በብዛት ወጣት ከሚገኝባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ ታዲያ ወጣቱ ክፍል ከመስራትና አገርን ከማሳደግ ይልቅ ባልባሌ ትርክቶች ተጠምዶ እርስ በርስ ሲጋጭ ማስተዋል ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል። በአገሪቱ የሚሰራ ስራ ጠፍቶ ሳይሆን አለመስማማቶች በመበራከታቸው የሚሰሩ እጆች ለጥፋት እየዋሉ ይገኛሉ። በመንግስትም ደረጃ ጠንከር ያሉ ስራዎች ባለመከናወናቸው ዝርፍያና ቅምያ በከተሞች አካባቢ እየተስፋፋ ይገኛል። ይህን ጉዳይ ያለ ምክንያት አይደለም ያነሳሁት። ለጥፋት የሚውሉ እጆች እንዳሉ ሁሉ ለበጎ ተግባራት የሚሰነዘሩ እንዳሉ ለማሳየት ፈልጌ ነው። የተቸገሩ አረጋውያንንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚደግፉና አለንላችሁ የሚሉ በርካታ በወጣቶች የተመሰረቱ ማህበራት እንዳሉ በዚሁ አምዳችን አስቃኝተናችሁ ነበር። አብዛኛዎቹ ማህበራት እውቅናና ፈቃድ አግኝተው እርዳታ በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቱ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን፤ አቅመ ደካማዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በሁሉም ቦታዎች እየተቀጣጠለ ሲሆን፤ በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ወጣቱ ግንባር ቀደም ነው። መንግስትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቸገሩትን በማብላትና ቤታቸውን በመጠገን ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው። ይህም እንቅስቃሴ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ነው። የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ በሁሉም ቦታዎች በጎ አድራጎት ማህበራት እየተበራከቱ ይገኛል። በተለይ የህብረተሰቡን ችግር ከስሩ ለመፍታት ውጤታማ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
ሰው ከእንስሳ ከሚለይባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ከፍ ያለ አስተሳሰብ የሚያራምድ አእምሮ ባለቤት መሆኑ ነው። ይህ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ለሰዎች በምናደርገው ድጋፍ ነው። በአገራችን ሰዎችን መርዳት እንደ ጠንካራ ባህል የሚወሰድ በጎ ተግባር ነው። ሰውን መርዳት እንደ ፅድቅ የሚቆጠር ተግባርም ነው። አብዛኛው ለፈጣሪው ይበልጥ የሚቀርብበት መንገድ አድርጎ ስለሚቆጥረው በተለያዩ አካባቢዎች ድሆችን መርዳት የተለመደ ነገርም ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት በጎ ተግባራት አሁን…አሁን ከተወሰኑ ምክንያቶች ጋር ብቻ እየተያያዙ በሌላ ጊዜ የሚጠፉበት ሁኔታ ይስተዋላል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ አቅም የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳትና ለመደገፍ ብዙ በጎ አድራጎት ማህበራት ተመስርተዋል። ማህበራቱ የእለት የምግብ ድጋፍ ከማቅረብ በተጨማሪ በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ እስከማድረስ ተሻግረዋል። ማህበራቱ በወጣቶች የተደራጀ በመሆኑ የደም ልገሳ፣ የከተማ ፅዳት እንዲሁም ቤት ለቤት በመሄድ አቅመ ደካሞችን በስራ እያገዙ ይገኛሉ። በሁሉም ክልሎች በዓላትን ጠብቆ ቤት የማደስ፣ ማዕድ ማጋራት እንዲሁም በዘላቂነት ድጋፍ የሚፈልጉትን በመደገፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውጤታማ ስራ ሰርቷል። ይህም ስራ ብዙ ወጣቶችን አበረታትቶ በአሁኑ ወቅት ብዛት ያላቸው ማህበራት ፈቃድ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ መንገድ ከፍቶላቸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የተቋቋሙት የበጎ አድራጎት ማህበራት ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ባላቸው አቅም እርዳታ ቢያደርጉም ከህብረተሰቡ ግን የሚፈለገውን ያህል ተቀባይነት እያገኙ አይደሉም። ህብረተሰቡ ያለውን በአቅሙ እንዲያዋጣ ሲጠየቅ ከመሳደብ እስከ መማታት የደረሰ ሁኔታ እንደሚፈጠር ብዙ ማህበራት እንደ ችግር ያቀርባሉ። ህብረተሰቡም አጭበርባሪዎች በመብዛታቸው ህጋዊውን ማህበር ለመለየት ተቸግረናል የሚል መማረር ያሰማል። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው የበጎ አድራጎት ማህበራትና ህብረተሰቡ ተጋግዞ የሚሰሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።
ለዛሬ የመረጥነው በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንን በመደገፍ የሚታወቀው ህሊና የበጎ አድራጎት ማህበርን ነው። ማህበሩ የተመሰረተው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቢሆንም በቻለው አቅም አረጋውያንን እየጦረ ይገኛል። ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም ሁሉን ተቋቁሞ ድጋፍ ማድረጉን ቀጥሏል። ስለማህበሩ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ከማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ዮርዳኖስ በቀለ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
የማህበሩ አመሰራረት
ማህበሩ በህጋዊነት ከመመስረቱ በፊት በአንድ ሰፈር አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች የተለያዩ ስራዎችን ያከናውኑ እንደነበር ወጣት ዮርዳኖስ ይናገራል። በሚኖርበት ሰፈር የሚገኙ ወጣቶች በመሰባሰብ ቤት የፈረሰባቸውን አረጋውያን ቤታቸውን በማደስ እንዲሁም ሌሎች ስራዎችን ከህብረተሰቡ ገንዘብ በመሰብሰብ ይከናወን ነበር። በወቅቱ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንደነበሩም ይናገራል። በአሁኑ ወቅትም የማህበሩ አባላት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እየተማሩ እንዳለም ይጠቅሳል። እንደ ማህበር በህጋዊነት መንቀሳቀስ የጀመሩት መስከረም 17 ቀን 2012 ዓ.ም ላይ ነበር። በወቅቱም ማህበሩ የሚተዳደርባቸውን ህግና ደንቦች በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱንም ይናገራል።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ ሲመሰረት በዋነኝነት ዓላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አረጋውያንን በመርዳት ላይ ሲሆን፤ አረጋውያኑን ማሳከም፣ ቤት ለሌላቸው ቤት በመስራት እንዲሁም ከፍተኛ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ ከባለሀብቶች ጋር በማገናኘት እንዲረዱ እንደሚደረግ ይጠቅሳል። በሌላ በኩልም ለአረጋውያኑ ቤት ለማግኘት ከሚመለከተው የአስተዳደር ክፍል ጋር በመነጋገር የቀበሌ ቤቶች የማሰጠት ስራ እንደሚከናወን ይናገራል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ቤታቸው የፈረሰባቸውን አረጋውያን የመጠገንና የማደስ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቀሰው ወጣት ዮርዳኖስ፤ በገንዘብም የሚደጎሙበትን ሁኔታ ማህበሩ እያመቻቸ እንደሚገኝም ይናገራል። የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በከተማው በመዞር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ይጠቁማል። በቦዲቲ ከተማ በግንባር ቀደምትነት ስለ በሽታው ማስተማር የጀመረው ማህበሩ ሲሆን፤ የእጅ ማስታጠብ ስራዎች መከናወናቸውን ይገልፃል። ታመው በቤታቸው የነበሩ ህሙማንን እንዲታከሙ የማድረግ ስራም መሰራቱን ያስረዳል።
አረጋውያንም ቤታቸው ሲፈርስባቸው ከሰው በሚገኝ ጥቆማ ቦታው ድረስ በመሄድ ታይቶ ለማደስ ወደ ስራ እንደሚገባ ይገልፃል። አብዛኛው የከተማው ነዋሪ የማህበሩን የስራ እንቅስቃሴ ስለሚያውቅ በችግር ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንን እንዲረዱ ወደ ማህበሩ እንደሚያመጣ ያመለክታል። ማህበሩም በየአካባቢው በመሄድ ድጋፍ የሚፈልጉ አረጋውያንን እንደሚረዳ ይጠቅሳል። ማህበሩ ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ ስለሌለው ከሰዎች በሚያገኛቸው ድጋፎች ስራዎችን እንደሚያከናውን ይገልፃል። የትንሳኤን በዓል ከአረጋውያኑ ጋር ለማክበር ከአካባቢው ማህበረሰብ የገንዘብ መዋጮ መደረጉንም ያመለክታል።
ከከተማው አስተዳደር እስካሁን ይህ ነው የሚባል ድጋፎች እየተደረጉ አለመሆኑን የሚጠቅሰው ወጣት ዮርዳኖስ፤ እስካሁን ማህበሩ የሚንቀሳቀሰው ግለሰቦች በሚያደርጉለት ድጋፎች መሆኑን ያመለክታል። ከመንግስት ጋር አብሮ ለመስራት ጅምር እንቅስቃሴ ቢኖርም አብዛኛው ለፖለቲካ ትርፍ እየተጠቀሙበት በመሆኑ ሳይሳካ መቅረቱን ይናገራል። እስካሁን በቋሚነት ከመንግስት የሚደረግ ምንም አይነት ድጋፍ አለመኖሩን ያብራራል።
ሌላው የማህበሩ አባል የሆነው ወጣት ሳምሶን ሳዶር እንደሚናገረው፤ ማህበሩ አንድ አካባቢ በሚኖሩ ወጣቶች ጥምረት የተመሰረተ ነው። ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ አረጋውያንን መደገፍና ተንከባካቢ የሌላቸውን ሰዎች የመርዳት ስራ አከናውኗል። የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ህብረተሰቡን የማስተማር ስራ እንዲሁም በበዓላት ወቅት ለአረጋውያኑ አስፈላጊ ግብዓቶች ይሟሉላቸዋል። ለአረጋውያኑ አልባሳትን በማልበስ፣ ምግብ ነክ የሆኑ እና ዱቄትና ዘይት ገዝቶ በመስጠት ድጋፍ ያደርጋል።
ለአረጋውያን የሚደረጉ አብዛኛዎቹ ድጋፎች ከህብረተሰቡ የሚሰበሰቡ ሲሆን፤ በጎ ፈቃደኛ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችና አቅም ካላቸው ባለሀብቶች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ እንደሆነ ወጣት ሳምሶን ይጠቅሳል። በሌላ በኩል ደግሞ ከአባላት በሚገኝ ወርሃዊ መዋጮ ድጋፎች እንደሚደረጉ ይገልፃል። የከተማው መስተዳድር ለማህበሩ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። የእቃ አቅርቦትም በተወሰነ መንገድ አስተዳደሩ እንደሚረዳ ይጠቅሳል። የአካባቢውም ህብረተሰብ በቻለው አቅም ስራዎችን በትብብር እንደሚሰራ ያመለክታል።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ቦዲቲ ከተማ ላይ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ የተለያዩ አላማዎችን በመያዝ አጠቃላይ በወላይታ ዞን ለመስራት ያቀደ ነው። ከፍተኛ የሚባሉ ችግሮች እስካሁን ያላጋጠሙ ሲሆን፤ ማህበሩ እየሰራ ባለው ሁኔታ ላይ የመንግስት ድጋፍ ቢታከልበት ወላይታ ዞን ውስጥ የሚገኙ ባለሀብቶችም ድጋፍ ቢያደርጉ ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለ ወጣት ዮርዳኖስ ያመለክታል።
ለአረጋውያን ቤት ለመስራት ገንዘብ ለማሰባሰብ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ በመግለፅ፤ ከኪስ በሚደረግ መዋጮና ከሰዎች በሚገኝ ገንዘብ እየተሰራ መሆኑን ወጣት ዮርዳኖስ ያብራራል። ባለፈው ዓመት ለሶስት አረጋውያን ቤት ለመስራት እንጨት የተገኘ ቢሆንም ቤቱን ለመስራት የሚያስችል ገንዘብ በማጠሩ ስራዎች መቆማቸውን ያስታውሳል። እስካሁንም ቤቱ አለመሰራቱንም ይጠቅሳል። በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች በተቻላቸው አቅም ለማህበሩ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ያመለክታል። ቋሚ ገቢዎች ቢኖሩ ብዙ መስራት እንደሚቻል ያስረዳል።
ወጣት ሳምሶን ሳዶር እንደሚናገረው ከሆነ፤ ማህበሩ ስራዎችን የጀመረ አካባቢ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት እንቅፋቶች ይፈጠሩ ነበር። በዚህም በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አስቸጋሪ የነበረበት ወቅት ነበር። በሂደት የማህበሩን ስራ ህብረተሰቡ ሲመለከት ወደ መደገፍ ገብቷል። የከተማ አስተዳደሩ በቻለው አቅም ለአረጋውያን ቤት ሲሰራ ቆርቆሮ በመስጠት ትብብር ያደርጋል። እንጨትና ሚስማርም ገዝተው ለማህበሩ አበርክተዋል። የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ቦታ ላይ ማህበሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
ማህበሩ ለመስራት ያሰባቸው ብዙ ስራዎች አሉ። የራሱ የሆነ ቦታ ቢያገኝና ቢሮዎች ቢመቻቹ አረጋውያኑን በዘላቂነት የመርዳት ሀሳቦች እንዳሉት ወጣት ዮርዳኖስ ይናገራል። የቦታውን ጉዳይ የከተማ አስተዳደሩ እንዲመቻች ጥያቄ ቀርቦ ቃል መገባቱንም ይጠቅሳል። ማህበሩ በዋነኛነት ዓላማ አድርጎ የሚሰራው የተቸገሩ ሰዎችን አብዛኛው አረጋውያንን መርዳት ነው። ከመንግስት በኩል አስፈላጊ የሚባሉ ድጋፎች ቢደረጉ ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚቻል ይጠቁማል። በመገናኛ ብዙሀን በኩልም ስለማህበሩ የሚሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ድጋፍ ለማግኘት እንደሚረዳ ያስረዳል። በቀጣይ በህፃናት ዙሪያ ለመስራት መታሰቡን ይናገራል።
በቀጣይ ማህበሩ ጥሩ ስራዎችን ለማከናወን እቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ ይገኛል። አሁን ካለው ቦታ የተሻለ ሰፋ ያለ ስፍራ ቢገኝ አረጋውያንን አንድ ላይ ሰብስቦ የመደገፍ ሀሳብ እንዳለ ወጣት ሳምሶን ሳዶር ይጠቁማል። በየመንገዱ ወድቀው የሚገኙ አረጋውያንን በመሰብሰብ በቋሚነት የሚጦሩበት ሁኔታ ለማመቻቸት ሀሳብ እንዳላቸው ያመላክታል። በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን በመሰብሰብ ድጋፍ ለማድረግ መታሰቡን ያብራራል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013