በተፈጥሮ ውበቷ፣ በዘመናት ታሪኳ፣ በህዝቧ ታታሪነትና በሰላም ወዳድነቷ የታወቀችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ጀግኖች ልጆቿ የመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ዓርማ፣ መመኪያና መከታ አድርገዋት አልፈዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሩ ሉዓላዊነትና ለአንድነት ታሪኩ ያደረገውን ተጋድሎ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችም ሆኑ የእነዚህ ኃይሎች መሳሪያ የሆኑት የአገር ውስጥ ተላላኪዎች በፅኑ የተረዱት ከመሆን አልፎ የውስጥ እግር እሳት ሆኖባቸው ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት ጊዜና ሁኔታዎችን እያመቻቹ በተናጠል ለማጥቃት እያደቡ የኢትዮጵያ ህዝብን ፍላጎት ገትቶ ጥቅምና መብት ረግጦ ለመኖር ያልማሉ።
አገራችን በታሪክ ለአንዴም የሰው መሬት አልፋ የወረረችበት ወቅት የለም። የልጆቿን ጀግንነት ሳያውቁ ግን ወራሪዎች ለበርካታ ጊዜ የማይደፈረውን ሊደፍሩ ሲሞክሩ ተስተውሏል። ምንም እንኳን ደጋግመው የእጃቸውን አግኝተው ቢመለሱም ከቀጥታ ወረራው ባለፈ በሴራም አገር ለማፍረስ የተደረገው ሙከራ ቀላል አልነበረም።
ከበርካታዎቹ ወረራ ሙከራዎች መካከል በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ወቅት ጣልያኖች ኢትዮጵያን እስከመጨረሻ በቅኝ ግዛት ስር ለማዋል ብዙ ሙከራ ቢያደርጉም ህዝባችን ግን አልተቀበላቸውም ነበር። በተለይ ወረራውን ባለመቀበል በየዱር ገደሉ መሽገው የነበሩ አርበኞች በወራሪው ኃይል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።የጠላትን እንቅስቃሴ በመከታተልም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ወራሪዎችን መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተዋል። በዚህም ወራሪው የጣሊያን ኃይል ዳግም ሀፍረትን ተከናንቦ ወደመጣበት ተመልሷል። በትናትናው ዕለት መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያከበሩት ቀንም ይህንኑ ድል የሚዘክር ነው።
ይህን የድል ቀን በማስመልከት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት “ይህች ታሪካዊ ቀን ጀግኖች አርበኞቻችን ሀገራችንን ከአምስት ዓመቱ የኢጣልያ ወረራ ነጻ ያደረጉበት ቀን መታሰቢያ ነው። ይሄንን ቀን ስናስብ ከጀግኖች አርበኞቻችን ሦስት ነገሮችን እየተማርን ነው። የመጀመሪያው ከምንም ነገር በላይ ሀገርን ማስቀደም ነው።
በወቅቱ የነበሩት ሁሉም አርበኞች በንጉሡ አገዛዝ የሚደሰቱ፣ የሚስማሙና የሚደግፉ አልነበሩም። በመንግሥት አስተዳደር ቅሬታ የነበራቸው፣ የተገፉ፣ የተለያዩ አማራጭ የአስተዳደር ዘይቤዎችን የሚያቀርቡ ነበሩ። በንጉሡ ላይ አምጸው የሸፈቱም ነበሩ። በወቅቱ ጠላት እጁ ላይ ካለው አቅም ይልቅ አሸናፊ ያደርገኛል ብሎ ያሰበውን የኢትዮጵያውያንን ብሶትና ቅሬታ እንደ መሳሪያ ሊጠቀምበት ተንቀሳቅሶ ነበር።
በዚህም ከንጉሡ ጋር የማይዋደዱና በሆዳቸው ቅሬታ የያዙትን በስልጣንና በማባባያ ዝም አሰኝቶ ኢትዮጵያን የመጨበጥ ፍላጎት ለማሳካት ሞክሯል። ነገር ግን አርበኞች ሁሉም ለሀገራቸው ከብር፣ ፍቅር እና የጸና አቋም ነበራቸው። ቅሬታቸውና ልዩነታቸው ከመንግሥት አስተዳደር ጋር እንጂ ከሀገራቸው ጋር አልነበረም። በዚህም የተነሣ በሉዓላዊነታቸው ሳይደራደሩ፣ ለፋሽስት ጥቅም ሳያጎበድዱ፣ የሀገራቸውን ነጻነት ለማስከበር ዱር ቤቴ ብለው ዘመቱ።
ሁለተኛው ለሀገር ማንንም አለመጠበቅ ነው። ለሀገር ለሚከፈል ዋጋ ማንም እንዲጠይቅ፣ እንዲያስተባብር ወይም እንዲቀሰቅስ አይጠበቅበትም። ሁሉም ዜጋ የሚያውቀውን፣ የሚያምነውንና የሚችለውን ለማድረግ በራሱ መንፈስ መነሣት አለበት። አርበኞቻችን ያስተማሩንም ይሄንን ነው። በወቅቱ ንጉሡ ከሀገር ወጥተዋል። ሊያስተባብሩ የሚችሉ ተቋማትና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አልነበሩም። በዚያ ጊዜ ዜጎች ለሀገራቸው ራሳቸውን ነው ያስተባበሩት።
የሚሰጥ የለምና በጀት፣የሰው ኃይል፣ ቁሳቁስ አልጠየቁም። ስለሆነም ይዘው የወጡት የራሳቸውን መሣሪያ፣ የራሳቸውን ስንቅ እና ራሳቸውን ብቻ ነበር። ምናልባት ከስንቃቸው ጋር የሀገር ፍቅር በልባቸው ይዘው ስለወጡ እሱ ገመድ ሆኖ አስተሳስሯቸው እንደ አንድ ጦር ሆነው ጠላትን እንዲፋለሙ አድርጓቸው ይሆናል፤ ግን ለዚያ የሀገር ፍቅር የማንንም ቅስቀሳ ወይም የየትኛውንም ተቋም ውትወታ አላሻቸውም።
ሦስተኛው ትልቅ ቁም ነገር ሀገርን የሚታደገው የዜጎች አንድነት መሆኑ ነው። አርበኞች በየአካባቢያቸው በጎበዝ አለቃ እየተመሩ በመዝመት ትግሉን ጀምረውታል። ትግላቸው ፍሬ ማፍራት የጀመረው ግን በየአቅጣጫው የነበረው የአርበኞቻችን ተጋድሎ እየተቀናጀና እየተናበበ ሲመጣ ነው። የሚችሉት በአካል፣ ያልቻሉት በመልዕክት እየተገናኙ አንድነታቸውን አጠናከሩ። የውስጥና የውጭ አርበኞች ተቀናጁ።
ብሔር፣ ቋንቋና እምነት ገደብ ሳይሆንባቸው ሀገር አንድ አደረገቻቸው። ለአንዲት ሀገር በአንድነት ቆሙ። ይህም ፍሬውን በቶሎ እንዲለቅሙት አደረጋቸው። እኛ የእነዚህ አርበኞች ልጆች ነን። የእነዚህ አርበኞች ባለ ዕዳዎችም ነን። ሀገራችን በየዘመናቱ ዋጋ እየተከፈለባት እዚህ የደረሰች ናት። የምትቀጥለውም ዋጋ በሚከፍሉ ልጆቿ ነው። እንደ አርበኞች እናትና አባቶቻችን ከምንም ነገር በላይ ሀገራችንን እናስቀድም”።
እውነት ነው ኢትዮጵያውያን ይሄን ሁሉ ዘመን አልፈው እዚህ የደረሱትና ነጻነታቸውን አስከብረው በኩራት የሚኖሩት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በአገር ሉዓላዊነት ላይ ግን ተመሳሳይ አቋም ይዘው በመታገላቸውና አኩሪ መስዋዕትነት በመክፈላቸው ነው። ይህ ጽናት አባቶችን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ የዘለቀ እንደመሆኑ ከውስጥም ይሁን ከውጭ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ወይም እበትናለሁ ብሎ የሚነሳ ኃይል ትርፉ ውርደትና ሽንፈት መሆኑን ቀደም ብሎ ሊያጤነው ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2013