አገራችን በአሁኑ ወቅት በርካታ ተግዳሮቶች እየፈተኗት ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒው ያሉት ተስፋዎች እና መልካም እድሎች ግን እጅግ የበዙ ናቸው:: ኢትዮጵያን ወደብልጽግና እንደሚያሸጋግራት ተስፋ ከተጣለባቸው መልካም አጋጣሚዎችም ውስጥ አንዱ የተሳካ ምርጫ ማካሄድ ነው::
ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ ለአንድ አገር ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል:: በተለይ በምርጫው ላይ የሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በእውነት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ቁርጠኛ ሆነው ከተነሱና በሁሉም መስፈርት ዋነኛ ግባቸው የአገራቸው ማሸነፍ መሆኑን ካመኑ ለሰላማዊ ምርጫ ትልቅ ቦታና ክብር ይሰጣሉ:: በዚህ መንገድ ሁሉም ከተቃኘም እያንዳንዱ ፓርቲ አገርን አስቀድሞና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መሸነፍም እንደሚኖር አስቦ ሁለቱንም አማራጮች በእኩል ለማስተናገድ ከወዲሁ ቁርጠኛ አቋም ይዞ ይነሳል::
ከዚህ አንጻር ዘንድሮ በሚካሄደው 6ኛው አገርአቀፍ ምርጫ በርካታ ፓርቲዎች በተመቻቸው የምርጫ ሜዳ ውስጥ ገብተው ነገ አገርን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን የህዝብ ይሁንታ ለማግኘት እስካሁን የመጡበት መንገድ መልካም ጅምር ነው:: በዘንድሮ ዓመት እየታየ ያለው የክርክር ሂደትም ሆነ በገዢው ፓርቲም ሆነ በመንግሥት በኩል ሰላማዊ፣ ተዓማኒና አሳታፊ ምርጫ ለማካሄድ የያዙት ቁርጠኝነት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው::
ኢትዮጵያ ይህንን ምርጫ የምታካሂደው ልክ እንደቀደሙት ምርጫዎች ምርጫ አካሂደናል ለማለት ብቻ እንዳልሆነ እስካሁን የመጣንባቸው መንገዶች ያመላክታሉ:: የለውጡ መንግሥት ገና ከመነሻው ጀምሮ በአገራችን ዘላቂ ልማትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠርና ዜጎች በሁሉም የአገራቸው ጉዳይ ላይ ባይተዋር የማይሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ በገባው ቃል መሰረት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል::
በዚህም መሰረት በመጀመሪያ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገሪቱ የፖለቲካ ሜዳ የተገፉና ለስደት የተዳረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም አክቲቪስቶች በአገራቸው ጉዳይ ላይ በነጻነት እንዲሳተፉ በማድረግ መንገዱን ማመቻቸቱ አንዱ ማሳያ ነው:: በዚህ መሰረት በለውጡ ማግስት በውጭ ሆነው የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩትን ጨምሮ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ ፓርቲዎች ጭምር ወደአገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በማድረግ መንገዱን ማመቻቸቱ ለዚህ ትልቅ ማሳያም ነው::
ከዚያም ባሻገር በተለይ ቀደም ሲል በተለያዩ መንገዶች ለገዢው ፓርቲ ያደላሉ ተብለው ሲታሙ የነበሩ የዴሞክራሲ ተቋማት በተለይ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት በተቻለ መጠን ገለልተኛ አቋም ባላቸው አካላት እንዲመሩና በአዲስ መልኩ እንዲደራጁ በማድረግ ለዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታና ለፍትሃዊ ምርጫ መንገዱን ሲያመቻች ቆይቷል::
መንግሥት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫም ያለምንም ችግር በሰላማዊ መንገድ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲከናወን ቁርጠኛ አቋም ይዞ መስራት የጀመረውም ከዚህ ሁሉ ዝግጅት ጋር ነው::
ይህ የሆነበት ምክንያትም በአንድ በኩል በአገራችን የተጀመረውን ዴሞክራሲዊ ስርዓት ከዳር ለማድረስና አገራችንን ለማሻገር ዋነኛው መስመር ዴሞክራሲያዊና ሁሉንም ዜጎች ያሳተፈ መንገድ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደጋግመው እንደገለጹትም ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ ከተጠናቀቀ ማንም ያሸነፍ ማንም ኢትዮጵያ አሸነፈች ማለት ነው:: የኢትዮጵያ ማሸነፍ ደግሞ ነገ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እንደሚያረጋግጥ ጥርጥር የለውም::
ላመንም ግልጽ እንደሆነው የውስጥና የውጭ ኃይሎች በተለይ ምርጫውን ለማደናቀፍ በርካታ ሴራዎችን ሲሸርቡ ቆይተዋል፤ አሁንም እየሸረቡ ነው:: ከነዚህም መካከል አንዱ ምርጫው አንዳይካሄድ በተለያዩ መንገዶች ጫና መፍጠር ነው:: በዚህ መሰረት ይህ ምርጫ አስፈላጊ እንዳልሆነ በተለያዩ አካላት ጭምር ሲሰብኩ ይስተዋላል::
ከዚህም አልፎ ምርጫው መካሄዱ እንደማይቀር ሲገነዘቡ በአንድ በኩል ኅብረተሰቡ ካርድ እንዳይወስድ በተለያዩ መንገዶች የመቀስቀስና የማደናቀፍ ሥራ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ይህም ሳይሳካ ቀርቷል:: ሌላው መንገድ ደግሞ የውጭ ታዛቢዎች በምርጫው ላይ በታዛቢነት እንዳይሳተፉ እንቅፋት መፍጠር ነው::
ከዚህም አልፎ አሁን አሁን ምርጫው በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ እንደማይቀርና ለዚህም በርካታ ፓርቲዎች በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑ ሲታወቅ ብጥብጥና ሁከት ለመፍጠር የሚካሄዱ ሴራዎች አሉ:: ይህ ደግሞ በአገሪቱ ሰላም እንደሌለ በማስመሰል የዓለም ማህበረሰብ በአገሪቱ ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ ነው::
ነገር ግን ኢትዮጵያ ይህንን ምርጫ በሰላማዊና ዴሞክራሲዊ መንገድ ካካሄደች ሊያፈርሷት ሌት ተቀን ጉድጓድ የሚምሱ ጠላቶች ሁሉ ያፍራሉ፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜም ከላይዋ ላይ ወርደው ወደራሳቸው መስመር ይገባሉ:: ምክንያቱም ምርጫው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይበልጥ መተማመንንና አንድነትን የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን ነገ ለሚከናወነው የልማትና የብልጽግና ጉዞ ትልቅ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ይህንን መንገድ ለማደናቀፍ አቅም አይኖራቸውም::
በማንኛውም መንገድ ግን ኢትዮጵያን ከተያያዘችው የብልጽግና ጉዞ የሚያደናቅፍ አንዳችም ሃይል እንደማይኖር መገንዘብ ተገቢ ነው:: ለዚህ ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚሰሩ ኃይሎችን እየለዩ መመከትና የብልጽግና ጉዞውን አጠናክሮ ወደፊት መጓዙን መቀጠል አለበት:: በሌላ አባባል “ውሾቹ ይጮሃሉ፤ ግመሎቹም ጉዟቸውን ቀጥለዋል”::
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም