የተወለዱትና ያደጉት በቀድሞው አጠራር ጎጃም ክፍለሃገር ሞጣ ከተማ ነው:: ሞጣ አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: ከልጅነታው ጀምሮ አረብኛ ቋንቋ የመማር ፍላጎት ያደረባቸው እንግዳችን 12ኛ ክፍል እንደረሱ በጓደኞቻቸውና በዘመዶቻቸው እርዳታ ሱዳን ይሄዳሉ:: ሱዳን በሚገኝና ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አፍሪካ በተባለ የትምህርት ተቋም ውስጥ ገብተው ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ለሚሆን ጊዜ አረብኛ ቋንቋ ተማሩ:: በኋላም ለስድስት ወራት ያህል በመምህርነት እንደሰለጠኑ በፋይናስ የሚደግፋቸው ባለመኖሩ እና የአገሪቱ ምግብም አልመች ስላላቸው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ:: ይሁንና በእንደአጋጣሚ ሆኖ ፓኪስታን ሲማር የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ ማስተርሱን ሊቢያ ለመማር ሲል ሱዳን መጥቶ ይገናኛሉ:: ይኸው ኢትዮጵያዊ ታዲያ የዛሬውን የዘመን እንግዳችንንና የሌሎች ጓደኞቻቸውን የትምህርት ማስረጃ ይዞላቸው ወደ ሊቢያ ይሄድና ነፃ የትምህርት እድል ሊቢያ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል:: በዚያ መሰረትም ወደ ኢትዮጵያ ሳይመለሱ በመርከብ 24 ሰዓት ተጉዘው ሊቢያ ይገባሉ::
በሊቢያዋ መዲና ትሪፖሊ በሚገኝ ዳዕሮ በተባለ የትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን መከታተል ይጀምራሉ:: ይሁንና ሱዳን የተማርከው በቂ አይደለም ተብለው ዳግመኛ የአረብኛ ቋንቋ አንድ አመት ለመማር ተገደዱ:: ለአራት አመት በአረብኛ ቋንቋና ስነፅሁፍ ትምህርታውን አጠናቀቁና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ:: ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አገራቸው ተመለሱ:: የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያሳትመው አልአለም ጋዜጣ ተቀጥረው ለስድስት ዓመት በሪፖርተርነት እና የቱሪዝም አምድ አዘጋጅ ሆነው ሰሩ:: በድርጅቱ ውስጥ በነበራቸው ቆይታም ከሶስት መቶ በላይ አርቲክሎችን እና በርካታ ዜናዎችን የፃፉት እኚሁ ሰው ከአረብኛ ቋንቋ ባሻገር በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ዜናዎችን በመፃፍ ለአዲስ ዘመንና ለሄራልድ ጋዜጣ ሳይቀር አስተዋፅኦ ያደርጉ እንደነበር ይጠቀሳል:: በጠንካራ ሰራተኛነታቸው የሚታወቁት እኚሁ ሰው ባበረከቷቸው ፅሁፎች ለሁለት ጊዜ ያህል ገንዘብና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል:: ከዚህም አልፎ በድርጅቱ ድጋፍ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በስነ ልሳን ትምህርት መስራት ችለዋል::
በዛው ዩኒቨርሲቲ በወጣው የስራ ማስታወቂያ ተወዳድረውም የአረብኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህርነት በ2002 ዓ.ም ተቀጠሩ:: ከመምህርነት ባሻገር ትምህርት ክፍሉን ለአምስት ዓመታት መርተዋል:: በአሁኑ ወቅትም በዛው ትምህርት ክፍል በማስተማር ላይ ሲሆኑ በአዋሽ 90 ነጥብ 7 ላይ የአየር ሰዓት በመግዛት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብፅን ጨምሮ የአረቡ አለም አገራት የሚያወጧቸውን መረጃዎች በሳምንት ሶስት ቀናት ይተነትናሉ:: በተጨማሪም ከአባይ ጓዳ የተባለና ለሁለት ሰዓታት የሚቆይ ፕሮግራም ያዘጋጃሉ:: ይህ ፕሮግራም አድማጮችም እየገቡ አስተያየት የሚሰጡበት በመሆኑ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያገኘ ሲሆን ለመንግስትም ጠቋሚ መረጃ በመስጠትና የግብፅን ሴራ በማጋለጥ የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ በመሆኑ ከፍተኛ ምስጋና ተችሯቸዋል:: አልፎ አልፎም በውጭ መገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው አገራቸውን ወክለው በአባይ ጉዳይ ላይ ይሟገታሉ:: ከዛሬው የዘመን እንግዳችን ጋዜጠኛና ተንታኝ ኡመር መኮንን ጋር በታላቁ ህዳሴ ግድብና በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ውይይት እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል::
አዲስ ዘመን፡– ከመምህርነት ባሻገር በአባይ ጉዳይ ላይ ብቻ ተንተርሰው ፕሮግራም ለማዘጋጀትም ሆነ የግብፅን ሴራ ከስር ከስር እየተከታተሉ ለማጋለጥ ያነሳሳዎት የተለየ ምክንያት ምን እንደሆነ ለአንባቢዎቼ ይግለፁልኝና ውይይታችን ብንጀምር?
አቶ ኡመር፡– በመጀመሪያ እንግዳ አድርገሽ ስለጋበዝሽኝ ከልብ ለማመስገን እወዳለሁ:: ወደጥያቄሽ ስገባ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ተያይዞ ሴራቸውን የማጋለጥ ፍቅሩ ያደረብኝ ውጭ አገር በነበርኩበት ጊዜ ነው:: ሊቢያ እያለሁ ግብፆች ስለአባይ ሲያወሩ እሰማ ነበር:: በተለይም አባይን የእነሱ ብቻ አድርገው ሲያወሩ የምሰማው ነገር በጣም ያመኝ ነበር:: እኔ ጎጃም ተወልጄ ያደኩኝ ስለሆነ እና አባይንም በቅርበት ስለማውቀው፤ የእኔም አባት አባይን የሚሰነጥቅ ጎበዝ ዋናተኛም ስለነበርና ስለዓባይ ይነግረኝ ስለነበር እንዴት አባይን ከግብፅ ጋር ብቻ ያስተሳስሩታል የሚለው ቁጭት ነበረብኝ:: እንዳውም አንድ ጊዜ ሊቢያ ትሪፖሊ እያለሁ ታክሲ ውስጥ በአጋጣሚ ከአንድ ሱዳናዊና ግብፅዊ ጋር እንገናኛለን:: አረቦች መጠየቅ ስለሚወዱ ሹፌሩ ሁላችንም ከየት እንደመጣን ይጠይቀናል:: መጀመሪያ የመለሰው ግብፃዊው ነበር:: ‹‹ እኔ ከአባይ ነኝ›› የሚል ምላሽ ሲሰጥ ስሰማ በጣም ተናደድኩኝ:: እኔም በተራዬ ከአባይ ምንጭ ነኝ የሚል ምላሽ ሰጠሁኝ:: ያን ጊዜ ግብፃዊው እጅግ በጣም ተናደደ:: ምክንያቱም እንዲህ አይነት ምላሽ ይሰጣል ብሎ ባለማሰቡ ነበር:: በጣም የሚገርመው ደግሞ የታክሲው ሹፌር ልክ ምላሼን እንደሰማ ‹‹ ከኢትዮጵያ ነህ ማለት ነው›› አለኝ:: ይህም የሚያሳየው የውሃው ምንጭ ኢትዮጵያ መሆንዋን እንደሚያውቅ ነው:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአባይ ጉዳይ ላይ የራሴን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር::
በኋላም የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲነሳ እነመሃመድ አላሩሲና ሌሎችም ሰዎች በየሚዲያው ላይ አገራቸውን ወክለው ሲከራከሩ እሰማ ነበር:: በውጭ ያለውን ክፍተት እነሱ ስለያዙት እኔ ደግሞ ያልታየውንና ብዙም ትኩረት ያልተሰጠውን የህዝቡንም የመረጃ ክፍተት መሙላት እንዳለብኝ አመንኩኝ:: አብዛኞቻችን ስለኢትዮጵያና ስለአባይ በአረብ መገናኛ ብዙሃን ምን እየተባለና እየተፃፈ እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም:: በመሆኑም ያንን ክፍተት መሙላት እንዳለብኝ አመንኩኝ:: በሌላ በኩልም በአብዛኞቻችን ዘንድ ያለውን ጭፍን ጥላቻም የትም እንደማያደርሰን ስለማምን ስለአረቡ አለም ያለንን እውቀት በመረጃ ላይ የተደገፈ መሆን አንደሚገባው አሰብኩኝ:: በእርግጥ እኔ የእነሱን ሚዲያዎች ቀን-ተቀን ስለምከታተል ምንአይነት ሴራ እንደሚያሰራጩ አውቃለሁ:: በመሆኑም ዝም ብዬ እየሰማሁ ብቻዬን ከምታመምና ከምቆስል ቢያንስ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ማወቅ ይገባቸዋል በሚል ነው በሬዲዮ ፕሮግራም ማዘጋጀት የጀመርኩት:: በጣም አስገራሚ መረጃዎችን ይዤ ለአድማጮቼ አደርሳለሁ:: በርካታ አድማጮቼ በሚሰሙት ነገር ከፍተኛ ቁጭትና መነሳሳት እንዲያድርባቸው ማድረግ ተችሏል:: በነገራችን ላይ ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ የግብፅና የሱዳን ጋዜጦች ሳይፅፉ ውለው አያውቁም:: በተመሳሳይ የእኛ ጋዜጦች ስለገዛ ግድባችን ሲፅፉ አይሰተዋልም:: ሆን ብለን መረጃ ለመስጠት ብለን የምንፅፍ በጣም ውስን ነን:: ግብፆች ግን ሁሌም ይፅፋሉ:: እኔ እንኳን በየሳምንቱ እነሱ የሰሩትን ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ዜናዎችን እተረጉማለሁ:: በዚህም በርካቶች መጠቀማቸውንና ጥሩ መረጃዎችን እንዳገኙ ይነግሩኛል::
አዲስ ዘመን፡– በዘርፉ ለምትሰጣቸው ትንታኔዎች ሙያዊ እገዛ የሚያደርግልህ አካል አለ?
አቶ ኡመር፡– እንዳልሽው እኔ ጋዜጠኛ ነኝ እንጂ በዘርፉ ያጠናሁ ተንታኝ አይደለሁም:: ነገር ግን ማንኛውም ሰው በአንድ ዘርፍ ላይ ረጅም ጊዜ ሲሰራ እና ሲያነብ እሱ ራሱ ባለሙያና ተንታኝ እየሆነ ይመጣል:: ግን መጀመሪያ አካባቢ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎችን ይሰጡኛል:: ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም እንደዚሁ መረጃ አገኛለሁ:: በተለይም ደግሞ ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፅህፈት ቤት ካሉ ሰዎች ጋር በመሆን የምሰራቸው ስራዎች አሉ:: በዚህ መልኩ በጣም ብዙ መረጃዎችን ስለማገኝ እኔ ራሴ የእነሱንም ምላሽ በማቀናጀት ብዙ ትንታኔዎችን እሰጣለሁ::
አዲስ ዘመን፡– በምትሰራቸው ስራዎች የደረሰብህ ነገር አለ?
አቶ ኡመር፡– ፈጣሪ ይመስገን እስካሁን የደረሰብኝ ነገር የለም:: ግን ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው:: ምክንያቱም ግብፆች እጃቸው በጣም ረዥም በመሆኑ ነው:: እርግጠኛ ሆኜ የምነግርሽ ደግሞ ኡመር መኮንን የሚለውን ግብፃውያኑ አጥንተው መጨረሳቸውን ነው:: የዚህ አይነት ፍራቻም ስላለኝ አዋሽ ሬዲዮ ሰርቼ ስወጣ መኪናዬን ከታችም ከላይም ፈትሼ ነው የምገባው:: ምክንያቱም እጃቸው ረጅም ስለሆነ የምጠራጠር በመሆኔ ነው:: በነገራችን ላይ አሁን ኢትዮጵያ በሚዲያ እያሸነፈችን ነው የሚል ዘገባም መስራት ጀምረዋል:: ይህንን የምነግርሽ ራሴ ዜናውን ስለማገኘው ነው:: ሌላው እነሱ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰሩት ሴራ በማጋለጥ የምሰራቸውም ስራዎች ቀላል አይደለም::
አዲስ ዘመን፡– የግብፆች ሴራ እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ ምን ምን ጉዳት አድርሷል ማለት ይቻላል?
አቶ ኡመር፡– የግብፆች ሴራ በጣም ከባድ ነው:: በነገራን ላይ እነሱ ይህን ያህል በተንኮልና በሴራ ስራ ላይ የተጠመዱት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስለሚጎዳቸው አይደለም:: እንደማይጎዳቸውም ደግሞ በደንብ ያውቁታል:: በእ.ኤ.አ 2015 ካርቱም ላይ በተደረገው ስምምነት ላይም ደግሞ ሁሉም ነገር በግልፅ ተቀምጦ እነሱም ወደውት የፈረሙት ነው:: ግን ትልቁ ችግራቸው ግብፆች ‹‹ኢትዮጵያውያኖች ያለምንም እርዳታና ብድር ይህን ግድብ አይገነቡትም›› ብለው ለህዝባቸው ቃል ገብተው የነበረ መሆኑና የሆነው ግን በተቃራኒው በመሆኑ ነው:: እኛ ግን ወደፊት እየተጓዝን ስለነበርና በጣም ስናመልጣቸው ነው በኋላ ሴራውን ማጧጧፍ የጀመሩት:: እናም የግብፅ ህዝብ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ያስብ የነበረው ኢትዮጵያ ይህንን በአለም 10ኛ በአፍሪካ አንደኛ የሆነ ግዙፍ ፕሮጀክት ብቻዋን ልትገነባው አትችልም፤ አለም ባንክ እንዳይሰጣትም እኛ የተቻለንን ያህል እንቅፋት በመፍጠር እንዳታገኝ እናደርጋታለን፤ ስለዚህ ተረጋግታችሁ ተቀመጡ ብለው ለህዝባቸው ቃል ገብተው ነበር:: ይሄ ግን አልሆነም:: የግድቡ ግንባታ በሚገርም ሁኔታ ወደ 79 በመቶ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በህዝባቸው ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት ያሳጣናል የሚል ስጋት ስላላቸው ነው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያ ስለምትገነባው ግድብ ጎጂነት የሚደሰኩሩት::
ሌላው ትልቁ ቁምነገር ደግሞ ከዚህ በፊት ግብፆች አፍሪካ ቀንድ ላይ ያለማንም ከልካይ ይፈነጩ እንደነበር በደንብ ይታወቃል:: ኤርትራን እንደፈለጉ ያዙ ነበር:: ጅቡቲ ላይ ሆነ ሱማሊያ ፈላጭ ቆራጮች ነበሩ:: አሁን ግን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ እየተጠናከረ ሲመጣ ይህንንም ቦታ አጥተዋል:: በተጨማሪም ደግሞ በኢኮኖሚም ልትበልጠን ትችላለች የሚል ስጋት አለባቸው:: ይህም ማለት በተለይም የህዳሴ ግድብን ተሳክቶልን አጠናቀነው ስራውን የሚጀምር ከሆነ የአረብ አገራቱ ከሚያገኙት ገቢ ያልተናነሰ ስናገኝ፣ መብራት መሸጥ ስንጀምር፤ እንዲሁም ከእነዚህ አገራት ጋር ያለን ግኑኝነት በኢኮኖሚ እየተሳሳረ ሲመጣ የግብፅ ተሰሚነት እየቀነሰ እንደሚመጣ ተገንዝበውት ነው ፍራቻቸው እየጨመረ የመጣው:: ስለዚህ ግብፆች የሚከተሉት ፖለቲካ እያዋጣቸው አይደለም የሚል እምነት ነው ያለኝ::
አዲስ ዘመን፡– የሚከተሉት ፖለቲካ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ኡመር፡– የግብፅ ፖለቲካ እኔ ሁልጊዜ እንደምናገረው የሴራ፣ የምቀኝነትና የህፃን ፖለቲካ ነው:: የሴራ ፖለቲካቸው በእኛ ጉዳይ ላይ ገብተው ውስጥ የሚፈተፍቱት ነገር ነው:: ለምሳሌ በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮ- ሱዳን የድንበር ግጭት እንዲፋፋም፣ እንዲጧጧፍ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ወደለየለት ጦርነት እንዲገቡ የሚያደርጉት ሴራ ሁላችንም የምናውቀው ነው:: ከዚያ በላይ ግን በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ እየገቡ የሚፈተፍቱትን ነገር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አያውቅም:: ለምሳሌ አሁን ብነግርሽ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተገነባው በቤኒሻንጉል ምድር ላይ ነው:: ቤኒሻንጉል ደግሞ በ1902 ዓ.ም ኢትዮጵያ አባይን ላትጠቀም ከሱዳን የተበረከተላት መሬት ነው ብለው ነው የሚያምኑት:: ስለዚህ ኢትዮጵያ ውሉን ልታፈርስ አትችልም የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ:: የሚገርመው ያንን ውል ሱዳኖች ሳይሆን የፈረሙት እንግሊዞች ናቸው:: እነሱ ያልፈረሙትን ያንን ስምምነት ነው እንግዲህ ወደዚህ ሊያመጡ ጥረት የሚያደርጉት:: ይህም ማለት ሱዳን ቤኒሻንጉልም የሚል ጥያቄ እንድታነሳና ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ጦርነት እንዲነሳ ለማድረግ የሚሄዱበት ሴራ ነው::
ሌላው በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ የሚፈተፍቱት ነገር በጣም የሚገርም ነው:: ለምሳሌ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የተገደለ ጊዜ የግብፅ ሚዲያ ምን ይላል? እንዴት አድርገው ዘገቡት የሚለውን ነገር ለማየት የግብፅ ቴሌቭዥኖችን በሙሉ እያገለባበጥኩኝ ስመለከት ነበር:: የሚገርምሽ ሁሉም በሚባል አይነት መንገድ ሁከቱ ሲነሳ የነበረበትን ቪዲዮ እየለቀቁ ‹‹ታላቁና የተከበረው አርቲስት አርፏል፤ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው›› እያሉ ነበር ሲዘግቡ የነበሩት:: ሌላው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር እርምጃ ስትወስድ የግብፅና የሱዳን ሚዲያዎች በተለይም የግብፅ ሚዲያዎች እንዴት ሲዘግቡት እንደነበረ ስትመለከቺ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በጣም ነው የሚያምሽ:: ‹‹ አፍሪካ ‘ትግራይ’ የተባለች አዲስ አገር ልታገኝ ነው›› እያሉ ነበር ሲዘግቡ የነበሩት:: በተለይ ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ከድተው ወደ ትግራይ የሄዱ ጊዜ በጣም አሟሙቀውት ነበር ያቀረቡት::
በተመሳሳይ ህወሓት ምርጫ ሲያካሂድ ‹‹ኢትዮጵያ ልትገነጣጠል ነው›› እያሉ ሲፅፉ ነበር:: ጦርነቱ መካሄድ ሲጀምር ደግሞ ‹‹ጦርነቱ በአጭር ጊዜ አይጠናቀቅም፤ ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ናት፤ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት አታከብርም›› እያሉ ለአለም ህዝብ መልእክት ያስተላልፉ ነበር:: በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ላይ የሰብአዊ መብትን በተመለከተ ከፍተኛ ጫና እንዲኖርባት ካደረጉት ሚዲያዎች ውስጥ የግብፅ ሚዲያዎች ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል:: ይሄ በደንብ መታወቅ አለበት:: ያ ማለት ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ በጦርነት ሁኔታ ውስጥ ያለች አገር ስለሆነች ኢትዮጵያ ላይ መዋዕለንዋይ ማፍሰስ አያዋጣም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን ማድረግ አይመከርም›› ብሎ አለም እንዲሸሸን አሁንም እየሰሩ ነው:: እኔ ማጋለጥ የምፈልገው እንዲህ አይነቱን ነገር ነው:: ይህንን በተመለከተ በምፅፋቸው ፅሁፎችና በማቀርባቸው ትንታኔዎች የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፅህፈት ቤትም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጣም እያመሰገኑኝ ነው:: በደህንነት መስሪያ ቤቱም ‹‹እኛ ፈልገን የማናገኘውን ትልልቅ መረጃ ከአንተ እያገኘን ስለሆነ በጣም ልትመሰገን ይገባል›› ተብያለሁ:: እውነት ለመናገር በዚህ በጣም እኮራለሁ::
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ አኳያ ግብፅ የአለምን ዲፕሎማሲ አሸንፋለች ማለት ይቻላል?
አቶ ኡመር፡– ይሄም በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው:: የዲፕሎማሲው ነገር እኔም በጣም ትኩረት አድርጌ ከምከታተላቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው:: የግብፅ ሚዲያና የኢምባሲ ፅህፈት ቤቶቻቸው ሙሉ ለሙሉ የዲፕሎማሲ ስራ የሚሰሩት በህዳሴ ግድብ ላይ ነው:: ውጭ አገር ያሉ የግብፅ ፅህፈት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ማለት ትችያለሽ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ ነው ያሉት:: ውጭ አገር የሚገኙ ግብፃውያንን በማስተባበር ፣ በራሪ ወረቀቶችን አሳትሞ በመላክ ትክክለኛ ያልሆኑ እና የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ላይ ነው አሁን ተጠምደው ያሉት:: በተለይም በቅርቡ የኪንሻሳ ድርድር ያለ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ግብፆች አሁን የያዙት ትልቁ ስራ የዲፕሎማሲ ዘመቻቸውን አጠናክሮ መቀጠል ነው:: የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ውሃና መስኖ ሚኒስቴር እና የኢሜግሬሽንና የስደተኞች ሚኒስትሮች በአንድ ላይ ሆነው አንድ ዘመቻ ጀምረዋል:: ዘመቻው ‹‹ኢትዮጵያ 150 ሚሊዮን ህዝብ ውሃ ልታስጠማ ነው›› የሚል ነው:: ይህንን ሃሳብ የያዘው ፅሁፍ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያን የአለም ህዝብ እንዲያስቆም ጥሪም ቀርቦበታል:: ይህንን በደንብ የተሰራበትና የተቀናጀ ሴራ ለመላው ግብፃውያን ደግሞ በፌስቡክና በተለያዩ ሚዲያዎች እንዲበትኑት ተደርጓል:: ይህንን በማክሸፍ በኩል ግን ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ይህንን ፅሁፍ ራሱን ወስደው ‹‹ግብፅ ውሸቷን ታቁም›› ብለው የሃሰት ዜና ብለው ማሰራጨት ሲጀምሩ ግብፆች የጀመሩትን ዘመቻ አቆሙት::
በሌላ በኩል እንደምታውቂው ግብፆች የሚፅፉት በአረብኛ ቋንቋ ነው፤ አረብኛ ደግሞ በአለም በሰፊው የሚነገር፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት ቋንቋ ነው:: ሰሜን አፍሪካ ላይ በርካታ አገራት አረብኛ ተናጋሪዎች ናቸው:: ሌላው በመላው አረብ የሚገኙ አብዛኛዎቹ አረብኛ ይረዳሉ:: ስለዚህ እነሱ የሚፅፉት እያንዳንዱ ነገር በጥንቃቄ ነው መታየት ያለበት:: ከጠየቅሽኝ ጥያቄ አንፃር ተፅዕኖ ማሳደር ችለዋል:: በምን በኩል? ካልሽኝ ባለፉት አስር አመታት ሲደረጉ የነበሩት ድርድሮች በሙሉ ‹‹በኢትዮጵያ ግትር አቋም ምክንያት ነው›› የሚለውን ሃሳብ ሌሎች የአረብ ሚዲያዎችም እንዳለ ወስደው ሳይቀይሩ ማራመድ መቻላቸው ነው:: ሌላው መርሳት የሌለብሽ ነገር ግብፆች በህዝብ ብዛትም ከፍተኛ ቁጥር አላቸው፣ ብዙ የተማረ ሃይል አላቸው፤ግን ደግሞ የተማረው ሰው ሁሉ ግብፅ ስራ አያገኝም፤ ስለዚህ ወደ ተለያዩ አገራት ይሄዳሉ:: ይህም በተለያዩ አለምአቀፍ ሚዲያዎች የሴራ አላማቸውን የያዘ መረጃ ለማሰራጨት አስችሏቸዋል::
ከቢቢሲና አልጀዚራ ባሻገር በብዙ ሺ የሚቆጠሩ በአረብኛ የሚፅፉና ተቀጥረው የሚሰሩት ግብፆች ናቸው:: ስለዚህ ለአገራቸው ይሰራሉ:: ለአገራቸው ሲሰሩ ይሄንን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ነው የሚያሰራጩት:: በመሆኑንም የእነሱን ሚዲያ በቀላሉ ማሸነፍ አይቻልም:: እኛም በአቅማችን እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው:: ግብፆች የኢትዮጵያ ግትር አቋም የሚለውን እስካሁን ድረስ እየሄዱበት ነው:: ይህ እሳቤ አሁን ሌሎች የአረብ አገራቶችም ላይ እየተንፀባረቀ ነው:: እኛ ግን እያልን ያለነው ምንድን ነው ይሄ የኢትዮጵያ ግትር አቋም ሳይሆን በአቋም መፅናት ነው:: በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ከምትደነቅባቸው ነገሮች አንዱ ለአመታት ያለመሰልቸት፣ ያለመፍራት እና ያለማወላወል አቋሟን ሙሉ ለሙሉ ይዛ ማስቀጠሏ ነው:: ግድቡን በራሴ ልጆች እሰራለሁ ብላ ቀጠለች፤ የመጀመሪያውን ሙሌት ብትፈቅዱም፣ ባትፈቅዱም እሞላለሁ እንዳለች ሞላች፣ ሁለተኛውን ሙሌት ለማድረግ እየተዘጋጀች ነው::
አሁን ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ትልቁ ጫና በሚዲያ እየተደረገ ያለው ዘመቻ ነው:: የውስጥ ጉዳዮቻችንን እያነሱ ማባባስ፣ እናም ወደ ለየለት ጦርነት እንዲሄድ የማድረግ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ጦርነት እንዲነሳ የመገፋፋት፣ የአባይ ንስሮች በሚል የጦርነት ልምምድ ማድረግ፤ ይሄ ትንኮሳ ነው:: ኢትዮጵያን ትግስቷን ለመፈታተንና ወደ ጦርነት እንድትገባ ነው:: ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ህግ እያስከበረች ባለችበት ሰዓት ላይ ደግሞ ሆን ተብሎ ተመርጦ ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት እንድትወር ተደርጓል:: በተለይም በአልቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ መንግስት ‹‹ኢትዮጵያን ወርሬ መሬቴን አስመልሻለሁ፣ የኢትዮጵያን የጦር ሰፈሮች አውድሚያለሁ›› እያለ ነበር መግለጫ ሲሰጥ የነበረው:: ኢትዮጵያ ከየትኛው ትሁን ? በሰሜን በኩል ጦርነት ነበረባት፤ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ሱዳን የምታወጣው መግለጫ አለ:: መታወቅ ያለበት የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን መሬት ሲወር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር ገጥሞ ሳይሆን ከታጣቂዎችና ከሚሊሻዎች ጋር ባደረገው ጦርነት ነው:: ይህንን እንደጦርነት ልንጠቅሰው የምንችለው አይደለም:: በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ትዕግስትና ሆደሰፊነት ባይኖር ኖሮ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር:: በዚህ በኩል ከፍተኛ የሆነ ምስጋና ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል:: ከእኛ ብቻ ሳይሆን ከአለምአቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ምስጋና መሰጠት አለበት:: የትኛው አገር ነው መሬቱ ተወሮ ፣ እዛ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገው፣ የለየለት የዘረኝነት እርምጃ ተወስዶባቸው ዝም የሚለው?
አዲስ ዘመን፡–ግን መሬት አየተወረረ በኢትዮጵያ መንግስት ዝም መባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ቁጭት አይፈጥርም? የአገሪቱ መንግስት ድንበሩን ማስጠበቅ አልቻለም ወደሚል ድምዳሜስ ለመድረስ አይጋብዝም?
አቶ ኡመር፡– ለምንድን ነው መሰለሽ፤ የእኔ እይታ
በአንድ በኩል አብዛኛው ኢትዮጵያውያን በሚሉት ሃሳብ እስማማለሁ:: ለምሳሌ ማስከበር አልቻለም በሚለው ሃሳብ እስማማለሁኝ:: ግን መታወቅ ያለበት ነገር አሁን ጦርነት ውስጥ ብንገባ ጦርነቱን ከማን ጋር ነው የምናደርገው? የሱዳንን የውስጥ ጉዳይ ደግሞ በደንብ መመርመር ያስፈልጋል:: እንደሚታወቀው የሱዳን የሽግግር መንግስት በሁለት መንግስታት የተመሰረተ ነው:: የሲቪሉ መንግስት ዶክተር አብደላ ሃምዶክ የሚመራ ሲሆን የወታደራዊ መንግስቱ አብዱልፈታ አልቡርሃን የሚመሩት መንግስት አለ:: ይሄ ወታደራዊ መንግስትን እየመራ ያለው ቡድን አብዛኛውን የመንግስት ስፍራ የያዘ ቡድን አይደለም:: 80 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱን ቦታ እየመሩ ያሉት ዶክተር አብደላ ሃምዶክ ናቸው:: ሲቪልና የኢትዮጵያ ወዳጆች ናቸው:: ሁልጊዜ የሚያወጡት መግለጫቸው በሙሉ ሰላማዊ ነው:: አሁን ባለው ሁኔታ ከሱዳን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት ትክክል ነው ብዬ አላምንም::
ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ዲፕሎማሲን መጠቀም ነው የሚያዋጣን:: አልቡርሃን ግን ከማን ጋር ነው የሚገጥመው:: በአንድ ወቅት ይህ ሰው አምስትና ስድስት ጀነራሎችን አዋቅሮ ካይሮ ልኮ ስልጠና ተሰጥቷቸው ነበር:: ጀነራል ሸምሰዲን ከባሽ የሚባል ሱዳናዊ እነዚህን ጀነራሎች መርቶ ሄዶ ከነአልሲሲና ከሌሎች የጦር መሪዎች ጋር ተገናኝቶ ከመጡ በኋላ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የሱዳን መግለጫ ተቀይሮ ነበር:: ስለጦርነትና ስለኢትዮጵያ መጥፎነት ነበር የሚያወሩት፣ ይሄን ሁሉ ግን መቻል ያስፈልግ ነበር:: ምክንያቱም በጣም አንቱ የተባሉ ትልልቅ የሱዳን ምሁራኖች፣ አክቲቪስትና ጎበዝ ጋዜጠኞች እነዚህ አካላት የኢትዮጵያ ወዳጆች ናቸው:: ኢትዮጵያና ሱዳን መጋጨት የለባቸውም፤ አንድአይነት ህዝቦች ናቸው፣ አንድአይነት ቀለም ያለን፣ አንድአይነት የአኗኗር ዘይቤ ያለንና ባህል ያለን ነን:: ስለዚህ ይህንን ህዝብ ማጋጨት ሥለሌለብን ነው ወደ ጦርነት ውስጥ መግባት የሌለብን:: ትዕግስት የተደረገበት ምክንያት ይሄ ነው ብዬ ነው የማምነው:: ሌላው የሰሜኑን ጉዳይ ሳታጠናቅቂ ደግሞ ሌላ ጦርነት ውስጥ መግባቱ ደግሞ ኢትዮጵያን ወደ ኪሳራ ሊወስዳት ስለሚችል አንዳንድ ጊዜ መረዳት ያለብንን ነገር መረዳት አለብን::
አዲስ ዘመን፡– ከዚሁ ጋር አይይዘን ሱዳን ከዚህ ቀደም በነበሩት ውይይቶችና ድርድሮች የተለሳለሰ የሚባል አቋም ነበራት:: አሁን ላይ ግን ከግብፅም በላይ ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ ሃሳቦችን ስታራምድ ትስተዋላለች:: ይህ የአቋም መዋዠቅ ጉዳይ ከምን የመነጨ ነው?
አቶ ኡመር፡– አሁን ላይ የሱዳንን አቋም ስናየው በአልበሽር ዘመን የነበረውን አቋማቸውን እና አሁን ያለውን አቋም ማየት እንችላለን:: በአልበሽር ዘመን የነበረው አቋማቸው እጅግ በጣም የተለሳለሰ ብቻ ሣይሆን ደጋፊም ጭምር ነበር:: ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋነኛ ድጋፍ ይሰጥ የነበረው ከሱዳን ነበር:: በነገራችን ላይ ቦንድ የገዙ ሱዳናውያን እንዳሉ ምን ያህሎቻችን ነው የምናውቀው? ሱዳኖች እኮ የፐብሊክ ዲፕሎማሲው አካል ሆነው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን ጎብኝተውታል:: እንዳውም ሱዳኖች ‹‹ለግድቡ ግንባታ እያንዳንዳችን ብንችል እኛ ልናዋጣ ይገባል›› ወደማለት የገቡበት ሁኔታ ነበር:: ምክያቱም የኢትዮጵያ ህዳሴ ለሱዳን አመቱን ሙሉ ውሃ እንድታገኝ ያደርጋታል:: ከዚህ በፊት በክረምት ላይ ነበር ውሃ የሚሄድላቸው የነበረው:: በጋ አካባቢ ላይ ደግሞ የመድረቅ ነገር ይታይበት ነበር::አሁን ግን አባይ ራሱ ባለው ፍሰት በተጨማሪም ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚፈሰው ውሃ ተደምሮ ሱዳኖች በአመት ሶስት ጊዜ እንዲያመርቱ ያስችላቸዋል:: ይህንን በደንብ የተገነዘቡ ሱዳናውያን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደጋፊዎች ነበሩ::
አሁን ሱዳኖች የአቋም ለውጥ እያሳዩ ያሉበት ምክንያት ምንድነው? ካልሽኝ አሁንም ወደ ግብፅ ነው የምመልስሽ:: ምክንያቱም የሱዳንና የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋነኛ ደጋፊ መሆናቸው ለግብፆች የማያዋጣቸው በመሆኑ ነው:: አስቀድሜ እንደነገርኩሽ ግብፆች የሚከተሉት የምቀኝነት፣ የሴራና የህፃን ፖለቲካ በመሆኑ ነው:: የህፃን ፖለቲካቸው ምንድን ነው? ልትዪኝ ትቺያለሽ፤ ይህም ማለት ለምሳሌ አንድ ህፃን ልጅ እሱ ከተጣላው ልጅ ጋር ጓደኛው ሲሄድ ካየው ይጣላዋል፤ የግብፅ ፖለቲካም እንደዚሁ ነው:: ለምሳሌ ኤምሬቶች መጥተው ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት ከፈጠሩ ኤምሬቶችን ይጣላሉ:: ቱርኮች እኛ አገር በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት ስላደረጉ ‹‹ቱርኮች ናቸው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሚገነቡት›› ይሉሻል:: ኢትዮጵያ ጋር መጥቶ ግንኙነት ለመመስረት የሚፈልግ አረብ አገር ሁሉ በአረብሊግ አማካኝነት ያሸማቅቁታል:: በነገራችን ላይ በደንብ መታወቅ ያለበት ነገር የአረብ ሊግ ዋና መስሪያ ቤት ያለው ካይሮ በመሆኑ አብዛኛው ሰራተኞች ግብፃውያን ናቸው:: በአጠቃላይ በግብፅ ቁጥጥር ስር ያለ ሊግ ነው ማለት ይቻላል:: እንደፈለጉ አጀንዳቸውን ሊያራምዱ የሚችሉበት ተቋም ነው::
ስለዚህ አሁን ላይ በግብፆች ሴራ አማካኝነት ሱዳኖች የአቋም ለውጥ አድርገዋል:: ሱዳኖችን ከሃሳባቸው አንዲንሸራተቱ ያደረጓቸው ግብፆች ናቸው:: ለዚህ ደግሞ በዋናነት ሲቃወሙ ይዘውት የተነሱት ሃሳብ ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ችግር አለበት›› በሚል ነው:: ግድቡ የቴክኒክ ችግር ስላለበት ከተደረመሰ ሙሉ ለሙሉ የምትወድመው ሱዳን በመሆንዋ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ከማድረጓ በፊት አስገዳጅ ውል ልትፈርም ይገባል የሚል ሃሳብ በማንሳት ላይ ናቸው:: ሱዳኖች በሚያሳዝን ሁኔታ ይህንን ሃሰት ነው ተቀብለው ማራመድ የጀመሩት:: ይህንን ሲሉ ግን በትክክል ስጋቱ ካለባቸው ባለሙያ ልከው እንደገና ማስፈተሽ ይችሉ ነበር:: ግን አላደረጉትም፤ በደፈናው ነው ኢትዮጵያ አስገዳጅ ውል መፈረም አለባት ሲሉ ሲሞግቱ የነበሩት:: ሌላው ይቅርና ሁለቱም አገራት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የጉብኝት ግብዣ አልተቀበሉትም::
አዲስ ዘመን፡– ታዲያ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ለመጎብኘት ያልፈለጉበት ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ኡመር፡– ምን መሰለሽ፤ የኢንጅነሪንግ ስራው ሲጀመርም አይተውታል:: በባለሙያዎች ችግር የለውም ቀጥሉበት ነው የተባለው:: ግን እንዳልኩሽ ‹‹ ኢትዮጵያውያን ይጀምሩታል እንጂ አይጨርሱትም›› የሚል አመለካከት ስለነበራቸው ነው በጊዜው የተዉት:: ከዚያ በኋላ የቴክኒክ ጉዳይ በጣም በተደጋጋሚ ከማለታቸው የተነሳ ቱርክ ‹‹እናንተ እንደምትሉት ሶስታችሁን ያላስማማችሁ ጉዳይ የቴክኒክ ችግር ከሆነ እኔ ከፍተኛ ባለሙያዎች ስላሉኝ እነዚህን ባለሙያዎች ልስጣችሁ›› ብላ ጠይቃለች:: እነሱ ግን አይቻልም አሉ:: ከዚያ በኋላ ሩሲያም ጠይቃለች:: አሜሪካም ጠይቃለች:: ግን የተሰጣቸው መልስ የለም:: ይህ የሚያሳየው የግብፆችና የሱዳን ቅሬታ ሁሉ በሃሰት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው:: ምክንያቱም የቴክኒክ ችግር እንደሌለበትም ራሳቸው ያውቁታል:: በነገራችን ላይ አሁን ስራውን እያከናወነ ያለው የጣሊያኑ ኩባንያ ሳሊኒ ማለት እኮ በርካታ ግድቦችን የሰራ ትልቅ ድርጅት ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሳሊኒም ሆነ ኢትዮጵያ የሚፈርስ ግድብ እንዴትና ለምንድነው የሚሰሩት? ከእያንዳንዳችን በተለይም ከደሃ እናቶቻችን መቀነት እየተፈታ ፣ ሊስትሮ ሳይቀር ከሚያገኛት ሳንቲም ላይ አዋጥቶ የሚፈርስ ግድብ ለምንስ ሲባል ነው የምንገነባው? እንዴትስ አሳማኝ ሊሆን ይችላል?:: አንድ ጀሚል ሙስጠፋ የተባለ ሱዳናዊ የፃፈው ፅሁፍ ነበር:: ይህ ሰው የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው:: ‹‹ሱዳን የማትጠቀምበት ጦርነት ውስጥ መግባት ለምን ትፈልጋላችሁ›› በሚል ርዕስ በግልፅ የግብፆች አካሄድ ተገቢ እንዳልሆነ አስፍሯል:: ቢቻል እንዳውም ኢትዮጵያን ማገዝ ሲገባ ለምን አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ እንገባለን እያለ የሚያትት ጽሁፍ ነው የፃፈው:: ይህ ሱዳናዊ በዚሁ ፅሁፉ ላይ በአለም ላይ 45 ሺ የሚሆኑ ግድቦች መኖራቸውን፣ ነገር ግን አንድም ግድብ ተናደ ተብሎ የሰማው ግድብ አለመኖሩን ይጠቅሳል:: እንዳውም መፍራት ካለባችሁ የግብፁ ሰንደልአሊ የሚባለውና በ1960ዎቹ በጣም ኋላቀር በሆነ ቴክኖሎጂ የተገነባውን ግድብ እንደሆነ ያነሳል:: ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለው በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ ዘመናዊ የተባሉ ቴክኖሎጂዎችን አሟልቶ የተሰራ ፣ ለዚያውም ደግሞ በአውሮፓውያን እየተሰራ ያለ ግድብ እንዴት ይፈርሳል?›› ብሎ ይጠይቃል:: በዚሁ ፅሁፉ ስለኢትጵያና ስለሱዳን መልካም ግንኙነት በስፋት ነው የፃፈው:: ይህንን ሬድዮ ላይ አቅርቤው በጣም ነው የተወደደው:: ስለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ብለሽ ለጠየቅሽኝ ጥያቄ የሱዳኖች አቋም እየተቀየረ የመጣው የግብፆች ውትወታና ሴራ እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት የለም የሚል ነው ምላሼ::
በተመሳሳይ ‹‹አራትዮሽ›› እየተባለ የሚቀርበው ሃሳብ እንዳውም አሁን ያልኩሽ ሙስጠፋ ጀማል የተባለው ሱዳናዊ ‹‹እባካችሁ ሱዳኖች አንዳንድ ጊዜ በደንብ ቆም ብለን ልናስብ ይገባል:: ሱዳን አራትዮሽ ድርድር ይኑር የሚለውን ሃሳብ እንድታቀርብ ያደረገቻት ግብፅ መሆንዋን ልናውቅ ይገባል›› ይላል:: በነገራችን ላይ ግብፅ ድርድሩ አራተኛ አካል ይግባ የሚለውን ሃሳብ በቀጥታ ያላቀረበችው በአፍሪካ ህብረት ጥርስ እንዳይነከስባት ነው:: በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ኢትዮጵያም ሆነች የአፍሪካ ህብረት የሚቀበሉት መስሏቸው ድርድሩን ከአፍሪካ ህብረት ቀምተው ለሌላ ለመስጠት ፈለጉ:: የኢትዮጵያ አቋም ግን ጠንካራ ነበር:: ‹‹የአፍሪካ ችግር የሚፈታው በአፍሪካውያን ብቻ ነው›› በሚል ያሳየችው አቋም እና ‹‹ይሄ የአፍሪካ ህብረትን መናቅ ነው›› ብላ የሰጠችው መግለጫ በጣም ድምፁ ከፍ ያለ ስለነበር በመላው አፍሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ አግኝቶ በአሁኑ ሰዓት ከናይጄሪያ ከቡርኪናፋሶ ፣ እና ከሌሎችም አገሮች የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሚደግፉ አክቲቪስቶች እየመጡ ነው:: ‹‹ ይሄ የአፍሪካ ግድብ ነው›› ብለው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ምስል የማህበራዊ ድረገፃቸው መክፈቻ አድርገው ስለኢትዮጵያ የሚከራከሩ አፍሪካውያ እየመጡ ነው::
ስለዚህ ጥርስ የተነከሰባት ሱዳን ብትሆንም ሃሳቡን ያፈለቁት ግብፆች ናቸው:: ይህም የሚያሳየው የግብፆችን መሰሪነት ነው:: ግን አሁንም ቢሆን መረዳት አለብን:: ሱዳን ላይ ቅድም እንዳልኩሽ የሽግግር መንግስቱንና ወታደራዊ መንግስቱን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን:: የወታደራዊ መንግስቱ አካሄድ የሚቀጥል አይመስለኝም:: ምክንያቱም ተሞክሯል፤ ኳታር ሄደው የኳታር መንግስት ግልፅ ግልፁን ነው የነገሯቸው:: በህዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት መግጠም መፍትሄ አይሆንም ብለዋቸዋል:: ስለዚህ ቁጭ ብላችሁ ልትነጋገሩ ነው የሚገባው ብለው ለአልቡርሃን ከነገሩት በኋላ ሆን ብለው በሚመስል ሁኔታ ኳታር ከሚኖሩ ሱዳኖች ጋር እንዲገናኝ ያደረጉት:: እነዚህ ሱዳናውያን ለአልቡርሃን በጣም ከባድ ከባድ ጥያቄ አንስተውለታል:: ‹‹አገራችንን ወዴት ልትወስዳት ነው? ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ገጥመህ ከማን ጋር ልትኖር ነው? ኢትዮጵውያን ወንድሞቻችን ናቸው፤ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይጠቅመናል፤ ምንድነው አቋምህ?›› ብለው ሲያፋጥጡት እንደገና ‹‹ጦርነት አልፈልግም፤ በሰላም መኖር ነው የምፈልገው››ወደሚል አቋም ተንሸራቷል:: እናም ይህ በግብፅ የመነዳቱ ሁኔታ የሚቀጥል አይመስለኝም::
አዲስ ዘመን፡– አሁን ላይ ግብፅ ድርድሩ ከአፍሪካ ህብረት እጅ እንዲወጣ የምታደርገው ጥረት በብዙ ሃያላን አገራ ተቀባነት ማጣቱ ለኢትዮጵያ ምን አንድምታ አለው? በአለም ሃያላን አገራት መካከል ጎራ እንዲፈጠር አያደርገውም ወይ?
አቶ ኡመር፡– በመጀመሪያ ደረጃ የዚህ ሁኔታ አንድምታ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ እያሸነፈ መምጣቱን ነው የሚያሳየው:: እንዳልኩሽ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስለምሰራም እኔ ኢትዮጵያ የሄደችበት የዲፕሎማሲ ርቀት ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል:: በሌላ በኩል ደግም ታላላቅ የምንላቸው አገሮች እንደነአሜሪካ ፣ ሩሲያና ቻይና ያሉ አገሮች አቋማቸውን ግልፅ አድርገዋል:: ከዚህ አንፃር በሃያላኑ አገራት መካከል ጎራ ይፈጠራል የሚል እምነት የለኝም:: በእርግጥ ዶናልድ ትራምፕ አሸንፎ ቢሆን ኖሮ ይህ የሚፈጠርበት ሁኔታ ሊኖር ይችል ነበር:: ምክንያቱም ትራምፕና ግብፅ ከፍተኛ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ይታወቃል:: በምርጫቸው ሰሞንም በሲቲ ባንክ አማካኝነት ትራምፕ በምርጫው አንዲያሸንፉ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ግብፅ እንዳስገባች ይታወቃል:: ትራምፕ ቢመረጥ ኖሮ ደግሞ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ይታወቃል:: ሆን ብሎ ከአንድ የአሜሪካ መሪ የማይጠበቁ ንግግሮችና አቋሞችን ሲያራምዱ እንደነበር ይታወሳል:: ሆኖም ግን አለምአቀፍ ውግዘት ነው የገጠመው:: በኋላ ደግሞ ምርጫው ላይ አልተሳካላቸውም:: ኢትዮጵያውያኖችም ጆ ባይደንን በመደገፍ ጥሩ ስራ ሰርተዋል::ከዚያ በኋላም በርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሚባል ስልጣን እንዲሰጣቸው ተደርጓል::
ስለዚህ አሜሪካ በዚህ አቋሟ ትቀጥላለች የሚል እምነት ነው ያለኝ:: ከዚህም ባሻገር በግልፅ ‹‹ሶስቱም አገራት ተስማምተው ለማደራደር ካልጠሩኝ በስተቀር ግብፅ እና ሱዳን ስለጋበዙኝ ብቻ አልመጣም›› የሚል አቋም ማሳየታቸው ኢትዮጵያውያን የሰሩት የዲፕሎማሲ ውጤት ነው ባይ ነኝ:: ራሺያም ሆነ የሌሎች አገራት አቋም ተመሳሳይ ነው:: አለምም እየተረዳን መሆኑን ያሳያል:: በተጨማሪም 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ ኢትዮጵያ እየላከች (እያዋጣች) ነገር ግን እስካሁን ድረስ አንድ በመቶ የሚሆነውን ውሃ እንኳን መጠቀም ያልቻለች አገር መሆንዋ በአለም ህዝብ ዘንድ ትልቅ አሳማኝ ጉዳይ ሆኗል:: 60 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ መብራት የለውም:: ስለዚህ ይሄ አሳማኝ ጉዳይ ስለሆነ ኢትዮጵያ አሁን በአለምአቀፉ መድረክ ተሰሚነት እያመጣች ነው የሚመስለኝ:: በሌላ በኩል ግብፅና ሱዳን የተቀናጀ ዲፕሎማሲ መጀመራቸው ይታወቃል::
ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን ጥረት የሚያከሽፍ ከባድ ስራ እየሰራች መሆኑን የሚያሳይ ነገር አለ:: ስለዚህ በዚህ በኩል እኔ ስጋት የለኝም::
አዲስ ዘመን፡–በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በተለይም የአፍሪካውያንን ድጋፍ እያገኘች መሄድዋ በአፍሪካና በአረብ አገራት መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ያደርጋል የሚል ስጋት የሎትም?
አቶ ኡመር፡– ይህንን ስጋት ያመጣችው አሁንም ግብፅ ናት:: ግብፆች በሴራ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አለማቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው የሰሩት ስራ የተሳካ የሚባል ነው::ምክንያቱም ይህንን የልማት ግድብ በተመለከተ ይህንን ያህል አምባጓሮ የሚፈጥር እና ለአለምአቀፍ መነጋገሪያ የሚውል ጉዳይ አልነበረም:: ግብፆች ግን በአንድም በሌላም የተለያዩ ስልቶችን እየተጠቀሙ አለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው አድርገዋል:: ሌላኛው ነገር ግድቡ አረብ አገር ይዘት እንዲኖረው የተሰራበት አካሄድ ከባድ ነው:: እንዳልሽው ስጋት አለኝ:: ስጋቴ በተለይም ከሰሞኑ መሬየም ሳድቅ የምትባለው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካይሮ ሄደው የተናገሩት ጉዳይ ነው:: እኔን ብቻ ሳይሆን በጣም በርካታ የአፍሪካ አገራትን አስቆጥቷል:: በዚህ ምክንያት አንድ አንድ የአፍሪካ አክቲቪስቶችም ‹‹የአፍሪካ ግድብ ነው›› እያሉ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ከዚያ ጊዜ በኋላ ነው:: በኋላም ግብፆችና ሱዳኖች የአፍሪካ ህብረትን ንቀው ከአፍሪካ ህብረት ድርድሩ እንዲወጣ የጀመሩት አካሄድ በርካታ አፍሪካውያኖችን አስቆጥቷል:: ስለዚህ ከዚህ አኳያ እንዲህ አይነት ጎራ ያመጣል የሚል ስጋት አለኝ:: ይሁንና ደግሞ ግብፅ አፍሪካ ውስጥ ባሉ አረብ አገራት ድጋፍ የላትም:: ለምሳሌ ሊቢያ ብትመለከቺ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ደካማነት ነው እንጂ ሊቢያን ሙሉ ለሙሉ ወደ እኛ ማምጣት ይቻላል:: ምክንያቱም ከሊቢያ ጋር ተያይዞ ግብፆች ገብተው ህጋዊ መንግስቱን አይደግፉም፤ ነገር ግን አማፂውን ነው እየደገፉ ያሉት:: ይሄ በራሱ በሊቢያዎች ዘንድ ጥርስ እንዲነከስባቸው ሆኗል:: ከአልጄሪያ፣ ከሞሮኮ ጋር ያላቸው ግንኙነት ይሄን ያህል ጠንካራ የሚባል አይደለም:: ሞሪታኒያ ሙሉ ለሙሉ የእኛ ደጋፊ አገር ናት:: እንዳውም ሞሪታኒያኖች የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ አልጀዚራ ላይ ከቀረቡ ‹‹ኢትዮጵያ መብቷ ነው›› ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ናቸው:: ስለዚህ ስጋቴ ይህንን ያህል የጎላ ችግር ያመጣል የሚል እምነት የለኝም::
ሌላው የህዳሴ ግድቡ ሃይማኖታዊ ይዘት እንዲኖረው ያደረጉበትም ሁኔታ አለ:: ይህም ማለት ‹‹ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የምትገነባው እስራኤል ናት›› በሚል መላው ሙስሊም አለም እስራኤልን ስለማይወድ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑትን እንደነቱርክ ያሉትን ኢንዶኔዢያ፣ ማሌዢያ ሌሎች እስላማዊ አገሮችን ወደ ጎኗ ለማሰለፍ ያደረገችው ጥረት ነው:: ግን ይሄም አልተሳካም:: ስለእስራኤልና ኢትዮጵያ ግንኙነት ከምናወራ ይልቅ ስለ እስራኤልና ግብፅ ወዳጅነት ብናወራ ጥሩ ይመስለኛል:: ምክንያቱም ከፍተኛውን የእስራኤል እርዳታ የምታገኘው ግብፅ በመሆንዋ ነው:: ሁለተኛ ደግሞ አረባዊ የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ‹‹እኔ አስጨርስላችኋለሁ›› በማለት የእስራኤል ጉዳይ አስፈፃሚ ሆና እየሰራች ያለችው ግብፅ ናት:: ስለዚህ ይህ ደግሞ ሌሎች አገራትም ያውቁታል::
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ዲፕሎማሲያዊ ስራ ሰራችም፤ አልሰራችም አፍሪካ ላይ ያላት ተቀባይነት ከባድ ነው:: እንደኛ ነገር በቀኝ ግዛት ያልተገዛች አገር ናት፤ አድዋ ላይ የተደረገው ድል በመላው አፍሪካውያን ዘንድ የላቀ ስፍራ አሰጥቷታል:: የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና አድዋ ተመሳሳይ ናቸው:: ምክንያቱም መላው አፍሪካውያኖችን ለነፃነት በማነሳሳት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል:: ህዳሴ ግድብ ደግሞ አፍሪካ በልጆቿ ሀብት ብቻ ምንም ብድርና እርዳታ ከውጭ ሳትጠይቅ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ነው:: ግብፆች በነገራችን ላይ የሚፈሩት ይህንን ነው:: ኢትዮጵያ በአፍሪካ እያደረገች ያለችውን ነገር አልወደዱትም:: ምክንያቱም ሌሎች የተፋሰሱ አገራት ‹‹ኢትዮጵያውያኖች የጀመሩት አይነት እኛስ ለምን አንሰራም?›› ብለው ቢነሱና መጠቀም ሲጀምሩ ግብፅ በተለይም የታችኛው ተፋሰስ አገር በመሆንዋ ‹‹ድርሻዬ እየተመናመነ ይመጣል›› የሚል ስጋት ነው ያላት:: ለዚህም ነው የውሃ ድርሻ ላይ ማውራት የማይፈልጉት::
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውሃ ሙሌቱ የጎላ ጉዳት አያደርስብንም ማለታቸው ከልባቸው አምነውበት ነው ወይስ ህዝባቸውን ዝም ለማሰኘት ሲሉ የተናገሩት ነው?
አቶ ኡመር፡– ይህን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ በምክርቤታቸው የአፍሪካ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ነው:: ይሄ ንግግራቸው እኛም በጥርጣሬ ነው ያየነው:: በአጠቃላይ እውነታው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምንም ጉዳት እንደማያደርስ ምንም ክርክር የሚያስገባ ጉዳይ አይደለም:: ነገር ግን ግብፆች ረጅም አመት ሲያራግቡት የነበረው በአንድ ቀን ግልብጥ ብለው ጉዳት አያደርስብንም ማለታቸው እውነት ነው የሚለውን ነገር በደንብ እንድናይ ነው ያደረገን:: ግን እውነት አይደለም:: ምክንያቱም የመጀመሪያው ሙሌት ከመሞላቱ በፊት የግብፅ ሚዲያዎች አንዲት ጠብታ እንዳትነካ ሲሉ ማስፈራሪያ ሲያሰሙ ነበር:: ኢትዮጵያ ግን ምንም ሳትናገር ሞልታ ከጨረሰች በኋላ ‹‹ሞልቻለሁ›› አለች:: ከተሞላ በኋላ የግብፅ ሚዲያዎች በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ቅልብስ ብለው ‹‹የመጀመሪያው ሙሌት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ብቻ ስለሆነ በግብፅ ላይ ምንም ጉዳት አያደርስም፤ ስለዚህ ተረጋጉ›› ማለት ጀመሩ:: ይሄ ማለት አባይን ለውስጥ ፖለቲካቸው ሲጠቀሙበት እንደነበር ያሳያል:: አሁን ሁለተኛው ዙር ሙሌት ቢከናወንም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የምጠብቀው:: ምክንያቱም እውነታውም ይሄ ነው::
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ከመከናወኑ በፊት በዲፕሎማሲ ረገድ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ኡመር፡– ግብፆች እየሄዱበት ያለው ሁኔታ ከበድ እያለ ስለመጣ በተለይ ደግሞ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ‹‹ከግብፅ ድርሻ አንድ ጠብታ ውሃ መንካት ቀይ መስመር ነው›› ብለው ተናግረዋል:: በነገራችን ላይ ይሄ የቀይ መስመር ወሬ በእሳቸው ብቻ የተጀመረ ሳይሆን ሁሉም የግብፅ ፕሬዚዳንቶች ከጀማል አብዱልናስር ጀምሮ የነበሩት መሪዎች ሁሉ ተመሳሳይ ንግግር ሲናገሩ ነው የኖሩት:: በ1835 ዓም ደግሞ መሀመድ አሊ ፓሻ የሚባል የግብፅ ፕሬዚዳንት ‹‹እኛ እንቅልፍ የሚወስደን አባይን ከምንጩ መቆጣጠር ስንችል ነው›› ብሎ ዘመቻ ከፍቶብን አንደነበር በታሪክ ይታወቃል:: በሱዳን በኩል አድርገው ኢትዮጵያን ለመውረር ሙከራ አድርገዋል:: አሁን ላይ ደግሞ ዲፕሎማሲውን አጠናክረዋል:: ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት አንዳታከናውን ከፍተኛ ጫና እያደረጉ ነው ያሉት:: እርግጥ ነው ዝም ብለን ብንሞላም ምንም አይመጣም:: ግን የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ እንድናገኝ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራት አለበት:: በተጨባጭ የሚሞላው የውሃ መጠን ምን ያህል አንደሆነ የሚሞላውም በ2015ዓ.ም ካርቱም ላይ በሶስቱ አገሮች በተደረገው ስምምነት መሰረት እንደሆነ ማስረዳት ያስፈልጋል::
እኛ እየሞላን ያለነው በጉልበት ሳይሆን ሶስቱ አገራት በተስማሙት ስምምነት መሰረት መሆኑን ከፍተኛ ዲፕሎማሲ ስራ መሰራት መቻል አለብን:: ሌላው ትልቁ ነገር በማንም ላይ ጉዳት እንደማያመጣ ፣ አንዳውም ጥቅሙ እንደሚበልጥ የሚያሳዩ የተለያዩ ዶክመንተሪ ፊልሞችን ማሳየትም ተገቢ ነው:: በተጨማሪም ኢትዮጵያ ወዳ ሳይሆን ተገዳ ይህንን ፕሮጀክት እየሰራች መሆንዋን፣ እኛ በድህነት ውስጥ የምንኖር ህዝቦች መሆናችንን፤ አሁንም 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የመብራት ተጠቃሚ አለመሆኑን ማሳየት መቻል አለብን:: አሁን ድረስ በጭስና በኩበት የሚጋግሩ በርካታ እናቶች ምግብ ለማብሰል ሲሉ አይናቸው እየጠፋ እየተጎዱ ስለመሆኑ ማሳየትና በተጨባጭ ዶክመንተሪ መስራትና ማሳየት መቻል ይገባናል:: ግብፆች በርካታ ዶክመተሪዎችን ሰርተዋል፣ በአማርኛ ሳይቀር አስተርጉመውታል፤ በርካታ መፅሃፍቶችን ፅፈዋል፤ ይህንን የሚያደርጉትም በሃሰት ላይ ተመርኩዘው ነው:: እኛ ደግሞ ሃቁን ይዘን ወደኋላ ማለት የለብንም:: ከሙሌቱ በፊት እነዚህ ነገሮች መስራት ቢቻል የበለጠ የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ከጎናችን እንዲሆን ያግዛል::
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ ምሁራን ግድቡ የእኛ ነው ድርድር ውስጥ መግባቱ በራሱ ተገቢ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፤ እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ኡመር፡– እኔ በሁለት መንገድ ነው ከፍዬ የማየው:: ድርድሩ ሙሉ ለሙሉ አያስፈልግም ሳይሆን ከዚህ ቀደም ድርድሩ ወደ አሜሪካ ተጎትቶ የተወሰደበት ሂደት ተገቢ አይደለም ብዬ ነው በግሌ የማምነው:: አንደኛ ሶስቱ አገራት መነጋገር ነው የሚገባቸው፤ ጀምረውታልም ደግሞ:: አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ የተደረገበት ምክንያት በግብፅ ጫና እንደሆነ ይታወቃል:: ኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ ቢፈትኗትም ከአቋሟ ልትንፏቀቅ ባለመቻሏ ድርድሩ ወደ አሜሪካ እንዲሄድ አደረጉ:: ከመጀመሪያ መሄዷ ተገቢ አልነበረም:: ነገር ግን ምንም እንኳ ተጎትተን ወደ አሜሪካ ብንሄድም አንቀፆችን አንድ በአንድ በመመልከት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙርን ለመሙላትም ሆነ አባይን ለልማት ለመጠቀም ግብፅና ሱዳን ማስፈቀድ አለባት የሚል ወደ 1959ኙ የቅኝ ግዛት ውል ኢትዮጵያ ጎቶቶ ለማስገባት የተደረገ ጥረት ነው:: ይህንን ኢትዮጵያ በጀብደኝነት እምቢ ብላ መውጣቷ በታሪክ ሊመዘገብ የሚገባ ጉዳይ ነው:: አንደአጠቃላይ ድርድር አስፈላጊ ነው:: ባይሆን ስንደራደር የእኛን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት አደጋ ውስጥ በማይከትና ሉዓላዊነታችንን አሳልፎ በማይሰጥ ሁኔታ እንዲቀጥል ነው ማድረግ የሚገባው:: አሁንም በዚያ መልኩ ነው እየተከናወነ ያለው:: እንዳውም ኢትዮጵያ ያሰበችውን ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማትል ያሳየችበት ድርድር ነው:: ይሄ ድርድር በመኖሩ በእኔ በኩል አባይ የኢትዮጵያውያን መሆኑን ማሳየት አስችሎናል ባይ ነኝ:: በርካታ ግብፃውያን እኮ አባይ ከዚያው ከግብፅ የሚነሳ ነበር የሚመስላቸው:: ስለዚህ ይህንን ማሳየት በራሱ ቀላል ነገር አይደለም::
ሌላው መታወቅ ያለበት አባይ 11 አገራትን የሚስተሳስር አለምአቀፍ ወንዝ ነው:: አባይ ምንም እንኳ የእኛ ቢሆንም ከእኛ ሲወጣ ደግሞ ናይል ነው:: ይሄ በደንብ መታሰብ አለበት:: በእርግጥ ፈጣሪ በሰጠን ፀጋ አብዛኛው ውሃ ከእኛ ነው የሚሄደው፣ መልክዓምድሩ የተመቸ ነው፣ በርካታ ገባር ወንዞች አሉ:: ምንም እንኳን ይሄ ቢሆንም ሌሎች አገራትም የሚዋሰኑት ወንዝ በመሆኑ መነጋገሩ ጥሩ ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ:: እንዳውም ድርድር ውስጥ ባንገባ ኖሮ ሌላ ጫና ይፈጠር ነበር የሚል ሃሳብ አለኝ::
አዲስ ዘመን፡– በአገር ውስጥ በየቦታው የሚነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በግድቡ ግንባታ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅእኖ እንዴት ትገልጻለህ? በዚያ ረገድስ መሰራት ያለበት ነገር ምንድን ነው?
አቶ ኡመር ፡– ከዚህ አንፃር የግብፅ ሴራና እጃቸው በጣም ረጅም ነው:: ኢትዮጵያን ለማዳከም የሞከሩት በተለያየ መስክ ነው:: የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም:: ለምሳሌ ሊቢያ እያለሁ ሶስት ማዕዘን አፋር በሚል የተፃፈ መፅሃፍ ኢትዮጵያን ለመበታተን ምንያህል አደገኛ አካሄድ እንደሚከተሉ ያሳያል:: ይህም ማለት ኤርትራ፤ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ያለውን አፋር ተገንጥሎ አንድ ትልቅ አገር ለመፍጠር የወጠኑት እቅዳቸው በጣም ከባድ ነበር:: ቤኒሻንጉል ላይ ያለው ነገር ከባድ ነው:: ቤኒሻንጉል የሱዳን አካል ነው ወደ ማለት መጥተዋል:: ከዚህ ጀርባ ግብፆች ናቸው ያሉት:: አሁንም የግብፅ ሚዲያዎች እያራገቡት ነው ያለው ፣ ንፁሃን ዜጎች ቤኒሻንጉል ላይ እየተገደሉ ያሉት በግብፁ ሴራ እንደሆነ ግልፅ ነው:: ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎች መኖራቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አምኗል:: ስለዚህ በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች በግድቡ ላይ ተፅዕኖ አንደሚያሳድር ምንም ጥርጥር የለውም:: ይህም በዋናነት ግድቡን ሁላችንም በአንድ አይን እንዳናየውና እኩል ስሜት እንዳይኖረን ያደርጋል:: በመሆኑም በዚህ መንገድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል:: ነገር ግን የግድቡ ግንባታ እንዲሰናከል ያደርጋል ብዬ አላምንም:: እንዳውም የአገራችን ሰው ‹‹ሚስማር በተመታ ቁጥር ይጠብቃል›› አንደሚለው ችግሩ በበዛ ቁጥር ለግድቡ የምንሰጠው ትኩረት ስር እየሰደደ እና እየጠነከረ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ:: ምንአልባት አሁን የምናያቸው ነገሮች ያሳዝናሉ:: ምንም ጥርጥር የለውም:: ሰሞኑን በአጣዬ ፤ በከሚሴ የተከሰተውን ጉዳይ ግብፆች ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማፈራረስ ጊዜው አሁን ነው እያሉ ሁከት የተነሳባቸውን አካባቢዎች እየጠቀሱ ሲፅፉ ነበር:: ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ልንማር ይገባል:: ማንም እንደፈለገ እንዲያሽከረክረን መፍቀድ የለብንም:: ኢትዮጵያ እንድትፈርስ መፍቀድ የለበትም:: ይሄ ሴራ ነው፤ ምንጩ ሲደርቅ መድረቁ አይቀርም:: አንድ ግብፃዊ ፀኃፊ ለአገሩ መንግስት የሰጠው ምክር ግድቡን እንዲያፈርሱት ሳይሆን ኢትዮጵያኖች የግድቡን ደስታ እንዳያጣጥሙት ለማድረግ መስራትን ነው:: ይህም ማለት ገንብተነዋል ብለው ሲያስቡ በውስጥ በሚደረግ ጦርነት እንዳናጣጥመው እናደርጋለን ማለት ነው:: ስለዚህ እኔ ለመላው ኢትዮጵያውያን የማስተላልፈው መልዕክት ለውጭ ሴራ፣ ኢትዮጵያን ለሚያፈራርስ ነገር መተባበር የለብንም :: ዞሮ ዞሮ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን:: ሱዳንና ኢትዮጵያም አንድአይነት ህዝቦች ናቸው፤ ለምንድነው እርስበርሳችን የምንጣው:: ከጀርባው ያለውን ነገር በደንብ መመርመር መቻል አለብን:: ምክንያቱም የርስበርስ ግጭታችን አይጠቅመንም::
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ሰፊ ውይይት በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
አቶ ኡመር፡– እኔም አመሰግናለሁ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013