ለክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ:: የሰሞንኛው ሰላምታችን መነሻውም መድረሻውም መልካም የበዓል ምኞት መግለጥ ስለሆነ እኔም እድሌን ልጠቀም::
የጽሁፉን መንደርደሪያ በአባትና ልጅ መካከል የሆነን ታሪክ አድርገናል:: በልጁ ውስጥ በአባትነት ያልተገኘው ሰው የገባበት ሃዘንና የሄደበት የመፍትሄ መንገድ:: ታሪኩ እንዲህ ነው:: አባት በሥራ ጉዳይ ኑሮውን ያደረገው ከቤተሰቡ ርቆ ነው:: እንደ ሰሞኑ አይነት በዓላት በመጡ ቁጥር አቅሙ የፈቀደውን ይዞ ከቤቱ ይደርሳል:: የገዛ ልጁ ለበዓል መጥቶ የሚሄደውን ሰው እንደ አባት የሚያይበት እይታን ግን ፈጽሞውኑ አላገኘም ነበር::
በአንድ በዓል አባት በግ ይዞ ሲመጣ ልጅ በረንዳ ላይ እየተጫወተ ነው:: ልጅም ለበዓል ከቤታቸው በግ ይዞ የሚመጣውን ሰው ይመለከትና ወሬውን ለእናቱ ለመንገር ወደ ቤት እየሮጠ ሄዶ እናቱን “እማ እማ ለበዓል የሚመጣው ሰውዬ በግ ይዞ እየመጣ ነው::” ይላታል:: እናት በልጇ ስለ አባቱ ባለው ግንዛቤ ላይ ደንግጣ ለባሏ ትነግረዋለች::
አባትም ልጁ የተናገረውን ከሚስቱ በሰማ ጊዜ ስሜቱ ይጎዳል:: “ለካንስ ለልጄ አባት አይደለሁም፤ የበዓል ሰሞን የሚመጣ አንድ ተራ ሰው ነኝ::” ሲል ከራሱ ጋር ይሟገታል፤ ራሱንም በልጁ ውስጥ የሞተ በድን አድርጎ ይቆጥረዋል:: ይህ ሰው በልጁ ውስጥ የሞተውን አባት በማስነሳት ለልጄ አባት ካልሆንኩ ሥራዬ ለምኔ ብሎ፤ ስራውን ለቆ ከቤተሰቡ ጋር መሆን እንዳለበት ይወስናል፤ በተግባርም ያደርገዋል::
ይህ ታሪክ እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ ከነገረኝ ሰው ለመረዳት ችያለሁ:: አባት የሆነ ሰው በልጆቹ እንዲህ ቢባል ሊሰማው የሚችለውን ስሜት በውስጣችን ይዘን አብረን እንቆዝም:: በልጆቹ ልብ ውስጥ በህያውነት የሌለ አባት ምን ሊሰማው ይችላል? ይህ አባት በበዓሉ ዋዜማ የቆየበትን ስሜት፣ የበዓል ቀኑን ስሜት እና ከበዓሉ ማግስት የወሰነውን ውሳኔ በውስጣችን እያብላላን ከመቃብር ወጥቶ ትንሣኤን ለማየት በብዙ መንገድ መረዳት እንደሚቻል እያሰብን እንዝለቅ::
የአባት የበዓል ዋዜማው ቀን ማለትም በግ እየጎተተ የመጣበት ቀን የደስታው ቀን አልነበረም፤ ልጁን ፍለጋ የባዘነበት ዋዜማ ልንለው ግን እንችላለን:: ለዚህ አባት የፋሲካው በዓል የትንሣኤው ጉዳይ በልጁ ውስጥ አባት ሆኖ መገኘት ነውና፤ እዚያ ላይ መድረስ ሲችል ትንሣኤ ሆነልኝ ሊል ይችላል:: አባት ሆኖ በልጁ ውስጥ እንደሚገኝና ትንሣኤ እንዲሆንለት ሊወስነው የሚገባውን ነገር ወስኖ ትንሣኤውን ሲያገኝ የሚቀጥለው ነገር ትንሣኤውን መጠበቅ ነው፤ የትንሣኤው ማግስት ማሳያ አድርገን ልንወስደው እንችላለን::
በእያንዳንዳችን የህይወት መንገድ ላይ ጥብቅ ውሳኔያችንን የሚፈልጉ ነገሮች መከሰታቸው ልክ አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ይሆናል እንደምንለው የሂሳብ ስሌት ቀላል ነው:: ትንሣኤ እንዲሆን በምንፈልግበት ነገር ላይ በጥሞና ጊዜ መውሰድ እንድንችል መሆን እንደመታደል ይቆጠራል:: አባት በልጁ ውስጥ ያለውን መልክ ወስዶ ማስተካከል እንዲችል ያቺ ቅጽበታዊ ሁኔታ ትርጉሟ ብዙ ነው፤ የትንሣኤ ዋዜማዋ::
ዛሬ ስለ ትንሣኤ ዋዜማ ጥቂት እናነሳለን፤ ስለ ትንሣኤ እለትም እንዲሁ በጥቂቱ እናነሳለን ነገርግን ስለ ትንሣኤ ማግስት በስፋት እንዘልቀዋለን:: መዳረሻ ሃሳባችንም በሥኬት ከመውደቅ ራሳችንን ለመጠበቅ ስኬትን መጠበቅ ወይንም ትንሳኤን መጠበቅ አድርገን እናቀርበዋለን:: የትንሣኤ ማግስት ትልቁ ስራ ትንሣኤን መጠበቅ ነውና፤ ለብዙዎች ታላቅ ፈተና ሆኖ ዳግም ወደ መቃብር እንዲወርዱ ምክንያት የሆነ::
የትንሣኤ ዋዜማ
የትንሣኤ ዋዜማን በምን እንመስለው? እንዴትስ እንግለጸው? ትንሣኤ የሆነበት ጉዳይ ወደ መቃብር የወሰደን በራሳችን ችግር ወይንስ ስለእውነት ባለን አቋም የሚለውም የትንሣኤ ዋዜማ ትርጉማችንን ሊወስን ይችል ይሆናል:: ለዛሬው ስለ እውነት ብለን ይሁን ወይንም በራሳችን ጥፋት ያለንበትን የመቃብር ኑሮ የሚያሳየውን ወይንም ትንሣኤ የሚሻውን ሁሉ አንድ ላይ እንመልከት:: ዋናው ነጥባችን ድል በምንፈልግበት ጉዳይ ላይ የምንፈልገውን ድል ባገኘን ጊዜ ልንኖረው የተገባውን ኑሮ በትንሣኤ ማግስትነት ማንሳት ስለሆነ:: ስለዚህ የትንሣኤ ዋዜማን በምን እንመስለው? እንዴትስ እንግለጸው?
የትንሣኤ ዋዜማ በመቃብር ውስጥ ያለ ህይወት ማሳያ ተብሎ ሊቀርብ ይችል ይሆናል:: ትንሣኤ ትርጉም የሚኖረው አስቀድሞ በመቃብር ውስጥ መሆንን የሚጠይቅ ስለሆነ የሚል አመክንዮም ሊቀርብበት ይችላል:: እውነታው ግን እርሱ አይደለም:: በመቃብር ውስጥ መኖር ብቻውን የትንሣኤ ዋዜማ ማሳያ አይደለም:: በመቃብር ውስጥ ያሉ በሙሉ ትንሣኤ ላይ ሊደርሱ አይችሉምና:: የትንሣኤ ዋዜማ ትክክለኛው ትርጉም በመቃብር ውስጥ ከመሆን ባሻገር ትንሣኤ እንዳለ በማመን ውስጥ የሚገለጽ ስለሆነ::
በህይወት ጉዞ ውስጥ ፈተና የሚጠበቅ ነው:: በተመሳሳይ ፈተና ውስጥ የሚያልፉ ሁለት ሰዎች ቢኖሩ ሁለቱ ግለሰቦች ፈተናውን በሚያስተናግዱበት አቅም ግን ይለያያሉ:: ፈተናውን ተሻግሮ ተስፋን ማየት ውስጥ የሚገኘው አቅም ደግሞ ዋናው ልዩነት መፍጠሪያ ነው:: አንዱ ሰው ከፈተናው ባሻገር ትንሣኤ ሊኖር እንደሚችል ሲያምን፤ ሌላው ሰው ግን ለፈተናው በመረታት ከፈተናው ባሻገር ትንሣኤ እንዳለ ማየት ሳይችል ቀርቶ ፈተናው አብሮት የሚኖር አድርጎ ይቀበላል::
በምሽግ ውስጥ ያለ ወታደርን እናስብ:: ወታደሩ ምሽግ ውስጥ የመግባት ምክንያቱ ምሽግ ከሞት እንዲጠብቀው በማመን ነው:: ምሽጉ ለወታደር የዘለቄታው ቤት ግን አይደለም:: ምሽጉ የቤት ቁጥር የተሰጠው የአድራሻው መገለጫም አይደለም:: ምሽግ ውስጥ ሆኖ ለውጊያ ዝግጁ መሆኑ ተስፋ በሚለው አጥር ውስጥ መሆኑን ከውጌያው ድልን አሳቢ መሆኑን ያሳያል:: የትንሣኤ ዋዜማ ላይ ያለም ሰው እንዲሁ ነው፤ ከምሽጉ አሻግሮ የድል ጮራ ሊኖር እንደሚችል ማመን፤ ድልን ከሚያበስሩት መካከል እንደ አንዱ ለመቆም ተስፋን መሰነቅ::
እንደ አገር ያለንበት ሁኔታ በብዙ ጨለማ የሚመሰል ነው:: ከአገር መለስ በቤተሰብ ደረጃ የምናልፍበት ህይወት እንዲሁ በመቃብር ውስጥ ህይወት ይገለጥም ይሆናል:: የግል ህይወታችንን ስንመረምር እንዲሁ የምናልፍበት ነገር የማያስደስት ሊሆን ይችላል:: የእምነት ሰዎች እርምጃ ግን ለጨለማ እጅ መስጠት ሳይሆን ከጨለማው ማዶ ብርሃን ሊኖር እንደሚችል በማየት አቅም ውስጥ የሚገለጽ ነው:: በትንሣኤ ዋዜማ ላይ እንዳሉ የምናስባቸው ሰዎች ከጨለማው ማዶ ማየት የቻሉ መሆናቸው ለዚሁ ነው:: በፖለቲካው፣ በአኪኖሚው እንዲሁም በማህበራዊው እንቅስቃሴያችን የትንሣኤ ዋዜማ ቁመናችን የግድ ነው::
በመነሻችን ላይ ያነሳነው ታሪክ ይህን እውነት በሚገባ ያሳየናል:: በልጁ ውስጥ አባትነት እንዲሳል አባት ከተሰበረ ልቡ ውስጥ አሻግሮ የተመለከተው ብርሃን አለ:: ዛሬ ልጅ አለኝ ቢልም በተጨባጭ ግን ልጅ እንደሌለው ደምድሟል:: ነገርግን ከውሳኔው ባሻገር ይህ ልብ ሊቀየር እንደሚችል እምነት አድርጎል:: በስብራት ውስጥ ካለው ልብ ውስጥ ወደ ፊት መራመድ ያለበትን በውሳኔው ውስጥ አድርጓል:: ውሳኔውም ትንሣኤን ፍለጋ የሆነ ሊባል ይችላል::
በትንሣኤ ዋዜማ ያለ አንባቢ፤ ዛሬ ያለበት ምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን የማበረታቻ ቃሌ ይህ ነው፤ ትንሣኤ አለ:: ትንሣኤውን ለማየት ግን በዋዜማው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሳለን ትንሣኤ እንዳለ ማመንን ይጠይቃል:: አምኖ መራመድን! እምነት ማለት በዛሬ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ የማይታይ ነገርግን ከዛሬ ወደፊት አሻግረን የምንመለከተው ነውና::
ዙሪያችንን ለማየት ስንሞክር የልብ ስብራት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ ነገሮችን እናያለን:: እኒህን አያሌ የችግር አይነቶች ደርድሮ መውጣት እንደማይቻል ለራስ ከመናገር መፍትሄው ትንሣኤ እንዳለ በመመልከት ውስጥ አቅምን ማበርታት ነው:: የትንሣኤው ዋዜማ ገጽታን ግን ፈጽሞውኑ መዘንጋት አይገባም:: የትንሣኤ ዋዜማ ትርጉምም ከፈተናው ማዶ ድል እንዳለ ማመን እንደሆነ መረዳትም እንዲሁ::
የትንሣኤ እለት
ሰውዬው በግ ይዞ እየመጣ ነው የሚለውን መልእክት ለመናገር ወደ እናቱ የሮጠው ብላቴና ታሪክ ተቀይሮ አባቱ ሲመጣ ሮጦ አባዬ ብሎ በአባቱ ላይ ሲጠመጠም ያኔ በአባት ልብ ውስጥ የትንሣኤ ደስታ ይሆናል:: በልጅ ውስጥ ሙት የነበረው አባት ዛሬ ህይወትን አግኝቶ ተነስቷልና:: ይህ ቀን የደስታ ቀን ነው:: በትንሣኤ እለት ፊቱ በብርሃን ያልተሞላ ሰውን ማየት አይቻልም:: በድል እለት፤ በስኬት ምእራፍ፣ ከጭንቅ በመውጣት ቅጽበት፣ የመጨረሻውን የማሸነፊያ ገመድ አልፎ በመግባት ውስጥ ወዘተ ታላቅ የደስታ ህይወት አለ::
ህይወት ውስጥ ሁሌም አንገት መድፋት የለም፤ አንገት ቀና የሚልበት ጊዜም አለ:: በህይወት ውስጥ ሁሌም ፈተና የለም፤ ፈተናው በድል ተሸንፎ እፎይ የሚባልበት ወቅትም አለ:: ጠቢቡ “ለሁሉም ጊዜ አለው” ማለቱን ልብ ይሏል:: የትንሣኤ እለት ልዩ እለት ነው፤ የተረጋገጠ አሸናፊነት እለት:: በሞት ላይ ድል ማድረግ የሆነበት እለት:: ከመቃብር ወጥቶ በሙላት የመታያ እለት::
የትንሣኤ እለት እንዳለ አምኖ ዋዜማውን የኖረ ሰው እለቷን እንደጠበቃት ስላገኛት ስለ እምነቱ ሃሴትን ያደርጋል:: ኢትዮጵያ ትንሳኤን ትሻለች የሚለው ለሁሉም የሚያስማማ ቢሆንም የትንሣኤው ቀን ይመጣል በአይኔም አያለሁ የሚለው እምነት ግን አንዳችንን ከሌላችን የሚለይ ነው:: እነሆ የምስራች የትንሣኤ ቀን አለ! በግል ሕይወት፣ በትዳር፣ በቤተሰብ እንዲሁም በአገር ከጨለማው ባሻገር ብርሃን እንዳለ በማመን ጉዞን ለሚያደርጉ ሰዎች የትንሣኤ እለት የሚባል እለት አለ:: በብዙ አቅጣጫ ዛሬ በትንሣኤ እለቴ ላይ እገኛለሁ ለምትሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ:: አጠገባችሁ ያሉ የትንሣኤ እለት ለራቀባቸው የምስራች ነጋሪ ትሆኑ ዘንድ ምክሬ ነው:: ዛሬ በኑሮ ውድነት፣ ዛሬ በፖለቲካ ቀውስ፣ ዛሬ በቤተሰብ መናጋት ወዘተ አንገታቸውን ደፍተው የማዶውን ማየት ለተሳናቸው የእናንተ ምስክርነት ወሳኝነት አለው:: በትንሣኤ ዋዜማ ላይ ላሉት በዋዜማ ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ ከመቃብሩ ማዶ ትንሳኤ እንዳለ የሚያሳይ ምስክርነት አስፈላጊ ነው::
የትንሣኤው ዋዜማ ትርጉም ትልቅ ቢሆንም፤ የትንሣኤው እለትም እንዲሁ ትርጉሙ የጎላ ቢሆንም የትንሣኤው ማግስት ግን የዛሬው ዋና መልእክታችን ነው::
የትንሣኤ ማግስት
የትንሣኤ ማግስትንም እንዴት እንየው? የሚለው ጥያቄ አሁንም ሊነሳ ይገባዋል:: በትንሣኤ ዋዜማ ላይ አሻግረን ባየነው የትንሣኤ እለት ተለይተን፣ ያየነውን መጨበጥ ችለን ወደፊት ስንራመድ የትንሣኤው ማግስት ጋር እንደርሳለን::
የትንሣኤውን ማግስት ስናስብ በጥሞና ልናስባቸው የሚገቡ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች አሉ:: ካለፈው የተማርነው ትምህርትና በቀጣይ የምንራመደው የተግባር እርምጃ፣
የጉዞው ትምህርት፡-
የትንሣኤ ማግስት የጉዞው ትምህርት ተሰርቶ የተጠናቀቀበት ነው:: በፈተናው ውስጥ ስናልፍ ከምናልፍበት ሁኔታ ውስጥ የሚቀዳ ትምህርት አለ:: የትንሣኤው እለት ውስጥ ሊቀመር የሚችል እንዲሁ ትምህርት አለ:: ንድፈ-ሃሳባዊ የሆነ ትምህርት ብቻ ሳይሆን የተግባር ትምህርት መሆኑ ደግሞ ልዩ የሚያደርገው:: በቀለም ትምህርት በብዙ ምእራፎች በሚገለጽ ደረጃ ላይ ደርሰው ከህይወት ትምህርትቤት ያልተማሩ ነገሮችን ሲያበላሹ ብናይ ልንገረም አይገባም:: በፈተና ውስጥ የሚጸኑ እነርሱ ትልቅ ትምህርትቤት ናቸው:: በፈተና ውስጥ ጸንተው ለውጤት ደርሰው ከንጋታቸው ማግስት አንዳች ቢገኝባቸው ብላችሁ ከደጃፋቸው ከደረሳችሁ ባዶእጃችሁን እንደማትመለሱ እርግጠኛ ሁኑ፤ ምክንያቱም ትምህርት ላይ ደርሰዋልና::
የትንሣኤ ማግስት በትምህርትቤትነት መመሰሉ ለአንባቢው ግልጽ ይመስላል:: አንድ ጥያቄ ግን እንጠይቅ ከትላንት የፈተና ምእራፍ፣ የትንሣኤ ዋዜማና የትንሣኤ ወቅት መማር ያልቻለን ሰው እንዴት እንመልከተው? ይህ ጥያቄ የትንሣኤው ማግስት ሁለተኛውን ቁልፍ እንድናገኝ ይረዳናል::
የቀጣዩ ጉዞ ተግባር ተኮርነት፡-
በአገራችን ብሂል “አድሮ ቃሪያ” የሚባል አባባል አለ:: ይበስላል ሲባል ነገር እዚያው ባለበት አመታትን የሚረግጥ ሲሆን አድሮ ቃሪያ እንለዋለን:: አድሮ ቃሪያ በሕይወት ጉዞ ውስጥ የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ ነው:: አድሮ ቃሪያነት ፍጹም ተገቢ አይደለም:: በስህተት ውስጥ አልፎ መማር እንዳይሆን ትላንት በመንገዱ ከሄዱ ሰዎች መማር መቻል ብልህነት ነው:: ነገር ግን ራስ በመንገዱ ሄዶ በሚገኝ ትምህርት አለመማር ግን ፍጹም ተቀባይነት የለውም::
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት እንደ እርግብ የዋህ እንደ እባብም ብልህ መሆን ሳንችል ቀርተን መክፈል የሌለብንን ዋጋ ከፍለን ትንሣኤ ሆኖልን ከጨለማው መውጣት ከሆነልን በኋላ በተመሳሳይ ችግር አዙሪት ውስጥ የምንገኝ ከሆነ ችግሩን ምን እንበለው? በመቃብር መገኘታችን ምክንያቱ የእኛ ጥፋት ይሁን ስለ እውነት መቆማችን ትንሣኤ ላይ መድረስ ችለን ከትንሣኤ ማግስት ግን በትላንቱ ጉዞ ላይ ትምህርት መውሰድ ካልቻልን ችግሩ የራሳችን ነው::
የትንሣኤ ማግስት ትምህርትቤት ነው ስንል ትምህርትቤትነቱ ለሁሉም ነው:: በእውነታቸው ለመቃብር የሆኑ ከመቃብር በመውጣትና ለትንሳኤ በመቅረብ ውስጥ ትምህርት አለ:: ትምህርቱም ለእውነት የትኛውንም ዋጋ መክፈል አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል:: ትምህርቱም እውነት ብትቀበርም ትንሣኤ እንደሚኖራት ሊሆን ይችላል:: ትምህርቱም ስለሌሎች ዋጋ መክፈል የተገባ መሆኑን የሚያስረዳ ሊሆን ይችላል:: ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከትንሣኤው ማግስት በተቃራኒው መኖር አሳዛኝ ነው::
ትላንት የገባንበት ፈተና መነሻው ምንም ይሁን ምን ትንሣኤ ላይ መድረስ ከቻልን ስለ ትንሣኤው ማግስት ማሰብ አስፈላጊ ነው:: በቅኝ ግዛት ውስጥ ያሉ አገራት ከቅኝ ተገዢነት በተጨባጭ ነጻ ቢወጡም ሥነ-ልቦናቸው ግን እንደዚያ እንዳይደለ ይነገራል:: አንዳንዱ ነጻነትን በአግባቡ መጠቀም ሳይችል ሲቀር በነጻነቱ ጥፋትን ይጋብዛል:: በገንዘብ ችግር የፈተና ጥግ ላይ የደረሰ ሰው ትንሣኤ ከሆነለት በኋላ ገንዘብ ወለድ በሆኑ ፈተናዎች ተጠላልፎ ይወድቃል:: ዛሬ ያጣነው ነገር እስከ መጨረሻው የምናጣው ፈጽሞ ሊሆን አይችልም:: የማጣት ጊዜ እንዳለ የማግኘት ጊዜም ይኖራል፤ ዋናው ቁምነገር ግን ያጣነውን ባገኘነው ጊዜ የሚኖረን የህይወት ጉዞ አጥተን ባገኘነው ነገር መጥፋት ወይንስ በእድገት ጎዳና መቀጠል::
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ከሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች መካከል የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ሁሉንም ነገር ከፍቶ መለቀቁ ነውይላሉ:: ዴሞክራሲ የሌሎችን መብትም ማክበር እንደሆነ ዝቅተኛ ግንዛቤን ይዞ በአንድ አዳር ዴሞክራሲያዊ መሆን አለመቻል በስፋት ይነሳል::
የትንሣኤ ማግስት የሚኖረን ትምህርት በትንሣኤ ዋዜማና በትንሣኤ እለት ላይ ከሚሆነው የሚነሳ ነው:: በመቃብር የተገኘህበት ምክንያት የትንሣኤህን ትርጉም ይወስነዋል:: የትንሳኤው ትርጉም ደግሞ የትንሣኤውን ማግስት::
በትላንት ውስጥ የተቀመጠው ትምህርት አስቀድመን እንዳልን በአግባቡ ሊታወቅ ይገባዋል:: የከበሩ መአድናትን ለማግኘት ጠልቀን እንደምንፈልግ በቀደመው ጉዞ ውስጥ ያለውን ትምህርት ፈልጎ ማግኘት ይገባል:: በጥሞና ሆኖ መመርመር:: ዛሬ ከትንሣኤው ማግስት ከሆነ ግርግር ሰወር ብሎ ምን ነበር የሆነው ብሎ መመርመር ይገባል:: ኢትዮጵያ የበረከተ ምጥ የገባችባቸው ከምጥም በብዙ ጸሎትና ትግል የተሸጋገረቻቸው አያሌ ፈተናዎች አሉ:: ችግሩ አንዱ ፈተና በምጥ ሲታለፍ መውሰድ የሚገባውን ትምህርት ባለመውሰድ በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ መገኘት ሆኖብናል:: የትንሣኤው ትምህርት ለሁላችንም እንደ ገጠመን ሁኔታ የሚያስፈልግ መሆኑን መረዳት ይገባል::
የትንሣኤውን ማግስት ተንተርሶ የሚመጣው ቀጣዩ እርምጃ ድልን ተከትሎ በሚመጣ ውድቀት ውስጥ እንዳንሆን ማሰብን የሚፈልግ ነው:: ድልን ተከትሎ የሚመጣው ፈተናን ማሸነፍ ለብዙ ሰው ቀላል አይደለም:: ለሁሉም ቀላል እንደማይሆን ይታሰባል:: ድህነት ውስጥ ፈተና እንዳለ ባለጸግነትም ውስጥ ፈተና አለ::
የሱስ እስረኛ የሆኑ ሰዎች ከገቡበት ሱሰኝነት ለመውጣት ወደ መልሶ ማገገሚያ ማእከላት ሊገቡ ይችላሉ:: በማገገሚያ ማእከላት ቆይታቸው ያሰቡት ሰምሮላቸው ከእስራቱ ተላቀው የወጡቱ ሰዎች ከእስራት ነጻ ወጥተዋልና ትንሣኤ ሆኖላቸዋል ማለት እንችላለን:: ጥያቄው ግለሰቡ መልሶ በተመሳሳይ እስራት ውስጥ በሚጨምረው መንገድ ላይ የሚገኝ ከሆነ ነው:: ሱሰኝነትን ተላቆ ወደ ትንሳኤው መድረስ እንደሚችል አምኖ ወደ ማእከላቱ የተራመደው ሰው ጤንነቱን ካገኘ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣው ጉዳይ ጤንነቱን መጠበቁ ላይ ነው:: ልትወገር የቀረበችውን ሴት “ደግመሽ ኃጢአትን አትስሪ” እንዳላት ኢየሱስ::
የትንሣኤው ማግስት እርምጃ የትላንት ስህተትን ባለመድገም የሚገለጽ የተግባር ጉዞ መሆን አለበት:: ይህ በሆነ ጊዜ የትንሣኤ ማግስት ትንሣኤን አስጠብቆ ዘወትር በትንሣኤው መንፈስ መኖርን ያስችላል:: ለኢትዮጵያ የምሻው ለሁላችንም በግልም በቤተሰብም እንዲሆን የምመኘው ይህን ነው፤ ፈተናን አሸንፎ ለድል በቅቶ ዳግም ድል-ተኮር ፈተና ጥሎን እንዳንገኝ
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013