የዛሬዎቹ የዓለማችን ፍርድ ቤቶች ፣ ችሎቶች የበርካታ ሺ ዓመታት ሒደታዊ ለውጥ ውጤት ናቸው፡፡ የሕግ ታሪክ ከየትነት ከባቢሎን እስከ ፋርስ፣ ከግሪክ እስከ ሮማ ፣ ከአውሮፓ እስከ ፈረንሳይ ፣ ከግብፅ እስከ ኢትዮጵያ ያካለለ ነው፡፡ ከታላቁ መፅሐፍ ፣ ከቅዱስ ቁራን ፣ ከባህላዊ ፣ ሃይማኖታዊ ዳኝነቶች ተቀድቶ የተቀመረ ነው ፡፡
በሀገራችንም የመጀመሪያው ሕገ መንግስት እስከረቀቀበት 1923 ዓ.ም ፣ በእንግሊዝ እገዛ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከተሰየሙበት ፣ የፍትሐብሔርና የወንጀል ሕጎችን ከፈረንሳይና ሌሎች ሀገራት አምጥተን እስክናነብር በፍትሐ ነገስትና በባህላዊ ሽምግልና ነበር
የምንዳኘው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ፣ የአየር መንገድ ፣ የቴሌኮምንኬሽን ፣ የባንክ ፣ የአውራ ጎዳና ፣ ወዘተ. ድርጅቶች ቀደምት መስራቾች የውጭ ሀገር ዜጎች እንደነበሩት ሁሉ የሀገራችን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት እንግሊዛዊ እንደነበር ይወሳል፡፡
በፍርድ ቤቶች ፍትሕ ሲከበርም ፣ ሲዛባም ፣ ሲጓደልም አጋጥሞን ያውቃል፡፡ በችሎት አዳራሽ የበዳይና የተበዳይ ወገኖች ለጠብ ሲገባበዙ ፣ አንዱ በሌላው ላይ ከንፈሩን ሲነክስ ፣ አይኑን ሲያጉረጠርጥ አይተናል፡፡ የሟች ወገኖች በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተደስተው ችሎቱን በእልልታ ሲያቀልጡት በተቃራኒው የገዳይ ወገኖች ችሎቱን በዋይታ ሲያደባልቁት ታዝበናል፡፡ ተከሳሾች በማዕከላዊ ፣ በፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ስም የተፈፀመባቸውን ግፍ ፣ ስቃይ ልብሳቸውን ሱሪያቸውን አውልቀው ሰንበራቸውን ፣ የተኮላሸ ብልታቸውን ለችሎቱ ሲያሳዩ የተበዳይ ወገኖችና ታዛቢዎች በእንባ ሲራጩ ተመልክተናል ፡፡
ተጠርጣሪዎች ስማቸው ሲጠራ አቤት ባለማለት ከመቀመጫቸው ባለመነሳት ችሎቱን ወይም ዳኞቹን ገለልተኛ አይደለህም ብለው ሲቃወሙ አይተናል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱን ነጻነት ሲሞግቱ ታዝበናል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ከችሎት አደባባይ የተነፈጉትን ፍትሕ በእጃቸው ሊቀዳጁ ሲሞክሩ ፣ ሌሎች ፍትሕን ከችሎት አደባባይ በላይ ከፈጣሪ ሲለማመኑ ተመልክተናል፡፡
በሀገራችን ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀዋሳ በአንድ ጠበቃ ላይ ከተፈፀመ ግድያ በቀር የተለመደ ባይሆንም በኮሎምቢያ ፣ በሜክሲኮ ፣ በኤልሳቫዶር እና በሌሎች ሀገራት ጠበቆች ፣ ዳኞች ሲታገቱ ፣ ሲገደሉ በቴሌቪዥን መስኮት አይተናል፡፡ በፈጠራው ዓለም ችሎትም በዊሊያም ሼክስፔየር” የቬኑስ ነጋዴ “ሻይሎክ ከአራጣ ተበዳሪው መቀመጫ ሙዳ ስጋ ለመቁረጥ ሲቋምጥ አንብበናል፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 4 /2019 በዩናይትድ ስቴትስ ዳላስ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በአንዱ የሆነው ግን በአግራሞት ፣ በአድናቆት እጅን በአፍ ያስጫነ፣ ታዳሚውን ፣ ተከሳሹን ፣ ዳኛዋን ሳይቀር በእንባ ያራጨ ፤ በቴሌቪዥን ፣ በዩቲውብ የተመለከቱትን ሚሊዮኖችን ሳይቀር ያስለቀሰ ፣ የይቅርታን ጥግ ያመላከተ ነበር፡፡ የሟች ታናሽ ወንድም ቦታም ጅን ከተቀመጠበት የምስክር ሳጥን ድንገት ልብን በሚሰብር ድምፅ እንባ ያቀረሩ አይኖቹን ወደ እለቱ ዳኛ ወርውሮ በዚያ ችሎትም ሆነ በሌሎች ፍርድ ቤቶች ተጠይቆ የማያውቅ እንግዳ ጥያቄ ለዳኛዋ አቀረበ፡፡ “ ክብርት ዳኛ ! ይፈቀድ አይፈቀድ አላውቅም፡፡ የወንድሜን ገዳይ አምበርን አቅፌ ይቅርታ እንዳደረግሁላት እንድነግራት እባክዎ ይፍቀዱልኝ!? “
ዳኛዋ ያልጠበቁት እና ስሜታቸውን የነካ ጥያቄ ስለነበር እንባቸውን በመሀረባቸው እየጠረጉ ዝም ሲሉት አይን አይናቸውን እያየ አንጀትን በሚበላ ለሆሳስ እንደገና “ እባክዎ …! ? “ ሲል ይማፀናቸዋል፡፡ ዳኛዋም በመጨረሻ ይሁንታቸውን ሰጡት፡፡ አምበር ከተከሳሽ ሳጥን ተነስታ ቦታም ከምስክሮች ሳጥን ተነስቶ ከዳኛዋ ፣ ከታዳሚው፣ ከዓለም ካሜራ ፊት ፤ ለዓመታት ተነፋፍቆ እንደተገናኘ ፍቅረኛ ተቃቀፉ ፡፡ በሳግ ስቅስቅ ብለው ተላቀሱ ፡፡ ይሄን ከስንት አንድ የሚያጋጥም የችሎት ውሎ መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎች ለመላው ዩናይትድ ስቴትስ አዳረሱት ፡፡
ነጭ አክራሪ ፣ ለዘብተኛ ፣ ኢንዲያንስ ፣ ጥቁር፣ እስፓኒክ ፣” ብላክ ፓንተር “ ፣ ብላክ ላይፍ ማተር፣ ዴሞክራት ፣ ሪፐብሊካን ፣ ቲ ፓርቲ ፣ ኬ ኬ ኬ …፤ ሳይለይ ፡፡ ቦታም በእቅፉ ስር ሆና ስቅስቅ ብላ በጸጸት የምታነባውን የታላቅ ወንድሙን ገዳይ” እንደ ሰው እወድሻለሁ፡፡ ምንም አይነት ክፉ ነገር እንዲደርስብሽ አልፈልግም፡፡ “ ሲል አደመጡት፡፡ ዓለም ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ተመለከተው፡፡ ችሎቱ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ዋይታ ቤት ይመስል በለቅሶ ተሞላ፡፡
የወንድማችንን ፣ የእህታችንን ፣ የአባታችንን፣ የእናታችንን ፣ የምንወዳትን ፣ የምንወደውን ፣ የቅርብ ቤተሰቦቻችንን ገዳይ ለዛውም ተመጣጣኝ ፍርድ ባልተሰጠበት ችሎትና ሚዲያ ፊት ይቅር ማለት ለዛውም ገዳይን አቅፎ ማፅናናትን ለአፍታ በምናባችን ስናንሰላስለው ተምኔታዊ (utopian )ከአእምሮ በላይ ቢሆንም ፤ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርሁት ዳላስ በዋለው በዚህ ታሪካዊ ችሎት ከሰውነት በገዘፈ ተክለ ሰብዕና ወጣቱ ቦታም ጅን ለዓለም ተገልጧል ፡፡
ይህ የይቅርታ እጅ የተዘረጋው ገዳይ የታላቅ ወንድሙ መኖሪያ ቤቱ ድረስ ሄዳ ለፈፀመችው ግድያ በ10 ዓመት እስር ብቻ እንድትቀጣ ከተወሰነባት በኋላ ነው ፡፡ ቦታም ይሄን ሲያደርግ ነጭ ስለሆነች ነው ቅጣቱ የቀለለላት በሚል ቅሬታ በችሎቱ አዳራሽ የሚሰማው ጉርምርታም ጋብ አላለም ነበር፡፡ ስለዚህ የይቅርባይነት ጥግ የሰማሁት ከCNN ጉምቱ ጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፓር ነው፡፡
የችሎቱን ውሎ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል ዩቲውብ ላይ ሰውነቴን እየወረረኝ እንባ እየተናነቀኝ ደግሜ ደጋግሜ ተመልክቸዋለሁ፡፡ ምን ይሄ የይቅርባይነት መንፈስ አትላንቲክን በተአምር ቀዝፎ ቀጣናውን አሳብሮ ኢትዮጵያን ባዳረሰ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ይቅርባይነት ፣ ፍቅር ግዘፍ ነስቶ የሚዳሰስ የሚጨበጥ መሆኑን ነው የተገነዘብሁት፡፡ በሟች ፣ በሟች ወንድምና በገዳይ መካከል የተገነባው የቂም ፣ የዘር ፣ የቀለም ፣ የመልካዕ አጥር ፈርሶ በዳላሱ ፍርድ ቤት ይቅርታና ፍቅር ሲነግስ ስመለከት በዚያ የተገኘሁ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡
ሰው የመሆን ሚስጥሩ የተገለጠበት ክስተት ከመሆኑ ባሻገር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደ ፈጣሪ ፍጹም ፍቅር የተገለጠበት መለኮታዊ ክስተት ነው ፡፡ ወጣቱ ቦታም ያለበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይቅርባይነትና ፍቅር ከፍ ብሏል፡፡ ጥላቻ ፣ ልዩነትና ዘረኝነት አየሩን ፣ መልክዓውን በተቆጣጠረበት ዓለም ይህን መሰል ይቅርታ ከሰማይ እንደወረደ መና ቢቆጠር ሊያስደንቀን አይገባም፡፡
የሟች ወንድም ቦታም ጅን ገና የ18 አመት ብላቴና እያለ ነው ይቅርባይነትን ኖሮ በተግባር ያሳየን ፡፡ የልጅ አዋቂ ሆኖ የይቅርባይነትን አይን ፣ ልቡና የገለጠልን ፡፡ብዙዎቻችን አይደለም በቦታም እድሜ በማምሻ እድሜያችን እንኳ ደፍረን “ ይቅርታ ! “ ለማለት ይተናነቀናል፡፡ በፋና ቴሌቪዥን ከወላጅ እናቱ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ ተኮራርፎ ባለፈው ጥምቀት ሰሞን እንደታረቀ ስንሰማ ብዙዎቻችንን አስገርሞን ነበር ፡፡
ዳሩ ግን ቂምን በቀልንና ጥላቻን እንደተሸከምን የምናልፍ ፣ ወደ መቃብር የምንወርድ መኖራችንን ስንረዳ እናቱን ይቅር ባለው ጎልማሳ ብንጽናና አይፈረድም ። በእውር ቤት አንድ አይና ብርቅ ነው እንዲሉ፡፡ በወላጆቻችን ፣ በእህት ወንድሞቻችን ፣ በትዳር አጋሮቻችን ፣ በልጆቻችን ፣ በቅርብ ዘመዶቻችን ፣ በአብሮ አደጎቻችን ፣ በክፍል ጓደኞቻችን ፣ በመምህራኖቻችን ፣ ወዘተ . እንዳኮረፍን ፣ ቂም እንደያዝን ከዚህ ዓለም በሞት እንለያለን ፡፡ ባስ ሲልም ከራሳችን ጋር ሳይቀር እንደተጣላን እንደተኳረፍን ወደማይቀርበት ዓለም እንሄዳለን፡፡
ሌሎቻችን ደግሞ ከአምላካችንና ከተፈጥሮ ጋር እንደተጣላን ይቅር ሳንባባል እንሞታለን፡፡ ቦታም ጅን ግን ከዚህ አልፎ የሚወደውን የታላቅ ወንድሙን ገዳይ ነው ይቅር ያላት ፡፡ አንዳንዶቻችን ፌስቡክ ፣ ቲዊተር፣ ቴሌግራም ፣ ኢኒስታግራም ፣ ዩቲውብ ፣ ወዘተ . ላይ በተሰጠን አስተያየት መልስ ለመስጠት እንቅልፍ የምናጣ፣ የስድብ ውርጅብኝ የምናወርድ ፣ ይህ አልበቃ ብሎን ጉድኝታችንን የምናቋርጥ unlike የምናደርግ ከፍ ሲልም ጥርቅም አርገን የምንዘጋ block በማድረግ ቂማችንን የምንወጣ ጉዶች ነን ፡፡
በጥሞና በሰከነ አእምሮ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ልዩነትን የመፍታት ልምምድ የለንም፡፡ ፈልጎ ፣ ወዶና ፈቅዶ ባላገኘው ማንነት ሳይቀር የምንጣላ ፣ ቂም የምንይዝ እና ለበቀል የምንነሳ ስንት ደመ ነፍሳውያን አለን፡፡ በቀደሙ ነገስታት የተፈፀመን ስህተት በዚህ ትውልድ ለማወራረድ የምንቀዠቀዥ ከንቱዎች ነን ፡፡ ቦታም “ ይፈቀድ አይፈቀድ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የወንድሜን ገዳይ አቅፌ ይቅር እንድላት የተከበሩ ዳኛ ሊፈቅዱልኝ ይችላሉ !? እባክዎ ! “ የሚለው ድምፅ ዛሬ ድረስ በእዝነ ህሊናዬ ይሰማኛል፡፡ የዕለቱ ዳኛ ታሚ ኬምፕ ባልጠበቁት ጥያቄ ግራ ተጋብተው ይሁን በጅን የይቅርባይነት ልብ ልባቸው ተነክቶ ለደቂቃዎች ዝምታን ከመረጡ በኋላ ሲፈቀዱለት የሚያሳየውን ምስልም በመደነቅ ከመድገም በላይ ሰላልሸዋለሁ፡፡
የወንድሙ ገዳይ የዳላስ ፖሊስ ባልደረባ የነበረችው ነጯ አምበር ጉይገርም 911 ላይ ደውላ ከተናገረችው እንደተደመጠው ፤ “ ስራ ውየ ቤቴ እንደደረስሁ በሩ ተከፍቶ ጠበቀኝ፡፡ እኔም ሌባ የገባ ስለመሰለኝ ሽጉጤን አቀባብዬ ወደ ሳሎን ስዘልቅ እንግዳ ሰው ሶፋ ላይ ተቀምጦ ሳይ ደንግጬ ተኩሼ ገደልሁት ፡፡ ወደ አእምሮዬ ስመለስ ግን ለካ የገባሁት እኔ ቤት ሳይሆን በስህተት ጎረቤቴ ሟች ቤት ነበር፡፡ “የገዳይን ሰንካላ ቃል አምኖ ለመቀበል አዳጋች ቢሆንም በዚህ መንገድ የወንድሙን ህይወት ለነጠቀች ፖሊስ ነው ቦታም ይቅርታ ያደረገላት፡፡ ሌሎች የቤተሰቡ አባላትና የጥቁር መብት ተሟጋቾች ግን ገዳይ በ10 ዓመት እስር ብቻ መታለፏን በመቃወም ከፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ቁጣቸውን በመፈክር እየገለጹ ነበር፡፡ አንተ ፣ አንቺ ብትሆን /ኚ / ታደርገዋለህ / ጊዋለሽ !?
እንደ መውጫ
የእርቅ ፣ የይቅርታ ፣ የፍቅር ተምሳሌት ፣ አባት ፣ ረቡኒ/አስተማሪ / የሆነው የደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ትግል መሪና የነጻዋ ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ /ማዲባ / አፈር ይቅለለውና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1995 ለንባብ በበቃው” Long Walk to Freedom” በተሰኘው ድንቅ ግለ ታሪክ መፅሐፉ ፤ “ ሁሉም ሰው ጥላቻን ተምሮ እንጂ ከእናቱ ማህፀን ይዞት አልተወለደም፡፡ ጥላቻን የተማረ አእምሮ ደግሞ ፍቅርንና እርቅን መማር አይከብደውም፡፡ “ እንዳለው ቦታም ፍቅርን ይቅርታን ከእናቱ ማህፀን ይዞት አልተወለደም፡፡ ከፈጣሪው ከእምነቱ ተምሮት እንጂ ፡፡
እኛም ከቦታም የይቅርታ ልብ ብዙ ብዙ መማር ማትረፍ እንችላለን፡፡ ጥላቻን ልዩነትን ባለፉት 50 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሊባል በሚችል ደረጃ ተጋትነው እንጂ ከእናታችን መሀፀን ይዘነው አልተወለድንም፡፡ ከእናታችን ማህፀን ይዘነው ያልተወለድነውን ግን በአንድም ሆነ በሌላ መልክ የተማርነውን ጥላቻ ፣ ልዩነትና ቂም በቀል ፤ ከአእምሮአችን ለመሰረዝ ፣ ለማጥፋት እንደ ቦታም ካሉ ባለግዙፍ ተክለ ሰብዕና ባለጸጋዎች መማር እንችላለን፡፡ ከእነ ማንዴላ ፣ ማህተመ ፣ ሉተር ተዝቆ የማያልቅ የይቅርታ መዝገብም መማር ይቻላል፡፡ ለዛውም ጥላቻን ከመማር ይልቅ ፍቅርንና ይቅርባይነትን ማማር ይቀላል፡፡
ምክንያቱም ፍቅር ይቅር ባይነት አምላካዊ ሲሆን ጥላቻ ደግሞ ሰይጣናዊ ነው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ አምላኩ በአምሳሉ የፈጠረው ስለሆነ አእምሮው ለፍቅር ፣ ለይቅርታ ይቀርባል፡፡ ያደላል፡፡ ከቦታም ይቅርባይነትን ያረጋገጥነው ይሄንኑ ነው፡፡ መቼም ስለ ፍቅር ፣ ይቅርባይነት በተነሳ ቁጥር ከፈጣሪ ቀጥሎ ስሙ የሚወሳው ማንዴላ ነው ፡፡ ከፍ ብዬ በጠቀስሁት መፅሐፉ ስለ ይቅርባይነት ከፍታና ኃያልነት ፤” ይቅርባይነት ነፍስን ነጻ ያወጣል፡፡ ፍርሀትን ያስወግዳል፡፡ “ ሲል እማኝነቱን ፣ ምስክርነቱን ገልጿል፡፡
ስለዚህ ይቅር በመባባል ነፍሳችንን ከባርነት ነፃ እናውጣ ፡፡ በይቅር ባይነት ቀይዶ አላላውስ ካለን የፍርሃት ቆፈን እንላቀቅ ፡፡ ወገኖቼ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የበደልኋችሁ ፤ በዚህ ጋዜጣ በምጽፋቸው መጣጥፎች የተቀየማችሁ ብትኖሩ ከእግራችሁ ስር ወድቄ ይቅር እንድትሉኝ እለምናለሁ፡፡ እንዲሁም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የበደላችሁኝንም ከልብ ይቅር ብያለሁ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2013