሳ::
ልጁንም ጠርቶት “አንድ ትልቅ ነገር እንድትሰራ እፈልጋለሁ:: እኔ በሌለሁበት ጊዜ ሁሉ እናትህን መንከባከብ የአንተ ኃላፊነት ነው:: እናትህ ስትወልድ ግን አንድ ነገር እንድታደርግልኝ እፈልጋለሁ:: ይኸውም የሚወለደውን ህፃን ተመልክተህ ሴት ልጅ ከሆነች ግደላትና ደሟን ጦር ሜዳ ድረስ አምጣልኝ:: ነገር ግን ወንድ ልጅ ከሆነ ጥቁሩን በግ አርደህ ደሙን ጦር ሜዳ ድረስ ይዘህልኝ ና::” አለው::
ይህንንም ያደርግ ዘንድ ልጁን ቃል አስገብቶ ወደ ጦር ሜዳ ሄደ:: ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እናትየው ሴት ልጅ ወለደች:: ልጁ ታዲያ ህፃን እህቱን ወዲያው ስለወደዳት ሊገድላት አልፈለገም:: ስለዚህ ጥቁሩን በግ አርዶ ደሙን ወደ ጦር ሜዳ ይዞ በመሄድ እናቱ ወንድ ልጅ እንደወለደች ለአባቱ ዋሽቶ ነገረው::
ከዚያም ተመልሶ ከእናቱና ከእህቱ ጋር አብረው ሲኖሩ አባታቸው በጦር ሜዳ ለብዙ ዓመታት ቆየ:: አንድ ቀን ታዲያ የአባትየው መመለሻ መድረሱን ልጁ በሰማ ጊዜ ወደ እህቱ ሄዶ እንዲህ ብሎ አስጠነቀቃት “ተጠንቀቂ! አባታችን ሲመለስ የእሱ ልጅ መሆንሽን ማወቅ የለበትም:: ስለዚህ አባዬ ወይም አባቴ ብለሽ በመጥራት የልጅነት ፍቅርሽን ከማሳየት ይልቅ ልጁ እንዳትመስይው እንደ ሌሎቹ የመንደሩ ልጆች አባባ ብለሽ ብቻ ጥሪው::”
አባትየውም ሲመለስ ልጁ አባዬ ብሎ ሠላምታ ከሰጠው በኋላ ወደ ጎጆው ተመልሶ እህቱን በቅሎ ላይ በመጫን ህይወቷን ለማትረፍ ይዟት ጠፋ::
ከዚያም ብዙ አስማተኞች ወደሚኖሩበት ጫካ ሄደው መኖር ጀመሩ:: ወንድምየውም ብዙዎቹን አስማተኞች ቢገድላቸውም የተወሰኑት ቀርተው ነበር:: በጫካው ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሲኖሩ ከአስማተኞቹ አንድ ወደቤታቸው ይመጣ ነበር:: ቀስ በቀስ ከእህቱ ጋር በመግባባት “አግቢኝ” ብሎ ጠየቃት::
እሷም “ይህማ በባህላችን እንደማይፈቀድ ታውቃለህ:: ስለዚህ ወንድሜን ነው መጠየቅ ያለብህ::” አለችው:: ነገር ግን ማንም ሰው እህቱንም ሆነ ወንድሙን ለአስማተኛ መዳር እንደማይፈልግ አስማተኛው ያውቅ ነበር::
ስለዚህ አስማተኛው ወደ ልጆቹ ቤት ተመላልሶ በመምጣት “ወንድምሽ በፍፁም እንዳገባሽ እንደማይፈቅድ ታውቂያለሽ:: ስለዚህ ወንድምሽን ገድለን እኛ እንጋባ::” እያለ ይወተውታት ጀመር::
በመጨረሻ በሃሳቡ ተስማምታ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠየቀችው:: እሱም የታመመች መስላ እንድትተኛና ከህመሟ ትድን ዘንድ የአስማተኛ ምግብ እንደሚያስፈልጋት ለወንድሟ እንድትነግረው ነገራት:: ከዚያም በኋላ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ይወያያሉ::
ወንድሟም ወደቤት በተመለሰ ጊዜ እህቱ ታማ ስላገኛት ምን ማድረግ እንዳለበት ሲጠይቃት መፍትሔው የአስማተኛ ምግብ ብቻ መሆኑን ነገረችው:: በዚህ ጊዜ ተነስቶ አስማተኛ ፍለጋ ሲሄድ በመንገዱ ላይ ሌላ አስማተኛ አገኘ:: ሌላውም አስማተኛ ማንም ሰው የአስማተኛ ምግብ ቢጠይቀው ክፉ ነገር እንዳለበት ሊያውቅ እንደሚያስፈልገውና ምናልባትም እሱን ሊገድሉት እንደሚችሉ ነገረው::
እናም አስማተኛው “ቢገድሉህም እንኳን አስከሬንህን በበቅሎ ጀርባ ላይ አስረው ወደ ገብስ ማሳ እንዲወስዱት ጠይቃቸው::” አለው::
በዚህ ጊዜ የእህቱ ወዳጅ የሆነው አስማተኛ ወደ እህቱ ሄዶ ምን ማድረግ እንዳለባት ነገራት:: ወንድምየው ወደ ቤት በተመለሰ ጊዜ እህቱ የአስማተኛውን ምግብ በልታ “አሁን ደህና ስለሆንኩ አንድ ጨዋታ እንጫወት::” አለችው::
ወንድምየውም “ምን ዓይነት ጨዋታ ነው የምንጫወተው?” ብሎ ጠየቃት:: እህትየውም “በቅድሚያ ምሰሶው ላይ እሰረኝ ከዚያ ደግሞ ያንተ ተራ ይሆናል:: አለችው::
የእርሱ ተራ በደረሰም ጊዜ ምሰሶው ላይ ካሰረችው በኋላ አስማተኛውን ጠርታ “ይኸውልህ፣ አሁን ልትገድለው ትችላለህ::” አለችው::
ወንድምየውም “በቅድሚያ ከሞትኩ በኋላ በቅሎ ጀርባ ላይ እንደምታስሩኝና በቅሎውን ወደ ገብሱ ማሳ እንደምትለቁት ቃል ግቡልኝ::” አላቸው::
እነርሱም አንዴ ከሞተ በኋላ ምንም ማድረግ አይችልም በማለት ከገደሉት በኋላ በበቅሎ ጀርባ ላይ አስረውት ጠመንጃውንም አብረው በመጫን በቅሎውን ለቀቁት::
በዚህ ጊዜ ሌላኛው አስማተኛ በቅሎውን፣ አስከሬኑንና ጠመንጃውን ከገብሱ ማሳ ውስጥ ስላያቸው ሁሉንም ወደ ቤቱ በመውሰድ አስከሬኑን ካስተካከለ በኋላ የወንድምየው አስከሬን ላይ ትንፋሹን ሲተነፍስበት ወንድሙ ህይወት ዘራ::
ጠመንጃውንም ለወንድምየው ከሰጠው በኋላ “በል፣ አሁን አድኜሃለሁ::” አለው::
ወንድምየውም ጠመንጃውን ወስዶ የእህቱ ወዳጅ የሆነውን አስማተኛ ከገደለው በኋላ እህቱን በበቅሎ ጭኖ ወደ ወላጆቻቸው መንደር ይዞ ሄዶ “ይህች እህቴ ናት፤ እኔ የእርሷን ነፍስ ሳድን እሷ ግን ገደለችኝ::” አለ::
ይህ የሚያሳየው መልካም ነገር ለሌሎች ብታደርጉም በምላሹ ክፉ ነገር ሊደረግባችሁ እንደሚችል ነው::
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች ድረገፅ
በይርጋ እጅጉ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ የጅቦች ልጅ ሞቶ ጅቦች ሁሉ ሃዘን ተቀምጠው ነበር:: ይህም ዜና ከአህዮች ጆሮ ደርሶ ነበርና አንድ አህያ እንዲህ አለ “ለምን ለቅሶ አንደርሳቸውም? ይህንንም ካደረግን እኛን ማደን ይተዋሉ::”
ሌሎቹም እንዲህ አሉ “ከጅቦቹ ጋር ወዳጅነት ለመመስረት ይህ መልካም አጋጣሚ ነው:: ስለዚህ እንሂድ::” ብለው ተስማምተው ወደ ጅቡ ቤት አቀኑ::
ጅቦቹም አህዮቹን በሩቅ ባዩ ጊዜ “እነዚያ ወደእኛ የሚመጡት እንስሳት እነማን ናቸው?” ብለው ጠየቁ:: ሁሉም በመገረም እያዩዋቸው ሳለ አህዮቹ በቀጥታ ወደ ጅቡ ቤት ገቡ:: የአህዮቹም መሪ እንዲህ አለ “የምትበሉት ነገር ጥቁር እንኳን ቢሆን የጅብ ፋንድያ ነጭ ነው:: የጌታዬን ልጅ ምን አገኘው?” ጅቡም እንዲህ ብሎ መለሰ “ምንም ብትለኝ አይገባኝም:: አሁን ጅቦቹ ሁሉ ተርበዋልና ምን ይበላሉ?”
አህዮቹም ሁሉ በጭንቀት እርስ በእርስ መተያየት ጀመሩ:: አንደኛውም “ብናመልጥ ይሻላል” ብሎ በለሆሳስ ተናገረ:: “ሌላኛው ግን አሁንማ በእጃቸው ውስጥ ነው ያለነው::” አለ::
“ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻለናል?”
“ከንፈራችንን እንስጣቸውና ያንን ይብሉ::”
በዚህም ተስማምተው አለቃቸው ይህንኑ ለጅቦቹ አስረዳ፤ ጅቦቹም በሙሉ ወደ እህዮቹ ዘለው ከንፈሮቻቸውን ቦጭቀው ጥለው በሁለት ጎራ ተፋጠጡ::
ስለዚህ አህዮቹ ከንፈር ስለሌላቸው በጅቦቹ የሚስቁ ይመስል ስለነበር አንዱ ጅብ “ልጃችን ሞቶ እያለ እንዴት ነው የምትስቁብን? ልታሾፉብን ነው የመጣችሁት? አለ::
በዚህም ጊዜ ጅቦቹ በሙሉ ዘለው አህዮቹን ይዘው በሏቸው::
ከዚያን ጊዜ አንስቶ አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ ይባል ጀመር::
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች ድረገፅ
በተስፋዬ ጪብሳ የተተረከ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2013