በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን በግዙፍ ፈተናዎች ውስጥ ትገኛለች፡፡ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ከምንጊዜውም በላይ ተባብረው ዘመተውባታል፡፡ በሀገር ውስጥ እዚህም እዚያም በዜጎች ላይ ዘግናኝ ግድያዎች ፣ማፈናቀል በመፈጸም በየአካባቢው አለመረጋጋትን በመፍጠር የመንግሥትን የልማት ፣የዴሞክራሲና የሰላም እና ደህንነት ሥራዎችን አቅጣጫ ለማሳት እየሰሩ ናቸው፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወሳኝ ምእራፍ ላይ መድረስ ጋር ተያይዞ ግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያን የልማትና የሰላም ጉዞ ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡
እነዚህ ኃይሎች ለኢትዮጵያ የቤት ሥራዎች ከመስጠት ተቆጥበው አያውቁም ፡፡ የሀገሪቱንና መንግሥትን ጉዞ ግን አላሰናከሉም፡፡ የእነዚህን ጸረ ሰላም ኃይሎች ሴራ ከማምከንና ያስከተሉትን ችግር በዘላቂነት ከመፍታት ጎን ለጎን ልማቱም ቀጥሏል፡፡ መንግሥት ችግሮች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ ፈጥኖ በመድረስ ህገ ወጦችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ለህግ ለማቅረብ ከሚያከናውነው ተግባር ጎን ለጎን ልማቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በጠላቶቹ የቤት ሥራ ተጠምዶ አልተቀመጠም፡፡
በዚህ የፈተና ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርቀው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተካሄዱ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አቅም እንደሚሆኑ የሚጠበቁት የአንድነት፣ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በዚህ ልምድ ላይ በመመስረት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በጎርጎራ፣ወንጪና ኮይሻ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል፡፡ አሁንም መቀጠል ያ ለበት ይሄው ነው፡፡
በግብርናውም መስክ በዚሁ ልክ እየሰራ ነው፡፡ ስንዴ በበጋ ወቅት በመስኖ ማምረት የተቻለበት ዘመን ይህ ዘመን ነው፡፡ በኩታ ገጠም እርሻም ተአምር እየተሰራ ነው፡፡ የግብርናው ሥራ በቀጣይም ብዙ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ያለ ግብርና ሀገራችንና ዜጎቿ የትም ሊደርሱ አይችሉም፡፡ ከህዝቧ 80 በመቶው አርሶ አደር የሆነባት ሀገራችን በአስቸጋሪ ወቅትም ቢሆን አርሶ አደሩ በአንድ እጁ እርፍ በሌላ እጁ ጠመንጃ ይዞ አገሩንና አካባቢውን ይጠብቃል፡፡ አሁንም አርሶ አደሩ ለሰላምና መረጋጋት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የእርሻ ሥራውንም አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
“ጆንያም የሚቆመው በእህል ነው“ እንዲሉ እህል ካልተመረተ የምግብ ዋስትና አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ ያለ ግብርና ትርፉ ድካም ነው፡፡ ወቅቱ ሀገር በተለያዩ ግዙፍ ችግሮች የተወጠረችበት ቢሆንም ፣በአሁኑ ወቅት ለእርሻ ሥራ የሚሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እየጣለ ያለበትም ነው፡፡ አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያው፣ የግብርና ምርምር ተቋማት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከግብርናው ስር ዞር የሚሉ ባይሆኑም ርብርባቸውን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አጠናክረው በሚቀጥሉበት ወቅት ላይ መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
ሀገሪቱ በመኸር፣ በበልግና በመስኖ እርሻ ላይ ተመስርታ ነው የግብርና ምርት የምታመርተው፡፡ የመኸር እርሻ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት የሚገኝበት ነው፡፡ ይህ ወቅት የበልግ እርሻ የሚጠናከርበት ፣የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ነው፡፡ ዝናቡ ለበልግ እርሻ ትንሽ ቢዘገይም ለመኸሩ እርሻ ግን በወሳኝ ወቅት ላይ የመጣ ነው፤ በዚህ ወቅት እንደ በቆሎ የመሳሰሉት የአገዳ እህሎች ይዘራሉ፤ ተዘርተው ብቅብቅ ያሉም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እንደ ድንችና የመሳሰሉትም ይህን ዝናብ በእጅጉ ይፈልጋሉ፡፡ በሬና ገበሬ ተገናኙ ዛሬ እንደሚባለው ሁሉ የዝናቡ አጣጣል በሬና ገበሬ እንዲሁም ዝናብ ተገናኙ ዘንድሮ ቢባልም ያስኬዳል፡፡
መሬቱም ገራም የሚሆነው ዝናብ ሲያገኝ ነው፡፡ እየጣለ ያለው ዝናብ መሬት ለመስንጠቅም ሆነ ለማለስለስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው እንደመሆኑ ዝናቡን መሻማት ያስፈልጋል፡፡ ዝናቡ ለእርሱም ለከብቶቹም ጠበል፤መድሃኒት ነው፡፡ እርሻውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ይህ የአርሶ አደሩ የተለመደ ሕይወት ነው፡፡ ለአርሶ አደሩ በግብርናና በግብርና ምርምር ባለሙያው ሙያዊ ምክር እየተሰጠው ለምርትና ምርታማነት እድገት ጠንክሮ እንዲሰራ ሊደረግ ይገባል፡፡
ግብርናችን ሁለ ነገራችን ነው፡፡ ግብርናችን የምግብ ዋስትናችን ነው፤ ለውጭ ገበያ እያቀረብን የውጭ ምንዛሬ ከምናገኝባቸው የወጪ ምርቶች መካከል ግብርናው የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ለዓመታት በወጪ ንግድ ቁልቁል ስንወርድ ከነበረበት ሁኔታ እየወጣን እንደመሆኑ ይህን ለማስቀጠልም ሆነ ተገቢውን ገቢ ለማግኘት ዘንድሮ ግብርናው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል፡፡
ሁሉም ሰላምን የማስጠበቅና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ በግጭትና ጥቃት ሳቢያ የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬቸው የመመለስና የማቋቋም፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መጠገን፣ ለፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ ወዘተ ሁሉ ሀብት ይፈልጋል፡፡እየተሰሩ ያሉ ግዙፍ መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ሀብት ያስፈልጋቸዋል፡፡ይህን ሀብት ለማግኘት ግብርናውን ጨምሮ በሁሉም መስክ ልማቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ግብርናው ለምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፣ለወጪ ንግዱ፣ የኑሮ ውድነት እያስከተለ ያለውን ጫና ለማቃለል እየተካሄደ ለላው ሥራ ሁሉ ወሳኝ ነው፡፡ ግብርናው ራሱን ወደ ዘመናዊ ግብርና ለማሸጋገር ያለ የሌለ አቅምን አስተባብሮ መስራትም ይኖርበታል፡፡አሁንም ሌሎች ዘርፎችን ሲያነቃቃ የኖረና በቀጣይም እንዲያነቃቃ የሚጠበቅ ነው፡፡
ይህን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ የሚቻለው ግብርናው የሚፈልገውን ግብዓት በአግባቡ ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡ ለበልግና ለመኸር እርሻ የሚያስፈልጉት ግብአቶች በሙሉ ተሟልተው መቅረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ላይ ሲሰራ
ቆይቷል፡፡ ማዳበሪው አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርስ ርብርብ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር ነው፡፡ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ማዳበሪው እየቀረበ አለመሆኑን ነው፡፡ ይሄ በአስቸኳይ መታረም ይኖርበታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዝናብ በጥሩ ሁኔታ እየጣለ ይገኛል፡፡ ግንቦት ወር በጣም ጸሐይ የሚበዛበትና ውሃ የሚሰጡ ጉድጓዶች ሳይቀሩ የሚነጥፉበት ነው ተብሎ ይታመናል፤ ግንቦት ዋዜማ ላይ ተሆኖ ይህን ያህል መጠን ያለው ዝናብ ማግኘት ትልቅ እድል ነው፡፡ ዝናቡ ለበልግ ትንሽ የዘገየ ቢሆንም ለመኸር እርሻ ግን ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ ይህን ስጦታ ለመጠቀም ከወዲሁ ርብርብ ማድረግ ይገባል፡፡
ግብአት በማቅረብ በኩል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን መፍታት ይገባል፡፡ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም ጭምር ግብአት ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ ባለሙያዎች እንደልብ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ፣ ግብአት የሚያቀርበው የትራንስፖርት አገልግሎት ምቹ ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡
የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በሙሉ ችግሩ ግብርናው ላይ እንዳያጠላ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ግጭትና በጥቃት ምክንያት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ የእርሻ ሥራቸውን ያለስጋት የሚያከናወኑበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ቤታቸው የተቃጠለ ፣ጥሪታቸውን ያጡ እንደመሆናቸው ሰብአዊ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ወቅቱ ወደ መኸር እርሻ ሥራ በስፋት የሚገባበት እንደመሆኑ የግብአት አቅርቦት ፣የእርሻ መሳሪያ አቅርቦት ወዘተ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ግብርናችን ከወቅት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ይህን ወቅት አሟጦ መጠቀም ላይ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡ በየደረጃው ያለ የመንግሥት አካል ይህን ተከታትሎ ማስፈጸም ይኖርበታል፡፡ እግዜሩም እየረዳ ነውና ይህን ዝናብ በሚገባ ለመጠቀም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ዘካሪያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2013