ቤተኛ ናት። የተቀባችው ሽቶ የቆመችበትን አካባቢ አውዶታል። የለበሰችው አንገትዬው ላይ ክፍት የሆነ ነጭ ቲሸርት ከጡቷ በላይ ያለውን ገላዋን እርቃኑን አስቀርቶታል። ስስ በመሆኑም የተቀረውን የሰውነት አካሏን በደብዛዛው ያሳያል። በማጠሩ ደግሞ እምብርቷን ሊሸፍንላት አልቻለም – እሷም ይህን ትፈልገዋለች። ከወደታች እንዲያው ለነገሩ ጣል ያደረገችው ስስ ጥቁር ጉርድ ቀሚሷም ቢሆን የገላዋን ቅላት የሚያሳብቅ ሆኗል።
የወቅቱ ፋሽን ሆኖ እንደሆነ እንጃ እንጂ ይህንኑ አለባበሷን ብዙዎቹ ለመዝናናት ወደ ምሽት ክበቡ የሚመጡት ሴቶችም የሚጋሩት ይመስላል። ምነው ቢሉ ሁሉም በተመስጥኦ የሚመለከቷት እሷኑ ነውና።
ምን እነሱ ብቻ! ከምሽት ክበባቱ ውጪ ከአውራው መንገድ ላይ ቆመው የለሊት ገዳቸውን የሚጠባበቁ ወጣት ሴቶችም ብርዱ ያንሰፍስፋቸው እንጂ ምርጫቸው ይኸው አለባበስ ነው። “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል” አይደል የሚባለው እስከነተረቱ።
ልቅም ያለች ቆንጆ ናት ባትባልም የደስ ደስ አላት። በአጭር…በአጭሩ የተከረከመችው ከርዳዳ ፀጉሯ ከመካከለኛ ቁመናዋ ጋር ተዳምሮ ዓይነ – ግቡ አድርጓታል – ሮዛን።
ሮዛ በግራ እጇ የያዘችውን ሲጋራ በላይ በላዩ ትምገዋለች። በብዙዎቹ የክበቡ ታዳሚዎች መጎብኘቷ ምስጢርነት የለውም። እኔም ለመቀራረብ ስል የውበቷ አድናቂ ሆኜ ተጠጋኋት። በሕይወቷ ዙሪያ በተለይም ስለወደፊት ዕጣ ፈንታዋ በውስጤ ማብላላትን ያዝኩ።
አዲስ አበባ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ሠፈር ተወልዳ ማደጓን በኩራት ነገረችኝ። በዚህ ሰዓት ከዚህ በላይ መግፋት አልፈቀድኩም። ብፈቅድም አልችልም። ይሁንና በአጭሩ ቆይታችን አንድ ነገር ተረዳሁ። እሷም ሆነች መሠሎቿ ስለ ነገ ምን ይሁን ምን የሚያስጨንቃቸው አሊያም የሚያሳስባቸው አንዳችም ነገር እንደሌለ። ለምን ብለን ነገ በራሱ ሌላ ቀን ነውና ስለምን እናስብ፣ ስለምንስ እንጨነቅ ያሉ እስኪመስሉ ድረስ።
ብቻ ዛሬን አምረው ዕድል ከሰጠቻቸው ጋር ወጥተው በየምሽት ክበባቱ ጨፍረው መኖርን – ይህም ኑሮ ከተባለ ይመርጡታል። ግን እንዲህ ተሁኖ እስከ መቼ የሚለውን አስበውበት ያውቁ ይሆን? እንጃ!
በካዛንቺስ እኩለ ለሊቱ ከቀኑ በበለጠ ይደምቃል። ካዛንቺስ ውስጥ “ፀሐይ አትጠልቅም እንዴ?“ ያሠኛል፣ ያኔ ድሮ ተመላልሼ እንዳየሁት። ቀን…ቀን በሮቻቸውን ከርችመው የሚውሉት ብዙዎቹ የካዛንቺስ የምሽት ክበባት ከእኩለ – ለሊት በኋላ ነው ታዳሚዎቻቸውን ለመቀበል መሰናዷቸውን የሚያጠናቅቁት። ከስንት ጊዜ መጥፋት በኋላ መከሰቴ ነው። እግሬ ወዳመራኝ ወደ አንደኛው የምሽት ክበብ ጎራ አልኩ።
ተመካክረው ያዘጋጁት ይመስል በካዛንቺስ አንደኛውን የምሽት ክበብ ከሌላው ለመለየት ያስቸግራል። ሁሉም በአደረጃጀታቸው ይቀራረባሉ፤ ብዙም አይለያዩም – ይመሳሰላሉ። እንግዳን ወደ ውስጥ እንዲዘልቅ የማይጋብዙት ለዚያውም በቤቶቹ ግድግዳ መሐል ተጣብቀው የተሠሩትና ከዳር ቆመው እንዲጠቀሙባቸው ብቻ የሚያስገድዱት የመፀዳጃ ቤቶች ርግጥ ነው ያመሳስላቸዋል። እንደልብ ከማያላውሰው ከዚሁ የመፀዳጃ ቤት ታከው ግልጋሎት የሚሰጡ የምግብ ማብሰያ ክፍሎች እንዳሉ ደግሞ ልብ ይበሉ።
ከቀርከሃ የተሠሩት የመጠጥ መደርደሪያዎች ከአናታቸው ላይ የሣር ክዳን ደፍተዋል። መደርደሪያዎቹ የያዟቸው መጠጦች ዋጋቸው እንደዋዛ አይቀመስም – በውድነታቸው የጠጪውን ኪስ ይገለብጣሉ፤ ያራቁታሉ።
በሁሉም የምሽት ክበባት ማለት ይቻላል ከእንጨት አሊያም ከብረት የተሠራ ትልቅ ወንበር ወይም ሶፋ መቀመጫ ብሎ ነገር አይታሰብም። በሚጠይቁት ከፍተኛ ዋጋ ይሁን አሊያም በሚይዙት ሰፊ ቦታ ምክንያት ተመራጭ የሆኑ አይመስልም።
በዚህ ምትክ አልፎ…አልፎ በየቦታው ከሚታዩት የቆዳ መቀመጫ ዱካዎች በተጨማሪ የጠባቦቹን ክፍሎች ግድግዳ ዙሪያ ተከትለው የተሠሩትና ባለትራስ መደገፊያ መደቦችን በመቀመጫነት መምረጣቸው የካዛንቺስ ምሽት ቤቶችን የሚያጋራቸው ሌላው ገጽታ ነው።
ጠባቧ የጭፈራ ቤት ሰው አልባ ሆና ተንፈስ የምትልበትን የቀኑን ውሎዋን የናፈቀች ትመስላለች። የሰው ዓይነት ያለው በካዛንቺስ ነው እንዲሉ ክበቧ እንደ ድርሻዋ በሰው ብዛት ተሞልታ መተንፈሻ አጥታ ልትፈነዳ ተቃርባለች።
ገበያውም የዚያኑ ያህል ደርቷል። የሲጋራው ጭስ፣ የሙዚቃው ጩኸት፣ የየዓይነቱ መጠጥ ሽታ፣ ግርግር ትርምስ…ትርምስምስ – በካዛንቺስ። ምሽቱ እየተጋመሰ ነው። ሰው መቆሚያ አጥቷል። መቀመጫ ብሎ ነገር አይታሠብም። በዚያ ላይ አዲስ ገቢ ጠጪው ወደ ውስጥ መዝለቁንም አላቋረጠም። ከበሮው ይደለቃል፣ ማሲንቆው ይገዘገዛል፣ ክራር ይደረደራል፣ አቀንቃኙም ያቀነቅናል፣ ጠጪውም እንዲሁ የጨበጠውን እንደያዘ ባለበት ቆሞ ይወዛወዛል – በካዛንቺስ ከእኩለ ለሊት እስከ ንጋት።
አብዛኛው ጠጪ አይታወቅም ወይም እርስ በራሱ አይነጋገርም። ባይተዋወቅም ችግር የለበትም። የሚተዋወቁ ቢሆንም ከዚህ ሥፍራ ቁም ነገር ማውጋት አይሞከርም። ስለመሸ እንኳን አይደለም። ይልቁን የቤቱን ጣሪያ ከላያቸው አሽቀንጥረው ለመጣል ግብግብ የገጠሙ የሚመስሉት የሙዚቃ መሣሪያዎች ከራሣቸው ድምፅ በስተቀር የሌሎችን ለማስተናገድ ስላልፈቀዱ እንጂ።
የጠጪውም የእስከ ንጋት የቆይታ ሚስጥር ምናልባት ይህ ሣይሆን ይቀራል? በአዲስ አበባ ምሽት ሥፍራውን ለንጋት ሲያስረክብ የሚታየው በካዛንቺስ ላለመሆኑ ማን ሙግት ይገጥማል። ይህ ሁኔታ ነበር የግሉን ሥራ እያከናወነ አምሽቶ የነጋበት አንድ የቅርብ ባልንጀራዬ “ሌቱና ንጋቱን አጨባብጬ ተነሣሁ” ያለኝን ያስታወሰኝ።
የደከመ አዕምሮን አሣርፎና ተከታዩን የሥራ ቀን በአዲስ መንፈስ አዘጋጅቶ ለመቅረብ የመዝናኛ ሥፍራዎች አጋዥነት አጠያያቂ አይደለም። መጽሐፍ ማንበብ፣ ፊልም መመልከት፣ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር፣ የቱሪዝም መስህብ አካባቢዎችን መጎብኘትና ሌላም ሌላ አዕምሮን እንደማዝናናት ይቆጠራል። ሆኖም የተለያዩ መዝናኛ ሥፍራዎችን በቀላል ወጪ ለማደራጀት ምቹ በሆነችው አዲስ አበባ የምሽት ክበባት ናቸው በብዛት ጎልተው የሚታዩት። የምሽት ክበባትን በብዛት በመያዝ ደግሞ ካዛንቺስ ቀድማ የምትጠራ ናት።
ለመሆኑ ማን ነው ካለ ምሽት ክበባት በስተቀር የመዝናኛ ሥፍራ የለም ብሎ ያለ? አብዛኛዎቹ የምሽት ክበባትስ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ እንደሌላቸው ስንቶች ያውቁ ይሆን? በመዲናዋ ከሚገኙ የምሽት ቤቶች ውስጥ ምናልባትም ግማሽ ያህሎቹ ሕጋዊ አይደሉም።
በአንድ ወቅት የከተማው አስተዳደር የሥራ ፈቃድ የሌላቸውን የምሽት ቤቶች ለመቆጣጠር ከተለያዩ ቢሮዎች የተውጣጣ አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ ሥራ ጀምሮ ነበር። ጀምሮ ነበር ልበል። አዎ ተግባራዊነቱ የወሬ ሽታ ሆኖ ቀረ እንጂ። የሥራ ፈቃድ የሌላቸው እንደሚዘጉ ካዛንቺስ ውስጥ ላሉ የምሽት ክበባት ማስጠንቀቂያም ተሰጥቷቸው ነበር። የሚገርመው ግን አሁንም ድረስ በዚያው ሥራ ላይ መኖራቸው ነው።
በምሽት ቤቶቹ ላይ ዕርምጃውን ለመውሰድ ያስፈለገው እንዲህ ነው። የቤቶቹ አሠራር ድምፅን ወደ ውጪ በማያስተላልፉ መልኩ አለመዘጋጀታቸው፣ የንጹሕ አየር ማስገቢያና ማስወጫ አለመኖር፣ ለጭፈራና ለመስተንግዶ ሥራ ምቹ አለመሆናቸውና በአጠቃላይ ለድምፅ ብክለት መጋለጣቸው ነው።
አልፎ…አልፎ በቦሌ፣ በሃያ ሁለት፣ በዳትሠን፣ በአዋሬና በቺቺንያ አካባቢዎች ያሉ አንዳንድ ምሽት ቤቶች የካዛንቺሱን ይጋራሉ። ከእኩለ – ሌሊት በኋላ እርቃናቸውን በሚወጡ ሴቶች እንደሚያስደንሱና አደንዛዥ እፆችን ጭምር እንደሚያስኮመኩሙ መታማታቸው ደግሞ የአንድ ሠሞን ወሬ ሆኖ ነበር።
ምን ይህ ብቻ! ሕገ ወጥ የጭፈራ ቤቶቹ ለልቅ የግብረ – ሥጋ ግንኙነት የተመቹ መሆናቸውን ብዙዎች ይስማማሉ። ጠጪው ያለችግር ያሻውን እየጎተተ በመሄዱም የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ተጋላጭነቱ እየጨመረ መጥቷል። በዚያ ላይ ኮሮናስ? እንዳይባል። በዚህ ሰዓትና ሥፍራ ኮሮናን ማን አንስቶት?! ማንስ አስታውሶት?
አንድ ዓለም አቀፍ የዜና ማሠራጫ ኢትዮጵያዊውን የማሕፀን እስፔሻሊስት ዋቢ አድርጎ በዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ /ኢንተርኔት/ ያሠራጨውን ዘገባ እዚህ ላይ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል። በአዲስ አበባ ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስ ጋር በተያያዘ ብቻ በየቀኑ ከሠላሳ የማያንሱ ሰዎች ለሕልፈተ – ሕይወት እንደሚዳረጉ ነው። የኮሮናው ሲጨመርበት ደግሞ ምኑ ተርፎ – አሐዙ ሌላ ነው።
እንደ ሕክምና ባለሙያው በመዲናዋ ጎዳናዎች ላይ በየዕለቱ ከሺህ የማያንሱ ወጣት ሴተኛ አዳሪዎችን ማየትም የተለመደ ነው። ለአብዛኛዎቹ ወደዚህ መስክ መሰማራት ዋነኛው ምክንያት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የወርቅ ሀብት አግኝተው ባለፀጋ እንደሚሆኑ የሚነገራቸውን ባዶ ተስፋ ይዘው ከገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍሎች እየፈለሱ መምጣታቸው ነው።
የሚያሳዝነው ግን በሀብት ናጠው ከቱጃሮቹ ተርታ አለመሰለፋቸው ብቻ ሣይሆን የዕለት ገቢያቸውም ቢሆን ከእጅ ወደ አፍ ያልዘለለ ጭምር መሆኑ ነው። የተሰማሩበት የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት የተደላደለና አልጋ በአልጋ ሆኖ አይጠብቃቸውም። ጥቂት የማይባሉት በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ሰባትና ስምንት ሆነው ተጨናንቀው እስከ መኖር ይደርሳሉ።
የማህበራዊ ሣይንስ ጠበብቶች እንደሚስማሙት ብዙዎቹ ሴተኛ አዳሪዎች ቀደም ሲል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ፣ በቤት ሠራተኛነት ጭምር ተቀጥረው የሚሠሩና ለተሻለ ሕይወት ሲባልም ትዳራቸውን ፈትተው ከክልል ከተሞች ወደመዲናዋ የፈለሱ ናቸው።
እዚህ ላይ አንድ አብነት እናንሳ፤ አባላዘርን ጨምሮ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በሦስት ወራት ውስጥ ወደ አንድ ጤና ተቋም በሄዱ 372 ሴተኛ አዳሪዎች ላይ ጥናት ተካሂዶ ነበር። በውጤቱም ከመቶ የሚልቁት ከኤድስ ቫይረስ ጋር አብረው እንደሚኖሩ ተረጋግጧል።
እናስ ሕይወት በዚህ ፈታኝ ክስተት ዙሪያ ተተብትባ በምትገኝበት በዚህ ወቅት በመዝናናት ሥም እየደረሰ ያለውን ጥፋት ልብ እያልን ይሆን? እስቲ ለአፍታ ቆም ብለን ጉዟችንን እንፈትሽ – እናጢን። እያወቁ ማለቅ እንዳይሆን ነገሩ ለመዝናኛ ሥፍራ ምርጫ ገደብ ሊበጅለት ይገባል – መተኪያ የሌለውን ሕይወት ላለማጣት ሲባል።
“የፍየል ጭራ ብልት አይከድን፤ ከብርድ አያድን” እንደሚሉት እርቃንን የመሆን ያህል በእራፊ ጨርቅ በየምሽት ክበባቱ የሚታዩት ሮዛና የሥራ ሸሪኮቿ እንዲሁም በውድቅት ሌሊት በጎዳናዎች ላይ ውርጭና ብርድ እየተፈራረቀባቸው የሚቆሙት ሴቶች በሕይወት የመቆየታቸው ምስጢር ዛሬ…ዛሬ አሣሳቢ ሆኗል። የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውስ?
ቀናው መንገድ ሁሉ በአንዲት ጀንበር ይመቻቻል ተብሎ ባይታሠብም ሁሉም ወገን የሮዛና የመሠሎቿን ሕይወት ለመታደግ በጋራ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር ሴተኛ አዳሪዎች ያለባቸውን ማህበራዊ ችግር ለማቃለል ምን ዕቅድና ምን ጅማሮ አለ? በወገን የተደገፈ ጥረት ማድረግ ያሻል።
ጋሻው ጫኔ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም