ከአሁን ቀደም “ኦ! ዴሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ!” የሚል ጽሑፍ ማስነበቤን አስታውሳለሁ።ጽሑፉን ያነበቡ ወዳጆቼም ይዘቱን ወደውት “ይበል!” ብለው ማበረታታቸውን አልዘነጋሁም።እኔም ብሆን ምንም እንኳን እስከ ዛሬ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ለንባብ ካበቃኋቸው ምናልባትም በሺህ ከሚቆጠሩ መጣጥፎቼ መካከል ያ ጽሑፍ ይበልጥ ለስሜቴና ለወቅታችን የቀረበ ስለነበር በቀዳሚነት መጠቀሱ ተገቢነት ይኖረዋል ባይ ነኝ፡፡
የሀገራችን ዴሞክራሲ “ከርሞ ጥጃ” ይሉት ቢጤ ስለመሆኑ በርካታ መከራከሪያዎችን እያጣቀሱ ማመላከት ይቻላል።“ታዳጊው ዴሞክራሲያችን” እየተባለ ከዓመት ዓመት ጨቅላነቱ የሚተረክለት ፍልስፍና መቼ ለወጣትነት፣ መቼ ለጎልማሳነትና ምራቁን እንደ ዋጠ አረጋዊ አንቱ እንደሚባል በግሌ እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ አለ።ነገር ያማረላቸው እየመሰላቸው ፖለቲከኞቻችንና መሪዎቻችን እንደ ካሮት ቁልቁል ሥር እየሰደደ የሚሄደውን ዴሞክራሲ “ገና በማደግ ላይ ያለው” በማለት የሞግዚትነት መብቱን ለራሳቸው አጽድቀው “የሕጻን ጥብቆ በማልበስ ጡጦ ማጉረሳቸውን” አልወድላቸውም፡፡
የዘመናዊ ዴሞክራሲ ስም በሀገራችን መተዋወቅ ከጀመረ አንድ ክፍለ ዘመን ሊሞላው የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ብቻ ናቸው።ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ስለ ዴሞክራሲ መናገር የጀመሩት ገና በአልጋ ወራሽነታቸው ዘመን አውሮፓን ጎብኝተው ከተመለሱ ጊዜ ጀምሮ ነበር።የደርግ መንግሥትም የዴሞክራሲ ባለሟል ነኝ በማለት ሲፏልልብን መክረሙን አንረሳም።ኢ.ሕ.ዲ.ሪ (የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) ብሎ በሰየመው የመንግሥቱ ስያሜ ውስጥ “ዴሞክራሲ” የሚለው ቃል አፍጥጦ መታየቱን ልብ ይሏል።ህወሓት/ ኢሕአዴግም ቢሆን ደምና መቅኒው “ከዴሞክራሲ የተቀመመ” መሆኑን እየጋተን ሲያላግጥብን የሦስት ዐስርት ዕድሜያችንን በፖለቲካ ቁማር በልቶ እርቃናችንን አስቀርቶናል።በፓርቲው ኢሕአዴግ ስም ውስጥም ሆነ “ኢፌዴሪ” በሚለው በመንግሥቱ ስያሜ ውስጥ እንደ ቅመም ጣል የተደረገውን “ዴሞክራሲን” ማስታወስ ብቻ ይበቃል።“መልክ ጥፉን በስም ይደግፉ” ይባል የለ፡፡
አልፎም ተርፎ በርካታ የዓለም ሀገራት ከዘመናዊ ዴሞክራሲ ጋር ከመተዋወቃቸው አስቀድሞ በሀገራችን አንዳንድ ባህሎች ውስጥ “አያ” ዴሞክራሲ ገዢ በመሆን ሥር ሰዶ እንደነበር በድፍረት ሲተርኩልን ባጅተዋል።ዛሬስ ቢሆን የዴሞክራሲ ስም በየአንደበቶቻችንና በብዕራችን ሳይንቆለጳጰስ የሚውል ከሆነ በተገዳዳሪዎቼ ፊት ብዕሬን አሲቼ እወራረዳለሁ፡፡
ስሙ እንጂ ግብሩ “መንፈስ” የሆነብን የሀገራችን የዴሞክራሲ ባህል መቼ “ከአንቀልባ ላይ ወርዶ” ድክ ድክ እንደሚል እኛም እግዚሃሩም ለማወቅ የተቸገርንበት ወቅት ነው።ባህሉ እንዳያድግና እንዳይፋፋ “ጥላ ወጊ” ሆነው ያመነመኑት ራሳቸው የፖለቲካው ካዳሚዎች መሆናቸው ተቃርኖውን ያጦዘዋል።እንጭጩ ፍልስፍና አሽቶ “ለመብል እንዳይደርስ” “በላዔ ዴሞክራሲ” ሆነው ሲያጨነግፉት የኖሩትና እያጨነግፉት ያሉት ራሳቸው “የጉዳዩ ጠበቆች ነን” በማለት ሰክረው የሚያሳክሩን የአይዲዮሎጂው ተመጻዳቂዎች መሆናቸው አልጠ ፋንም፡፡
የነበር ወግ ማዋዣ፤
ከሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት በዚሁ የአዲስ ዘመን ጋዜጣና የ“አብዮታዊ ዴሞክራሲ አጋፋሪ ሽፍቶቹ” ከጫካ ተንደርድረው ገና ከሥልጣን ላይ ፊጥ እንዳሉ እስትንፋሷን በነጠቋት በተወዳጇ ነፍሰ ሄር የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ የብዕር ሰዎችን አቧድኖ ክፉኛ በሃሳብ ያፋለመ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ተነስቶ ነበር።የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም አንዱ ተፋላሚ ስለነበር ታሪኩ የእርሱም ትዝታ አካል ነው።
በዚያ የጎምቱ ብዕረኞች ሰላማዊ የሃሳብ መሞሻለቅ ሂደት ውስጥ አንድ ሁለቱ አርእስት የአንባቢያንን ቀልብ መሳብ ብቻም ሳይሆን ጸሐፊዎቹ ራሳቸው እንደምን እርስ በእርስ በምጸት ይፋተጉ እንደነበር በጥሩ ማሳያነት የሚታወስ ነው።እነዚያ ሁለት አርእስት አንደኛው “ልጅነት ጅልነት” የሚል ሲሆን ለዚህ ጽሑፍ የተሰጠው የመልስ አጸፋ ደግሞ “ከጃጁ አይበጁ” የሚል ነበር። ልጅነትን በጅልነት አመሳስለው የጻፉት ወዳጄ አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ ሲሆኑ ጽሑፉ ያነጣጠረው ደግሞ የዚያን ጊዜው ጎረምሳ ብዕረኛ የነበረውን ይህንን ጸሐፊ ከሃሳብ ፍትጊያው ጨዋታ ገፍትሮ ለማስወጣት በማሰብ ነበር።ይህ ጸሐፊም ለወዳጁ በትር ጀርባውን ላለመስጠት ጨክኖ ለጎልማሳው አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ ምላሽ የሰጠው “ከጃጁ አይበጁ” በሚል ርእስ የመልስ ምት በማቅመስ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲም እንኳንም አድጎ ለጉልምስና ሊበቃ ቀርቶ ገና “በወተት ጥርስ” ላይ ጮርቃ ሆኖ እንዲቀር የፈረዱበትን የሀገሬን ፖለቲከኞች የፈረጅኳቸው ከዳግላስ ጴጥሮስ እና ከአሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ በተዋስኳቸው በእነዚያ ሁለት አርእስት አማካይነት ነው።እንዴት? “እንጭጩ ዴሞክራሲ” የፈቀደልኝን “ሙሉ መብት” ተጠቅሜ የብዕር ጉዞዬን እያዋዛሁ ልቀጥል፡፡
“ልጅነት ጅልነት” የሆነባቸው ፖለቲከኞቻችን፤
ይህ አገላለጽ ገና ቦርቀው ባልጠገቡት ታዳጊ ልጆቻችን ሥነ ልቦና ላይ አሉታዊ ትርጉም እንደማያሳድር ተስፋ አደርጋለሁ። ይህንን የአበው ብሂል በአባባልነቱ ተጠቀምኩበት እንጂ ለቤተሰባችን ድምቀት፣ ፍካትና በረከት፤ ለሀገራችንም ተስፋ በሆኑ ቡቃያዎቻችን ላይ ለመሳለቅ ተፈልጎ አይደለም፡፡
ርእሰ ጉዳዬ እንዳይጠንን ስለሰጋሁ “ለልጅነት ጅልነት” ማሳያ የሚሆን አንድ የጨቅላነት ዕድሜዬን ትዝታ ላስታውስ።በሳቂታዋ የኮልፌ ሠፈር ተወልደው እትብታቸው የተቀበረ፣ ወይንም የልጅነታቸውን ዕድሜ የኮልፌን ቀይ አፈር እያቦነኑ ያደጉ ዘመነ አቻዎቼ ዝነኛውን አባባ ዜማን ይረሷቸው ይሆን ብዬ በፍፁም አልጠራጠርም።አባባ ዜማ የካፒቴን አክሊሉ ንብረት የሆነው (አንዳንዶች የእቴጌ መነን ነው ይላሉ) የጌሾና የኮክ ጫካ ባለአደራ ጠባቂ ነበሩ።ታሪኩ የተፈፀመበትን ትክክለኛ ቦታ ለማረጋገጥ ለሚፈልጉ ደግሞ ከቀድሞው አሥረኛ ወረዳ ከዛሬው የኮልፌ ክፍለ ከተማ አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ዕውቀቴ ወገኔ ትምህርት ቤት ያለበትን ግቢ ሄደው ቢጎበኙ ቀጥዬ የምተርከው ታሪክ ዛሬም ድረስ አሻራው እንዳልጠፋ መገንዘብ ይችላሉ፡፡
ከቆቅ የነቁት፣ ከሚዳቆ የፈጠኑት አበባ ዜማ ደኑን ይጠብቁ የነበረው በልዩ ጥንቃቄና ንቃት ነበር።ለእኔና ለቢጢዎቼ ደግሞ ቆቅነታቸውንም ሆነ ሚዳቆነታቸውን “በልጅነታችን ረቂቅ ጥበብ” ለመፈታተን ዘዴው አልጠፋንም።በልዩ ልዩ ብልሃትና ዘዴ አበባ ዜማን እያታለልን የሽቦ ኬላ ሰብረን የምንገባው የኮክ ፍሬዎችን ለመስረቅ ነበር።ክፋቱ የኮኮቹን ፍሬ የምንለቅመው የበሰሉትን ብቻ እየመርጠን ሳይሆን ገና ያልበሰለውን ጮርቃውን ጭምር ያለርህራሄ በረጅም ዱላና በድንጋይ ውርወራ እያረገፍን ዛፉን በማራቆት ጭምር ነበር።አባባ ዜማን እርር ድብን አድርጎ የሚያበሳጫቸው የበሰለውን ኮክ መስረቃችን ብቻ ሳይሆን ጮርቃውን እያረገፍን የበደል በደል መፈጸማችን ጭምር ነበር፡፡
“የፖለቲካው ልጅነት ጅልነት” የሆነባቸው አንዳንድ ሳይሞቅ ፈላ ጉዶችም “ታዳጊው ዴሞክራሲ” በእንፉቅቅ እየሄደ እንዲኖርና ፍሬ እንዳያፈራ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ የሚፈነጩት በጨቅላ አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው በ“ድንጋይና በዱላ” ፍልሚያ ያሸነፉ እየመሰላቸው የሰላምን የሽቦ አጥር ጥሰው በመግባት ሕዝቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር በማወክ ይመስላል።ንግግራቸው ለከት የለው፣ ተግባራቸው ፍሬ አልባ፣ የሕይወታቸው ምስክርነት የተበላሸ ስለሆነም “ለዴሞክራሲው እድገት” የመሰናክል አለት በመሆን ሀገር ሲያምሱ ይውላሉ።“ልጅነት ጅልነት” ይሏል እንዲህ ነው።ሀገሬን የፈጠረ አምላክ ጸሎት ይሰማ ከሆነ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ “የፖለቲካ ጅሎች” እንኳን ሥልጣን ሊያጎናጽፋቸው ቀርቶ የሌሊት ቅዠታቸውንና ህልማቸውን ጭምር እንዲነጥቃቸው ምኞቴ ነው፡፡
“ከጃጁ አይበጁ” ብጤ ፖለቲከኞች፤
አንዳንዶችም አሉ “በፋሲካ የደነቆረች ሁልግዜም ፋሲካ ይመስላታል” እንዲሉ ገና ተማሪ እያሉ ጀምሮ ይዘምሩለትና ይሰብኩት የነበረውን የእነ ቼ ጉቪራን፣ የእነ ሆችሚንን የእነ ማኦን፣ የእነ ሌኒንንና ማርክስን ስብከተ-ፖለቲካ እንደ ጣዕም አልባ ማስቲካ እያመነዠኩ አደባባይ ሲውሉ ጥቂትም እፍረት፣ ትንሽም “ሼም” አይዛቸውም።እንኳን የትውልዱን ስሜት ሊማርኩ ቀርቶ ከአንደበታቸው የሚፈልቀው የራሳቸው ቋንቋ እንኳን የሚገባቸው አይመስልም፡፡
በአስተሳሰብ ጃጅተው፣ በእውቀት ኮስምነው፣ በሥነ ምግባር ደኽይተው ሕዝቡን ከዴሞክራሲ “ጠበል” ካላጠጣነው እያሉ ሲሰብኩ ስለ እነርሱ ተመልካቹ እንደሚያፍርላቸው እንኳን የተረዱ አይመስሉም። ያ ተወዳጁ መምህሬ ደበበ ሰይፉ ለካስ ቢቸግረው ኖሯል በአፍቅሮተ ፍሬ አልባ ፖለቲካ ተለክፈው የሚያንጎላጅጁትን እኒህን መሰል ለጉድ የጎለታቸውን የዘመን ጠበኞች “እናንት የአባቶቻችሁ ልጆች፤ የአያቶቻችሁ ቅድመ አያቶች” በማለት የተሳለቀባቸው።እንዲያውም እኮ “ከዘመን የተኳረፉ” የሚል ቅጽል ፈጥሮ በዘመነ ተማሪነታችን ለእኛ ለደቀ ማዛሙርቱ አስተዋውቆን ነበር። እንደሚመስለኝ “ጥሬ ጨው” የሚለውን ግጥሙን የጻፈው በዙሪያው ያያቸው የነበሩ “ብጤ” የዕድሜ ሳይሆን የሃሳብ ድንክዬዎች ሲተረማመሱ እያስተዋለ ሳይሆን አይቀርም።የግጥሙን አቀማመጥና ይዘቱን ሳልለውጥ እንደ ወረደ ላስታውስ፤
መስለውኝ ነበረ፣
የበቁ የነቁ
ያወቁ የረቀቁ
የሰው ፍጡሮች፣
ለካ እነሱ ናቸው፣
ጥሬ ጨው . . . ጥሬ ጨው
ጥሬ ጨዋዎች፣
መፈጨት-መሰለቅ-መደለዝ-መወቀጥ-
መታሸት-መቀየጥ
ገና እሚቀራቸው፤
“እኔ የለሁበትም!”
ዘወትር ቋንቋቸው፡፡
እንግዲህ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሁልግዜም ልምሻ እንዳጠቃው ሕጻን እየተሽመደመደ የኖረው “የፖለቲካ ልጅነታቸው ጅልነት፤ በመጃጃታቸው ሊበጁ ያልቻሉ” የዝና ምንደኞች ምህዳሩን ተቆጣጠረው ስለወረሩት ነው።በሰሞንኛው የስድስተኛው ሀገራዊ የምርጫ ፉክክር አየሩ እየታጠነ የምናስነጥሰው እንደነዚህ ዓይነቶቹ ዴሞክራሲ እንዳያድግ “ሾተላይ” የሆኑበት ባእድ ባለሀገር ፖለቲከኞች በሚያጨሱት “የሴራ እጣን” ስለታፈነ ይመስላል።ሀገሬ ሆይ! ጽናቱን ይስጥሽ። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013