የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 13ኛ መደበኛ ስብሰባ “ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)” እና “ሸኔ”ን በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህ መሰረት ሁለቱ ድርጅቶች በሽብርተኝነት ተፈርጀዋል።
እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በዚህ ደረጃ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ያደረጋቸው በርካታ መነሻዎች እንዳሉ ይታወቃል። ድርጅቶቹ ቀደም ሲል አይንና ናጫ መስለው አንዱ አሳዳጅ፤ ሌላው ተሳዳጅ ሆነው ቢቆዩም በኢትዮጵያ የመጣውን አዲስ የእድገትና የዴሞክራሲ መንገድ ሲመለከቱ ግን ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በማድረግ በጥፋት መንገድ ላይ አብረው ለመጓዝ አላዳገታቸውም። በዚህም መሰረት በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የጥፋት መንገዶችን በጋራ በመቀየስና በመናበብ ጥፋት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)ን ስንመለከት ለ27 ዓመታት በስልጣን ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ቆይቷል። በተለይ በዚህ የስልጣን ዘመኑ ካደረጋቸው በጎ ስራዎች ይልቅ በትውልዱ ላይ ጥሎ የሄዳቸው ጠባሳዎችና ቁርሾዎች ዛሬም ለተፈጠሩ ችግሮች መነሻዎች ናቸው። የድርጅቱ ራሶች ከሃገራዊ አንድነት ይልቅ ህዝብና ህዝብን በማጋጨት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር በሃገሪቱ እንዲንሰራፋ በማድረግና ከዚያም አልፎ ዜጎች በሃገራቸው በሰላም እንዳይኖሩ በርካቶችን ስደተኛና ሃገር አልባ አድርጎ የቆየ ነው።
ይህ ኃይል በተባበረ የህዝብ ትግልና በውስጥ በተፈጠረ እምቢተኝነት ከስልጣን ላይ ሲነሳ በሰራው ክፋት ልክ አልተገፋም። ይልቁንም ላለፉት ችግሮች ይቅርታ ተደርጎለት በአመራር ላይ እንዲቆይ የለውጥ ሃይሉ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቦለታል። ቡድኑ ግን “እኔው አቡክቼ እኔው ካልጋገርኩ” በሚል ብሂል እሱ በሚፈልገው መንገድ ከላይ ሆኖ ካላዘዘ መኖር አልፈለገምና ይህንን መንገድ ሳይቀበል ቀርቶ የተሰጡትን ዕድሎች ሁሉ ወደማበላሸት ተሸጋገረ።
በዚህም አንድ እግሩን በመንግሥት ስልጣን ውስጥ ሌላ እግሩን ደግሞ የሽብር ድርጊት ውስጥ በመዝፈቅ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሽብር ተግባራት እንዲፈጠሩ በፋይናንስና በሰው ሃይል ሲደግፍ ቆይቷል። በለውጡ ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ከተከሰቱ 113 የወንጀል ተግባራት ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጁን በማስገባት ዓላማው ሽብር መሆኑን በገሃድ አሳይቷል።
ቡድኑ “ትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ” በማለት ህገወጥ የታጠቀ ሃይል በማደራጀት ወደለየለት የጥፋት መንገድ ጉዞ ጀመረ። በፌዴራል ፖሊስ፣ በሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ በደህንነት እና ሌሎች ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ላይ የነበሩ አባላቱንና የጦር መኮንኖችን በማሰባሰብና አዳዲስ ወጣቶችንም በስፋት በመመልመል ራሱን የቻለ ወታደራዊ ሃይል በማዘጋጀትም በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ፈፀመ።
ይህ ቡድን ታዲያ ራሱ በለኮሰው ጠብ አጫሪነት በአጭር ጊዜ ተመትቶ ቢፈረካከስም የቡድኑ ፍንጥርጣሪዎች እዚህም እዚያም የተበተኑ በመሆኑ በቀላሉ የሚፀዳ አልነበረም። የተበታተኑት የቡድኑ አባላትና ከውስጥና ከውጭ ያሉ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ቡድኑ አልሞተም ለማለት ወደለየት የጥፋት መንገድ በመጓዝ የአጥፍቶ መጥፋት ስራ ውስጥ ገብተው ህይወት ማጥፋት፣ ንብረት ማውደምና ዜጎችን ማሸበር አዲስ የጥፋት መንገዳቸው አድርገዋል።
በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሸኔም ልክ እንደ ህወሓት እታገልለታለሁ ለሚለው ህዝብ አንዳችም ፋይዳ ሳይሰጥ ጥፋትና የሽብር ድርጊት መገለጫው ሆኖ የኖረ ነው። ይህ ቡድን ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) የወጣ ወታደራዊ ክንፍ ሲሆን ወደሰላማዊ ትግል እንዲመለስ ጥሪ ቢቀርብለትም ፈቃደኛ ሳይሆን በተለያዩ የሽብር ተግባራት ተሰማርቶ ቆይቷል።
ይህ ቡድን በተለይ በተለያዩ ኦሮሚያ ዞኖችና በውጭ ሃገር በመንቀሳቀስ በርካታ ጥፋቶችን ፈጽሟል። በ2013 ዓ.ም ብቻም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 463 ሰዎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን አድርሷል። 160 መኖሪያ ቤቶች፣ 44 ተሽከርካሪዎች፣ 84 የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን አቃጥሏል።
ቡድኑ ሃገር የማስተዳደር ፍላጎትና ዓላማ ቢኖረው የተለያዩ አማራጮችና እድሎች ነበሩ ይሁንና ያንን እድሉን ሳይጠቀምበት ወደ ጫካ በመግባት የሽብር ድርጊቱ ውስጥ ተዘፈቀ። ለመላ ኢትዮጵያውን የመጣው እድል ተጠቅሞ በሰላማዊ መንገድ መታል ቢቻልም ይህንንም ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የሰርክ ተግባር አድርጎ በያዘው የሽብር ተግባር በርካቶች ላይ ጉዳቶችን አድርሷል።
በመሆኑም ይህ ቡድን የፖለቲካ ርዕዮቱን ለማሳካት በትጥቅ የተደገፈ ጥቃት በመከተል እና ንፁሃን ዜጎችን በመግደል እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ እያደረገ ይገኛል።
በመሆኑም እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሃገራችን የጀመረችው የብልፅግናና የአንድነት ጉዞ ወደፊት እንዳይራመድ ትልቅ እንቅፋት በመሆናቸውና ዜጎችም በህገመንግስቱ የተጎናፀፉትን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በሚጋፋ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የሰላም ጠላቶች በመሆናቸው በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ተገቢ ነው። አሁን ሃገራችን የምትፈልገው በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉና ሃገራቸውን ወደፊት ማሻገር የሚችሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶችን በመሆኑ ሰላማዊ መንገድ ብቸኛው አማራጭ ነው። የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔም ቀደም ሲል አባላቱ ሲጠይቁና ሲታገሉበት የነበረ ሰላምን የማረጋገጥ አንድ አካል በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ይህ ሲሆን ዘላቂ ሰላማችን ይረጋገጣል፤ የሃገራችንም መፃኢ እድልም ብሩህ ይሆናል። የኢትዮጵያ ብልጽግናም ይረጋገጣል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013