የምርጫ ጉዳይ ለአንድ ሀገርና ህዝብ የሚኖረው ትርጉም ምርጫው ይዞት ከሚመጣው ትሩፋት ጋር የሚተሳሰር ነው። ከዚህ ተጨባጭ እውነታ የተነሳም የምርጫ እና የምርጫ ስኬታማነት ጉዳይ ከማንም በላይ ከምርጫው ባለቤት ሀገርና ህዝብ በላይ ሊሆን አይችልም። ሊሆን ይቻላል ብሎ ማሰብም “ እኔ እውቅልሀለሁ” ከሚል የቆየ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ባህል የሚመነጭ ነው።
እኔ አውቅልሀለሁ የሚለው የምዕራቡ የቆየ የፖለቲካ ባህል ባለፉት ዘመናት ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸውን የዓለም ህዝቦች በተለይም አፍሪካውያንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ከቅኝ ግዛት ዘመን ዋዜማ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስም ዋጋ እያስከፈላቸው ነው። የተደረጃ የፖለቲካ መሳሪያ በመሆንም የአሕጉሪቱ ህዝቦች የራሳቸውን የሕይወት ምርጫ እንዳይኖሩ የተግዳሮት ምንጭ ሆኗል፤ እየሆነም ነው።
ይህ በአንድ በኩል የራሱ የሆኑ አሻጋሪ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶች ባለቤት የሆነን ሕዝብ አሳንሶ ከማየትና ራስንና የራስ የሆነውን አልፋና ኦሜጋ አድርጎ ከማየትና ከመቀበል የሚመነጭ የአስተሳሰብ መዛነፍ ነው። ይህ የተዛነፈ አስተሳሰብ በአህጉሪቱ ሕዝቦች የሀገር ግንባታ ላይ የሚታይ ጫና ሆኖም እንደቀጠለ ነው።
እነዚህ ህዝቦች ጫናውን መቋቋም እያቃታቸው በሄዱ ቁጥር ያለፍላጎታቸው የሚገቡበት የፖለቲካና ማህበራዊ ስርዓት በትውልዶች ግንባታ ውስጥ የአሉታዊ ተጽእኖ ምንጭ በመሆን ሀገራቱ በትውልዶች ግንባታ ሄደት ውስጥ ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል ፣ እያደረጋቸውም ነው።
የምዕራቡ ዓለም ማህበራዊና ፖለቲካዊ እሴቶች በዘመናት መካከል እየመጡበት ያለው ሁሉንም ነገር እንደ ሸቀጥ የማየትና በዚሁ እይታ የመመዘን ችግር ለነዚህ ህዝቦች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆነባቸውም መጥቷል ።
የሰውን ሕይወት ተራ የፖለቲካ ሸቀጥ አድርጎ ወደ ማየት የወረደው የምዕራቡ አስተሳሰብ ዓለምን የቱን ያህል ዋጋ እያስከፈለ ለመሆኑ ሶሪያን ፣ ሊቢያን እና የመንን ማየት በቂ ነው። የነዚህ ሀገራት ህዝቦች ለተሻለ ሕይወት ብለው የጀመሩት ለውጥ ተጠልፎ የቱን ያህል ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ ማየት ተገቢ ነው።
ሰብዓዊ መብት ፣ ዴሞክራሲ ፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ — ወዘተ በሚሉ በምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ትርፍ በሚመዘኑ የተጣመሙ እሴቶች የተሸፈነው የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ መንገድ እስከአሁን ባለው ሁኔታ የአህጉሪቱን ሀገራት በየወቅቱ አለመረጋጋት ውስጥ ከመጨመር ባለፈ የፈጠረው አዲስ ነገር የለም።
ሀገራቱ እነዚህን ሰብዓዊ እሴቶች በራሳቸው መንገድ ገንብተው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርገዋቸዋል። በተለይም ሀገራቱ የሚያደርጓቸው ምርጫዎች በተቃርኖ እንዲሞሉ በማድረግ ትርጉም አልባ አድርገዋቸዋል። የሀገራቱ የምርጫ አጀንዳዎች በየወቅቱ እየተጠለፉ ሰላማዊና ስኬታማ ሳይሆኑም ቀርተዋል።
በአሁናዊ የሀገራችን እውነታም የሚስተዋለው ይኸው ነው። ህዝባችን ብዙ ዋጋ ከፍሎ ወደስልጣን የመጣው የለውጥ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እየሄደበት ያለውን መንገድ ለመቀልበስና ለመጥለፍ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፤ እየተደረጉም ነው።
ይህ እውነታ ለሀገራችን አዲስ አይደለም ፣ በተለያዩ ወቅቶች የተፈጠሩ ህዝባዊ የለውጥ መነሳሳቶች ትርጉም ያለው ሀገራዊ አቅም ከመሆን ይልቅ በብዙ ተግዳሮቶች ተጠልፈው እንዲሰናከሉ የሆኑት በአንድም ይሁን በሌላ በነዚህ ኃይሎች ግልጽ እና የስውር ሴራ ስለመሆኑ መናገር እንደ ድፍረት የሚቆጠር አይደለም።
በለውጥ ማግስት ያደቡ ኃይሎች ወደ ስልጣን እንዲመጡ ፣ የመጡበት መንገድ ጤነኛ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ጠንካራ ያለመሆናቸው እውነታ በሕዝባችን ላይ የተደራራቢ ችግሮች ምንጭ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ከዚህ የታሪክ አዙሪት ለመውጣን መንገድ በጀመርንበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት ችግሩ ዳግም ተግዳሮት ሆኖ ከፊታችን ቆሟል።
የምርጫ ጉዳይ ከዚህ አዙሪት መውጫ መንገዳችን ነው ብለን ቆርጠን በተነሳንበት ፣ ከዚህም በላይ በምርጫ ወደንና ፈቅደን የምንሰይመው መንግሥታችን እንደመንግሥት ጠንካራ ሆኖ ያሻግረናል ብለን ተስፋ በሰነቅንበትና ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት በፈጠርንበት ወቅት እነዚህ ኃይሎች ምርጫውን ትርጉም ለማሳጣት እየሠሩ ነው።
በአንድ በኩል የምርጫው ባለቤት እኛ በሆንበትና የምርጫውን ትሩፋት ከማንም በላይ ለኛ በሆነበት የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሆነን በምንገኝበት በዚህ ወቅት ከምርጫው ከኛ በላይ ባለቤት ለመሆን የሚሞክሩ፣ ይህንንም ለኛ ሊነግሩን የሚፈልጉ አሉ። ለዚህም ደግሞ የአውሮፓ ህብረት እየሄደበት ያለው ያልተገባ መንገድ ተጠቃሽ ነው።
ህብረቱ የሚታዘበው የሉዓላዊ ሀገር ምርጫ መሆኑንና ምርጫው የሚካሄደው የኢትዮጵያ ህዝብ ከምርጫው አተርፋለሁ በሚል ተስፋ ብዙ ተስፋዎችን ሰንቆ መሆኑን በአግባቡ የተረዳው አይመስልም። ህብረቱ በምንም መመዘኛ በምርጫው ጉዳይ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ሊሆን አይችልም። ነኝ ብሎ የሚያስብ ከሆነም የምርጫው ባለቤት የሆነውን ህዝብ እንደማሳነስ ይቆጠራል።
ይህ የህዝባችንን ስነልቦና የተዋቀረበትን ውቅር በአግባቡ ካለመረዳት ወይም ተረድቻለሁ ብሎ ከመሳሳት የመነጨ መሳት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ምርጫችንን ታዘቡልን ያልነው ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል በቂ ማህበራዊ መሰረት ያለን መሆኑን ዓለም አቀፉ ህብረተስብ እንዲረዳው ነው። ከዚህ ውጪ በሉአላዊነታችን ላይ ለመደራደርና ሉአላዊነታችንን በምርጫ ስም ለማስደፈር አይደለም። ይህንን የቀደመውም ሆነ የአሁን ማንነታችን አይፈቅድልንም።
የአውሮፓ ህብረት የትላልቅ ሀገራት ህዝቦችን የሚወክልና የሀገር ሉአላዊነት ምን እንደሆነና የቱን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ እንደሚያስከፍል በተጨባጭ ታሪኮቻችው ያስተዋሉ ህዝቦች ህብረት ነው።
ከዚህ አንጻር ህብረቱ ለሀገር ሉአላዊነት ተገቢውን ክብር ሊሰጥ ይገባል። የህዝባችንን ሉአላዊነት ከሚፈታተን መንገድ ወጥቶም በተጋባዥ እንግድነት ምርጫውን መታዘብ የሚያስችል የተስተካካለ ቁመና ሊኖረው ይገባል። ከዚህ ውጪ የምርጫው ባለቤት ለመሆን የሄደበት መንገድ የሚወክለውን ህዝብ ማህበረሰባዊ ስነልቦና የሚወክል አይደለም፤ የህግም ሆነ የሞራል መሰረት የለውም። ምርጫ የምናካሄደው የአውሮፓን ህብረት ለማስደሰት ሳይሆን የህዝባችን ፍላጎትና የመሻገሪያ መንገዳችን ስለሆነ ብቻ መሆኑ ሊታወቅም ይገባል !
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013