ለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ከሆኑት ምግብ፣ መጠጥና ልብስ ቀጥሎ መጠለያ ወይም ጎጆ አንዱ ነው:: በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች ረዘም ያለ ጊዜያቸውን ከቤታቸው ውጭ የሚያሳልፉ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ…ኖሮ ከመሬት እንዲሉ የሰው ልጅ ሁሉ ውሎ የሚገባበት እንዲሁም ቤተሰቡን እና በገጠሩ አካባቢ ደግሞ እንስሳቱን ጭምር ሰብስቦ የሚያርፍበት መኖሪያ ጎጆው ነው:: የሰዎች መኖሪያ ጎጆ አሰራር ደግሞ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ ከመሆኑም በላይ የግለሰቦች አቅም የሚታይበትም ይሆናል:: በመሆኑም ሰዎች ያላቸውን አቅምና ፍላጎት መሰረት በማድረግ መኖሪያቸውን ከሳር ቤት እስከ ቅንጡ ህንጻ ይገነባሉ::
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ እንደመሆኗ የበርካታ ባህል ባለቤት ናት:: ከዘርፈ ብዙ ባህሎቿ መካከልም የቤት አሰራር ባህል አንዱ ነው:: በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባህላዊ የመኖሪያ ቤት አሰራሮች አሉ:: በሁሉም አካባቢዎች የሚታዩት የመኖሪያ ቤት አይነቶች እንደየአካባቢው ባህልና ወግ የሚለያይ ሲሆን፤ ለቤት መስሪያነት የሚጠቀሙት ግብዓትም በየአካባቢው ይለያያል:: ለአብነትም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ትግራይ አካባቢ ድንጋያማ በመሆኑ ይመስላል ቤቶቹ በሙሉ ድንጋይ ቀመስ ናቸው:: በደቡብ ክልል አካባቢ የሳር ክዳን ያላቸው የጎጆ ቤቶች የተለመዱና የአካባቢው መገለጫዎች ናቸው:: በዛሬው የጎጆ አምዳችንም የሀድያ ዞን ባህላዊ የቤት አሰራር ምን እንደሚመስል ለመዳሰስ ሞክረናል::
የሀድያ ዞን የቱሪስት መስህቦች ጥናት፣ ልማትና ግብይት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መኮሮ ኤሮሴ የሀድያ የቤት አሰራርን አጋርተውናል፤ ፌንጋሞና ሁጉሞ የሚባሉ ሁለት አይነት የሀድያ ባህላዊ ቤት አሰራሮች አሉ:: ይሁንና ሁጉሞ የሚባለው የቤት አሰራራ በአሁኑ ወቅት እየቀረ የመጣው ነው:: አሰራሩም እንደማንኛውም የሳር ቤት ምሰሶ ይኖረዋል:: ጣራው ከምሰሶ ጫፍ እስከ መሬት ጫፍ የሚገጥምና ሳር የሚከደነውም ሙሉ ለሙሉ ከመሬት ጫፍ እስከ ዋልታው ድረስ ነው:: የቤቱ ስፋት ከአምስት እስከ ሰባት ክንድ ተኩል የሆነና ግድግዳው በፍልጥ የሚሸፈን ይሆናል::
ግድግዳውን ለመሸፈንም ካለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በፊት አገር በቀል የሆኑ ወይራ፣ ጥድ፣ ዝግባ፣ ቀረሮና መሰል እንጨቶችን በመጠቀም ግድግዳውን ይሸፍኑ ነበር:: ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እነዚህ አገር በቀል የሆኑ ዛፎች በመጥፋታቸው ምክንያት በባህር ዛፍ ፍልጥ ግድግዳው ይሰራል:: ማገር ይኖረዋል:: ከማገሩ ላይም ጭቃ በመለጠፍ ይሰራል:: ቤቱ ከኋላ በኩል በር መውጫ አይኖረውም:: መግቢያም ሆነ መውጫ ከፊት ለፊት ባለው አንድ በር ብቻ ነው::
በቤቱ ግድግዳ ላይ የተለያዩ ባህላዊ የሆኑ ጌጣጌጦች ይሰራሉ:: በተለይም ለዕቃ ማስቀመጫ የሚያገለግል በሀዲያ ‹‹ኮዶዶ›› የሚባለው መደርደሪ መሰል ይሰራለታል:: በጣም የሰለጠኑት ደግሞ ተጨማሪ ጭቃ በማድረግ መደርደሪያ ይሰሩለታል:: የሀድያ ቤት አንዱ ብቻ ክፍል ሲኖረው ሌሎች አራት ክፍት ቦታዎች የሚኖሩት ይሆናል:: አንደኛው በሀዲያ ‹‹ጋድራ›› የሚባለው የከብቶች ማደሪያ ጋጣ ይሰራል:: ይህ የከብቶች ማደሪያ በእንጨት ተከልሎ ለከብቶች ማደሪያ ይሆናል:: ሁለተኛው ገጣ ወይም ወለል ሲሆን፤ ለእንግዳ መቀበያ የሚያገለግል ነው:: ሶስተኛው ጉለንታ ወይም የመኝታ አካባቢ ይሆናል:: አራተኛው ከምሰሶው ወደ ውስጥ ገባ ብሎ የሚገኘው ዱማ ወይንም ዕቃ ማስቀመጫ ነው:: ይህ ቦታ በተለይም የእናቶች ቦታ ሲሆን፤ እናቶች ቂቤን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ግብዓቶችን በትርፍ የሚያስቀምጡበት ቦታ ነው::
በዞኑ በአሁኑ ወቅት እንዲህ ያለው ባህላዊ የቤት አሰራር እየቀረ የመጣ ነው:: ምክንያቱም ከመሬት ጀምሮ እስከ ላይ ምሰሶ ወይም ጉልላቱ ጫፍ ድረስ በሳር የሚሸፈን በመሆኑ፤ ከኋላ በኩል መውጫ በር የሌለው በመሆኑ ለአደጋ የተጋለጠ ነው:: ከዚህም ባለፈ በአካባቢው ለቤቱ ክዳን የሚፈለገው ሳር እየጠፋ የመጣና ውበቱም ቢሆን ያን ያህል አስደሳች ባለመሆኑ ይህ አይነቱ ባህላዊ የቤት አሰራር በሀድያ ዞን እየቀረ ይገኛል::
አሁን ላይ በደቡብ ክልል የሚገኙ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀድያና ከንባታ ላይ የሚሰሩት ባህላዊ ቤቶች ‹‹ፌንጋሞ›› የሚባለው ተቀራራቢና ተመሳሳይነት ያላቸው የቤት አሰራሮች ናቸው:: ፌንጋሞ ባህላዊ ቤት በሀድያ ዞን የሚሰራው በአካባቢው በሚገኙ የዛፍ አይነቶች ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ቀይ እና ጥቁር ባህር ዛፍ በተባሉት የዛፍ አይነቶች ይሰራል:: ቤቱ ከውጭ በኩል ግድግዳው በማገር ግጥም ተደርጎ የሚሰራ ሲሆን፤ ለግድግዳው ቀርከሃ ይመረጣል:: ነገር ግን ቀርከሃ በአሁኑ ወቅት የማይገኝ በመሆኑ ባህር ዛፍን በጌጠኛ ተበጅቶ ይሰራበታል:: የቤቱ ጣራ መሬት የማይደርስና በታዛ ወደ ላይ የሚቀር ሲሆን፤ ከኋላና ከፊት ሁለት በሮች አሉት።
በአብዛኛው የፌንጋሞ ቤት ስፋት ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ክንድ የሆነ ሰፊ ቤት ነው:: እንደ ቤቱ ስፋት አንድ ወይም ሁለት መደገፊያ ይፈልጋል:: ጣሪያው በአጠና በጥሩ ሁኔታ ይሰገሰጋል:: አከዳደኑም በሰንበሌጥ ሆኖ በሚያምር መልኩ ጌጠኛ ይሆናል:: ይኼኛውም ልክ እየቀረ እንደመጣው ‹‹ሁጉሞ›› የቤት አሰራር ሁሉ ጉለንታ የመኝታ አካባቢ፣ የሳሎን ቦታ፣ የከብቶች ጋጣ፣ ጓዳ አለው። ጓዳው ወደ ኋላ ወይም ለጓሮ በር የተጠጋ ይሆናል:: በጓሮ በር ኪስ ቤት የሚደገፍለት ሲሆን፤ ከፊት ለፊት ደግሞ እልፍኝ ይኖረዋል:: ይህም በአካባቢው አጠራር ‹‹ጎያ ጀገራ›› ይባላል:: ጎያ የሚባለው ትልቁ ቤት ሲሆን፤ ጀገራ ማለት ደግሞ እልፍኝ የሚባለው ነው::
የውስጥ ጌጦቹም ልክ እንደ ሁጉማ ቤት አሰራር ሁሉ ጓዳው አካባቢ ለዕቃ ማስቀመጫ መደርደሪያ ይሰራለታል:: ምሰሶው አካባቢም ምድጃ ይኖረዋል:: ከኋላ በኩል ባለው በር አካባቢም አነስተኛ ለሆኑ በግ ፍየልና ጥጃ ለመሳሰሉት እንስሳት ማደሪያ ጉሮኖ ይኖረዋል:: የፈረስ፣ የበቅሎና የከብቶቸ ቤት ይኖረዋል:: ቤት ሲባልም እዚያው ጋጣ ውስጥ ሆኖ ክፍል በክፍል የተለየለት እንደማለት ነው:: ከዚህ በተጨማሪም እንደ መጋዘን የሚያገለግሉ ሶስት ቆጦች ይሰሩለታል::
አንደኛውና ከጋጣው በላይ የሚሰራው ቆጥ ማገዶን ጨምሮ የተለየዩ ቁሳቁሶች ይቀመጡበታል:: ሁለተኛው ጓዳ ተብሎ በሚጠራበት አካባቢ የሚሰራ ቆጥ ሲሆን፤ በዚህ ቦታ ላይ ቅቤን ጨምሮ እናቶች የሚፈልጉትን በሙሉ የሚያስቀምጡበትና የእናቶች ቦታ ተብሎ ይለያል:: ሶስተኛው ቆጥ ከምድጃ በላይ የሚሰራ ሆኖ እንዲደርቁ የሚፈለጉ ቁሳቁሶች የሚቀመጡበት ይሆናል:: ለአብነትም የበልግ ሰብሎች፣ እንዳይበላሹ የሚፈለጉና በቶሎ እንዲደርቁ የሚፈለጉ ነገሮች በዚህ አካባቢ በሚገኝ ቆጥ ላይ ይቀመጣሉ::
በመኝታ አካባቢም እንዲሁ ባለ ብዙ ባላ እንጨት በራስጌ እና በግርጌ በኩል የሚቀመጥ ይሆናል:: በራስጌ ባለው ባለብዙ ባላ እንጨት ላይም ኮርቻና የኮርቻ ዕቃዎች ተሰቅለው ይቀመጣሉ:: ወደ ሳሎኑ ወገን ባለው ጠርዝ ላይ በሚገኝ ባለ ብዙ ባላ እንጨት ላይ ደግሞ ቶሎ…ቶሎ የሚፈለጉ አልባሳትና የጌጥ ዕቃዎች ይሰቀላሉ:: ብርቱ ሰው ከሆነ ተጨማሪ ሶስት እና አራት ባላ ያለውን ከወይራና ከጥድ የተገኙ እንጨት አስቀምጦ እንደ ወጪት ያላ የጭኮ ማስቀመጫ ዕቃ ያስቀምጥበትና ይፎከርበታል:: ፉከራውም ለጌታው ሲሆን፤ ጭኮው ሳይበላ ላይ በላይ እየተሰራ የሚቀመጥለት መሆኑን ይገልጻል::
የቤቱ መዝጊያ የሚሆነውም ሁለት አይነት ሲሆን፤ እንደ አቅም የሚለያይ ነው:: አንደኛው ከሀረግና ከሰንሰል በእጅ የሚሰራ ሲሆን፤ መዝጊያ ወይም ጡፋ ይባላል:: ሁለተኛው ጣውላ ተሰንጥቆ የሚሰራ መዝጊያ ሲሆን፤ ባህላዊ በሆነ መንገድ ይገጠማል:: ሀድያ በቆላ፣ በደጋና በወይናደጋ ይኖራል:: በደጋ የሚኖሩት ከዋናው መዝጊያ በተጨማሪ በውጭ በኩል ወደ ውስጥ የሚዘጋ ግማሽ መዝጊያ የሚገጥሙ እንደሆነ አቶ መኮሮ አስረድተዋል:: ይህ በትልቁ ቤት ወይም በዋናው ቤት የሚሰራ ይሆናል::
አንድ የሀድያ አባወራ በርካታ ከብቶች ካሉት ከቤቱ ጋር በረት አይሰራም:: ከዋናው ቤት ትንሽ ወጣ አድርጎ አነስተኛ ጎጆ ወይም ክፍት በረት ይሰራል:: ይህም በሀድያ “ሆት ሚሌ” ይባላል:: አንድ አባወራ በርካታ ከብቶች ካለውና “ፌንጋሞ” ቤት ከሰራ አንደኛ ከደጁ እልፍኝ ይኖረዋል:: ሁለተኛ “ሆያ” የሚባለው ትልቁ ቤት አለው:: ሶስተኛ የጭስ ቤት ይሰራል:: አራተኛ የከብቶች በረት ይኖረዋል::
በሀድያ አካባቢ የከብቶች ቤት ለብቻ ለመስራት የከብቶቹ ቁጥር ከ60 እስከ 70 የሚደርሱ ከሆነ ከዋናው ቤት ውጭ በተሰራ የከብቶች ቤት ወይም በረት እንዲያሳድር ይመከራል:: እንደ አካባቢው ዕምነት ደግሞ ከብቶች ከዋክብትን ሲያዩ ይባዛሉ ተብሎ የሚታመን መሆኑን ያነሱት አቶ መኮሮ፤ ለዚህም ሲባል እስከ 40 ከብቶች ያሏቸው ግለሰቦች ጭምር ከብቶቻቸውን በረት ማሳደር ይመርጣሉ:: ከ40 በታች ከብቶች ያሏቸው ግን በቤት ውስጥ በሚሰራ ጋጣ ውስጥ ያሳድራሉ::
ወጣቶች በቤት ውስጥ ካሉ እንዲሁም ቤተሰቡ እንግዳ የሚበዛበትና አቅም ያላቸው ከሆነ ከዋናው ቤት በተጨማሪ እልፍኝ ይሰራል:: የጢስ ቤት ለብቻ መስራት ግን አሁን…አሁን የግድ እየሆነ መጥቷል:: በተለይም እንሰት አብቃይ በሆኑ ወይናደጋ እና ደጋ አካባቢዎች ግን እልፍኝና ጢስ ቤት ይለያል:: ይህ የሚሆነውም አባወራው ወደ ቤቱ የሚመጣበትን እንግዳውን በእልፍኝ ሲያሳድር ክብር ስለሚሰማውና በጢስ ቤቱ ደግሞ ምግብ ብቻ አብስሎ ለማቅረብ ይጠቀምበታል::
በሀድያ አካባቢ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ባህላዊ የቤት አሰራር በአሁኑ ወቅት በሁለት አስገዳጅ ምክንያቶች እየቀረ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ መኮሮ፤ በዋናነት ለቤቱ ክዳን የሚያገለግሉ ሁለት አይነት ሳሮች አሉ እነሱ ሳሮች ከአካባቢው እየጠፉ ይገኛሉ:: ከዚህ የተነሳ በሳር ፋንታ ገለባ በመሸፈን ለመስራት እየተሞከረ ነው:: ወጪውን በተመለከተም ለሳር ቤት ክዳን ብቻ የሚወጣው ወጪ ግድግዳውን ሳይጨምር ቆርቆሮ ቤት እየሰራ ይገኛል:: ስለዚህ በአካባቢው ቆርቆሮ ቤቶች እየተበራከቱ ነው::
ይሁንና የሀድያ ማህበረሰብ ቤት ሰራሁ ብሎ የሚለውና በሰራው ቤት የሚኮራው ባህላዊ የሆነውን የሳር ቤት ሲሰራ ነው:: ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ሳይወድ በግዱ በአስገዳጅ ሁኔታ ቆርቆሮ ቤት ይሰራል:: ይህም ካለው የገንዘብ አቅም ጋር የሚያያዝ ነው:: ይህም ማለት አንድ ባህላዊ የሳር ቤት በሚሰራበት ገንዘብ ሶስት የቆርቆሮ ቤቶችን መስራት ይቻላል:: በዚህ ምክንያትም በአካባቢው ከባህላዊ ጎጆ ቤቶች ይልቅ የቆርቆሮ ቤቶች እየተበራከቱ መጥተዋል::
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013